Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕዝብ የሚፈልገው አማራጭ ሐሳቦችን ነው!

የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላምና በነፃነት እንዲኖር ከተፈለገ አማራጭ ሐሳቦች ሊቀርቡለት ይገባል፡፡ አማራጭ ሐሳቦች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ዜጎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ነፃነት እንዲሰማቸው ይረዳል፡፡ ዴሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ነው የሚባለው፣ ለአገር እስከጠቀመ ድረስ ማንኛውም ሰው የሚሰማውን ማንፀባረቅ ስለሚችልበት ነው፡፡ ዜጎች የመሰላቸውን በነፃነት ከመናገራቸው በላይ፣ ነፃና ግልጽ ማኅበረሰብ ለመፍጠርም ይረዳል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ይህ መልካም እሳቤ ብርቅ ነው፡፡ ተቃራኒ ሐሳብን ላለማዳመጥ ሲባል ብቻ ማናናቅ ወይም በኃይል ገለል ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ሐሳቦች እየተቀጩ የአንድ ወገን የበላይነትን የሚያንፀባርቁ ብቻ ሲንሰራፉ፣ አገርን ምን ያህል ወደ ኋላ እንደጎተቱ ያለፉት ታሪኮች ያስገነዝባሉ፡፡ አሸናፊነት የትክክለኛነት መገለጫ ሆኖ በርካታ ወርቃማ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ ከምክር ጀምሮ አቅጣጫ ጠቋሚ ሐሳቦች ተገፍተውና ተጥለው፣ በአይረቤ ሐሳቦች አገርና ሕዝብ አሳር አይተዋል፡፡ አሁን ግን ይበቃል መባል አለበት፡፡

የሩቁን ጊዜ ትተን ከምርጫ 97 በኋላ ያጋጠሙ ክስተቶችን በጨረፍታ ስንቃኝ ችግሮች ቁልጭ ብለው ይታያሉ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ የመጡት የፕሬስ አዋጅ፣ የሲቪል ማኅበራትና በጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ይጠቀሳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በርካታ ጭቅጭቆችን ያስነሱት እነዚህ አዋጆች በገዥው ፓርቲ ማስተባበያ ቢቀርብላቸውም፣ የውጤታቸው አስከፊነት ግን በግልጽ ታይቷል፡፡ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱበትና አወዛጋቢው የፕሬስ አዋጅ ከወጣ በኋላ የግሉ ፕሬስ በሰበብ አስባቡ ተሽመድምዶ ቀርቷል፡፡ የማይሰሙ ድምፆችና አማራጭ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት የግሉ ፕሬስ መሽመድመድ ብዙዎችን ድምፅ አልባ አድርጓል፡፡ የሐሳብ ነፃነት እንዲገታ ምክንያት ሆኗል፡፡ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦችን ይዘው የሚወጡ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጠፍተዋል፡፡ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት የማያስተናግዷቸው ድምፆች ታፍነዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በንፅፅር ቀደም ሲል ይቀርቡ የነበሩ የተለዩ ሐሳቦች ባክነው ቀርተዋል፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነው፡፡ ለዚች ታላቅ አገር የማይገባም ነው፡፡

የሲቪል ማኅበረሰቡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ቢኖረውም በአዋጁ ሳቢያ ቀንጭሯል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ በመንግሥት እንደሚነገርለት ለልማት ያለው ፋይዳ ያን ያህል ነው ቢባል እንኳ፣ የዜጎችን ንቃተ ህሊና ለመገንባትና ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ማኅበረሰብ እንዲፈጠር አስተዋጽኦው ጉልህ ይሆን ነበር፡፡ ሦስቱ የመንግሥት ዓምዶች ማለትም ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው ተናበው እየሠሩ መሆኑን ለማረጋገጥና ተጠያቂነት እንዲኖር ለማድረግ ይረዱ ነበር፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ውጤት የሆኑት ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር  ዕጦት፣ የፍትሕ መስተጓጎልና በዜጎች መካከል ኢፍትሐዊ ግንኙነት መስፋፋት የአገር በሽታ አይሆኑም ነበር፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡ በነፃነትና በኃላፊነት መንፈስ ሲሠራ በኅብረተሰቡ ውስጥ በነፃነት የመነጋገር፣ የተለዩ ሐሳቦችን የማዳመጥና የመከራከር ባህሉ ያድግ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ሲቪል ማኅበረሰቡ እንዳለ አይቆጠርም፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩባቸው መድረኮችም የሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ የት ድረስ መጓዝ ይቻላል? የትም፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ለአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች እኔ ብቻ እበቃለሁ ማለቱ አላዋጣም፡፡ የፓርላማውን መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ቢቆጣጠርም ከየአቅጣጫው ተቃውሞዎች ይሰማሉ፡፡ ከራሱ ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሰብ ጋር የማይጣጣሙ ሐሳቦችን ጥግ ማስያዙ የፈጠረው ተቃውሞ እንጂ ድጋፍ አይደለም፡፡ ይህ ተቃራኒ ሐሳብን ያለማስተናገድ ጎጂ ልማድ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲው ላይ ጭምር ጉዳት ፈጠረ እንጂ ያስገኘው ትርፍ የለም፡፡ ሐሳቦች በነፃነት እንዳይንሸራሸሩ መገደብ ቅሬታን ለማባባስና ተቃውሞ ለማቀጣጠል ይጠቅም ይሆናል እንጂ ፋይዳ እንደሌለው ይታወቃል፡፡ እዚህ ግቡ ከማይባሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ውይይት ወይም ድርድር ውጥረቶችን ለማርገብ ከመሯሯጥ ይልቅ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ጋር በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መነጋገር ይገባል፡፡ እነዚያ የባከኑ ወርቃማ ዕድሎች ካመለጡ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ አሁን ግን ወደ ቀልብ ተመልሶ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ የወቅቱ መሠረታዊ ጥያቄ ነውና፡፡

