Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየማዕድን ሚኒስቴር ለከፊ ሚኒራልስ የወርቅ ምርት ፈቃድ ሰጠ

የማዕድን ሚኒስቴር ለከፊ ሚኒራልስ የወርቅ ምርት ፈቃድ ሰጠ

ቀን:

የማዕድን ሚኒስቴር ከፍተኛ ደረጃ የወርቅና የብር ማዕድን ማምረት ፈቃድ ከፊ ሚኒራልስ ለተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ ሚያዝያ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰጠ፡፡ ከፊ ሚኒራልስ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቱሉ ካፒ በተባለ አካባቢ የሚገኘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ጽንስ ወርቅ ለማምረት የሚያስችለውን ጥናት አጠናቋል፡፡ ከፊ ያጠናውን የአዋጭነት ጥናትና የሥራ ዕቅድ ለማዕድን ሚኒስቴር አቅርቧል፡፡ ሚኒስቴሩ ኩባንያው ያቀረበውን ዕቅድ ገምግሞ የከፍተኛ ወርቅና ምርት ፈቃድ እንዲሰጠው ወስኗል፡፡ ሚኒስቴሩ ለኩባንያው የሚሰጠውን የወርቅና የብር ምርት ፈቃድ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በቅርቡ አቅርቦ አፀድቋል፡፡ ከዚህ በኋላ የማዕድን ሚኒስቴርና ከፊ ሚኒራልስ የከፍተኛ ደረጃ የወርቅና የብር ማዕድን ማምረት ሥራ ፈቃድ ስምምነት ሰነድ ሚያዝያ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ሚኒስቴሩ አዲስ ባስገነባውና በቅርቡ በሚያስመርቀው ሕንፃ ውስጥ ተፈርሟል፡፡ ስምምነቱን የፈረሙት የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊና የከፊ ሚኒራልስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ሐሪ አዳምስ ናቸው፡፡ የማዕድን ልማት ስምምነቱ ለ20 ዓመት እንደሚፀና፣ የፈቃድ ዘመኑ ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረት በእያንዳንዱ የፈቃድ ዕድሳት ከአሥር ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ሊታደስ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ለኩባንያው የተሰጠው የወርቅ ማምረቻ ሰባት ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ነው፡፡ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ቶሎሳ፣ ኩባንያው 151.6 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት መመደቡን፣ ኩባንያው ሥራ ሲጀምር ለ700 ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው ወደ ምርት ሲገባ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 28,875 ኪሎ ግራም ወርቅና ብር እንደሚያመርት፣ ከዚህም 1.2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝና ለመንግሥት 130 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያደርግ አቶ ቶሎሳ አስረድተዋል፡፡ የወርቅ ኤክስፖርት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገባ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የወርቅ ምርት የተሰማራው ብቸኛ ኩባንያ ሚድሮክ ጐልድ ሲሆን፣ በዓመት በአማካይ አምስት ቶን ወርቅ እንደሚያመርት የገለጹት አቶ ቶሎሳ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሦስት ኩባንያዎች ወደ ከፍተኛ ወርቅ ምርት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡ ባህላዊ የወርቅ ምርት ለወርቅ ኤክስፖርት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በአምስት ክልሎች ወርቅ በባህላዊ መንገድ የሚመረት ሲሆን፣ በዓመት ከሰባት እስከ ስምንት ቶን ወርቅ በባህላዊ መንገድ እንደሚመረት ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ከወርቅ ኤክስፖርት በዓመት ከ450 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር የምታገኝ ሲሆን፣ ገቢው በመጪዎቹ ዓመታት በእጥፍ እንደሚጨምር ይጠበቃል፡፡ የኤፈርት ኢዛና ማይኒንግ በትግራይ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት በማግኝቱ የምርት ፈቃድ ወስዶ ወደ ምርት ለመግባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሱዳን ድንበር አቅራቢያ የወርቅ ፍለጋ ሥራ የሚያካሂደው አስኮም ማይኒንግ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ከፍተኛ መጠን ያለው የወርቅ ክምችት አግኝቶ የመጨረሻ ደረጃ ጥናት በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ አስኮም ጥናቱን እንዳጠናቀቀ የምርት ፈቃድ እንደሚሰጠው አቶ ቶሎሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ንብረትነቱ የሼክ መሐመድ አል አሙዲ የሆነው ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን በደቡብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወርቅ ክምችት አግኝቶ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ሚድሮክ ጐልድ በበኩሉ ከለገንደምቢ የወርቅ ማውጫ በተጨማሪ ሳካሮና መተከል አካባቢ ባካሄደው መጠነ ሰፊ የፍለጋ ሥራ የወርቅ ክምችቶች አግኝቶ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም የሳካሮ ወርቅ ክምችትን ወደ ምርት ለማስገባት በመጨረሻ ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ሚስተር ሐሪ ኩባንያቸው የቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችትን ለማልማት ቆርጦ መነሳቱን ተናግረዋል፡፡ የወርቅ ማምረቻውን ለመገንባት 100 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሚስተር ሐሪ፣ ግንባታው በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት የመጨረሻ ሩብ ዓመት እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ ግንባታው 18 ወራት እንደሚፈጅ ገልጸው፣ እ.ኤ.አ. በ2017 ምርት እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡ ከአካባቢው ለሚነሱ ነዋሪዎች አስፈላጊው ካሳ እንደሚከፈል አስታውቋል፡፡ በቱሉ ካፒ 28 ቶን የሚገመት የወርቅ ክምችት መኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከፊ ሚኒራልስ በተሰጠው 130 ካሬ ኪሎ ሜትር የወርቅ ፍለጋ ይዞታ ሰፊ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ተጨማሪ የወርቅ ክምችት ለማግኘት ዕቅድ ነድፏል፡፡ ኩባንያው በመጀመሪያ በክፍት ጉድጓድ (Open Pit) ወርቅ የሚያወጣ ሲሆን፣ በቀጣይ የከርሰ ምድር ወርቅ ምርት ለመጀመር ዕቅድ ይዟል፡፡ የቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችት ረጅም ታሪክ ያለው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት፣ ጣሊያኖቹ ከቱሉ ካፒ ወርቅ በአነስተኛ መጠን (በባህላዊ መንገድ) በማምረት ወደ አገራቸው ሲያግዙ እንደነበር ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ ጐልደን ፕሮስፔክት የተሰኘ ኩባንያ በቱሉ ካፒ የወርቅ ፍለጋ ሥራ እ.ኤ.አ. በ2004 ሲያካሂድ ቆይቶ ናዩታ ሚኒራልስ ለተሰኘ ኩባንያ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ናዩታ ሚኒራልስ በበኩሉ ሰፊ የፍለጋ ሥራ አካሂዶ ዋናውን የወርቅ ክምችት እ.ኤ.አ. በ2006 ዓ.ም. አግኝቷል፡፡ ናዩታ ሚኒራልስ ጥናቱን አጠናቆ ወደ ግንባታ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ሳለ የወርቅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በማሽቆልቆሉ፣ ኩባንያው ለልማት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ማግኘት አስቸጋሪ ስለሆንበት ይዞታውን ለከፊ ሚኒራልስ በስድስት ሚሊዮን ፓውንድ ሸጧል፡፡ የከፊ ሚኒራልስ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ከበደ በለጠ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በቱሉ ካፒ 643 ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡ እያንዳንዱ ጉድጓድ ከ200 እስከ 600 ሜትር ጥልቀት ያለው ሲሆን፣ በድምሩ ጉድጓዶቹ 123,000 ሜትር ጥልቀት አላቸው፡፡ ‹‹የቱሉ ካፒ የወርቅ ፍለጋ ፕሮጀክት መጠናቀቅ ታሪካዊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከለገደምቢ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከፈተ የወርቅ ማውጫ የለም፤›› ብለዋል ዶ/ር ከበደ፡፡ ዶ/ር ከበደ ጐልደን ፕሮስፔክት፣ ናዩታ ሚኒራልስና ከፊ ሚኒራልስን በሥራ አስኪያጅነት የመሩ የዕድሜያቸውን አብዛኛውን ክፍል በወርቅ ፍለጋ ሥራ ያሳለፉ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ጂኦሎጂስት ናቸው፡፡ ሚስተር ሐሪ ዶ/ር ከበደ የቱሉ ካፒ ፕሮጀክትን ከመጀመሪያ ጀምሮ በመምራት ለፍሬ በማድረሳቸው ከፍተኛ ምሥጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...