Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ባለሀብቱን ‹‹የጋብቻ ያህል›› ያቆራኘው የአሉሚንየም ኢንቨስትመንት

አቶ ብሩክ ኃይሌ የሥነ ሕንፃ (አርክቴክት) ባለሙያ ሲሆኑ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአውቶሞቲቭ ምህንድስና በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በብረታ ብረት የትምህርት ክፍል (ሜታለረጂ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይዘዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በከተማ ልማት (Urban Develoment) የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ አቶ ብሩክ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት በአሉሚንየም ሥራ ላይ ተሰማርተው በመንግሥታዊና የግል ድርጅቶች ሠርተዋል፡፡ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሮዥን የተባለ የአሉሚንየም ፋብሪካ ገንብተዋል፡፡ በሥራዎቻቸው ዙሪያ ዮናስ ዓብይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የዶክትሬት ዲግሪዎን እየሠሩ እንደሆነ ይሰማል፡፡ ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርትዎን የቀጠሉት ከዚሁ ከአሉሚንየም ጋር ይገናኛል?

አቶ ብሩክ፡- አሁን የፒኤችዲ ትምህርቴን የከተማ ልማት በምንለው ዘርፍ ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ከዚሁ ከሥነ ብረት የጥናት መስክ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በዋነኝነት የሜታለረጂ ጥናት ወይም የሙያ ዘርፍ በከተማ ልማት ላይ በሚኖረው አስተዋጽኦ ላይ ያተኩራል፡፡ በእርግጥ አሁን ካለሁበት የሥራ ባህሪ ጋር ባለብኝ ኃላፊነት የፒኤችዲ ሥራዬን የመጀመርና የማቋረጥ ሁኔታ ስላለብኝ መጨረስ ካለብኝ ጊዜ ትንሽ እየተራዘመብኝ ነው፡፡ አሁን ግን በአብዛኛው እየተገባደደ ስለሆነ በቅርብ ጊዜ እጨርሳለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የእርስዎና የአሉሚንየም ትስስርዎ በምን ሁኔታ ነበር የጀመረው፡፡ አሁን ያላችሁ ቁርኝት እንዴት ሊታይ ይችላል?

አቶ ብሩክ፡- እኔና አሉሚንየየም ያለን ቁርኝት የጋብቻ ነው ሊባል ይችላል፡፡ አሉሚንየም ለእኔ ምን እንደሆነ ለመግለጽ ይቸግረኛል፡፡ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ቁርኝታችን እስከ ዛሬ ድረስ ዘልቋል፡፡ በእነዚህ 12 ዓመታት ውስጥ የአሉሚንየም ዕውቀትን ቆፍረን ነው የያዝነው፡፡ በማያቋርጥ ማዕበል ውስጥ ነው እያደገ ያለው ማለት እችላለሁ፡፡ እኛም በማያቋርጥ ክትትል አስፈላጊውን ዕውቀት እያገኘን ነው፡፡ ትምህርት ከጨረስኩበት ጊዜ ጀምሮ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ስሠራ በነበሩኝ አጋጣሚዎች የተለያዩ ሕንፃዎችን ዲዛይን አደርግ ነበር፡፡ በዚህ የሕንፃ ሥራዎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ ኩባንያዎች የአሉሚንየም አገጣጠምን ስመለከትና ወደ ሜታለረጂ አተኩሬ በምሠራበት ጊዜ አሉሚንየምን ወደድኩት፡፡ ይህ የብረት ዓይነት ገና ወጣት የብረት ዓይነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በጊዜው የቅንጦት ዕቃ ሆኖ የሚታይበት ወቅት ነበር፡፡ አሉሚንየምን ለቤት ግብዓት መጠቀም እንደ ቅንጦት ይታይም ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን አሉሚንየም ቅንጦት ሳይሆን መሠረታዊ ግብዓት ነው፡፡ እና አሉሚንየም ትርፍ የሚገኝበት ሥራ ሳይሆን ለእኔ ቴክኖሎጂውን አገር ውስጥ አስገብቶ ወደ ተሻለ ደረጃ መሄድና የግብዓቱ አዲስ መሆን ብዙ ነገሮችን ታሳቢ ተደርጎ ከሕይወታችን ጋር ተቀናጅቷል፡፡ አሁን አሉሚንየም ትንፋሻችንም ደማችንም ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቁርኝታችሁ ሙሉ ለሙሉ እዚሁ አገር ቤት በተገኘ አጋጣሚና ዕውቀት ብቻ ነው?

