መንግሥት በተደጋጋሚ ከሚተችባቸው በርካታ ችግሮቹ መካከል አንዱ የግልጽነት አለመኖር ነው፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከፀደቀባቸው ዋነኛ ዓላማዎች መካከል ደግሞ አንደኛው በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በመጠቀም በነፃ ፍላጐት፣ በሕግ የበላይነትና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጦ መነሳትን ያሳያል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ማኅበረሰብ የሚፈጠረው ደግሞ በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን ላይ የሚወጣ መንግሥት ግልጽነትን ሲላበስ፣ ተጠያቂነት ሲኖርበትና ኃላፊነት ሲሰማው ነው፡፡ የግልጽነት ችግር ሲኖር ጠያቂና ተጠያቂ አይኖርም፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ወገንም አይገኝም፡፡ እንኳን ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለመነጋገር የአገርን ህልውና ማስቀጠልም ይከብዳል፡፡ ብዙ ጊዜ የግልጽነት ችግር የሚፈጥራቸው ጉዳዮች ሲወሱ፣ በግንባር ቀደምትነት የሚነሳው የመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የተቀላጠፈ አለመሆን ነው፡፡ በራሱ የሚተማመን፣ በብቃት የተደራጀና ከወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የሚመጥን አቅም ያለው የሕዝብ ግንኙነት ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተቋም በፍጥነት የመረጃ ልውውጦችን ማቀላጠፍ አለበት፡፡ ተቋሙ ኖሮ ሥራውን በአግባቡ መወጣት ሲያቅተው ግን በርካታ የመንግሥት የዕለት ተዕለት ተግባራት ይድበሰበሳሉ፡፡ በግልጽነት ጉድለት ምክንያት ግለሰቦች ከተቋማት በላይ ይሆናሉ፡፡ የሕግ የበላይነት አይኖርም፡፡ ሙስና ይንሰራፋል፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች በየቦታው ይከሰታሉ፡፡ ሚስጥራዊ ተግባራት ይበዛሉ፡፡ ለአገር የማይበጁ ችግሮች ይፈለፈላሉ፡፡ መንግሥትን በመምራት ላይ ያለው ፓርቲ ብዙ ነገሮችን በሚስጥር መያዝ ‹‹ባህሉ›› እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከራሱ አንደበት ተሰምቷል፡፡ በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበረ ድርጅት ሚስጥር ‹‹ባህሉ›› ቢሆን አይገርምም፡፡ ነገር ግን አገር መምራት ሲጀምር ግን ይህ ዓይነቱ ‹‹ባህል›› ይቀየራል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን ላይ የሚወጣ መንግሥት ተጠሪነቱ ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ አሠራሩ በሙሉ ግልጽ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚጓዝ ግን አምባገነን ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነትን በተመለከተ በማያሻማ ሁኔታ ደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት፣ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ለማንሳት እንደሚችልና ዝርዝሩም በሕግ እንደሚወሰን ሕገ መንግሥቱ በግልጽ አስፍሯል፡፡ ከዚህ አንፃር በተጨባጭ ያሉትን ችግሮች ስንገመግም ግልጽነት ተጓድሏል፡፡ የኃላፊነትና የተጠያቂነት ወሰንም በግልጽ አይታይም፡፡ የመንግሥት አሠራርን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች በርካታ ጉድለቶች አሉባቸው፡፡ በጐ ተግባራትን ከመዘከርና ስኬትን አጋግሎ ከማቅረብ ውጪ ችግሮችን ለማመልከትና ለመፍትሔ የሚረዱ ግብዓቶችን ለመፈለግ ፍላጐት አይታይም፡፡ ይህ ችግር በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ በብዛት ይታያል፡፡ የመረጃ ፍሰቱ በመዘጋጋቱ በርካታ የመንግሥት አሠራሮች ሚስጥራዊ ሆነዋል፡፡ ችግሮች ተከስተው ጥያቄ ሲቀርብ አመርቂ ምላሽ አይገኝም፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ መገናኛ ብዙኃን የመንግሥትን ጠንካራ ጐን ብቻ ሲያነፈንፉ፣ ቁጥራቸው እየተመናመነ የመጣው የግል መገናኛ ብዙኃን በቂ መረጃ እያገኙ አይደሉም፡፡ በዚህም ምክንያት ከሚጠበቅባቸው በታች ወርደው እየሠሩ ነው፡፡ ያገኙትን መረጃ እንኳን በማተሚያ ቤት በሚፈጠር ተደጋጋሚ መዘግየት ወቅታቸውን ጠብቀው አያወጡም፡፡ ይኼ የአገር ችግር ሆኖ ሳለ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የመንግሥት ባለሥልጣን የለም፡፡ ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በዚህ መሀል መረጃ የማግኘት መብት ያለው ሕዝብ እየተጐዳ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት እየተጣሰ ነው፡፡ በእርግጥ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚጐዱ መረጃዎች በአደባባይ በግልጽ ይነገሩ የሚል ጭፍን አመለካከት ሊኖር አይገባም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ጉዳዮች ሲነሱ ዳር ድንበራቸው ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ከዚያ በመለስ ያሉ የመንግሥት አሠራሮች፣ የፖሊሲ አቀራረጾች፣ የሕግ አወጣጦችና ተግባራዊነታቸው በግልጽ ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት፡፡ አንዳንድ የተዛቡ መረጃዎች ሲወጡ መንግሥት በግልጽ ለሕዝብ የማስረዳት ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር እጦት ሲሰቃይ፣ የአገሪቱ ሀብት በሙሰኞች ሲዘረፍ፣ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ ትልልቅ የፖሊሲ ውሳኔዎች ሲኖሩና ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶችን በግልጽ ሕዝብ ይወቃቸው፡፡ በሹክሹክታና በአሉባልታ የሚሰሙ ጉዳዮች ሲያጋጥሙም መንግሥት ወጣ ብሎ እውነታውን ማስረዳት አለበት፡፡ ሕዝቡ አማራጭ የመረጃ መንገዶቹ መሰናክል ሲበዛባቸው መንግሥት ሕመሙ ይሰማው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እያጋጠመ ነው፡፡ አስመጪዎችና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ዜጐች ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተሟጦ አልቋል? ወይስ የውጭ ምንዛሪ ለተወሰኑ አንገብጋቢ ጉዳዮች እየዋለ ነው? የውጭ ምንዛሪ ክምችቱስ አስተማማኝ ነው? ችግር አለ? አገሪቱ በሕጋዊ መንገድ የምታገኛቸው የውጭ ምንዛሪዎች በአግባቡ እየገቡ ነው? ወይስ የጥቁር ገበያ ሰለባ ሆነዋል? የአገሪቱ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ አያያዝና አጠቃቀም ይዞታ ይመረመራል? ክትትል ይደረግበታል? የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ መንስዔ ምንድነው? ችግር ካለስ ለመፍትሔው ምን ታስቧል? ሕዝብ የማወቅ መብት አለው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነውና፡፡ አገሪቱ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የነዳጅ ዘይት በመፈለግ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ፍለጋም በዚህ ዘመን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ይህ ጥረት ቢቀጥልም ቁርጥ ያለ ነገር አልተገኘም፡፡ ያም ሆኖ ግን አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የጋዝ ክምችት አግኝታለች ተብሎ ‹‹የብራ መብረቅ›› ዓይነት መረጃ ሲወጣ፣ መንግሥት ነውም አይደለምም ሲል አልተደመጠም፡፡ የነዳጅ ጉድጓድ መቆፈሪያ ማሽን ባልተተከለበት አገር ውስጥ ጋዝ በብዛት ተገኘ ሲባል የተነገረውን መልካም ዜና ማረጋገጥ፣ ካልሆነም ቆይ ተረጋጉ ማለት ያለበት ማን ይሆን? መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይም በግልጽነት ወደ ሕዝቡ መቅረብ አለበት፡፡ ይህም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ቀደም ሲል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በየሁለት ወራት የመንግሥታቸውን አሠራር በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ይሰጡ ነበር፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትም በየሳምንቱ በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መግለጫ ይሰጥ ነበር፡፡ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲከናወን እነዚህ ሁለት ጋዜጣዊ መግለጫዎች ጠቃሚ ነበሩ፡፡ ከሞላ ጐደልም መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ፍንጮች ይታዩ ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ከመደበኛው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ውጪ መንግሥት ምን እየሠራ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ማብራሪያም መግለጫም መስጠት ተረስቷል፡፡ በሕዝቡ ዘንድም ለሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ እየተገኘ አይደለም፡፡ ውኃ ከሳምንት በላይ ይጠፋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል በየቀኑ ይቆራረጣል፣ ለቀናትም ይጠፋል፡፡ የሞባይል ስልክ ኔትወርክና ኢንተርኔት በጣም ያስቸግራሉ፡፡ የትራንስፖርት ችግሩ የባቡር አገልግሎት እስኪጀመር ድረስ አሁንም ፈተና ነው፡፡ የበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ቢሮክራሲ ያስመርራል፡፡ ሙሰኞች በዝተዋል፡፡ በርካታ አቤቱታዎች አሉ፡፡ ቅሬታ ሰሚ ግን አልተገኘም፡፡ የሕዝቡን ሕገ መንግሥታዊ መብት ማን ያክብር? እነዚህ ከላይ የተነሱት ችግሮች ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ በመሆናቸው አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ጥንካሬ አስተማማኝ አይደለም፡፡ በኃላፊነት የሚቀመጡ ተሿሚዎች አቅም ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ መንግሥት በሕዝብ ግንኙነት ተቋሙ አማካይነት በብቃት መንቀሳቀስ ካልቻለ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን ካቃተው ችግር ነው፡፡ መንግሥት በእርግጥም ተጠሪነቱ ለሕዝብ መሆኑን በተግባር ያረጋግጥ፡፡ ይህንንም ማረጋገጥ የሚችለው አሠራሩን ግልጽ ሲያደርግ ብቻ ነው!
- Advertisment -
- Advertisment -