በኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኘውን የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ የሚመራና የሚያግዝ፣ ብሔራዊ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ እየተቀረፀ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብርሐቱ መለስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱን የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍ የኢንዱስትሪውን ዕድገት የሚያግዝ ብሔራዊ የሲሚንቶ ልማት ስትራቴጂ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመቅረፅ ላይ ይገኛል፡፡ ስትራቴጂው ካለፈው ሐምሌ 2006 ዓ.ም. ጀምሮ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአዳማ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ዶ/ር መብርሐቱ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር መብርሃቱ ገለጻ፣ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ያሉበት ዋና ዋና ችግሮች ከፍተኛ የሆነ የምርት ወጪ፣ የገበያ ውስንነት፣ የትራንስፖርት ችግርና የማሸጊያ ምርቶች በአገር ውስጥ አለመመረት ናቸው፡፡ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች አጠቃላይ ወጪ 60 በመቶ የሚወጣው ለኃይል መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር መብርሐቱ፣ አብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች በኃይል ምንጭነት የሚጠቀሙት የድንጋይ ከሰል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች የድንጋይ ከሰል ክምችት ቢኖርም፣ እስካሁን ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ምክንያት ሲሚንቶና ሌሎችም ፋብሪካዎች ከውጭ በማስገባት ይጠቀማሉ፡፡ ይህም የማምረቻ ወጪያቸውን ያንረዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥም ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከፍተኛ የሲሚንቶ እጥረት ተከስቶ ከውጭ ሲሚንቶ ይገባ ነበር፡፡ መንግሥት የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ማበረታቻ በመስጠቱ በጥቂት ዓመታት በርካታ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ተገንብተዋል፡፡ ሰባተኛው የአፍሪካ የሲሚንቶ ንግድ ጉባዔ ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በተከፈተበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ዶ/ር መብርሐቱ፣ በአሁኑ ወቅት በሲሚንቶ ምርት የተሰማሩ 18 ኩባንያዎች መኖራቸውን፣ አጠቃላይ ዓመታዊ የማምረት አቅም 11.2 ሚሊዮን ቶን መድረሱን፣ በትክክል እየተመረተ ያለው ግን 5.47 ሚሊዮን ቶን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሲሚንቶ ኢንዱስትሪው እያመረተ ያለው ካለው ጠቅላላ አቅም 50 በመቶ ብቻ እንደሆነ፣ ይህም ከዓለም አማካይ የምርት አቅም አጠቃቀም (60 በመቶ) ሲነፃፀር አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ያለው የማምረት አቅም ከፍላጎቱ በላይ በመሆኑ ተጨማሪ ገበያ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱ አጠቃላይ የሲሚንቶ የማምረት አቅም በ2016 ዓ.ም. 17.15 ሚሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካና ሐበሻ ሲሚንቶ ወደ ገበያ ሲገቡ ከፍተኛ ትርፍ ምርት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 2.5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም እንደሚኖረው ሲጠበቅ፣ በቅርቡ የሙከራ ምርት ጀምሯል፡፡ ሐበሻ ሲሚንቶ በዓመት 1.4 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም እንደሚኖረው በመጪው ዓመት ምርት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት ያለውን የገበያ ውስንነት በመመልከትና የዋጋ ጦርነት እንዳይነሳ በመሥጋት፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ለጊዜው እንዳይሰጥ ዕግድ ጥሏል፡፡ ዕግዱ ጊዜያዊ እንደሆነና ገበያው እየታየ እንደሚነሳ የተናገሩት ዶ/ር መብርሐቱ፣ ገበያ የማነቃቃት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ በመዘጋጀት ላይ ያለው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ይህንና ሌሎች በርካታ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጉባዔውን በክብር እንግድነት የከፈቱት የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ መንግሥት በማካሄድ ላይ ያለው የመንገዶች፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የባቡር መስመሮችና የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ከፍተኛ የሲሚንቶ ፍላጐት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ዓመታዊ የሲሚንቶ ፍላጐት ሰባት ሚሊዮን ቶን መድረሱን የጠቆሙት አቶ መኩሪያ፣ የማምረት አቅም ከፍላጐቱ ቢበልጥም የሲሚንቶ ዋጋ አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ዋና ግብዓት የሆነው የሲሚንቶ ዋጋን ለመቀነስ መሥራት እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 7.4 በመቶ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን፣ ዘርፉ በየዓመቱ 30 በመቶ በማደግ ላይ ይገኛል፡፡ የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ዝግጅት በቅርቡ ተጠናቆ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በጉባዔው ላይ ገለጻ ያደረጉት የዳንጐቴ ሲሜንት የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ክልል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር አልበርት ኮርኮስ፣ ዳንጐቴ ሲሜንት ሲሚንቶ ፋብሪካ ባቋቋመባቸው አገሮች 60 በመቶ ገበያውን የመቆጣጠር ዕቅድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ዳንጐቴ ሲሜንት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ17 የአፍሪካ አገሮች የሲሚንቶ ፋብሪካ የገነባ ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የሲሚንቶ ምርት አቅራቢ ኩባንያ መሆኑ ይነገራል፡፡ ኩባንያው አፍሪካ ውስጥ በአጠቃላይ በዓመት 50 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህን እ.ኤ.አ. በ2017 ወደ 60 ሚሊዮን ቶን ከፍ የማድረግ ዕቅድ ሰንቋል፡፡ ሚስተር ኮርኮስ በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተ ልማት፣ የኃይል እጥረት፣ የሠለጠነ የሰው ኃይልና የትራንስፖርት አቅርቦት ችግሮች እንዳሉ ጠቁመው፣ ኩባንያቸው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ በቂ የጭነት ተሽከርካሪዎች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ባለመኖራቸው ዳንጐቴ የራሱን የትራንስፖርት ክፍል ለማቋቋም መገደዱ ተገልጿል፡፡ ዳንጐቴ ሲሜንት በናይጄሪያ 7,000 የጭነት ተሽከርካሪዎች እንደሚያስተዳድር የጠቀሱት ሚስተር ኮርኮስ፣ በኢትዮጵያ ለገነባው ፋብሪካ 600 የጭነት ተሽከርካሪዎች ለማስገባት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ የመጀመርያዎቹ 300 ተሽከርካሪዎች በዚህ ወር መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ አስታውቀዋል፡፡ ዳንጐቴ ሲሜንት በኢትዮጵያ ለገነባው ፋብሪካ የሲሚንቶ ከረጢቶችን ከሳዑዲ ዓረቢያ እንደሚያስገባ፣ በቀጣይ ግን እዚሁ የሲሚንቶ ከረጢት ማምረቻ ሊያቋቁም እንደሚችል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ዓመታዊው የአፍሪካ የሲሚንቶ ንግድ ጉባዔ ‹‹ሴንተር ፎር ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ›› በተሰኘ የሲንጋፖር ኩባንያ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ጉባዔው በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ ናይጄሪያዊው ቢሊየነር ሚስተር አሊኮ ዳንጐቴ ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጉባዔው በኢትዮጵያ የተዘጋጀው ከኢንዲስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መሆኑ ታውቋል፡፡ ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባዔ ከ150 በላይ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በሙገር ከተማ አቅራቢያ የተገነባው የዳንጐቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተጐብኝቷል፡፡