Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየምግብ ዘይት ለተጠቃሚዎች ሳይደርስ እየታገተ መሆኑ ተሰማ

የምግብ ዘይት ለተጠቃሚዎች ሳይደርስ እየታገተ መሆኑ ተሰማ

ቀን:

መንግሥት ድጎማ በማድረግ ከሚያቀርባቸው መሠረታዊ ሸቀጦች ውስጥ በተለይ ከፓልም የሚመረተው የምግብ ዘይት ለተጠቃሚዎች በአግባቡ ሳይደርስ በሕገወጦች እየታገተ መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ፡፡ መንግሥት በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ በማድረግ ለኅብረተሰቡ በድጎማ የሚያቀርበው የምግብ ዘይት፣ በቀጥታ ለኅብረተሰቡ ሊደርስ አለመቻሉ እየተገለጸ ነው፡፡ የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓሊ ሲራጅ አማካሪና የአለ በጅምላ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመጋቢት ወር ብቻ መንግሥት ለአዲስ አበባ ከተማ 8.5 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት፣ በአማራ ክልል ደግሞ ስምንት ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ከቀረበው ዘይት ውስጥ በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለተጠቃሚው መድረስ ሳይችል የሆነ ቦታ ታግቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ትልልቅ ባለኮከብ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ለኅብረተሰቡ በድጎማ የሚቀርበውን የምግብ ዘይት እየተጠቀሙ መሆኑ የተደረሰበት በመሆኑ፣ የቀድሞው ጂንአድ የአሁኑ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት (ኢኢግልድ) ፓልም ዘይት እንዳይሸጥላቸው መመርያ መተላለፉ ታውቋል፡፡ አቶ ኑረዲን ጨምረው እንደገለጹት፣ መንግሥት ዘይት በድጎማ የሚያቀርበው ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ነገር ግን ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች በመንግሥት ድጎማ ቀመር ውስጥ ያልተካተቱ ቢሆንም፣ ለዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል የሚቀርበውን ዘይት እየተጠቀሙ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማስቀረት ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ከኢኢግልድ እንዳይገዙና ከዚህ በኋላ ከአለ በጅምላ ብቻ ግዥ እንዲፈጽሙ መወሰኑ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ የንግድ ተቋማት ከአለ በጅምላ እንዲገዙ የሚጠበቀው ሌሎች የዘይት ዓይነቶችን መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ መንግሥት በዘላቂነት በዘይት ንግድ ላይ ያለውን የገበያ ሥርዓት ለማስተካከል የተመረጡ ነጋዴዎችን ለማሳተፍ እያጤነ መሆኑ ይነገራል፡፡ መንግሥት በጂንአድ በኩል የሚያስመጣውን ፓልም ዘይት በራሱ በኢኢግልድ፣ በኢትፍሩትና በአለ በጅምላ፣ እንዲሁም በተለያዩ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ሲያሠራጭ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ወራት ወዲህ ወደ አገር ውስጥ የገባው ዘይት ለኅብረተሰቡ እንዳይደርስ እያደረገ ያለ ኃይል አለ እየተባለ ነው፡፡ ወደ መሸጫ ማዕከላት የገባ ዘይትን ለማግኘት ረጃጅም ሠልፎች እየታዩ ሲሆን፣ በዚህ ምክንያት ኅብረተሰቡ ባገኘው አጋጣሚ ምሬቱን ሲገልጽ፣ መንግሥት ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግ መገደዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አቶ ኑረዲን ለግል ኩባንያዎች ሥራው ሊሰጥ ታስቧል ለሚለው ሐሳብ ማረጋገጫ ባይሰጡም፣ ምንጮች እንደገለጹት በዘይት ንግድ ልምድ ያላቸውን ኩባንያዎች በተናጠል እየጠራ እያነጋገረ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ራሳቸውን ችለው ከውጭ አስገብተው ያከፋፍላሉ? ወይስ መንግሥት ያስመጣውን ዘይት ተረክበው ያከፋፍላሉ? የሚለው ጉዳይ ውሳኔ አለማግኘቱን የሚናገሩት ምንጮች፣ ለሁሉም ነጋዴዎች ሥራው ክፍት ይሆናል ወይ? የሚለው ጉዳይ እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱንም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በዓመት 360 ሺሕ ሜትሪክ ቶን (360 ሚሊዮን ሊትር) ዘይት ለገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህ የዘይት አቅርቦት በመንግሥት ብቻ የሚካሄደውን ንግድ የሚያመለክት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...