ሊጠናቀቅ ስምንት ጨዋታ የቀረው የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባልተለመደ መልኩ እያሳየ የሚገኘው ትዕይንት ለብዙዎች አነጋጋሪ ሆኖ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ከመርሐ ግብር አወጣጥ እስከ ሜዳ ቅያሬ፣ ከተጨዋቾች አቅም መዋዥቅ እስከ አሠልጣኞች ስንብት የዘንድሮ ፕሪሚየር ሊግ ዓበይት ክስተቶች ሆነዋል፡፡ ወትሮም ቢሆን በውድድር መርሐ ግብር አወጣጥ ችግር የማያጣው ሊግ፣ ዘንድሮ አገሪቱ ባስተናገደችው የ12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ምክንያት ለዕድሳት በተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም ምትክ ክለቦች የአበበ ቢቂላን ስታዲየም ለመጠቀም ተገደው ነበር፡፡ ይሁንና በአንዳንድ ክለቦች አቋም ላይ የሜዳ ለውጡ ያሳደረው ተፅዕኖ ስለመኖሩ አሠልጣኞችና ተጨዋቾች ሲናገሩ መደመጡ ይታወሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ዘንድሮ በተለየ ሁኔታ እየታየና እየተከሰተ ያለው የአሠልጣኞች ሹም ሽር የበለጠ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ እስካሁን ድረስም ከግማሽ በላይ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ይህንን ሹም ሽር ሲያካሄዱ በቀጣይም የሚጠበቁ ተመሳሳይ ክስተቶች ሊስተናገዱ እንደሚችሉም እየተነገረ ይገኛል፡፡ የአሠልጣኝ ሹም ሽር በየትኛውም አገር ሊግ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የታየው ግን ለየት ያለ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ከነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ፕሪሚየር ሊጉን ከሁለት አሠርት በላይ እንደተከታተሉ የሚናገሩት አቶ ሽፈራው ተክሌ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለይም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ክለቦች ለውጤታቸው መበላሸት እንደ ሙያ አሠልጣኝ የመጀመርያው ተጠያቂ መሆኑ ባይካድም፣ ግን ደግሞ አሁን ላለው የእግር ኳስ ውድቀት የአሠልጣኝ ስንብት ብቻውን መፍትሔ ተደርጎ መወሰዱ ትክክል እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ አስተያየት ሰጪ እንደመከራከሪያ የሚያነሱት በሌላው ዓለም የአሠልጣኝ ሹም ሽር በዋናነት ከክለቡ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴና ውጤት ማጣት ጋር የተቆራኘ ሲሆን፣ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግን እየታየ ያለው ሁኔታ ከራሳቸው ከክለቦቹ መዋቅራዊ ብልሽት ጋር የሚያያዝ እንደሆነ በአደባባይ እየተነገረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በውድድር ዓመቱ አሠልጣኝ ካሰናበቱት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ውስጥ በዚሁ ውድድር ዓመት ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ወልዲያ ከነማ፣ ሐዋሳ ከነማ፣ ደደቢት፣ አርባ ምንጭ ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ዳሽን ቢራ ይጠቀሳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ሌሎችም በተመሳሳይ አሠልጣኞቻቸውን በከባድ ማስጠንቀቂያ ያለፉ ስለመሆኑም የሪፖርተር ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ ከ14 የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሰባቱ የአሠልጣኝ ለውጥ ማድረጋቸውን እንደሰሙ የሚናገሩት አቶ ሽፈራው፣ ክስተቱ በደፈናው በአሠልጣኞች ላይ ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔን ከማስተላለፍ ጋር ይገናኛል፡፡ ምክንያቱም፣ ‹‹አሠልጣኞች አንድ ቡድን የሚፈልገውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴም ሆነ ውጤትን ለማሻሻል ጊዜ ሊወስድባቸው ግድ ነው፡፡ ይህንን የምልበት ምክንያት ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት የአገሪቱ ክለቦች በዕድሜ አንጋፋዎቹን ጨምሮ ማንም ሰው ሊክደው የማይችል የመዋቅር ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ መሬት ባለበት የተጨዋቾች ጥራት በራሱ ይህንን ጊዜ ሊያሳጥረውም፣ ሊያስረዝመውም ይችላል፡፡ ይኼ ከግምት ባልገባበት ሁኔታና ሥርዓት በዘፈቀደ አሠራር አሠልጣኞች ብቻ ሳይሆን የክለቦቹ አስተዳደራዊ መዋቅር ጭምር ሊያዩት ይገባዋል፤›› ይላሉ፡፡ ሌሎች ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጭዎች፣ መፍትሔው አሠልጣኝ ማሰናበት ብቻውን አማራጭ እንደማይሆን፣ ቀድሞ የጓዳን ሥራ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ይገልጻሉ፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ 28 ነጥብ ይዞ በአራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ቡድናቸው በቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ጥላሁን መንገሻ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ከውጤት ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተጨባጭ ለኢትዮጵያ ቡና ውጤት አሠልጣኝ ጥላሁን በብቸኝነት ተጠያቂ መሆን ይችላል ወይ? ለሚለው ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ‹‹አሠልጣኝ ጥላሁን እንደ ዋና አሠልጣኝነቱ የመጀመርያው ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በቀጣይ ግን ክለቡ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከተጨዋቾች ጭምር ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡ ክለቡ የአሠልጣኙን ስንብት አስመልክቶ በድረ ገጹ ባስነበበው መረጃ፣ ‹‹አሠልጣኝ ጥላሁን በ2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ቡናን ለማሠልጠንና ለውጤት ለማብቃት ነው ቡድኑን የተረከበው፡፡ እስካሁን ባለው ሒደት ግን የሚጠበቅበትን ውጤት ማምጣት አልቻለም፡፡ ክለቡ ከዚህ በፊት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ሲሆን፣ አሁን በይፋ ከዋና ቡድን አሠልጣኝነቱ ተነስቷል፤›› ይላል፡፡ በምትኩ የቡድኑ ምክትል አሠልጣኝ አንዋር ያሲን የአሠልጣኝነቱን ኃላፊነት ተረክቦ እንደሚቀጥልም መረጃው ይፋ አድርጓል፡፡ ሌላው ከትናንት በስቲያ (ሚያዝያ 5 ቀን 2007 ዓ.ም.) የክለቡን ዋና አሠልጣኝ አቶ ሳምሶን አየለን ስንብት ይፋ ያደረገው ዳሸን ቢራ ይገኝበታል፡፡ ክለቡ በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ውስጥ በስፋት ከተሳተፉ አንዱ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በፕሪሚየር ሊጉ 17 ነጥብ ይዞ በወራጅ ቀጣና ውስጥ ሲገኝ ደረጃውም አሥረኛ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ዘገባ ተጠናቅሮ ለኅትመት እየተዘጋጀ ባለበት ማክሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን የ18ኛው ሳምንት ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኤሌክትሪክ ከሙገር ሲሚንቶ፣ ክልል ላይ ወልዲያ ከነማ ከሐዋሳ ከነማ ይጫወታሉ፡፡ የአሠልጣኙን ስንብት አስመልክቶ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ መክብብ ዓለሙ፣ ‹‹የቡድኑ ውጤት ሁለተኛው ግማሽ የውድድር ጊዜ ላይ ይሻሻል ተብሎ ሲጠበቅ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ አቻ ሲወጣ፣ በሦስቱ ሽንፈትን አስናግዷል፡፡ በዚህም አሠልጣኙ ውጤቱን እንዲያሻሽል ተደጋጋሚ ተግሳፅና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ በሠለጠነው ዓለም በአንድ ቡድን ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ ተደጋጋሚ የውጤት ቀውስ ሲፈጠር አሠልጣኞች በራሳቸው ጊዜ መልቀቂያ ያስገባሉ፤ በእኛ አገር ግን በግዳጅ ካልሆነ አልተለመደም፡፡ በመሆኑም ክለቡ ህልውናውንም ለማስጠበቅ አሠልጣኙን ለማሰናበት ተገዷል፤›› ብለዋል፡፡