Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነትን እንዴት መፋለም ይቻላል?

በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነትን እንዴት መፋለም ይቻላል?

ቀን:

በዋሺንግተን ዲሲ፣ ዋይት ሐውስ በተባለው የአሜሪካ ከፍተኛ የጉባኤ አዳራሽ በአመጽ/ በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነትን አጥብቆ የሚቃወም ዓለም አቀፍ ጉባኤ መሰንበቻውን ተካሂዶ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤም የኤሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ጆን ኬሪን፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባን ኪ-ሙንም ጨምሮ የስድሳ አገሮች ልዑካን ተገኝተዋል፡፡ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱትና የዘጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ‹‹አሜሪካ እየተዋጋች ያለችው ከጥላቻ አስተሳሰቦች ጋር እንጂ ከእስልምና ጋር አይደለም›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ በአንድ በኩል ሚዛናዊ በሆነ ንግግራቸው ያመሰገኗቸው እንዳሉ ሁሉ ያስከፏቸውም አሉ፡፡ የፕሬዚደንቱ ንግግር ከአሜሪካ ፖሊሲና ከረዥም ጊዜ የስትራቴጂ ጥቅም ጋር የተያያዘ ቢሆንም ለሀገራችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ፋይዳ ሊኖረው ይችል እንደሆነ በዝርዝር ለመፈተሸ ጥረት ይደረጋል፡፡

በዚህ ጽሑፍ በቅንፍ ውስጥ የተቀመጡት ጸሐፊው በትርጉም ወቅት አንድም ሐሳቡን ለማያያዝና ፍሰት እንዲኖረው ለማድረግ፣ ወይም ለማብራራት፣ ወይም ለማጣቀስ፣ ወይም ተመሳሳይ በሆነ ምክንያት የተጠቀመባቸው መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል፡፡

- Advertisement -
  1. በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነት ማለት

ፕሬዚደንት ኦባማ ‹‹በዓለም የሚከናወነውን አስመልክተን ስንናገር እምነት ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ ተደጋግፈው ለመነሳት፣ ረሃብተኞችን ለመታደግና ድሆችን ለመንከባከብ፣ የተጨነቁትን ለማጽናናትና ጸብን አብርደው ሰላም ለማስፈን ጥረት የሚያደርጉ መኖራቸውን እንገነዘባለን፤›› ካሉ በኋላ ‹‹ይህም ሆኖ እምነት ተጠምዝዞና ተዛብቶ ሕዝብን የሚከፋፍል ሽብልቅ እንዲያውም ከዚያ የከፋ የጦር መሣሪያ እየሆነ ነው፤›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

ኦባማ እንዳሉት ከፓኪስታን ትምህርት ቤት እስከ ፓሪስ ድረስ ለሃይማኖት ቆመናል በሚሉ ሰዎች ኡከትና ሽብር እየተፈጸመ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሃይማኖቱን ካዱት እንጂ አልተከተሉትም፡፡ በሦሪያና በኢራቅ ውስጥ በኢስላም ስም የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛና አሸባሪ ኃይል በአንደበት ሊገለጽ የማይችል ድርጊትና አረመኔያዊ ግፍ በራሳቸው እምነት ተከታዮች ላይ እየፈጸሙ ነው፡፡ ሴቶችን መድፈር እንደጦር መሣሪያ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ በናይጀሪያ ደግሞ ኢስላማዊ ጽንፈኞች በሆኑ ኃይሎች ክርስቲያኖችም ሙስሊሞችም እየተገደሉ ነው፡፡ በማዕከላዊው አፍሪካ ሪፐብሊክ ተመሳሳይ ሁኔታ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች እየተገደሉ ነው፡፡ በአውሮፓ አብዛኛውን ጊዜ በሃይማኖት ስም በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ወንጀል እየተፈጸመ ነው፡፡ እንደ ኦባማ ገለጻ በአሁኑ ጊዜ የምናየው የጽንፈኛነትና የኽውከት ድርጊት ለአንድ ቡድን (ለእስልምና እምነት ተከታዮች) ወይም ሃይማኖት ተነጥሎ የሚተው ሳይሆን በኛም (ከክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ) ውስጥ ሃይማኖታችንን የሚያዛባና የሚያፋልስ አዝማሚያ አለ፡፡ በዛሬው ዓለም ጥላቻን የሚያራምዱ ኃይሎች ትዊተር (ኢንተርኔት) ከፍተው የራሳቸውን በዘረኝነት፣ በጠባብነት፣ በትምክህተኛነት፣ እብሪተኛነት፣ የተሞላ አስተሳሰባቸውን እያሰራጩ ነው፡፡ ይህ አስከፊ ስርጭት በቀላሉ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ዓይነት ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የነገሩ አሳሳቢነት ቀላል እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡›› በማለት  በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነት በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚስተዋል መሆኑን ሰፋ አድርገው ተመልክተውታል፡፡

  1. አሜሪካ የሃይማኖት እኩልነት የሰፈነባት አገር

‹‹እዚህ አሜሪካ ውስጥም ሆነ ከአሜሪካ ውጭ መሠረታዊ ነጻነት በተለይም የሃይማኖት ነጻነት፣ ማለትም የፈለግነውን በፈለግነው መንገድ ለመተግበር፣ ከፈለግንም እምነታችንን ለመቀየር፣ ከፈለግንም ማንኛውም ሃይማኖት የማንከተል ሆነን ለመኖር የምንችል እንጅ፣ ማንም ተነስቶ የማያስፈራራን ከቶ መሆን የለብንም፡፡ እመን ወይም አትመን ተብለን የምንነዘነዝ ወይም በሃይማኖት ምክንያት የምንፈራና የምንገለል መሆን የለብንም፡፡›› ሲሉ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ አድርገው በጥንቃቄ ያቀረቡት ኦባማ ‹‹እነዚህ መብቶች ውስብስብ በሆነውና ብዝህነት ባለው ሕብረተሰብ በቅንነትና በዘመናዊ መንገድ በሥራ ላይ ይውሉ፣ እንዲሁም (ለሚቀጥለው ትውልድ) ተጠብቀው ይቆዩ ዘንድ ከእየአንዳንዳችን መልካም ስነምግባር፣ እራስን መቆጣጠር መቻልና የህሊና ፍርድ ይጠበቃል፡፡ ይህንንም የምናደርገው አገራችን ሁሉም የእምነት ተከታዮችን እጆቿን ዘርግታ የምትቀበል እነርሱም ሙሉና እኩል የሀገራችን አባላት በመሆናቸው ነው፡፡›› በማለት በአሜሪካ የሚኖሩ አሜሪካውያን ተረጋግተው እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡

በእምነታችንና በመንግሥት መስተዳድር መካከል እንዲሁም በቤተክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን የገለጡት ኦባማ ሀገራቸው የበለጸገች አገር ለመሆን የበቃችው የአገራቸው መስራቾች ቤተ ክርስቲያንና መንግሥትን ለይተው በማስቀመጣቸው፣ መንግሥት በሃይማኖት በጀርባ ሆኖ የማይደግፍ ሲሆን ማንም ሰው አንድ የታወቀ ሃይማኖት እንዲከተል ወይም እንዳያምን ተጽእኖ ባለማድረጋቸው፣ በዚህም ምክንያት አገራቸው የተለያየ አስተዳደግና እምነት ያላቸው ሁሉ ያለ አንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ በነጻና በኩራት የሚያመልኩባት ለመሆን እንደበቃች ተንትነዋል፡፡ ‹‹ስለሆነም የሃየማኖት ነጻነት እሴታችንን እዚህ በሀገራችንና በዓለም ዙሪያ የመጠበቅ ተግባራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ ዘብም እንቆምለታለን፡፡ (ይህንን ስናደርግ) ሃይማኖታችን ምንም ይሁን ምን፣ ባህላችን ምንም ይሁን ምን የሠላም መሣሪያዎች ለመሆን መሻት፣ ጨለማ ባለበት ብርሃን ማምጣት፣ ጥላቻ ባለበት ፍቅርን መዝራት አለብን፤›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

  1. አሜሪካና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሁከት ላይ የተመሠረተን ጽንፈኝነት ስለመዋጋት

ፕሬዚደንቱ በዕለቱ ‹‹እዚህ የተገኘነውም በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነትን በተመለከተ ለመወያያት ነው፡፡ በሁከት ላይ የተመሠረት ጽንፈኝነት ስንል ግን ንጹሐን ዜጎችን የሚገድሉ አሸባሪዎች ብቻ ማለታችን አይደለም፡፡ የጽንፈኛነት ርዕዮተ ዓለምንና መዋቅራቸውን ማለትም ፕሮፓጋንዳቸውን፣ ምልመላቸውን፣ አክራሪነት እንዲጠናከርና ሰዎች ወደ አመጽ እንዲገፋፉ ለማስቻል የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ጭምር ማለታችን ነው፡፡  ይህም እኩይ ተግባር የአንድ ቡድን፣ ወይም በአንድ መልክአ ምድር አሰፋፈር፣ ወይም በአንድ ወቅት የሚወሰን አይደለም፤›› በማለት በምን መልኩ በሁከት ላይ የተመሠረተ ዓመጽን መዋጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

አልቃዒዳና አይሲል የኢራቅና የሌቫንት/የሻም/የሦሪያ (በዓረብኛ-አል-ደውላሀ አል-ኢስላሚያህ ፊልኢራቅ ወሻም) እና እነሱን የሚመስሉ ቡድኖች አመለካከቶችን አዙረው ጠምዝዘው (ገለባብጠው) ሰዎችን ለአመጽ ለማነሳሳት እንቅስቃሴያቸውን ሕጋዊ ለማደረግ በቀቢጸ ተስፋ እየተወራጩ መሆናቸውን ጠቁመው ‹‹ራሳቸውን እንደ ሃይማኖት መሪዎች አድርገው በማቅረብ ኢስላምን ለመታደግ ቅዱስ ጦርነት እናካሂዳለን ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አይሲኤል ራሱን ኢስላማዊ መንግሥት እንደሆነ አውጇል፡፡ አሜሪካና የተቀሩት የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በኢስላም ላይ ጦርነት ያወጁ አስመስሎም የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ እያካሄደ ነው፡፡ ጀሌዎቹንም የሚመለምለው እንዲያ በማለት ነው፡፡ ወጣቶችን አነሳስቶ ለእኩይ ዓላማው የሚያሰልፈው በዚህ መንገድ ነው፡፡ …(አባላቱም) ሃይማኖታዊ መሪዎች ሳይሆኑ አሸባሪዎች ናቸው፡፡›› ካሉ በኋላ  ‹‹እኛም ብንሆን ከኢስላም ጋር በጦርነት ላይ አይደለንም፤›› በማለት አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ኦባማ አክለውም ‹‹ከሙስሊም ማኅበረሰብ ውጭ የሚገኙም አሸባሪዎች ምዕራባውያንና ኢስላሞች ወይም ዘመናዊው ሕይወትና ኢስላም በግጭት ላይ ናቸው ብለው የሚያስወሩትን ታሪክ ልንቀበለው አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ ሙስሊሙ ሕብረተሰብም ይህንን ሐቅ የማስረዳት ኃላፊነት አላቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አልቃዒዳና አይሲአይኤል ከኢስላማው ጽሑፎች መርጠው በማቅረብ ኢስላም ከሥር መሠረቱ በሁከት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስመስለው እያቀረቡ ነው፡፡›› ሲሉ አስመሳይነትን ካወገዙ በኋላ (ይህም ሆኖ ኽውከተኞቹና ጽንፈኞቹ ለራሳቸው በሚመቻቸው መንገድ) አጣመው የሚተረጉሙትን (ኢስላማዊ እምነት) አጥብቀው የሚቃወሙ የተከበሩ (ሙስሊም) የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን እዚህ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ አሉ፡፡ እነዚህ የሃይማኖት አባቶችና ምሁራን ኢስላም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ዛሬም  ከሃይማቱ መሪዎቹ ጥቂቱ ከኛ ጋር ተሰብስበዋል፡፡ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎችና ምሁራን ኢስላም ለሰላም፣ ለፍትሕ፣ ከሌሎች ጋር ተቻችሎ ለመኖር፣ አሸባሪነት የተከለከለ መሆኑን፣ አንድን ንጹሕ ዜጋ መግደል ሁሉንም ሰው የመግደል ያህል እንደሚቆጠር አጥብቀው እያስገነዘቡ መሆኑን ሚስተር ኦባማ አውስተዋል፡፡ 

  1. በሁከት ላይ የተመሠረተን ጽንፈኝነት ለመዋጋት ምን መደረግ አለበት?