ኢትዮጵያ 76 ብሔር ብሔረሰቦች፣ በጣም በርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ እምነቶች፣ ወዘተ. ያሉባት የብዝኃነት አገር ናት፡፡ በዚች አገር ውስጥ በአንድ ርዕዮተ ዓለም ወይም የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ አገር ለመምራት መሞከር ፈጽሞ አይሞከርም፡፡ ቢሞከርም አያዋጣም፡፡ የሐሳብ ብዝኃነት ባለው ሕዝብ ውስጥ አንድ ዓይነት መዝሙር ብቻ እንዘምር ማለት ጤናማ አይደለም፡፡ በግልም ሆነ በቡድን ሐሳቤ ተወክሎልኛል ለማለት የማይደፍር ኅብረተሰብ ውስጥ አንድ ዓይነት ነገር እናመንዥግ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ከዚህ ዓይነቱ ቀልድ ውስጥ በአስቸኳይ መውጣትና ምኅዳሩን ማስተካከል አለበት፡፡ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያሉትም የጠነዛና የማይረባ ትርክታቸውን ትተው ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ይዘጋጁ፡፡ ከጅምላ ፍረጃና ከእኛ በላይ ለአሳር ከሚባልለት ነጋሪት ጉሰማ በመውጣት ለሐሳብ ብዝኃነት ይታገሉ፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የተለያዩ ሐሳቦች በሚያደርጉት ግልጽ፣ ነፃና ፍትሐዊ ውድድር እንጂ በጉልበት ወይም በአስማት አይደለም፡፡ ደመነፍሳዊ ጉዞ ለዘመኑም አይመጥንም፡፡

በአጠቃላይ ነፃ ማኅበረሰብ የሚፈጠረው ለነፃነት ትርጉም ያለው ጥረት ሲደረግ ነው፡፡ ሐሳቦች በነፃነት ሲወዳደሩ መራጩ ሕዝብ የተሻለውን ለመምረጥ ዕድሉን ያገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ነፃና ግልጽ የሆነ የሕዝብ ውይይት መኖር አለበት፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው መወያየትና መከራከር ሲችሉ ሐሳቦች እንደ ጅረት ይፈሳሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉን የሚሉዋቸውን አማራጮች ያቀርባሉ፡፡ ለአገር የሚጠቅም ሐሳብ አለን የሚሉ ወገኖች በነፃነት አደባባይ ይወጣሉ፡፡ ኃላፊነት የሚሰማቸው ብርቱና ትንታግ ጸሐፊዎችና ፖለቲከኞች ይፈጠራሉ፡፡ ሐሳብን በሐሳብ የሚሞግቱ ብርቱ አሰላሳዮች ይገኛሉ፡፡ ከፖለቲካው ውጪ በተለያዩ ዘርፎች ምሥጉን ዜጎች አስተዋጽኦቸውን ይዘው ይወጣሉ፡፡ ነፃነትና ኃላፊነት ሰምና ወርቅ እየሆኑ ኢትዮጵያ ከፍ ብላ ትደምቃለች፡፡ ይህ ሁሉ በተግባር ይታይ ዘንድ ጊዜው ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት መሆን አለበት መባል ይኖርበታል! ሕዝብ የሚፈልገው አማራጭ ሐሳቦችን ነው!

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...