Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አይ ማዘጋጃ ቤት?

በይኼነው ከተማው

ከዚህ ቀደም እንደገለጽኩት ረዘም ላለ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ተመድቤ በማገልገል ላይ ነኝ፡፡ ከዚህም በመነሳት በቅርብ የማያቸውን ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ስገልጽ ቆይቻለሁ፡፡ ነገር ግን ለውጥ ለማያመጣ ነገር ብዬ ሁሉንም ነገር ትቼው ቆየሁ፡፡ ሰሞኑን ግን የማየው ነገር አላስችል አለኝ፡፡ እናም ይኼን ጽሑፍ ለመላክ ወሰንኩ፡፡ ጽሑፌም የራሴ የግል አስተያየት ብቻ ከሆነ ወገናዊ ሆኜ የተዛባ አመለካከት እንዳልይዝ ስለሰጋሁ ሌላ አማራጭ ወሰድኩ፡፡ ስለሆነም የመሥሪያ ቤታችንን የግል ባለጉዳዮችን፣ መንግሥታዊና የግል ኩባንያዎችን ጉዳይ አስፈጻሚዎች አነጋገርኩ፡፡ በተለይ ችግር ይበዛባቸዋል በተባሉት ክፍላተ ከተሞችና ወረዳዎችም ጭምር በአካል ተገኝቼ ተመለከትኩ፡፡ ይኼንን መሥሪያ ቤታችንን ቀደም ያሉት አባቶቻችን ማዘጋጃ ብለው ሲያወጡለት፣ ቃሉ ጥሬ ትርጉም ማስተካከያ፣ ማሰናጃ፣ ተገቢ አገልግሎት መስጫ እንዲሆን አስበው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ማዘጋጃ ማበሳጫ፣ ማናደጃ፣ ነዋሪውን ማማረርያ ሆኗል፡፡

እንዳየሁት፣ በጥናትና በጥያቄ በሰበሰብኩትም መረጃ ይኼን ጽሑፍ ለማዘጋጀት በወሰንኩበት ጊዜ በቢሮአችን ለረዥም ጊዜ በተቀመጠ አንድ መጽሔት ላይ አይኔ አረፈ፡፡ በሽፋን ገጹ ላይ ያለው ቃል ወይም ጽሑፍ በጣም አስገረመኝና ሌላው ይየው አልኩ፡፡ የመጽሔቱ ስም በትልቁ ሽፋኑ ላይ ተጽፏል፡፡ ‹‹ማዘጋጃ ቤት›› ይላል፡፡ አሳታሚው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት ለመሆኑ በመጽሔቱ ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ቅጽ 1 ቁጥር 2 የካቲት 2003 የታተመው መጽሔት እንዲህ ይላል በፊት ሽፋን ገጹ፡፡ ‹‹ሥሩን እንደ ባህር ዛፍ ከመሬት ውስጥ የቀበረው የሙስና አሠራር ወቅት ጠብቆ እንዳያለመልም የሕዝብና የመንግሥት ዓይን ሐሩር ሆነው አድርቀውት ከሥሩ እስኪመነገል ድረስ፣ መንግሥትና ሕዝብ ወፍና ድንጋይ ሆነው ሌት ተቀን ሊከታተሉት ይገባል፡፡›› አነበባችሁልኝ አቤት ቃላቱ ደስ ሲሉ፡፡ ነገሩ ግን የተገለቢጦሽ ሆኖ ሥሩ አድጎና እንደ ባህር ዛፍ ውስጥ ለውስጥ ሄዶ ሕንፃውን ሊንደው ተቃርቧል፡፡

ዛሬ ማዘጋጃ ቤት ባለቤት ያጣ ሕንፃ ሆኗል፡፡ እንኳንስ ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸውን ባለጉዳዮች ራሱን የሚመለከተው አጥቷል፡፡ በጓሮ በኩል በባለጉዳይ መግቢያ የተበላሹና የቆሸሹ መኪናዎች ማከማቻ ሆኗል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በርካታ ገንዘብ ወጥቶ የታደሰው ሕንፃ ተሰነጣጥቋል፡፡ ለዓይን የሚስበው አፀድና አትክልት የለም፡፡ የሚገርመው በከንቲባው ቢሮ ግራና ቀኝ ያሉት መፀዳጃዎች እንኳን ሽታቸው አያስቀርብም፡፡ ኮሪደሮቹ ታኝከው በተጣሉ ማስቲካዎች ተጣብቀው ይታያሉ፡፡ ይኼ ሁሉ ባለበት ሁኔታ እያንዳንዱ ጽሕፈት ቤት የሚለጠፈው ማስታወቂያ እውነት ይኼ ቤት ባለቤት አጣ ያሰኛል፡፡ ማንም መጥቶ የሚያረጋግጠው ነው፡፡ የሕንፃው ምሰሶዎች፣ መወጣጫ ደረጃዎች፣ ግርግዳዎችና መስታወቶች ሳይቀሩ የማስታወቂያ መለጠፊያዎች ሆነዋል፡፡ ዛሬ ጠቅላላ ስብሰባ ስላለ አገልግሎት አንሰጥም፣ ለኢንዱስትሪ ቦታ ጠይቃችሁ ሰነድ ያላሟላችሁ በ…ክፍለ ከተማ የወጣው ሊዝ በስህተት ስለሆነ ተዘርዟል፣ የህዳሴ ግድብ መዋጮ ከፍላችሁ ያጠናቀቃችሁ ዝርዝር፣ የወሩ ምርጥ ፈጻሚ፣ ትምህርት ለመወዳደር የምትፈልጉ፣ ኧረ ስንቱ አንዱ ሳይላጥ አንዱ ላይ እየተደረበ ይለጠፋል፡፡ ሃይ የሚል ሰው ጠፍቷል፡፡