‹‹ጽንፈኝነትን ብቻውን ለማስቀረት የምንፈልግ ከሆነ፣ ወጣቶቻችንን እየመለመሉ ለእኩይ ዓላማቸው የማሰለፍ ተግባራቸውን ለማስቆም የምንፋለም ከሆነ፣ በሙስሊሙ ሕብረተሰብ ውስጥ የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህልን በሚመለከት ድምጻችንን ከፍ አድርገን የምናስተጋባ ከሆነ፣ ምዕራባውያን አገሮች በአንዱ ወይም በሌላው መልኩ ከኢስላም ጋር ቅራኔ ውስጥ ናቸው በማለት በብዙ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ዘንድ የሚያሰራጩትን ፕሮፓጋንዳ አከሸፍን ማለት ነው፡፡›› ያሉት ኦባማ ‹‹ሐቁ — ብዙ ሙስሊም መሪዎች እንደተናገሩት ሁሉ ኢስላም የአይሲል ታክቲክን የማያቅፍና አመጽን የማያስተናግድ ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ፣ ሙስሊሙ ዓለም ታሪካዊ ቅሬታ አለው፡፡ ይህ ቅሬታ አንዳንድ ጊዜ ትክክል ነው፡፡ በአብዛኛው ግን ለመካከለኛው ምሥራቅ አስከፊ ሁኔታዎች መከሰት ከቅኝ አገዛዝ ታሪክ ወይም ሤራ የመነጩ ናቸው ይላሉ፡፡ ቅኝ ገዥዎች (የዘመናዊ ስልጣኔ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጭ መሆኑን በመጋረድ) ኢስላም ለዘመናዊነትና ለመቻቻል ስፍራ የሌለው አድርገው ፈርጀውታል፡፡ …ስለዚህም ይህንን እውነታ ቅንንነት ተመርኩዘን ልንነጋገርበት ይገባል፡፡ እንዲህ ያሉትን አንዳንድ አስተሳሰቦችን እንዴት እንደማንቀበላቸው የበለጠ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡›› በማለት ያስገነዝባሉ፡፡

‹‹ሁላችንም፣ በአንድነት፣ በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነትን ላለመቀበል ስንሠራ፣ ሁላችንም በዚች ንብርብር ማንነት በሰፈነባት (በተዋሃደች) ዓለም ላይ የምናከብራቸው ሁለንተናዊ መርሆዎች እና እሴቶች መኖራቸው ግልጽ እንዲሆኑልን የየበኩላችንን ድርሻ ስንወጣ በጋራ ያ የጋራ ጥረታችን መጀመሪያ ይሆናል፡፡ ወደፊት እየቀጠልን ስንሄድም የሰላም፣ የመቻቻልና በአንድ የመሆን ድምጻችንን የምናስተጋባባት አዲስ መንገድ እናገኛለን፡፡—ይህንንም ስናደርግ በተለይ በአንድ ላይ (በአንድ መስመር) መሆን ይኖርበታል፡፡ …በዚህ ታላቅ ሥራ እንደግብዓት ሆኖ የሚያገለግለን እራሱ ሕብረተሰቡ ነው፤ በተለይም ዛሬ በመካከላችን እንደሚገኙት ያሉ ወጣቶች፡፡›› ብለዋል፡፡

  1. በሁከት ላይ የተመሰረተ አመጽን ለማስቀረት ያቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ

ፕሬዚደንት ኦባማ ለመላው ዓለም በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ባስታለፉት ጥሪ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የአዲስ ፈጠራና ማህበራዊ ሚዲያ በአዲስ ዘዴ መጠቀም የጀመሩ ብስለት ያላቸው ወጣት ወንዶችና ሴቶች በመካከላችን ይገኛሉ፡፡ … የእነዚህን ብሩህ አስተሳሰብና የፈጠራ ችሎታ ወጣት ሙስሊሞች የሚያሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሳይደናቀፍ ይቀጥል ዘንድ የጽንፈኞችን ቅጥፈቶች በማጋለጥ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ወጣቶች የበለጠ እንዲሠሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት፣ እዚህ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙና በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችን በማሻሻል ልናጠናክራቸው ይገባል፡፡ ይህ ለወጣቱ ትወልድ አስፈላጊውን ትኩረት እንድሰጥ የማቀርበው ጥሪ ነው፡፡  በዚህ ጥሪ ርዕዮተ ዓለማቸው (የጽንፈኞች) እርባና ቢስ መሆኑን ማሳየት ነው፡፡ አንገታችንን ቀና አድርገን ልንፋለማቸው ይገባል፡፡ በዚህ ውይይት ዓይን አፋር ልንሆን ከቶ አይገባም፡፡ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ሲነሱ ስሜታቸው ሊነካ እንደሚችል እንገነዘባለን፣ ዳሩ ግን በሐቀኝነትና በግልጽ ስለጉዳዮቹ ልንናገር ይገባል፡፡ ይህንን እድናደርግ የምጠይቀውም ሐቁን አውጥተን ስንናገር ስኬታማ እንሆናለን ብዬ ስለማምን ነው፡፡

‹‹ሁለተኛው ጥሪዬ አሸባሪዎች የኢኮኖሚውን ጨምሮ የሚያሰሙትን ብሶት ምን እንደሆነ መመልከት ነው፡፡ ድህነት ብቻውን ሰዎችን አሸባሪ አያደርግም ከድህነት በላይ የሆነ ነገር ሁሉ ወንጀለኛ ደርጋል፡፡ ሚሊዮን-ቢሊዮን- የሚሆኑ ሰዎች ተስፋ አስቆራጭ በሆነ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሲሆን እነዚህም ሰዎች የኽውከትን ርዕዮተዓለም ሳይቀበሉ ማንኛውንም ሕይወታቸውን ሊለውጥ የሚችል ነገረ ሁሉ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

‹‹…ወጣቶች ሳይማሩ ሲቀሩ፣ በተሞክሮ ላልታየውና መመዘን ለማይፈልገው ለአሉባልታ ጽንሰ ሐሳብ እና በዚህ ላይ ለተመሠረተ ሥር ነቀል ለውጥ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ ይህንንም እውነታ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜንና በምሥራቅ አፍሪካ አይተነዋል፡፡ አሸባሪዎች ይህን (የወጣቶችን ችግር) እንደመልካም አጋጣሚ ይጠቀሙበታል፡፡ ለእግረኛ ወታደሮቻቸው ደሞዝ በመቁረጥ ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ያደርጋሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም የአካባቢው መንግሥት ሊያደርገው ያልቻለውን ወይም የማያደርገውን እንደትምህርት ቤቶችንና፣ የጤና ክሊኒኮችን የመሳሰሉትን በማቋቋም ማሕበራዊ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ አመጻቸውንም ከፍትህ እጦት ጋር የተቆራኘውን ሙስናን ለመዋጋት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህንም የሚያደርጉት እንደአፈና፣ ሰዎችንን ድንበር እያሻገሩ በማሸሽ ለአደጋ እንደማጋለጥ እንዲሁም ሌሎችንም ከዚህ የከፉ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡

‹‹ስለሆነም ሰዎች ለጽንፈኞች የሐሰት ቃልኪዳን እንዳይዳረጉ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አንዳች የተሻለ ነገር ማቅረብ (መስጠት፣ ማበርከት) ይኖርበታል፡፡ አሜሪካ ይህንን በሚመለከት የራሷን ድርሻ ለማበርከት ተዘጋጅታለች፡፡ በርካታ ሰዎች ቤተሰቦቻቸቸውን በደንብ ለመርዳት ይችሉ ዘንድ በሰፊው ለመዳረስ የሚችል ልማትና እድገት እንዲኖር የማድረግ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡ አንዱ የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቅሞ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል የሚጎዳበት ምክንያት ስለሌለ የጉቦኝነት ባህል በመልካም አስተዳደር በመተካት ሙስናን ግንባር ቀደምነት የመምራት ጅምራችንን እንቀጥልበታለን፡፡

‹‹ሀገሮች የተለዬ ሥርዓት ለሚሻው ወጣቱ ሕብረተሰብ የሚያስፈልገው ትምህርት፣ ሙያና የሥራ ስልጠና ለማግኘት የሚረዷው ተቋም እውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ …በኢኮኖሚው ዘርፍ ያለውን እንደዳሰስነው ሁሉ አሸባሪዎቹ ዋነኛ መሣሪያቸው አድርገው የሚጠቀሙበትን ፖለቲካዊ ብሶቱን በሦስተኛ ተግዳሮት ስለሆነ በዝርዝር እንመልከተው፡፡ መንግሥታት ሕዝቦቻቸውን ሲጨቁኑ፣ ሰብአዊ መብታቸውን ሲገፏቸው፣ ሲያፍኗቸው፣ ብሔራቸውንም ሆነ ሃይማኖታቸውን እንደባእድ ሲመለከቱት፣ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው የበለጠ አድርገው ሲመለከቱ የጽንፈኝነትና የኽውከት ዘር መዘራት ይጀምራል፡፡ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለምልመላ የሚያጋልጣቸውም ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪዎች ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በአመጽ መሆኑን እያወጁ ነው፡፡ በእርግጥም፣ ሰላማዊ ለውጥ የማይቻል ከሆነ የሚቻለው የጽንፈኞች ፕሮፓጋንዳ መስሎ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ዘላቂ የሆነው እና ጽናት ያለው መንግሥት እንዲኖር የሚያስፈልገው ዲሞክራሲ መጠነኛ ሳይሆን ሰፋ ያለ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሕጋዊ ሥርዓትና ፍትሕ ለሁሉም እኩል መፈጸሙን መንግሥታዊ ተቋማት ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይሎች ሰብአዊ መብትን የሚያከብሩና የሰውን ክብር የሚጠብቁ መሆን አለባቸው፡፡ ሰዎች ተደራጅተውና ተሰብስበው ለሰላማዊ ለውጥ ለማምጣት የመናገር ነጻነትና  ጠንካራ ሲቪል ማህበረሰብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡  ሰዎች ያለፍርሃትና ያለስጋት እምነታቸውን ለመተግበር ይችሉ ዘንድ የሃይማኖት ነጻነት መኖር አለበት፡፡ እነዚህ ሁሉ በሁከት ላይ የተመሠረተ ጽንፈኝነትን ለመቋቋም ከሚያስችሉት ዘዴዎች አካላት ናቸው፡፡

‹‹አራተኛው በዚህ ሁሉ ጥረት ግለሰቦች ጽንፈኞች በዘረጉት የርእዮተ ዓለም ወጥመድ እንዳይወድቁ በማድረግ ዋነኛ ተባባሪዎቻችን ሊሆኑ የሚችሉት የራሳቸው ማህበረሰቦች ሲሆኑ በዚህ ረገድ የራሳቸው ቤተሰብ አባላት ዓይነተኛውን ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ለራሳችን ታማኞች መሆን አለብን፡፡ እንደ አልቃኢዳና አይሲል ያሉ አሸባሪ ቡድኖች ሆን ብለው የፕሮፓጋንዳ ዒላማቸውን የሚያነጣጥሩት የወጣት ሙስሊሞች በተለይም በቀላሉ የሚታለሉላቸውንና ከማንነታቸው ጋር የሚታገሉት ወጣቶችን ልብ ለማሸነፍ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ሐቁ ይህ ነው፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ቪዲዮዎች፣ የኢንተርኔት መጽሔቶች፣ የሶሻል ሚዲያዎች፣ የአሸባሪዎች ትዊተሮች ሁሉ ኢንተርኔትና ሳይበርስፔስ ተጠቃሚ ወጣቶች ተኮር ናቸው፡፡

ስለሆነም እነዚህ አሸባሪዎች ከሁሉ አስቀድሞ ዒላማ ያደረጓቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች (ወጣቶች) ሲሆኑ ኅብረተሰቡም ራሱን በመከላከል ግንባር ቀደም መሆን ይኖርበታል፡፡ …አንድ ሰው ከሌላው ሰው በተለየ ሁኔታ ሥር ነቀል ለውጥ ፈላጊ መስሎ ሲታይ በመጀመሪያ የሚያስተውሉት ቤተሰቦችና ጓደኞች ናቸው፡፡ መምህራን ተማሪዎቻቸው የትምህርት የመማር ዝንባሌያቸው ሲቀንስና ከራሳቸው ማንነት ጋር ሲታገሉ ሲመለከቱ ምን ችግር እንደገጠማቸው ቢጠይቋቸውና ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ምናልባት ከጥፋት መንገድ ሊመለሱ ይችላሉ፡፡ ቤተሰቦችና ጓደኞች፣ የሥራ ባልደረቦች፣ ጎረቤቶች፣ የሃይማኖት አባቶች የሚወዷቸው ሰዎች በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይጓዙ ሊታደጓቸው ይገባል፡፡  

ይሁንና ኅብረተሰቡ (ወደአዋኪነትና ጽንፈኝነት እየሄዱ መሆናቸውን የሚጠቁሙ) ምልክቶችን ሁልጊዜም ላያውቋቸው ይችላሉ፡፡ ወይም እንደምን ወደዚያ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎች ላይኖራቸው ይችላል፡፡…ስለሆነም ሕብረተሰቡን በጅምላ መወንጀልም ሆነ መፈረጅ ማስቆም ሥራችን መሆን አለበት፡፡ ማንም ሰው በእምነቱ ምክንያት ያልሆነ ስም ሊሰጠውም ሆነ በጥርጣሬ ደመና ሥር መውደቅ አይኖርበትም፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚኖረው ግንኙነትም በጥርጣሬ ዓይን በመመልከት መሆን አይኖርበትም፡፡ ከአሜሪካውያን ሙስሊሞች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በሕግ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መፈለግ አይኖርብንም፡፡ እነሱም በጥርጣሬ ዓይን ሊመለከቱን ይችላሉና፡፡ ይህ ከሆነ አብረን ለመሥራት የሚያስችለንን መተማመን ለመገንባት እንቸገራለን፡፡

በዚህ ጉባኤ ሙስሊም አሜሪካውያንን ጨምሮ በውጭ አገሮች የሚገኙ ማሕበረሰቦችን ያሚያቅፍ እንቅስቃሴ አጠናክረን እንደምንቀጥል እያወጅን ነው፡፡ ከተባባሪዎቻችን ጋር በመሆን ንቃተ ሕሊናቸውን በማዳበር በርካታ ሰዎች የሚወዷቸው ሰዎች ከጽንፈኝነት ለመታደግ እንዲችሉ ጥረታችንን ከፍ እያደረግን ነው፡፡  ለዚህ ጥረት መሳካትም ተጨማሪ በጀት መመደብ ይኖርብናል፡፡

እዚህ አሜሪካ ውስጥ ኢስላም አሜሪካ ሕልውናዋን ካገኘችበት ጀምሮ ድርና ማግ ሆኖ የኖረ ነው፡፡ ሙስሊም ስደተኞች ወደዚህ መጡ፣ እንደ ገበሬ፣ ነጋዴ፣ የፋብሪካ ላብ አደሮች፣ ሆነው ለሥራ ተሠማሩ፣ የባቡር መንገድ በመሥራት አሜሪካን ገነቡ፡፡ የመጀመሪያው የሙስሊም ማዕከል በኒው ዮርክ የተመሠረተው በ1980 (እ.ኤ.አ) ነው፡፡ የመጀመሪያው የሙስሊም መስጊድ የተገነባውም በሰሜን ዳኮታ ነበር፡፡

ሙስሊም አሜሪካውያን ፖሊስ መኮንኖች ሆነው አገራችንን ጠብቀዋል፡፡ እሳት አደጋ ሠራተኞች በመሆንም አገልግለዋል፡፡ መለዮ በመልበስ አገሪቱን እያገለገሉ ነው፡፡ በሀገር ውስጥና በውጭ አገር የሀገሪቱ ደህንነት ባልደረቦች በመሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ በሀገራችን በሚገኙ የመቃብር ስፍራዎች በአርሊንግተንም ሙስሊም ጀግኖች ሕይታቸውን የሁላችንንም ሕልውና ለማቆየት ሲሉ በሰላም አርፈዋል፡፡ …የአሜሪካ ሕብረተሰብም መዘንጋት የሌለበት ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም ጥላቻ፣ ዘረኛነት፣ መድልዎ፣  ብዥታ፣ አለመቻቻል በሀገራችን ቦታ እንደሌላቸው ማስታወስ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ መሆን ያለበት ጸረ ምርት ስለሆነ፣ ወይም አሸባሪዎችን የሚረዳ ስለሆነ ሳይሆን ትክክል ስላልሆነ ነው፡፡ ከኛ ማንነት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ነው፡፡

  1. የሚስተር ኦባማ የማጠቃለያ ንግግር

እነዚህን ፈተናዎች ለመጋፈጥ ወደፊት በተራመድን መጠን ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ ሁላችንም በዚህ ረገድ የሚጠብቀን ጠንካራ ሥራ አለ፡፡ ይህንን ጉዳይ የወረቀት ጉዳይ አናደርገውም፡፡ ፖለቲካዊ ትክክለኛነትን በመከተልም ችግርን ልናስወግደው አንችልም፡፡ … ጽንፈኞች መጠቀሚያ የሚያደርጓቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብሶቶች በማስወገድ፣ ሕብረተሰቡ የስልጣኑ ባለቤት መሆኑን በማረጋገጥ፣ እንደ ብዝህነት፣ የኅብረተሰብ መቻቻል ላሉ እሴቶቻችን በስጋት ላይ በምንሆንበት ጊዜ ሁሉ፣ በተለይም ስጋት ሲገጥመን በሐቅ ዘብ በመቆም ሌሎችን መርዳት ይኖርብናል፡፡

ይህም ከወታደራዊ እርምጃ የተጣመረ ሊሆን ይችላል፡፡ መቆም ያለባቸው በአረመኔነት ላይ የተመሠረቱ ጭካኔዎች አሉ፡፡ … ነገር ግን እነሱ ያደጉበትን አፈር ለማጥፋት እና ለሁሉም ብሩህ ተስፋ ለመስጠትና ዘላለም ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖር ከፈለግን እንግዲያው ሁሉም ልጆቻችን፣… ቦታ እንዳላቸው ግልጽ ማድረግ አለብን፡፡ እዚህ አሜሪካ ውስጥ ቦታ ይኖራችኋል፡፡ በምትኖሩባቸው አገሮች ቦታ ይኖራችኋል፡፡ የወደፊት ተስፋ ይኖራችኋል፡፡

በመጨረሻም ለአዋኪ አመጸኞቹ መድኃኒት የሚሆኑት እነዚህ ናቸው፡፡ ይህም ሁላችንም በአንድ ላይ የምንሠራው ሥራ ነው፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ የትውልድ ፈተናም ነው፡፡ ዳሩ ግን ከ238 ዓመታት በኋላ አሜሪካ ከዚህ የበለጡ በርካታ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡ ከሁለት ክፍለ ዘመናት በላይ ለሆነ ጊዜ ለቆዩ የጋራ አመለካከቶቻችን እና ለእየአንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር መልካም ዕድል፣ ለፍትሕ፣ ለክብሩ ተጠብቆ መቆየትም ታማኝ ሆነን በአንድነት እንዘልቃለን፡፡

  1. የጸሐፊው አስተያየት

በመሠረቱ አሸባሪነት፣ ጽንፈኛነት፣ አክራሪነት አዋኪነት፣ አመጸኛነት የሚባሉት ስሞች በእርግጥ ችግሮች ሳይሆኑ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት የፖለቲካ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው የማስፈራሪያ ቃላት ሆነው መታየት የሌለባቸው መሆኑ ነው፡፡ ቁም ነገሩ፣ እዚህ ላይ ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ ባለበጎቹን አስደንግጦ ለማሯሯጥ ሲል ተኩላ ሳይኖር ተኩላ መጣ እያለ መጮሁና እነሱ ሲመጡ ቀልዴን እኮነው እያለ በጎቹን እንዳስጨረሰው መሆን የለበትም፡፡

አንድ እውነት ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ሚስተር ኦባማ ለማስረዳት እንደሞከሩት በሁከት ላይ የተመሠረተ አመጽ ከአንድ ወገን ብቻየሚመነጭ አይደለም፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ክርሰቲያኑ የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ መሪዎች ዓለም የአንድ እምነት ተከታዮች እንድትሆን የሚፈልጉትን ያህል ሙስሊም የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ መሪዎችም ዓለም ኢስላም የሰፈነባት እንድትሆን ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ የአይሁድ እምነትም ከክርስትናና ከእስልምና የጎላ በነበረበት ዘመን ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳሳዬ ከታሪክ ምዕራፎች የምንረዳው ነው፡፡ የንጉሥ ሰለሞንን፣ የሳኦልን፣ የዳዊትንና የሌሎችን የመስፋፋት ታሪክ ከዚህ አኳያ የሚጠቀስ ነው፡፡ በሩቅ ምሥራቅም የቡድሂዝም፣ የኮንፊሸየሲዝም እምነት የበላይነት ለማስፋት ጥረት ተደርጓል፡፡ በሁሉም በኩል የበለጠ ተጽእኖ የሚያደርጉት የፖለቲካ መሪዎች እንደሆኑ ደግሞ ከጥንታዊው የዓለም ታሪክ ጀምሮ የምንረዳው እውነታ ነው፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ መሪዎቹ እንዲያ ቢሉም፣ ሃይማኖቶቹ አንድ ዓይነት ሃይማኖት ብቻ በዓለም እንዲሰፍን ይመክራሉን? ብለን ስንጠይቅም ‹‹አዎን፣ አይደለም›› የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ አዎን የሚለውን ጽንፍ የሚይዙ የፖለቲካ መሪዎች ስልጣኑን ሲይዙት ዓለም በሃይማኖት ምክንያት ትናጣለች፡፡ ‹‹ሃይማኖትን የተለያየ ያደረገው እራሱ ፈጣሪ ነውና በዚህ ምክንያት አንለያይ…›› የሚሉ የፖለቲካ መሪዎች ስልጣኑን ሲይዙት ደግሞ ሰላምና መረጋጋት ይታያል፡፡

ለምሳሌ ‹‹የሙስሊም ወንድማማችነት›› የሚለውን እንመልከት፡፡ የሙስሊም ወንድማማችነት የተመሠረተው ከኢስላም እምነት በመነጩ የመርህ ሐሳቦች ነው፡፡ እነዚህ የመርህ ሐሳቦች በአንድ መልኩ ሲወሰዱ ሙስሊሞች የትም ይኑሩ የት ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በመሬት ብቻ ሳይሆን በሰማይም በአንድነታቸው ይገናኛሉ፡፡ በአንድነት ይተዛዘናሉ፣ ኢስላማዊ ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ኢስላም እንዲስፋፋ በማድረግ የሙስሊም ወንድማማችነት ማሳደግ ይቻላል›› የሚል ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህ አመለካከት የይሁዲውም የክርስቲያኑም አመለካከት ሊሆን እንደሚችል መካድ ይቻላል?

ቀደም ሲል ለማውሳት እንደተሞከረው የሙስሊም ወንድማማችነት አንደኛው ዓላማ ኢስላም ያውም በኢስላም ወንድማማችነት የሚያምን ኢስላም እንዲስፋፋ ነው፡፡ ይህም ሲሆን ሃይማኖቱ ከሚስፋፋባቸው መንገዶች አንዱ በአንስተኛው በሌላው ላይ ተጽእኖ በማድረግ ይሆናል፡፡ ተጽእኖው ቀላል ሲባል በማስተማር፣ አነስተኛ ስጦታዎችን በመስጠት፣ በመገባበዝ፣ የወንድማማችነትን ስሜት በማሳየት ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ ተጽእኖው ከዚህ ከበድ ሲል የእነርሱን አመለካከት ከፍ ከፍ አድርጎ የሌሎችን መረጃዎችን እያቀሱ ከማንኳሰስ፣ ከዚያም የማዋረድ፣ የመሳደብ፣ የመማታትና የመግደል ተጽእኖ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የክርስቲያንና የአይሁድ ወንድማማችነትስ ከዚህ የተለየ ነውን?

በሀገራችን ሰላምና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ልማትና ዕድገት ይመጣ ዘንድ ይህንን እውነታ በሦስት ጠንካራ ምሳሌዎች ማስረዳት እንችላለን፡፡

አንደኛው የመስቀል ጦርነት ነው፡፡ የመስቀል ጦርነት ለ300 ዓመታት ያህል የተካሄደው ኢስላምን ጨፍልቆ ክርስትናን በመሬት ላይ ለማንገሥ ነበር፡፡ የመስቀል ጦርነት ሲደረግም የራሱ የሆነ የፖለቲካ መነሻና ትንተና ነበረው፡፡ ካለበለዚያ ከመላው አውሮፓ ተነስቶ እስልምና በተስፋፋበት ቦታ ሁሉ የደረሰው አመለካከቱን የሚቀበል ሳያሳምን አይደለም፡፡ ስለሆነም ዓለምን እስከ ምጽዓት ድረስ የክርስቲያን ለማድረግ ጦርነቱ በተደጋጋሚ ተካሄደ፡፡ ያኔ የመስቀል ጦርነት ያካሄዱት ሰዎች ደጋፊዎች ነበሯቸው፡፡ በዘመቻው ለሚሳተፉ ሁሉ ወሮታቸው በሰማይም በምድርም እንደሚመለስ፣ ትተዋቸው የሚሄዱ ቤተሰቦቻቸው አስፈላጊው ክብካቤ እንደሚደረግላቸው፣ በምርኮ አፍሰው (ዘርፈው) የሚያመጡት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ እንደሚያገለግላቸው እየተነገራቸው፣ ብዙ ነገሮች ቃል እየተገቡላቸው መዝመታቸው ከታሪክ ምእራፎች የምንረዳው ሐቅ ነው፡፡ በአጭሩ የመስቀል ጦርነት እንደዛሬው ያለ አግባብ በሥራ ላይ የዋለው የጅሀድ ጦርነት ሁሉ የኦሪት እምነትንና ኢስላምንና ደፍጥጦ ክርስትናን ለማስፈን ነበር፡፡ ይሁንና በዚህ የመስቀል ጦርነት ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ በሀገራቸው የሚኖሩ ብዙ ክርስቲያኖች የተገደሉበት፣ አይሁዶች የተጨፈጨፉበት፣ ሌሎችም እምነት ተከታዮች ለእልቂት የተዳረጉበት ስለሆነ ከሃይማኖታዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ነበር ማለት ይሻላል፡፡ ዛሬ በጅሃዲስቶች፣ በጽንፈኞች፣ በአዋኪዎችም የሚያልቀው በአብዛኛው ሙስሊሙ ነው፡፡ የሚደመሰሰው የሙስሊም ረቂቅና ተጨባጭ ቅርስ ነው፡፡ የሚወድመው የሙስሊሙ ህብረተሰብ ሀብትና ንብረት ነው፡፡ ስለዚህም ጉዳዩ ፖለቲካዊ እንጅ መንፈሳዊ ሊሆን አይችልም፡፡

ሁለተኛው ተጨባጭ ምሳሌ በሀገራችን ለ300 ዓመታት እስልምናን አጥፍቶ ክርስትናን ለማንገሥ ወይም በጂሃድ ስም ክርስትናን አጥፍቶ እስልምናን ለማንገሥ የተደረገው ጦርነት ነው፡፡ ከዚያ ቀደምም በኦሪት እምነት ተከታዮችና በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ እጅግ አስከፊ ጦርነት ተካሂዶ በአጭሩ ለኢትዮጵያ ስልጣኔ መዳከም አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በውጤቱም የኦሪት እምነት ተከታዮች ‹‹ፈላሾች›› አሰኝቶም በሀገራቸውና በወንዛቸው ስደተኛ እንዲሆኑ አብቅቷቸዋል፡፡ ችግሩ እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ቀጥሎም ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ ሰው አገር እንዲሰደዱ አድርጓቸዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ‹‹ኢማም አሕመድ ኢብራሂም›› በሚልና ‹‹መቻቻል›› በሚል አርእስት በጻፋቸው መጻሕፍት እንደጠቀሰው ሁሉ በሁሉም ጎራዎች በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ሀገራችን ከመደህየቷ፣ ጥንታዊ ቅርሷና ሀብቷ ከመውደሙ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብም ከመጎዳቱ በስተቀር ክርስትናም፣ እስልምናም፣ ኦሪታዊነትም አሉና አንድ ሃይማኖትና አንድ አገር ለማምጣት የተደረገው ጦርነቱ ያሰገኘው ጠቀሜታ የለም፡፡

ይህ ሐቅ ዴምከራሲያዊ ስርዓት እንገነባለን፣ ፍትሕና ርትዕ እናሰፍናለን፣ በአጭር ጊዜ ከድህነት አዘቅት አውጥተን ከባለጸጎች ተራ እንሰለፋለን እያል የራሳችን ሐቅ ስለሆነ ልንደብቀውም፣ ልንሸሸውም አንችልም፡፡ ይልቁንም የበለጠ ብልጽግና እናመጣለን ብለን በምናቅድበት ጊዜ ይህን እውነታ ሳናድበሰብስ ማስተዋል ይገባናል፡፡ የሚስተር ኦባማ ዋነኛ መልእክትም ይህን ይመስላል፡፡

በሀገራችን፣ ጥንት የኦሪት፣ ቀጥሎም የክርስትና ከዚያም የእስልምና እምነት ተከታዮች ሆነው ደግሞም ሁሉም እንደኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያን ስልጣኔ አሳድገዋል፡፡ ነጻነቷን ጠብቀውም ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያንም፣ ሙስሊምም ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑና እንደ ኢትዮጵያዊም እራሳቸውንና ሀገራቸውን ከወራሪ ሲከላከሉ እንደነበረ የሚካድ ሐቅ አይደለም፡፡ ስለሆነም ነገሮችን በቅንነት ስንመለከታቸው ከ10ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን በሃገራችን የተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ክርስቲያኖች ኢትዮጵያውያን ስለነበሩና ሙስሊሞች ኢትዮጵያውያን ስላልሆኑ ወይም የአንደኛው ኢትዮጵያዊነት ከሌላው ኢትዮጵያዊነት የላቀ ስለሆነ ወይም የገነነ ስለሆነ አልነበረም፡፡ ‹‹የእውነተኛው ኢትዮጵያዊ እኔ ነኝ እንጅ አንተ አይደለህም፡፡ ስለዚህ አንተ ተገዥ እኔ ደግሞ ገዥ ነኝ›› የሚለው አመለካከትም ለብዙ ጊዜ ሲያፋጃቸው እንደነበር ግን አይካድም፡፡  በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ሌሎች በርካታ እንከኖችም አሉ፡፡

