Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል​​​​​​​አደጋ ያንዣበበት ለገኦዳ

​​​​​​​አደጋ ያንዣበበት ለገኦዳ

ቀን:

‹‹የበረሀዋ ንግሥት›› ድሬዳዋ እንደ ወትሮዋ ሞቃታማ ሆናለች፡፡ እንደሚነገርላት ሞቅ ባለ አቀባበል እንግዶቿን ለማስተናገድ ማልዳ የነቃች ይመስላል፡፡ ረፋድ ላይ፣ የከተማዋን ስም ከሚያስጠሩ መስህቦች መካከል የለገኦዳ የዋሻ ሥዕሎችን ለመመልከት ከከተማዋ 38 ኪሎ ሜትር ርቀን መጓዝ ነበረብን፡፡ በመንገዳችን አልፎ አልፎ ከብት ከሚነዱ ታዳጊዎችና የድንጋይ ካብ ቤቶች ውጭ ብዙም አይታይም፡፡ በቅርብ ርቀት ሰንሰላታማ ተራራዎችና የተመልካችን ልብ የሚያሸብሩ ረዣዥም ገደሎች አሉ፡፡

 ወደ ለገኦዳ ዋሻ መዳረሻ ከሚገኝ ገደል ሥር ካለ ወንዝ ውኃ ለመቅዳት ቁልቁለቱን ያላንዳች ፍርኃት ይወርዱ የነበሩ ሴቶች ብዙ ናቸው፡፡ ያደፈ ልብስ ለብሰው በባዶ እግራቸው ወዲያ ወዲህ የሚሉ ሕፃናት ወደ አካባቢው የሚሄዱትን ፀጉረ ልውጦች በትኩረት ያስተውላሉ፤ እየተከታተሉ ውኃ መጠጫ ላስቲክ እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡

ለገኦዳን ከውጭ ሲመለከቱት ወደ አንድ ጎን የሾለ ነው፡፡ እርስ በርሳቸው የተደራረቡ ድንጋዮች በርካታ ስለሆኑ ለግዙፉ ዋሻ ግርማ ሞገስ ሰጥተውታል፡፡ ለዋሻው ጥቂት ሜትሮች ክፍተት ተትቶ ዙሪያው በሽቦ ታጥሯል፡፡ ከአጥሩ ውጪ ሳር የሚግጡ እንስሳትና የአካባቢው ነዋሪችም ጥቂት አይደሉም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ1920ዎቹ አካባቢ በተመራማሪዎች ዕውቅና ያገኙት የዋሻው ሥዕሎች ከ6,000 ዓመት በላይ ዕድሜ እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ሥዕሎቹ ወደ 600 የሚጠጉ ሲሆን፣ የቤትና የዱር እንስሳት፣ የመገልገያ ቁሳቁሶችና የሰዎችም ምሥሎች ይገኙበታል፡፡ ፍየል፣ ዝሆን፣ ግመልና ሌሎችንም እንስሳት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በብዛት በቀይ፣ በግራጫና በቢጫ ቀለማት ከተሠሩት ሥዕሎች መካከል ፊደል የሚመስሉ ቅርጾችም ይታያሉ፡፡

የሰው ዘር መነሻ በሆነችው ኢትዮጵያ መሰል ዕድሜ ጠገብ የዋሻ ሥዕሎችና ሌሎችም የጥበብ ውጤቶች የሚገኙበት  አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ተቀዳሚ ቦታ የሚሰጣቸው ቅሪተ አካሎች የተገኙበት አፋር ክልል ለድሬዳዋ ቅርብ መሆኑ ለገኦዳን የመሰሉ ጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች በአካባቢው መገኘታቸውን ምክንያታዊ ያደርገዋል የሚሉ ተመራማሪዎች አሉ፡፡

ቦታውን በጎበኘንበት ወቅት ከሥዕሎቹ መካከል ከፊል አካላቸው የደበዘዘ ተፈርክሶ የጎደለም አይተናል፡፡ ሥዕሎቹ በቂ ጥበቃ እየተደረገላቸውም አይደለም፤ ለሰው ሠራሽና የተፈጥሮ እክሎችም ተጋርጠዋል፡፡

እንደተገለጸልን፣ ሥዕሎቹን ለአደጋ ካጋለጡት ምክንያቶች አንዱ ወደ አካባቢው የሚሄዱ አንዳንድ ጎብኚዎች ደንታቢስነት ነው፡፡  ሥዕሎቹ ረዥም ዘመን ስላስቆጠሩና የተሣሉትም በድንጋይ ላይ በመሆኑ አቧራ ስለሚለብሱ በግልጽ አይታዩም፡፡ ጎብኝዎች ሥዕሎቹ በግልጽ እንዲታዩዋቸውና ፎቶግራፍ ለማንሳት እንዲመቻቸው ውኃ ይደፉበታል፡፡ በዚህ ምክንያት የሥዕሎቹ ቀለም እየደበዘዘ ነው፡፡