አቶ ብሩክ፡- በ1995 ዓ.ም. ሥራውን ስንጀምር አሉሚንየም ከሱዳን ነበር የምናስመጣው፡፡ ሱዳን ውስጥ አሉሚንየም ኤክስትሩዥ በስፋት ነበር ሄደን የምናስገባው፡፡ ያስገባነውንም አሉሚንየም እዚህ እየቆራረጥን፣ በተወሰነ ካፒታል ዲዛይን እናደርግ ነበር፡፡ ያንንም ዲዛይን ላደረግናቸው ሕንፃዎች እንጠቀም ነበር፡፡ በዚያም ላይ ብዙ ዕውቀት እናገኝ ነበር፡፡ ከሱዳን አልፎም ወደ ግብፅና ወደ ቱርክ በመሄድ ከቴክኖሎጂው ጋር ለመቀራረብ መልካም አጋጣሚዎች አግኝተንም ነበር፡፡ ከዚያም ማስመጣቱን በስፋት ተያያዝነውና ከኢጣሊያ፣ ከዱባይ እንዲሁም ከቻይና ካሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ጋር ኤጀንት በመሆን በሰፊው ማስመጣት ያዝን፡፡ ይህ በእንዲህ እንደቀጠለ በ2000 ዓ.ም. አንዳንድ ነገሮችን ማቀድ ጀመርን፡፡ ከአሉሚንየም ጋር ቁርኝቱ ስላለን ለምን ብረቱን እዚሁ አናመርትም በማለት ቴክኖሎጂውን ለማስገባት ተነሳን፡፡ ከዚያም በከፍተኛ የባንክ ብድር ማሽኑን እዚህ አምጥተን ተከልን፡፡ አሉሚንየም ኤክስትሩዥን ማሽኑን ተክለን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2002 ዓ.ም. አሉሚንየም በአገር ውስጥ ማምረት ጀመርን፡፡ ከዚያ ብዙ መቆየት አልቻልንም፡፡ ብዙ ተደራራቢ ችግሮች ገጠሙን፡፡ በእርግጥ ችግሮቹን ከመዘርዘሬ በፊት ስንቋቋም በአንድ ሚሊዮን ብር ካፒታል ነበር የጀመርነው፡፡ ከሱዳን ምርቱን ማስገባት ስንጀምር ማለት ነው፡፡ ፋብሪካውን እስከ ጀመርንበት ጊዜ ድረስ ባሉት ዓመታት ብዙ ትርፍ ነበረን፡፡ ነገር ግን ጊዜው ለእኛ መልካም አጋጣሚ ስለነበረው ማሽኑን በርካሽ ዋጋ ነበር ያገኘነው፡፡ በወቅቱ የዓለም ኢኮኖሚ የጋሸበበት ጊዜ ስለነበር ማሽኑን አቅማችን በሚችለው ዋጋ ነበር ያገኘነው፡፡ በአጠቃላይ ማሽኑን አስገብተን ፋብሪካውን በመትከል 100 ሚሊዮን ያህል ብር ነበር የወሰደብን፡፡

ሪፖርተር፡- በፋብሪካው ሒደት ያጋጠማችሁ ችግሮች ምን ነበሩ?

አቶ ብሩክ፡- ፋብሪካው ሥራ ጀምሮ ለስድስት ወራት ያህል ከሠራን በኋላ የተወሰኑ ችግሮች አጋጥመውን ነበር፡፡ በአሉሚንየም የምርት ሒደት ውስጥ ለግንባታ ግብዓት የሚሆን የመጨረሻ ምርትን አምርቶ ለማጠናቀቅ በተለያዩ ደረጃዎችን ያልፋል፡፡ በ2002 ዓ.ም. ብዙም መሄድ ያላስቻሉን ተግዳሮቶች ገጥመውን ነበር፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ በአገሪቱ መጀመርያ መሆናችን ራሱን የቻለ ችግር ነበር፡፡ የግብዓት እጥረት፣ በወቅቱ የነበረው ውስን የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ ከባድ የመለዋወጫ ዕቃ እጥረት፣ የቦታ እጥረት፣ የሰው ኃይል ከዚያም የገበያ ችግሮችና ተደራራቢ ፈተናዎች ነበሩ፡፡ አሉሚንየም የሀብታሞችና የቅንጡዎች ተደርጎ ይቆጠር ስለነበር ገበያ ማግኘቱ ራሱ ከባድ ፈተናም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በመመረቱ ብቻ ተቀባይነት ማግኘቱ ራሱ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮብንም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ ያመረታችሁትን ለገበያ ስታቀርቡ ተቀባይነትን ቶሎ እንዳታገኙ ያደረጋችሁ ከኅብረተሰቡ (ሸማቹ) አዲስ ነገርን ቶሎ አለመቀበል ችግር ጋር የተያያዘ ነው? ወይስ ይህ ዓይነት ችግር ከባለሙያዎች በኩልም ይታያል?

አቶ ብሩክ፡- በእኛ አገር አዲስ ነገርን ቶሎ ያለመቀበል ጉዳይ እውነት የሆነና  የሚታይ ባህሪ ነው፡፡ ለእኔም ያ ነገር ሁሌም ያስደንቀኛል፡፡ ምናልባት ይኼ ጉዳይ የሚያያዘው በብዙ ዘመናት በደብዛዛ ሁኔታ ስለቆየን ይመስለኛል፡፡ በቀደሙ ሥርዓቶች ዳፍንት ውስጥ እንድንቀመጥ ስላደረገንም ይመስለኛል፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር ተገልጦ መሥራት ቢጀመርም ያ የቀድሞው የአስተሳሰብ ውዝግቡ ዛሬም ድረስ አለ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ (አዲስ ነገር ያለመቀበል) ሙሉ ለሙሉ አይጠፋም፡፡ ለሆነ ምርት አዳዲስ ስያሜ ሲወጣለት ይታያል፡፡ ለምሳሌ ለዚህ ለአሉሚንየም ምርት የሚሰጠው ስያሜ በጣም ያስገርመኛል፡፡ በትምህርት ዓለም ውስጥ እንኳን እነዚህን ስያሜዎች አላውቃቸውም፡፡ ሌላው ቢቀር አሉሚንየምን ጥራት በማሽተት ለማወቅ አይቻልም፡፡ ወይ ደግሞ ልክ እንደ ዓመት በዓል በግ ወገቡን በመንካትና በመጨበጥ አሊያም ጥርሱን አይተህ እንደምትገዛው ዓይነት አሉሚንየምን በዚያ መንገድን ጥራቱን አትለካም፡፡ ራሱን የቻለ የጥራትና የደረጃ መለኪያ የሆነ ሳይንሳዊ መንገድ አለው፡፡ ያም ታዲያ ራሱን የቻለ ሙያዊ ብቃት ያለው የጥራት መመዘኛ ስልት አለው፡፡ ነገር ግን የእኛ ባለሙያ የተባሉት አማካሪዎቻችን ያንን ስልት አይደለም እያደረጉት ያሉት፡፡ በዚህ የተነሳ አሁን የሚታየው ነገር ውዝግብ በመሆኑ ብዥታዎቹ እያደጉ ነው የሚሄዱት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለባለሙያዎች የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖር ደንበኞች (ሸማቾችና ቤት አሠሪዎች) በአሉሚንየም ጥራት ጉዳይ ብዙም ግንዛቤ ስለማይኖራቸው ባለሙያው ለሚከፈላቸው ሥራ ትክክለኛ ነገሩን እንዲነግሩ ነው፡፡ ‹‹የእከሌ ምርት ጥሩ ነው፣ የእከሌ መጥፎ ነው›› ብለው ከመፈረጃቸው በፊት በአግባቡ የጥራት ደረጃ መስፈርቱን በሳይንሳዊ መንገድ በመፈተሽ ለደንበኞቻቸው ትክክለኛ መረጃ ቢሰጡ ለሁሉም ጠቃሚ ነው፡፡ አንድ የምርት ዓይነት የኢትዮጵያ ስለሆነ፣ የጃፓን ወይም የአሜሪካ ስለሆነ ጥራቱን አይይዝም፡፡ ጃፓን ስለተመረተ ብቻ አንድ ዕቃ ጥራት አለው ብሎ ሙሉ ለሙሉ ለመደምደም መሞከር ስህተት ነው፡፡ ትክክለኛና ሙያዊ በሆነ መንገድ መለካት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ በዚህ ዘርፍ ገበያው ጤናማ በሆነ መንገድ እንዳይሄድ የሚያደርግ አሠራር አለ ይላሉ?

