‹‹መንግሥት በፌዴራልና በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ገንዘብ ይሰጣል፡፡›› ይህ የሕግ አንቀጽ በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2000 ክፍል አምስት ሥር ከተዘረዘሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የገቢ ምንጭና የንብረት ሁኔታ ዝርዝር መካከል የሚገኝ ነው፡፡ ይህንንና ሌሎች ተያያዥ የሕግ ማዕቀፎችን በመጠቀም መንግሥት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት በአገሪቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የክልልና ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በዚሁ ሕግ መሠረት ፓርቲዎቹ ይህንኑ ድጎማ በጉጉት ይጠባበቁታል፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት፣ መንግሥት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ለማስፈን ፓርቲዎችን በገንዘብ እንደሚረዳ በመጠቆም፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ የተለያዩ አገሮችን ልምድ መቅሰሙንና ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቦርዱ ቀሰምኩት ባለው ልምድና ከአገሪቱ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርገው የገንዘብ ክፍፍል ፓርቲዎች ባላቸው የፓርላማ መቀመጫ ብዛት፣ የሴቶች አባላት ቁጥር፣ አጠቃላይ የዕጩዎች ብዛትና በእኩልነት መሠረት ገንዘብ የማደላደልና የማከፋፈል ሥልቶችን እንደሚከተል አስታውቋል፡፡ ከዚህ አንፃር ቦርዱ ለዘንድሮ ምርጫ የፓርቲዎች የገንዘብ ድልድልን ከወራት በፊት ይፋ ሲያደርግ 40 በመቶ ፓርቲዎች በሚያስመዘግቡዋቸው ዕጩዎች ብዛት፣ 25 በመቶ በሚያስመዘግቡት ሴት ዕጩዎች ቁጥር፣ 25 በመቶ ደግሞ ፓርቲዎች ባላቸው የፓርላማ መቀመጫ መጠን የተደለደለ ሲሆን፣ ቀሪው አሥር በመቶ ለሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት እንደሚከፋፈል ተገልጿል፡፡ ይህንን ዕቅድ ከግቡ ለማድረስም መንግሥት 30 ሚሊዮን ብር ለፓርቲዎች መመደቡን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጐላ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተለያዩ ችግር ካለባቸው የተወሰኑ ፓርቲዎች በስተቀር ለሁሉም ፓርቲዎች ገንዘቡን በቀመሩ መሠረት እንዲከፋፈል ተደርጓል፤›› በማለት አክለዋል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 573/2000 አንቀጽ 43 መሠረት ደግሞ መንግሥት ለፓርቱዎቹ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ምንጭ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ከመንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ ከመንግሥት የሚመደብ፣ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ከሚገኝ ድጋፍ ወይም ዕርዳታና ከሌላ ከማንኛውም አካል የሚመነጭ ነው በማለት የገንዘብ ምንጮችን ያስቀምጣል፡፡ የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 52 ደግሞ ስለመቀበል የተከለከለ ስጦታ ወይም ዕርዳታ በዝርዝር ያስቀምጣል፡፡ ከእነዚህም መካከል የውጭ ዜጎች፣ መንግሥታትና ድርጅቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ምንጩ ያስታወቀው ስጦታ ወይም ዕርዳታ እንዲሁ የተከለከለ ነው፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ፓርቲዎች ከቦርዱ የተመደበላቸውን ገንዘብ መውሰድ የጀመሩ ሲሆን፣ የገንዘቡ ክፍፍልና ድርሻ መጠን ላይ ፓርቲዎች የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ከገዥው ፓርቲ በመቀጠል በርካታ ዕጩዎችን ማስመዝገቡ በቦርዱ የተረጋገጠለት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ)፣ ‹‹ባስመዘገብኩት የዕጩዎች ብዛት ልክ የሚገባኝን ያህል ገንዘብ ከቦርዱ አልተሰጠኝም፤›› በማለት ተቃውሞውን ያሰማል፡፡ በርካታ የተመዘገቡ ዕጩዎቹን መሠረት ያላደረገ የገንዘብ ክፍፍል መደረጉን ይገልጻል፡፡ ‹‹በእኛ አባል ፓርቲዎች አማካይነት በየክልሉ በተመዘገቡ የዕጩዎች ብዛትና የምርጫ ቦርድ ባሳወቀው መካከል ከአንድ መቶ በላይ ያህል የዕጩዎች ብዛት የቁጥር ልዩነት አለው፤›› በማለት የመድረክ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ይህንንም ቁጥር ለማስረዳትና ቁጥሩ ስህተት መሆኑን ለመግለጽ ‹‹በየክልሉ ላሉ አባሎቻችን ከምርጫ ቦርድ የዕውቅና ሰርተፊኬት ያገኙ የዕጩ ተወዳዳሪዎችን ስም ዝርዝር እንዲልኩልን ጠይቀን እርሱን በማጠናቀር ላይ ነን፤›› በማለት አክለው አብራርተዋል፡፡ የዕጩዎችን ዝርዝር ለማረጋገጥ ምርጫ ቦርድን እንደጠየቁ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹የእነ ማን ፀድቆ የእነ ማን አለመፅደቁን ለማወቅ ፈልገን ጠይቀን የነበረ ቢሆንም፣ ቦርዱ ግን የዕጩዎችን ቁጥር ብቻ እንጂ ዝርዝሩን አልሰጠንም፡፡ ስለሆነም አባል ፓርቲዎችን ጠይቀን በመቀበል ላይ እንገኛለን፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹ሁሉም የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪዎች በፓርቲው ማጣራት ተረጋግጠው ሲታወቁና ተሟልቶ ሲቀርብ፣ ከምርጫ ቦርድ የተለቀቀውን ገንዘብ እናከፋፍላለን፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ አቶ ጥላሁን፣ ‹‹ከቦርዱ የሚለቀቀው ገንዘብ በጊዜ ለምርጫው በሚያገለግልና ፓርቲውን በሚጠቀምበት መልክ አልደረሰም፤›› በማለት፣ የገንዘቡ መጠን ከማነሱ በተጨማሪ ጊዜውን ጠብቆ አለመለቀቁንና እጅግ መዘግየቱን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መዘግየቱ ግልጽ ነው፤›› የሚሉት አቶ ጥላሁን፣ ከቦርዱ የሚለቀቀው ገንዘብ መዘግየቱን ለማሳየት እንደ አብነት የሚያነሱት ነጥብ ደግሞ የፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ሰሌዳን ነው፡፡ ‹‹የምርጫ ቅስቀሳ እንኳን ከተጀመረ ሁለት ወራት ያህል ሊያስቆጥር ነው፡፡ ነገር ግን የምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የሚያከፋፍለው ገንዘብ የተለቀቀው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው፤›› በማለት ችግሩን ያስረዳሉ፡፡ ቦርዱ በጊዜው ገንዘቡን አልለቀቀልንም የሚለውን አቤቱታ የሚጋሩት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ናቸው፡፡ አቶ አበባው፣ ‹‹ገንዘቡ በጊዜው አለመለቀቁ እግር ከወርች አስሮናል፤›› በማለት ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ በተመሳሳይም የአባላት ቁጥር በምርጫ ቦርድ መሰረዝና አለመመዝገብ ሌላው ችግር እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጐላ ቦርዱ ሆን ብሎ ገንዘብ አለማዘግየቱን ይናገራሉ፡፡ ከፓርቲዎቹ ቀርበው የተሰረዙ ዕጩዎች አለመኖራቸውን እንዲሁ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹የመጀመርያውን አሥር በመቶ በምርጫው ተሳታፊ ፓርቲዎች እነ ማን እንደሆኑ ካወቅን በኋላ ልከነዋል፤›› በማለት፣ መጀመርያ ለፓርቲዎች በእኩልነት የሚከፋፈለው ገንዘብ በጊዜ መላኩን አስገንዝበዋል፡፡ የቀረውን የገንዘብ መጠን ለመልቀቅ ደግሞ ሌሎች አሠራሮች በመኖራቸው የተፈጠረ ክፍተት መኖሩንም አቶ ወንድሙ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተቀረውን የገንዘብ መጠን ለመልቀቅ የዕጩዎችን ብዛት ማወቅ፣ አንድ ፓርቲ ምን ያህል ዕጩዎች ማስመዝገቡና ምን ያህል ሴት ዕጩዎች ማስመዝገቡ መታወቅ ስላለበት፣ እርሱ እስኪታወቅ ድረስ ትንሽ ከመቆየት ውጪ የተፈጠረ የማዘግየት ምክንያት የለም፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡ ይህን ማጣራት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ መንግሥት ለፓርቲዎች የሚያደርገው የገንዘብ ክፍፍል የሚሠራው በሕጉ መሠረት በመሆኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ዝም ብሎ ገንዘብ መልቀቅ ስለማይቻል የተፈጠረ ክፍተት ሊኖር ይችላል፡፡ ቢሆንም ቁጥሩ እንደደረሰን ገንዘቡን በቀመሩ ሥሌት መሠረት ለየፓርቲው ልከናል፤›› ብለዋል፡፡ የዕጩዎች ቁጥር መቀነስን በተመለከተ ከመድረክ በኩል የቀረበ ጥያቄ እንደሌለ የጠቆሙት አቶ ወንድሙ፣ ‹‹ፓርቲዎች በየምርጫ ክልሉ ያስመዘገቡዋቸውን የዕጩዎች ቁጥር ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ያንን ማጣቀስ በቂ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ድጋፉ በቂ ነው? መንግሥት በአምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተካፋይ ለሆኑ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ አማካይነት ያከፋፈለው ገንዘብ 30 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ደግሞ በምርጫው በተለያዩ ደረጃዎች ለሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከፋፈል ነው፡፡ በዘንድሮው ምርጫ በርካታ ዕጩዎችን በማስመዝገብ ከገዥው ፓርቲ በመቀጠል ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ግንባር ቀደም የሆነው መድረክ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ፓርቲው ከቦርዱ ሁለት ሚሊዮን 27 ሺሕ ብር አግኝቷል፡፡ ነገር ግን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገንዘቡ ‹‹እዚህ ግባ›› የሚባል እንዳልሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከመንግሥት የሚለቀቀው ገንዘብ ለምንም ጉዳይ የሚበቃ አይደለም፡፡ እኛ ለመሥራት ካቀድነው ዕቅድና ሥራ አንፃር የሚለቀቀው ገንዘብ በጣም አናሳ ነው፤›› በማለት፣ መድረክ ሥራውን ለማከናወን ከመንግሥት ተስፋ ያደረገው የገንዘብ መጠንና ከመንግሥት የተለቀቀለት ገንዘብ እንዳልተመጣጠነለት አቶ ጥላሁን ይገልጻሉ፡፡ ለፓርቲው የተለቀቀው ገንዘብ ምን ያህል መጠኑ ያነሰ እንደሆነ ለማስረዳት በምሳሌነት የሚያነሱት ነጥብ ደግሞ፣ በ50 ብር የቀን አበል ክፍያ መሠረት አድርጐ ፓርቲው ላሉት 24 ሺሕ የምርጫ ታዛቢዎች ለአንድ ቀን የሥራ እንቅስቃሴ ብቻ ፓርቲው 1.3 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚያደርግ በመግለጽ ነው፡፡ መድረክ ምርጫ ቦርድ በወሰነው የዕጩ ተወዳዳሪዎች ቁጥር ብዛት መሠረት አድርጎ እንኳን የተለቀቀውን ገንዘብ ቢያከፋፍል ገንዘብ የማያገኙ ዕጩዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል፡፡ ፓርቲው ገቢው በዋነኛነት የተመሠረተው የአባላት መዋጮ ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ከዚህ ውጪ ከውጭ አገርም ሆነ ከመንግሥት የሚሰጥ መደበኛ በጀት እንደሌለም አመልክተዋክል፡፡ ስለሆነም ለፓርቲዎች የሚደረገው የገንዘብ ክፍፍል ዋነኛ የፓርቲው ማንቀሳቀሻ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተመሳሳይ የገንዘቡ ማነስ እንዳሳዘናቸውና ከገመቱት በታች እንደሆነ የገለጹት የመኢአድ ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥት የሰጠን ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ዕጩ ሲከፋፈል 400 ብር እንኳን አይደርሰውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከቦርዱ የተለቀቀው ገንዘብ ምንም ሥራ የሚያሠራ አይደለም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ምንም እንኳን ትክክለኛ ቁጥሩን መግለጽ እንደሚቸገሩ አቶ አበባው ቢገልጹም፣ መኢአድ ዘንድሮ ከመንግሥት ያገኘው ገንዘብ ወደ 400 ሺሕ ብር እንደሚጠጋ ግን ጠቁመዋል፡፡ የፓርቲውን የበጀት ዝግጅት ዕቅድና ምንጭ በተመለከተ ‹‹ዕቅዳችን ዜሮ ነው›› ያሉት አቶ አበባው፣ የዚህ ምክንያት ደግሞ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ የወሰደው ውሳኔ እንደሆነ አመልከተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ይደግፈን የነበረው በውጭ አገር ይገኝ የነበረው ደጋፊያችን ድጋፉን አቁሟል፤›› ብለዋል፡፡ መኢአድ በዘንድሮው ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን ከምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያገኝ ታሳቢ አድጎ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ምርጫ ቦርድ በጀት ይሰጣል፡፡ እንዲሁም እንደ ከዚህ ቀደሙ ከደጋፊዎቻችን እናገኛለን በማለት ስንነሳ ያቀድነው ዕቅድ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱም የከሸፈ ነው፤›› በማለት፣ ፓርቲው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት አስታውቋል፡፡ ‹‹ምን ያህል ዕጩዎችን እንዳስመዘገብን ሳናውቅ የወጣው የገንዘብና የመገናኛ ብዙኃን ድልድል መሠረት ያደረገው ምንድን ነው?›› በማለት አስተያየታቸውን በጥያቄ የሚጀምሩት የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ፓርቲው ወደፊት በሕግ የሚያየው እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ከዚያ ውጪ ግን አምስትም ትሁን አሥር ሳንቲም ለትግል የሚያበረክተው አስተዋፅኦ አለ፤›› በማለት ፓርቲው ገንዘቡን የሚቀበልበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው የዘንድሮ ምርጫን በተመለከተ ከመንግሥት የተሰጠው የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን ፓርቲው የባንክ አካውንት እንዲከፍት በቦርዱ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት፣ እርሱን በማከናወን ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ፓርቲው ከመንግሥት የተለቀቀለትን ገንዘብ ለማንቀሳቀስና ለመጠቀም ሒደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የፓርቲውን የበጀት ዝግጅትና ዕቅድ በተመለከተ፣ ‹‹የዘንድሮ በጀት እስካሁን ከያዝናቸው የበጀት ዕቅዶች የተለየ ነው፤›› በማለት ገልጸው፣ በዚህም መሠረት የፓርቲው የዘንድሮ አጠቃላይ በጀት 92 ሚሊዮን ብር ያህል እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች የሚከፋፈለውን ገንዘብ ሥሌት ለመሥራት በምሳሌነት ከጠቀሳቸው አገሮች መካከል አንዷ ደቡብ አፍሪካ ናት፡፡ በደቡብ አፍሪካ ለፓርቲዎች የሚደረገው ድጋፍ 90 በመቶ መሠረት የሚያደርገው የፓርላማ መቀመጫን ነው፡፡ ነገር ግን የደቡብ አፍሪካው የምርጫ ውድድርና ውጤት አሠራር መሠረት የሚያደርገው የተመጣጠነ ውክልና (Proportional Representation) ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት ግን ከአንድ የምርጫ ክልል አንድን ፓርቲ ብቻ አሸናፊ የሚያደርግ ሥርዓት በመሆኑ ነው በማለት የሚተቹ አሉ፡፡ በደቡብ አፍሪካ ቀሪው አሥር በመቶ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የሚከፋፈለው በእኩልነት መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡ የዘንድሮውን ምርጫ በተመለከተ የምርጫ ቦርድ የለቀቀው የገንዘብ መጠን ለየፓርቲዎቹ መድረስ ጀምሯል፡፡ ፓርቲዎች ደግሞ የተለቀቀው የገንዘብ መጠን ከዕቅዳችንና ከግምታችን በታች ነው በማለት ይገልጹታል፡፡ በሁለቱ ጉዳዮች መካከል የሚዋልለው የፓርቲዎች የገንዘብ ጥያቄ የሚፈታውና ፓርቲዎች የራሳቸው የሆነ የተጠናከረ የገንዘብ ምንጭና የአባላት መዋጮ አግኝተው የሚንቀሳቀሱት መቼ ነው? በማለት የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው፡፡