በሰዎች ሳቢያ ከሚደርሰው ጉዳት የአካባቢው ነዋሪዎች ዋሻው ላይ ጭስ መልቀቃቸው ይነሳል፡፡ ዋሻው አናት ላይ ቤት የሚሠሩ ንስሮችና ሽኮኮዎችም በዋሻው ይፀዳዳሉ፡፡

በአካባቢው ያሉ የቤትና ዱር እንስሳትም በቦታው ስለሚፀዳዱ ሥዕሎቹ የቀደመ ይዘታቸውን እያጡ ነው፡፡ ዋሻው በዚሁ ከቀጠለ ሥዕሎቹ ሊጠፉ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ተመራማሪ  ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ እንደሚናገሩት፣ ዋሻው የበርካታ ተመራማሪዎች መዳረሻ መሆን የሚችልበት አቅም ቢኖረውም በቂ ጥናትና ምርምር ተደርጎበታል ለማለት አይቻልም፡፡ ዋሻው ጥበቃ እየተደረገለት ለምርምር ቢመቻች ከሥዕሎቹ በተጨማሪ ሌሎች ታሪካዊ ግኝቶች ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ ዋሻው ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ቢኖሩም ተደራሽነታቸው ውስን እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ጥናቶቹ የሚዳረሱበት መንገድ ከሰፋ ለዋሻው ጥበቃ የሚያደርጉ ተቋሞች የበለጠ ትኩረት ይሰጡት ይሆናል ይላሉ፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ አንድ ጫፍ ተነስተን ወደ ሌላው ስንሄድ በርካታ የዋሻ ሥዕሎች እናገኛለን፤ አሳሳቢው እንክብካቤ እየተደረገላቸው አለመሆኑ ነው፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፣ በተለይ ለገኦዳ ትኩረት ካልተቸረው፣ ሥዕሎቹ በቅርብ መጥፋታቸው አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡

ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ታሪክ ሁነኛ ቦታ እንደሚሰጣቸው የሚናገረው በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህር ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ነው፡፡ ሥዕሎቹ ከጊዜ ብዛት በተፈጥሯቸው ይዘታቸውን እየቀየሩ ቢሄዱም በቸልተኝነት ከሚደርስባቸው አደጋ መከላከል ዕድሜያቸውን ያራዝመዋል ይላል፡፡ ሥዕሎቹ በኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ታሪክ ያላቸው አስተዋጽኦ በተመራማሪዎች መጠናት እንዳለበት ገልጾ፣ የጥናቶቹ ውጤቶች ቢሰነዱ አሻራቸው ለዘመናት እንዲዘልቅ ያግዛል ይላል፡፡

ጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች ለዘመናዊ ሥነ ጥበብ ዕድገት መሠረት እንደሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ፡፡ የዋሻ ሥዕሎች በዘመናት ሒደት ለጽሑፍ ቋንቋ መፈጠር መነሻ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ ስለለገኦዳ ሥዕሎች ያብራራልን ሠዓሊ አገኘሁ ሥዕሎቹ የሚያሳዩትን ሰው፣ እንስሳ ወይም ቁስ አካል ሙሉ በሙሉ ባያንፀባርቁም በግልጽ የተቀመጡ ናቸው ይላል፡፡  እንዲተላለፍ ወደተፈለገው መልዕክት ወይም እንዲታይ ወደተፈለገው ቁስ በቀጥታ የሚወስዱ እንደሆኑና ተቀጥላ ነገሮች አለመካተታቸው ሥዕሎቹን ለዕይታ እንዳቀለላቸው ይገልጻል፡፡

‹‹ሥዕሎቹ የወቅቱ ማኅበረሰብ አረዳድ ከፍ ያለ እንደነበር ያሳያሉ፤›› በማለት ሥዕሎቹን ይገልጻቸዋል፡፡ በዓለም በዋሻ ሥዕሎች አሳሳል ዘዬ የተሳቡ ታዋቂ ሠዓልያን እንዳሉ በማንሳት፣ ከኢትዮጵያ በዋሻ ሥዕሎች ጥናት ካደረጉ መካከል እስክንድር ቦጎስያንና መሰል ዘዬ በሥራዎቹ የሚስተዋለውን ሠዓሊ መስፍን ታደሰን ይጠቅሳል፡፡

በድሬዳዋ አቅራቢያ ጥንታዊ ሥዕሎች ከሚገኙባቸው ዋሻዎች መካከል ፓርክ ኢፒክ ዋሻ፣ ሒንኩፍቱ ዋሻና ጎዳ አጀዋ ዋሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ፓርክ ኢፒክ ከድሬዳዋ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለ ሲሆን፣ ዝሆን፣ አንበሳና ጅብን የመሰሉ የዱር እንስሳት ሥዕሎችና ጥንታዊ የሰው ልጅ መገልገያ ቁሳቁሶች በዋሻው ተገኝተዋል፡፡

ስለ ሒንኩፍቱ ዋሻ የተሠራ በቂ ጥናት ባይኖርም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች በውስጡ  በደማማቅ ቀለማት የተሳሉ ሥዕሎች እንዳሉና ውስጥ ለውስጥ ረዥም ርቀት እንደሚያስጉዝ ይናገራሉ፡፡ ከድሬዳዋ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለው ጎዳ አጀዋ እንደ ሌሎቹ ዋሻዎች ልዩ ልዩ ዘዬ ያላቸው ሥዕሎችና ጽሑፎች የሰፈሩበት ነው፡፡

ስለዋሻ ሥዕሎች አያያዝ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር የባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል ምርምር ባለሙያው አቶ ኤርሚያስ ታደሰን አነጋግረናል፡፡ አቶ ኤርሚያስ የአስተያየት ሰጪዎችን ሐሳብ ይጋራል፡፡ ‹‹በዕድሜ ብዛትና በተፈጥሮ ሥዕሎቹ የተወሰነ ቢደበዝዙም በሰዎች እየደረሰበት ያለው ጉዳት ያመዝናል፤›› ይላል፡፡ ሥዕሎቹ የአገሪቱን ስም በዓለም ሊያስጠሩ የሚችሉ ቅርሶች እንደመሆናቸው ሊጠበቁ ይገባል ሲል ይገልጻል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ቢሮው በቂ በጀት መድቦ ዋሻው ጥበቃ ሊደርግለት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የአካባቢው ማኅበረሰብ ግንዛቤ መዳበር አለበት፡፡

በሱ እምነት፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ዋሻውን እንደ ሀብታቸው ቆጥረው ጥበቃና እንክብካቤ ካላደረጉለት ቢሮውም ይሁን ሌሎች ተቋሞች የሚሠሩት ሥራ ምሉዕ አይሆንም፡፡ ነዋሪዎች በዋሻው ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ጥረት ያላደረጉት ስለ ዋሻው ስላልተገነዘቡና አንዳች ጥቅም ስለማያገኙበት እንደሆነ የሚያስረዳው ኤርሚያስ፣ ዋሻው ለነዋሪዎቹ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ቢቻል ችግሩ እንደሚቃለል ይናገራል፡፡

‹‹የአካባቢው ነዋሪ ዋሻው የራሱ ሀብት እንደሆነ ተሰምቶት እንክብካቤ እንዲያደርግለት ከዋሻው ተጠቃሚ የሚሆንበት መንገድ ቢፈጠር የጥበቃ እንቅስቃሴውን ያግዛል፤›› በማለት የሚያስረዳው ባለሙያው፣ ሥዕሎቹ ቢጠፉ አገሪቱ የምታገኘው ገቢ ከመቀነሱ በላይ የጠለቀ ጥናት ተሠርቶ የሚገኙ አዳዲስ ውጤቶችን ያስቀራል ይላል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለገኦዳን በቅርስነት መዝግቦታል፡፡ አቶ ኤርሚያስ መመዝገቡ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው መንገድ እንደሚከፍት ያምናል፡፡ ቢሮው ባደረገው ጥናት መሠረት ድሬዳዋ ውስጥ ከሚጎበኙ ሥፍራዎች ዋሻው ዋነኛ እየሆነ መጥቷል፡፡

በተለያዩ አገሮች ያሉ የዋሻ ሥዕሎች የጥናትና ምርምር እንዲሁም ጉብኝት መዳረሻ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ስለሚገኙ የዋሻ ሥዕሎች በጥልቅ የሚያስረዳው ትረስት ፎር አፍሪካን  ሮክ አርት ድረ ገጽ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የዋሻ ሥዕሎች ሰውና እንስሳት ላይ ማተኮራቸው ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል ሲል ያትታል፡፡ 23,000  ዓመታት ያስቆጠረው የናሚቢያውን አፓሎ 11 ዋሻ፣ 3,000 ዓመታት ያስቆጠረው የደቡብ አፍሪካው ኩክሀላምን ዋሻና 5,000 ዓመት ያስቆጠረው የሶማሊያው ላስገል ዋሻ ይጠቀሳሉ፡፡

የደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ በአንድ ወቅት ‹‹የአፍሪካ የዋሻ ጥበብ የሁሉም አፍሪካውያን የጋራ ቅርስ ከመሆኑ ባሻገር የሁሉም የሰው ልጅ ቅርስም ነው፤›› ብለው ነበር፡፡

 

 

       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...