አቶ ብሩክ፡- ለዚያውም ሰፊና መጥፎ የሆነ አካሄድ ነው ያለው፡፡ በዚህ ጉዳይ መንግሥት ለማስተካከል ብዙ ጥሯል፡፡ በተለይ ለግብዓቱ ጥራት መመዘኛ በግልፅ በማስቀመጥ ሊያስተካክል ሞክሯል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቤት ሠሪ የሆነ ሰው አሉሚንየም ሲገዛ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ባለሥልጣን በመሄድ ቁራጭ አሉሚንየም ወስዶ ማስመርመር ነው፡፡ ካልሆነ ደግሞ ሌላ አገር ወስዶ ማስመዘን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በሌላ መንገድ ተጠቅሞ የአንዱን ምርት ጥሩ ነው ወይም አይደለም ብሎ ለመደምደም መሞከሩ ስህተት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምናልባት በሌላ የምርት ዓይነቶች ብንመለከት የአንድ ምርት ሁኔታን ከሚወስኑ ነገሮች አንዱ የሦስተኛ ወገን ወይም የደላላ ተፅዕኖ ነው፡፡ በእናንተም በኩል ተመሳሳይ ሁኔታ አለ ማለት ይቻላል፡፡

አቶ ብሩክ፡- በአሉሙኒየም ገበያው ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ አለው፡፡ ችግሩን እየተጋፈጥን ነው፡፡ በተለይ አሁን እየተወያየን ያለው የመጨረሻ የሆነውን ተጠቃሚ ወይም ሸማቹ ላይ ነው፡፡ ሸማቹ ታዲያ ለሚያሠራው ቤት በቀጥታ መርካቶ ሄዶ ጥሩ ምርት ነው ተብሎ የተነገረውን የአሉሚንየም ዕቃ ገዝቶ መምጣት ነው የሚፈልገው፡፡ አንድ ግለሰብ ታዲያ የገዛውን ዕቃ ወደ ሚመለከተው ድርጅት ሄዶ የተዝማሚነትን ምዘና ለማስመርመር ተጨማሪ ወጪ ሆኖ ስለሚያገኘው ላይገፋበት ይችላል፡፡ አሁን አሁን መንግሥታዊ ድርጅቶች የተስማሚነት ምዘና ጉዳይ እንደመመሪያ ስለሆነባቸው ወደዚያ ሄደው በማስመርመር ነው ግዢ የሚፈጽሙት፡፡ በእርግጥ ሌሎች ትልልቅ ድርጅቶችም ይህንኑ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ነገር ግን በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ ድርጅቶችና ግለሰቦች ወጪ አውጥተው በገዙት ዕቃ ላይ ሌላ የማስመርመርያ ወጪ ማድረጉን አለመፈለጋቸው በእነሱ ላይ አያስፈርድም፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ ገንዘብ አውጥተው ለማስመርመርያ ትንሽ ወጪ ቢያወጡ በኋላ ሊኖር ከሚችለው አላስፈላጊ ኪሳራ ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ትኩረት የተሰጠውና የተሻለ ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑ ይነገራል፡፡ በተለይ ደግሞ ከውጪ የሚገባን የግንባታና ሌላ ጥሬ ዕቃ ማስቀረት ለሚችሉ ኢንቨስትመንት የተሻለ ማበረታቻ ይሰጣል፡፡ ከዚህ አኳያ ከውጪ የሚገባን አሉሚንየምን በማስቀረትና በመንግሥት በኩል ድጋፍ እየተደረገ ነው?

አቶ ብሩክ፡- በዚህ አጋጣሚ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ድጋፍ የሚመሰገን ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ተቋም ትልቅ ተቋም መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከዚሁ ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ተቋማትም አሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን በማቋቋሙ የሚገርም ሥር አድርጓል፡፡ በእኛ ዘርፍም ሆነ በሌሎቹ እየተደረገ ያለውን ሥራ ስመለከት ትክክለኛ አገራዊ ተቋም እየተፈጠረ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ለምሳሌ እኔ የምፈልገው ነግጄ ትርፍ ማትረፍን ብቻ ቢሆን ወደዚህ ተቋም መሄድ አያስፈልገኝም ነበር፡፡ ነገር ግን በኢንቨስትመንት ተሰማርቼ አገሬን መጥቀም እፈልጋለሁ ላለ ሰው የእነዚህ ተቋማት መኖር እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለብንን ችግር ለመቅፈር፣ ያለውን መደናገር ሥርዓት ለማስያዝና ለመሻሻልም ጭምር ካስፈለገን ወደ እነዚህ ተቋማት መሄድ ብቻ ነው የሚያዋጣው፡፡

ለምሳሌ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ውስጥ ሁሉም ሥራውን የሚያውቅና ባለሀብቱን ለመርዳት ደስተኛ የሆነ ባለሙያ ያሉበት ተቋም ነው፡፡ ይህ ዘርፍ አዲስ ዘርፍ ነው፡፡ ለብዙ ዘመናት አካፋና ዶማ በመሥራት የሚታወቅ ዘርፍ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ተቀይሯል፡፡ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምን እየሠራ እንደሆነ ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዘርፍ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ተቋሙ እያደረገ ያለው እገዛን ስናይ በጣም አርኪ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከመርካትም ባሻገር አዲስ ለሚመጡ ባለሀብቶችም የተሻለ ነገር እንደሚኖር ተስፋ አለኝ፡፡ አቅማቸውን አውጥተው እየረዱን ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ቀበሌ ድረስ አብረውን በመሄድ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ እንድናገኝ እያገዙን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ የብረታ ብረት ተቋም ከአምና ጀምሮ ባለሀብቶች የብረት ምርታቸውን ወደ ውጪ እንዲልኩ ጥረት እያደረገ ነበር፡፡ አሁን እናንተም ምርታችሁን ወደ ውጪ መላክ ጀምራችኋል?

አቶ ብሩክ፡- የውጪ ገበያ ስላለ የኤክስፖርት ጥያቄውን ራሳችን አቅርበናል፡፡ በተለይ በኡጋንዳና ጂቡቲ ገበያውን ስላገኘን ራሳችን ጥያቄውን በቅርቡ አቅርበናል፡፡ ከውጪም ቢሆን የግዢ ጥያቄ ቀርቦልናል፡፡ ነገር ግን እዚህ አገር ቤት ውስጥ የአሉሚንየም አቅርቦትን በተመለከተ አሁንም ጥማቱ አለ፡፡ የግንባታ ሥራው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የአገር ቤት አቅርቦቱና ውጪ መላኩን ጎን ለጎን እየሠራን ነው፡፡ ይህ ደግሞም ከውጪ የሚገባውን በአገር ውስጥ ምርት ሙሉ ለሙሉ የመተካቱ ሒደት እንዳለ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ለፋብሪካችን ጥሬ ዕቃ አቅርቦቱን በማሟላት ረገድ የብረታ ብረት ልማት ተቋሙ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እንድናገኝ እየረዳን ነው፡፡ ከኮርፖሬሽኑ ብዙ የሆነ ተረፈ ምርት የምናገኘውን በማቅለጥ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ግዢዎችና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ የምናገኘውን የአገር ውስጥ ግብዓት አጠንፍፈን በመጠቀም 97 በመቶ በላይ የሆነ አገር ውስጥ የተመሠረተ ጥሬ ዕቃ ያለበት ምርት እያመረትን ነው፡፡ በዚህም መንገድ ከውጪ የሚገባን ምርትን የመተካቱን ሥራ አጠናክረን ይዘነዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ወደ ውጪ ገበያ መላክ የሚያስችለንን አቅምንም እየገነባን ነው፡፡ ፋብሪካችንን በማስፋፋት ወራዊ ምርታችንን ከ300 ቶን በላይ ለማሳደግ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በእርግጥ እንደ ዕቅዳችን ቢሆን ከሁለት ወራት በፊት ወደ ውጪ የመላኩን ሥራ መጀመር ነበረብን፡፡ በ2008 ዓ.ም. ወደ ውጪ ገበያ መላኩን እንጀምራለን ብለን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ለጊዜው ለአሉሚንየም ምርት ብቸኛው ፋብሪካ ወይም ኢንቨስትመንት ነው ያላችሁት፡፡ ብቸኛ መሆናችሁ በገበያ ረገድ ካላችሁ የገበያ ድርሻ አንጻር የራሱ የሆነ ችግር የለውም?