የከተማውን ነዋሪ በፅዳት ጉድለት የሚቆጣጠረውና ማስታወቂያዎች ያላግባብ ተለጠፉ የሚለው የበላይ መሥሪያ ቤት የእሱን የዓይን ጉድፍ የሚያወጣለት አጥቷል፡፡ ይኼ ቢሮ የከንቲባ እገሌ ቢሮ አይደለም፡፡ የአስተዳዳሩ መለያ የውጭ እንግዶች የሚጎበኙት ነው፡፡ ሰሞኑን ይባስ ብሎ በከንቲባው ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት ባለ ቦታ ላይ የብረት ምሰሶ ተደርጎ በቀለም ተሰምሮ ገመድ ተዘርግቶ የመረብ ኳስ መጫወቻ ሆኗል፡፡ ይኼ በእጅጉ አሳፋሪ ነው፡፡ ለነገሩ የእኛ ባለሥልጣናት በተመደባላቸው መኪና ሲወጡ ሲገቡ ይኼን አለማየታቸው አስገርሞኛል፡፡

መኪና ስል ሌላ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ መቼም መኪና ለመግዛት ያሰበ እዚህ ማዘጋጃ ያሉ ሾፌሮችን ቢጠይቅ ጥሩ መረጃ ያገኛል፡፡ የትኛው ይሞቃል? ዳገት ሲወጣስ ጥሩ ነው ወይ? ምቾትም ቢጠይቅ ይገለጽለታል፡፡ ለምን ቢባል ልክ እንደ ማሳያ የእንግሊዙ ፎርድ፣ የጃፓኑ ቶዮታ፣ ማዝዳና ኒሳን፣ ሚትሱቢሺ፣ የህንዱ ማሃንዲራ፣ የአገር ውስጥ ጄሊ፣ ዓባይ፣ ቢሾፍቱ ሁሉም አለ፡፡ የሚገርመው መኪኖቹ ተገዝተው ለቡራኬ ይመጣሉ መሰል ሁልጊዜ ነው ሜዳ ላይ ቆመው የምናያቸው፡፡ ከዚህ ጋር ሌላው አስገራሚ ነገር ባለጉዳይ ለሚፈልገው ሥራ መሐንዲስ ወይም ሌላ ተሽከርካሪ አቅርብ መባሉ ነው፡፡ ይበልጥ አስገራሚው ደግሞ ይህ ሁሉ ተሽከርካሪ ያለው መሥሪያ ቤት ባለሙያዎቹ ለሥራ ሲወጡ ሚኒባስ  ታክሲ ይከራያል፡፡ በማዕከልም በክፍለ ከተማም፡፡ የበጀት አመዳደቡ ቁጥጥር የለውም ወይ? ያሰኛል፡፡ የአስተዳደሩ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ቢሮ ይኼንና የመሳሰለውን ካልተቆጣጠሩ ምን እየሠሩ ነው? እንደማየው ከፍተኛው ወጪ የተሽከርካሪና የመስተንግዶ ነው፡፡ ሁልጊዜ በየሆቴሉ ድግስ ነው፡፡ አበሉ ለጉድ ነው፡፡ የሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ክፍላተ ከተሞች በስብሰባ ሰበብ በየሆቴሉ ሲዞሩ ይውላሉ፡፡ ስብሰባው የ20 ቀናት፣ የ30 ቀናትና የ40 ቀናት ሥልጠና ይባላል፡፡ እኔ መቼም እዚህ ያለው ሲቪል ሰርቫንት እንጂ ኳስ ተጨዋች አይደለም ዓመቱን ሙሉ ሥልጠና የሚሰጠው፡፡ ቢሠለጥንም ሕዝብ ማማረር ነው፣ ባይሠለጥንም ማማረር ነው፡፡

