የቻይና የመንግሥት ምክር ቤት የአማካሪዎች ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን፣ ከፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ኃላፊዎች ጋር በፖሊሲ ጥናት ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ውይይት አደረገ፡፡
የሁለቱ አገሮች የፖሊሲ አማካሪዎች ከፍተኛ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ሰኞ ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አዳራሽ ውይይት ሲያደርጉ፣ የቻይና የመንግሥት ምክር ቤት የአማካሪዎች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሚስተር ዛሆ ቢንግ የቻይናን ተሞክሮ አቅርበዋል፡፡
የቻይና የአማካሪዎች ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችን እንዴት እንደሚመለምል፣ የማዕከሉ ሠራተኞች ከየትኛው የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚውጣጡና የኃላፊዎች የዕድሜ ገደብ እስከ ስንት ዓመት እንደሆነና ሌሎች ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡
ከ60 ዓመት በላይ የቻይናን መንግሥት የማማከር ልምድ እንዳለው የተገለጸው የጽሕፈት ቤቱ አመራሮች የሚመረጡበት የዕድሜ ገደብ ከ55 እስከ 65 ዓመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዕድሜ ገደቡ ለምን ከ55 እስከ 65 ዓመት ሆነ የሚል ጥያቄ ከኢትዮጵያ ተነስቶ፣ ከዚህ በታች ያሉት ወጣቶችና ምሁራን ሌሎች ተደራራቢ ሥራዎች ሊኖራቸው ስለሚችልና ከዚህ ዕድሜ በላይ ያሉት ግን በአንፃራዊነት ጊዜ ያላቸው በመሆኑ እንደተመረጠ አብራርተዋል፡፡
የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞች በዋናነትም ከቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የማዕከሉ የኮሙዩኒኬሽንና መረጃ ዳይሬክተር አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ከቻይናው ተቋም ጋር ተባብሮ መሥራት ለማዕከሉ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡ ‹‹ከእነሱ የበለፀገ ልምድ እንማራለን የሚል ሐሳብ ስላለን በፖሊሲ ላይ እንዴት ምክረ ሐሳቦችን እንደሚያወጡ፣ እንዴት አድርገው ደግሞ ያወጡትን ምክረ ሐሳብ ከመንግሥት ጋር እንደሚያገናኙትና እንደሚጠቀሙበት መሠረታዊ የሆነ ውይይት አካሂደናል፤›› ብለዋል፡፡ ይህን መነሻ ውይይት በማድረግም ሁለቱ ጽሕፈት ቤቶች በዘላቂነት አብረው ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡
ሁለቱ ማዕከላት ወደፊት አብረው ለመሥራት ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ስምምነቱም በዋናነት የጋራ ጥናት ማድረግ፣ የአቅም ግንባታ መስጠት፣ የጋራ ሲምፖዚየምና ሴሚናር ማካሄድ፣ ማቴሪያሎችንና መረጃዎችን በመለዋወጥ ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
በተያያዘ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በ2010 ዓ.ም. አሥራ አንድ የምርምር ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ አቶ ሴኩቱሬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ማዕከሉ በአምስት ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦችን ያካተተ አሥራ አንድ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ነው፡፡ የትኩረት ነጥቦችም ዘመናዊ ግብርናና ባዮ ኢኮኖሚ፣ የመልካም አስተዳደርና የአቅም ግንባታ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የኢንዱስትሪና የከተማ ልማት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታትም 16 ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ ለመንግሥት ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡ ብዙዎቹ የጥናት ውጤቶችም በመንግሥት ተቀባይነት ያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖሊሲዎች ምንጭ በአብዛኛው ቻይና እንደሆነች በምሁራን በተደጋጋሚ ቢገለጽም፣ መንግሥት ግን ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን በመቀላቀል ከሚታወቁት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ልምድ እንደምትቀስምና የጋራ ግብ እንደምትጋራ ይናገራል፡፡