Tuesday, January 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአገር ሲወጣና ሲገባ በሚያዝ የብርና የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ማስተካከያ ተደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማንኛውም ግለሰብ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ወይም ሲወጣ መያዝ የሚችለው የኢትዮጵያ ብርና የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ማስተካከያ ማድረጉ ታወቀ፡፡

ከሳምንታት በፊት ባወጣው የማሻሻያ መመርያው መሠረት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ተጓዦች፣ በእጃቸው እንዲይዙ የሚፈቀድላቸው የኢትዮጵያ ብርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ጭማሪ አድርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው ተመሳሳይ መመርያ የወጣው በ1999 ዓ.ም. ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ከኢትዮጵያ የሚነሳ ማንኛውም ተጓዥ እስከ 1,000 ብር እንዲይዝ የሚፈቀድለት ሲሆን፣ ወደ ጂቡቲ የሚጓዙ ግን እስከ 4,000 ብር ድረስ እንዲይዙ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ማንኛውም ተጓዥ ከ200 ብር በላይ እንዲይዝ አይፈቀድለትም ነበር፡፡  

ከውጭ ምንዛሪ መጠን ጋር በተያያዘም ኤምባሲዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራተኞች፣ እንዲሁም የተለያዩ ዓውደ ጥናቶችንና ሥልጠናዎችን ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚጓዙ ግለሰቦች ከሦስት ሺሕ በላይ ዶላር መያዝ እንደሚችሉ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን ይኼን ፈቃድ ለማግኘት ግለሰቦቹ የድጋፍ ደብዳቤ ከቀጣሪዎቻቸውና ሥልጠናውን ከሚያዘጋጀው አካል ማቅረብና አስፈላጊውን የባንክ ሥርዓት ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው መመርያ የውጭ ምንዛሪ ጣሪያው አንድ ሺሕ ዶላር ብቻ ነበር፡፡

በተጨማሪም መመርያው ማንኛውም ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ነዋሪ ከአንድ ሺሕ ዶላር በላይ ያለው ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ ይዞ ከገባ ከ30 ቀናት በላይ በእጅ ይዞ እንዲገኝ አይፈቅድም፡፡ 30 ቀናት ከማለቃቸው በፊት ለሚመለከተው ማሳወቅና የውጭ ምንዛሪውን ወደ  ብር ሕጋዊ በሆኑ የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ ቢሮዎች መመንዘር አለበት፡፡

ነገር ግን መጠኑ ከአንድ ሺሕ ዶላር በታች ከሆነና ግለሰቡ አስፈላጊውን የጉዞ መረጃ ካሟላ፣ ገንዘቡን ከ30 ቀናት በላይ መያዝ ይችላል፡፡ ግለሰቡ የኢትዮጵያ ነዋሪ ካልሆነ ገንዘቡን ቪዛው እስከሚያገለግልበት ጊዜ ድረስ መያዝ ይችላል፡፡

ይህ አዲስ የውጭ ምንዛሪ መመርያ ከዚህ ቀደም የነበሩበትን ተመሳሳይ መመርያዎች የሻረ ሲሆን፣ ተፈጻሚነቱም አገሪቱ በቅርቡ ካስተዋወቀችው የ15 በመቶ የምንዛሪ ተመን ለውጥ ጋር አብሮ የመጣ ነው፡፡

ምንም እንኳን ይህ መመርያ ተጓዦች መያዝ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ መጠን ከፍ ያደረገ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ተጓዦች እዚህ ግባ የሚባል የውጭ ምንዛሪ ከባንኮች እያገኙ እንዳልሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡  

ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች ባጋጠማቸው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የተለያዩ አዳዲስ ፋብሪካዎች እያቋቋሙ ያሉ ባለሀብቶች ለጥሬ ዕቃ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው፣ የፍራንኮ ቫሉታ መብት ተጠቅመው ለማስገባት እየጠየቁ መሆናቸውን ታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ፍራንኮ ቫሉታ ለመጠቀም የሚቀርቡ ጥያቄዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ  የመንግሥት ኃላፊ አረጋግጠዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች