Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለቤቶች አስተዳደር የወጡ መመርያዎች ከአንዱ በስተቀር በዘጠኙ ክፍላተ ከተሞች ተግባራዊ መሆን ጀመሩ

ለቤቶች አስተዳደር የወጡ መመርያዎች ከአንዱ በስተቀር በዘጠኙ ክፍላተ ከተሞች ተግባራዊ መሆን ጀመሩ

ቀን:

  • ነዋሪዎች ቅሬታ እያሰሙ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀበሌ ቤቶችን በተመለከተ አሻሽሎ ባወጣው መመርያ ቁጥር 4 መሠረት፣ ከአራዳ ክፍለ ከተማ በስተቀር ዘጠኙ ክፍላተ ከተሞች ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ነገር ግን በመመርያው መሠረት እየተስተናገድን አይደለም ያሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ኤጀንሲ የከተማው ካቢኔ ያወጣውን የመንግሥት ቤቶች (የቀበሌ ቤቶች) መመርያ ቁጥር 4 እና የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር ያሻሻለውን መመርያ ቁጥር 2 በተመለከተ፣ ሰሞኑን በይፋ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሠረት አገልግሎቱን የፈለጉ ነዋሪዎች ወደ ወረዳዎች በሚሄዱበት ጊዜ፣ በመመርያው መሠረት እየተስተናገዱ አለመሆናቸውን እየገለጹ ነው፡፡

- Advertisement -

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ታምራት፣ ‹‹ቅሬታ ያላቸው ነዋሪዎች በመጀመርያ በክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ ሥር ለተደራጀ ቅሬታ ሰሚ ክፍል ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ካልተፈታ ግን ወደ እኛ መምጣት ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነባሩን የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር መመርያ ቁጥር 3/2007 ዓ.ም. አሻሽሎ መመርያ ቁጥር 4 ያፀደቀው፣ በአምስት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ተመሥርቶ መሆኑን ገልጿል፡፡

በቀበሌ ቤት ተከራይተው ከሚኖሩት ተከራዮች ጋር በሕጋዊ መንገድ በደባልነት የሚኖሩ ተከራዮች ግልጽ የሆነ የመብት ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ስለሆነ፣ በቀበሌ ንግድ ቤቶች ለሌላ ሦስተኛ ወገን የሚተላለፍበት መንገድ በግልጽ ያልተቀመጠ በመሆኑ፣ የቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሕጋዊ ተከራዮች ቤቱ ረዥም ጊዜ ከመቆየቱ የተነሳ ለማሳደስ በሚፈልጉበት ጊዜ በተመሳሳይ ማቴሪያል ብቻ መሆን አለበት ስለሚል፣ ይህ ድንጋጌ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ክፍተት እየፈጠረና ጥያቄውም እየሰፋ በመሄዱ፣ በውክልና የቀበሌ ቤት ውል ማደስ ያልቻሉትን ሕጋዊ የቀበሌ ቤት ተከራይ ግለሰቦች ጥያቄ እየበረከተ በመምጣቱና የማካካሻ ቤት ላላቸው የመልሶ ማልማት ተነሺዎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በማለም ማሻሻያው እንደተደረገ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር ወጥቶ የነበረውን መመርያ ቁጥር 1/2008 ለማሻሻል የፀደቀው መመርያ ቁጥር 2 በሥራ ላይ መዋል ጀምሯል፡፡

አስተዳደሩ መመርያውን ባሻሻለበት ወቅት ባቀረበው ማብራሪያ ላይ እንደገለጸው፣ በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ያሉ የመኖርያ ቤት ግንባታዎች አመርቂ ውጤት እየተመዘገበባቸው ቢሆንም፣ ከልማት ተነሺዎች አገልግሎት አሰጣጥ፣ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አነስተኛ መሆን፣ የተቋማት የመረጃ አደረጃጀት፣ አያያዝና አጠቃቀም ጉድለቶች መኖራቸው፣ የወጡ መመርያዎች ክፍተቶችን ሊፈቱ ያልቻሉ በመሆናቸው፣ በአጠቃላይ እነዚህ ሁኔታዎች የቅሬታ ምንጮች በመሆናቸውና የመልሶ ማልማት ሥራው በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጓዝ ስላደረጉ መመርያው መሻሻሉ ተመልክቷል፡፡

አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፣ አራዳ ክፍለ ከተማ የአመራር ለውጥ እያደረገ በመሆኑ መመርያውን ሥራ ላይ ለማዋል ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ ክፍላተ ከተሞች ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመሩና ኤጀንሲውም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...