አቶ ብሩክ፡- ብቸኛ መሆናችንማ ትልቅ ችግር ነው ያለው፡፡ ሌላ አጋዥ ከሌለህ፣ ካልተደራጀህና ማኅበር ከሌለህ ችግር ሲያጋጥም እንኳ በደንብ አትደመጥም፡፡ ብቻችንን በመሆናችን እኮ ነው የአገር ውስጥ ፍላጎቱን ማሟላት ያልቻልነው፡፡ እኛ ሌሎች እንዲገቡ ነው የምንፈልገው፡፡ ሌሎች ደግሞ መግባት ሲችሉ በአገር ውስጥ ምርትህን ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳል፡፡ ከገበያ ባሻገር ሁለት፣ ሦስት ስትሆን ደግሞ በማንኛውም ሁኔታ ተደማጭነት ይኖርሃል፡፡ ስትበዛ ደግሞ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖርህ አቅም ተፅዕኖ ማምጣት ስለሚችል ጥያቄአችንም ቶሎ መልስ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ያለብንንም የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት የሌሎች ባለሀብቶች መግባት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአምስት ዓመት ጉዞው በኋላ ፋብሪካው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ብሩክ፡- አሁን በአገሪቱ ትልቁን የገበያ ድርሻ ይዘናል፡፡ በአጠቃላይ በምርት አቅርቦቶች በአሉሚንየም ዘርፍ ትልቁ ተዋናዮችን ስንሆን ለማሳያ ያህል እንኳ በአገሪቱ ካሉ ታላላቅ የግንባታ ዘርፎች አንዱ ለሆነው በአዲስ አበባ እየተገነቡ ላሉት የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች የአሉሚንየም ግብዓት ሙሉ ለሙሉ የምናቀርበው እኛ ነን፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገነቡ ሕንፃዎችና ሌሎች የቦታ ግንባታዎች ከፍተኛ ምርት እያቀረብን ነው፡፡ የማምረት አቅማችን በየጊዜው እያደገ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ባለን አቅም በወር ከ300 ቶን ያላነሰ ምርት እናመርታለን፡፡ ዓመታዊ አጠቃላይ የማምረት አቅማችን ወደ 5,000 ቶን ደርሷል፡፡ በዋጋ እንኳን ብንመለከተው ከ500 ሚሊዮን ብር ያላነሰ የገንዘብ ዝውውር ይኖረዋል፡፡ የገበያ ትስስሩም ቢሆን ባለው የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ የተሻለ ትስስር አለን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከዓመታት በፊት የነበረው አስተሳሰብ ተለውጦ ምርታችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መጥቷል፡፡ የጥራት ደረጃው ተቀባይ ከመሆኑም በላይ በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ መመዘኛ ማሟላት በመቻሉ የ”ISO Certified” ደረጃ ተሸላሚ ለመሆን በቅተናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የረዥም ዓመት ዕቅዳችሁ ምንድን ነው?

አቶ ብሩክ፡- ኢንተር አፍሪካ ኤክስትሩዥን ያለውን አቅም ሁሌም እያሳደገ ብዙ ርቀት መጓዝ ነው የሚያልመው፡፡ በዚህ ዘርፍ ሌሎችም ገብተውበት ኢንዱስትሪውን በደንብ እንዲበለጽግ ነው የሚፈልገው፡፡ በዋናነት የውጪ ምርቱን ሙሉ ለሙሉ ከማስቀረት አልፎ በውጪ ያለንን የገበያ አድማስ በማስፋት መሄድ የሚያስችለንን አደረጃጀት በማየት ወደ ኢንዱስትሪ ዞን መግባት ነው፡፡ ከዚያም የምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የአሉሚንየም ዕምብርት (ማዕከል) መሆን እንፈልጋለን፡፡ በእርግጥ በአንዴ ግዙፍ የሆነ ፋብሪካ አምጥተን የምሥራቅ አፍሪካ የአሉሚንየም ዕምብርት መሆን እንችላለን ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን እስካሁን የሄድንባቸውን መንገዶች ባሳየን መሠረት አሁንም በሒደት ያለንን ልምድ አጠናክረን ቀስ በቀስ የኢኮኖሚውን ሁኔታ በደንብ እየፈተሽን ዕድገታችንን ያልተናጋ አድርገን ማስቀጠል እንችላለን፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በሰፊው ኢኮኖሚውን እያገዝን መሄድ ያስችለናል፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ እንደሚታወቀው ተረፈ ምርቶችን በማቅለጥ ነው የግብዓት ፍላጎታችንን የምናሟላው፡፡ በቅርብ ጊዜ ግን ወደ ማዕድን ማውጣት ሥራ ውስጥ እንገባለን፡፡ ሥራውን ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- የማዕድን ሥራውን በራሳችሁ ነው ወይስ ከሌሎች አጋሮች ጋር ነው ለማከናወን ያቀዳችሁት?

አቶ ብሩክ፡- ከውጪ አገር ኩባንያዎች ጋር በጋራ ፍለጋውን ለማድረግ አስበናል፡፡ የጂኦሎጂያዊ ዳታው አለን ግን ዝርዝር ጥናት ለማካሄድ ቀድመን ለመሥራት እየሞከርን ነው፡፡ ፈቃድ ማውጣቱም በሒደት ላይ ነን፡፡ የቦታ ምሪት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...