ሦስተኛው ምሳሌ ዛሬ ያለንበት ተጨባጭ እውነታ ነው፣ ሐቁን ቁም ለቁም ገልጠን ስናየው ዛሬም የኔ ሃይማኖት፣ የኔ ድርጅት፣ የኔ ዘር፣ የኔ ሥዕል፣ የኔ ምንትስ ወዘተ…የሚል አመለካከት የለም ማለት አንችልም፡፡ ይህ አመለካከት በልዩ ልዩ ሁኔታዎች እንደሚንጸባረቅም አሌ አይባልም፡፡ ሌላው ግልጽ ያልሆነውንና በቢሮክራሲው የሚፈጸመውን ለጊዜው  አቆይተን ለሁሉም ፊት ለፊት የሆነውን መገናኛ ብዙሃን እንመልከት፡፡ ያኔ ድሮ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ መገናኛ ብዙሃኑ የቆመው ለዙፋናዊው መንግሥት ነበርና የዕለት ተዕለት ሥራም ዜና ሆኖ ይቀርብ ነበር፡፡ በደርግ ጊዜም ለደርግ ነበር፡፡ የዚህ መንግሥት ፍላጎት ገና ከበረሃ ትግሉ ጀምሮ ዲሞክራሲን ማንገሥ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ሕያውነትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መስዋእት ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ዛሬ በየእለቱ የምናየውና የምንሰማው ይህንን ነው? ለምሳሌ በዚህ ምርጫ ተፎካካሪዎች ያቀረቡት ሐሳብ ምን እንደሆነ ሳናውቅ ‹‹ጸረ ሰላም፣ ጸረ ዲሞክራሲያዊ አቋም ስለሚያንጸባርቅ መከልከሉ›› ይነገረናል፡፡ ምን አሉ? ተብሎ ቢጠየቅ መልሱን የሚያቁት ከልካይና ተከልካይ ናቸው፡፡ በመሠረቱ ‹‹የኢሕአዴግን አባላት ሰላም አትበሉ፣ ቢሞቱ አትቅበሩ፣ አትድረሱ›› በተባለበት አገር ‹‹ኢሕአዴግን የመረጠ ጥቁር ውሻ ይውለድ›› ተብሎ በተማማለበት አገር፣ የሀገር ምስጢሮች ለጠላት በተጋለጡበት አገር፣ ጦርነት ቀስቃሽ ሐሳቦች አይሰነዘሩም ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የሚዲያው ሚና መሆን የነበረበት የተለያየ አመለካከትን ማቅረብ፣ ሐሳቡንም ሕዝብ እንዶዝነው ማድረግና ሃሳቡ ተዛብቶ የቀረበበት እንዲያስተባብል ዕድል መስጠት መሆን ነበረበት፡፡ ክርከሩ መጦፍና መጦዝ ነበረበት፡፡ ከዚያ ክርክርም ሕዝብ የፈለገውን እንዲመርጥ ማመቻቸት ነው፡፡ አሁን ግን አንድን ድርጅት ወክሎ የመቅረብ ይመስላል፡፡ መወከሉም ትክክል ባይሆንም ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠንካራውንና የማይበገረውን ድርጅት ሳይቀር ያለድጋፍ የማይቆም ሐረግ አስመሰለው፡፡ ትላንት በሽግግሩ ዘመን፣ የቃላት ሳይሆን የጦር መሣሪያ ተቃውሞ ያላንበረከከው ድርጅት ልፍስፍስና ፈሪ አስመሰለው፡፡  ለመሆኑ የመንግሥት ዴሞክራሲያዊት ዛሬ ካልታየ መች ሊታይ ነው? ከዚህ ወዲያ ቆራጭነት ብቻ ሳይሆን ፈላጭነት ምን አለ ቢባል አያስኬድም? ታዲያ ይህ ዲሞክራሲንም ሆነ ዲሞክራሲያዊነትን የሚያደበዝዝ እንጅ የሚያጎላ ነው? እንዴትስ ነው ይህች አገር የሁሉም አገር መሆኗን ማረጋገጥ የሚቻለው? ሌላውም እንደዚሁ ነውና የኦባማን መልእክት ልብ ልንለው ይገባል፡፡

በመጨረሻም፣ ሀገራችን የበለጠ እንድታድግና እንድትለማ ወይም ኢሕአዴግ የጀመራቸው በጎ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በአንድ ወገን ወይም ይህን ወገን በሚደግፉ ብፁዕ ወቅዱስ ወሐዋሪያዊ ሕዳሴ የሚባል መንግሥት ሳይሆን ሚዛናዊ የሆነ፣ ሕዝብን የሚያሳትፍ፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ተቀናቃኝን የማይንቅ፣ ሙገሳንና ሙከሻን ብቻ ሳይሆን መራርም ቢሆን የሚቀርብለትን ቅን አስተያየት የሚሰማ፣ ዓላማውን ለማሳወቅ ከሚያደርገው ጥረት አኳያ ሌሎች አማራጭ የሚለትን ሐሳብ በቅንነት የሚመለከት መሆን አለበት፡፡

በሃይማኖት ረገድም ቢሆን ማየት ያለበት ዝርዝር ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ገልጦና ገላልጦ በማየት መፍትሔ መፈለግ ሲገባው የሚያዳፍናቸው ከሆነ ውሎ አድሮ ችግር መከሰቱ አይቀርም፡፡ ራሳቸውን ነገደ እስራኤል ብለው አገራቸውን ጥለው የተሰደዱ ወገኖቻችን ጥቁር ኢትዮጵያውያን ቢሆኑም ‹‹ፈላሾች›› ተብለው ከብዙ በሺህ በሚቆጠሩ ዓመታት በደረሰባቸው የማግለልና መብትን የማፈን፣ ፍትሕን የማሳጣት ተግባር እንደሆነ መፈተሽ ይገባል፡፡ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ እንዲፈነጥቅባት ሚስተር ኦባማ ‹‹አሜሪካ የአሜሪካውያን ናት፣ አንዱ በሥጋት ሌላው በኩራት የሚኖርባት አገር አይደለችም›› እንዳሉት ሁሉ እኛም ይህንን ለማለት መቻል አለብን፡፡ በእርግጥም ሁሉም በዜግነቱ ኮርቶ የሚኖርባትን ኢትዮጵያ ከማየት የበለጠ ሊኖር አይችልም፡፡ በተለይም ይህን ፍትሕና ርትዕ አይተንና በተቀረው ዕድሜያችንም አጣጥመን በሰላም ለማለፍ ለምንመኝ ለእኛ፣ ለዲሞክራሲ ናፋቂ ለሽማግሌዎቹ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...