በዚህ በኩል የታዘብኩት የተለየ ነው፡፡ የሥራ ፀባያቸው ከባለ ጉዳይ ጋር አገናኝቶ ጥቅም የሚያገኙ ሥልጠናን በፍፁም አይወዱትም፡፡ ሌሎች ደግሞ የትራንስፖርት የወር ወጪ የከበዳቸው አበሉም አለ፣ እረፍቱም አለ፡፡ ሁልጊዜ የወሰዱት ሥልጠናም ቢሆን ከመድገም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ባብዛኛው ከጥቅም ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በተለይ እንደ ግንባታ ፈቃድ፣ ከተማ ፕላን፣ መሬት ባንክና ማስተላለፍ፣ ከተማ ማደስ ያሉ ባለሙያዎች በእጅጉ የሚጠሉት ነገር ቢኖር ሥልጠናና ስብሰባ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ አብዛኞቹ ሠራተኞች ይኼ የመሥሪያ ቤቱ ሥራ ሁለተኛ ሥራቸው እንጂ ቋሚ እንጀራቸውን የሚበሉት አይመስላቸውም፡፡ ሁሉም የጎንዮሽ ሥራ (Side Business) አለው፡፡ ይኼ ቢሮ ሰው ማግኛ ነው፡፡ በመንግሥት ቢሮና ማቴሪያል የግል ሥራ ሲሠራ ይውላል፡፡ በተለይ እንዳየሁት ጠዋት ገብተው ማታ የሚወጡት የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችና አንዳንድ የሥራ ፀባያቸው ከባለጉዳይ የሚያገናኛቸው ጸሐፊዎች ናቸው፡፡ ያው ምሳ ሰዓት ሲደርስ ከውኃ ቧንቧ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ቋጥረው የመጡትን ቀምሰው ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ፡፡ በእያንዳንዱ ጽሕፈት ቤት ባለጉዳይ ተቀብለው የሚያስተናግዱትን አንድ ብለን ከከተማ ፕላን እንጀምር፡፡ አይ አንተ መውጣት ያለብህ በዚህ ነው፣ የሕንፃው ከፍታ ይኼ ነው ካለ አለ ነው፡፡ መፍቻው ይነገረዋል፡፡ ከገባው እሰየው፣ ካልገባው ቀልጦ ይቀራል፡፡ በከተማ ማደስና መሬት ዝግጅት ፍፁም ሥርዓት ያጡ ሠራተኞች አሉ፡፡ ገና ለገና ተግባራዊ የማይሆነውን የአንተ ቦታ ‘ሬጉላራይዝ’ አይደረግም፣ ሸንሻኖ አልተሠራለትም፣ የፕላን ጥናቱን እኔ ካልሠራሁልህ ይላሉ፡፡ ይኼን የሚናገሩት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ነው፡፡ ማንም ማንንም አይፈራም፡፡ ንዑስ ሒደት መሪ ኦፊሰር ካጣመመ አጣመመ ነው፡፡ ባለጉዳዩ ጠንከር ያለ የሌለ መመርያ ይወጣበታል፡፡ (‹‹ተወኝ ልጄ…››) ያሉኝ በዚህ አካባቢ ሲማረሩ ያገኘኋቸው አንድ ግለሰብ ናቸው፡፡ እርግጥ በኃላፊ ደረጃ ላሉ ምሥጋና ማቅረባቸውን መግለጽ የግድ ይለኛል፡፡ ከአንደበታቸው የሰማሁት ነው፡፡

በዳይሬክተር ደረጃ ያሉትም ወርደው ሲቆጣጠሩ አይታዩም፡፡ ሌላው የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ነው፡፡ ተብሎ ተብሎ መፍትሔ ያላገኘ እዚያው መተረማመስ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ገልጨዋለሁ፡፡ በማዕከልም በክፍለ ከተማም ፕላኑን እኛ እንሥራልህ ነው፡፡ አይ የራሴ ባለሙያ አለኝ ካልክ ውኃ በላህ፡፡ ሌላ ጋ አሠርተህ ስትመላለስ መክረምህ ነው፡፡ ለይስሙላ በዚህ ቀን ይኼ፣ በዚህ ቀን ይኼ ተብሎ ተለጥፏል፡፡ ሥራው ሌላ ማስታወቂያው ሌላ፡፡ እዚህ አካባቢ አንዳንድ ሙያቸውን ለርካሽ ጥቅም የለወጡ የግል አርክቴክቶችና የሳኒተሪ፣ የስትራክቸርና የኤሌክትሪክ ባለሙያ የሆኑ የግል ድርጅቶች የሚሠሩት እኩይ ተግባር ተጠቃሽ ነው፡፡ የሙያ ፈቃዳቸውን ኮፒ ለእነዚህ የመንግሥት ሠራተኞች ሰጥተው ሳይሠሩ ኮሚሽን የሚቀበሉና ሌላው በሙያው ሠርቶ የሚመጣውም ተገቢውን መስተንግዶ እንዳያገኝ ከአፀዳቂዎቹ ጋር የጥቅም ትስስር የፈጠሩ አሉ፡፡ ይኼም አሠራር እኔ ፕላን ልሥራ ብሎ የሌላ ሰው ፈቃድ ማያያዝ፣ በየክፍላተ ከተማዎችም ጭምር የተለመደ ነው፡፡ በተለይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በቦሌ፣ በየካና በኮልፌ ቀራኒዮ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡

የመሬት ባንክና ማስተላለፍ እዚህ አካባቢም በኃላፊዎች ደረጃ ጥረት ቢደረግም፣ በተለይ ንዑስ የሥራ ሒደት ተብለው የሚጠሩት ዘወትር በራቸው ላይ ሰው የማይጠፋ፣ በሥርዓት የማያናግሩና በግልጽ የሚደራደሩ ናቸው፡፡ ለአገልግሎት ለውጥ የሊዝ ውል እንዲሻሻል የሚሉ ጥያቄዎችና የሊዝ ጨረታ ተግባራት ይገኙበታል፡፡ በ1995 ዓ.ም. አካባቢ በቢፒአር ወደ ክፍለ ከተማ የሄደው ሥራ ሁሉ ዛሬ እዚህ ማዕከል ይምጣ ተብሎ ሕዝቡ ሲንገላታ ይውላል፡፡ በፊት ብዙ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ የተጠናው የአገልግሎት ማሻሻያም ከዚያ በኋላ በወጡ ደንቦችና መመርያዎች ተቀይሮ፣ የከተማው ነዋሪ ለጥቃቅን ጉዳይ ማዕከል መሥሪያ ቤት ሲመላለስ መዋል ግድ ሆኖበታል፡፡ ይኼ በራሱ በግቢው ላይ የሚፈጥረው መጨናነቅ፣ በአካባቢው የትራፊክ ፍሰት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በጉልህ እየታየ ነው፡፡ በመቀጠልም በባለጉዳዩ ላይ የሚያደርሰው እንግልትና ውጣ ውረድ እንዳለ ሆኖ የሙሰኞች ሲሳይ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ለቦርድ አቀርብልሃለሁ፣ ለካቢኔ አቀርብልሃለሁ፣ በስቲሪንግ ኮሚቴ ይታያል ይባላል፡፡ እዚያው ክፍላተ ከተማ ማለቅ ያለበት ጉዳይ ሁሉ፡፡ ክፍለ ከተሞች ሥራቸው ደብዳቤ ጸሐፊነት ሆኗል፡፡ እርስ በርሱ ለሥራ ቀርቶ ለሰላምታ የማይገናኝ ካቢኔ ለጥቃቅኑ ጉዳይ ሁሉ እኔ መወሰን አለብኝ ብሎ በመመርያ ለማፅደቅ የሚፈጀው ጊዜ በራሱ ሌላ ድካም ነው፡፡

በቅርብ የማውቀውን የመሬት አስተዳደር ተናገርኩ እንጂ፣ በየሴክተሩ መሥሪያ ቤቱ ያለው ታሪክ አይ አዲስ አበባ እንዲህ ሆነሽ ቀረሽ? ያሰኛል፡፡ በመንግሥት በኩል እየተከናወኑ ያሉ በርካታ የልማት ተግባራት አሉ፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ነዋሪው እነዚህን መልካም ውጤቶች በበጎ እንዳያያቸው ይኼ መጥፎ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ የችግር አፈታት ዘዴ ሚዛን የደፋ በመሆኑ፣ ድምር ውጤቱ ሕዝቡ መንግሥትን እንዲያማርር የጎላ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከከተማው የካቢኔ አባላት እስከታችኛው የወረዳ መዋቅር ድረስ የግል ጥቅም ለማስከበር፣ የመኖሪያ ቤት ለማግኘት፣ ኑሮን በመደጎም ከሌላው በልጦ ለመታየት እንጂ፣ ኧረ ይኼን ሕዝብ በቅን መንፈስ እናገልግለው ብሎ የመጣ የለም፡፡ አዲስ አበባ ላይ መንግሥት በብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ዳይሬክተር፣ ሥራ አስኪያጅና የሥራ ሒደት ሁሉም መፈተሽ አለበት፡፡ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› ሲል የነበረ አስተዳደር ዛሬ ራሱ ነግሷል፡፡ ተበደልኩ፣ ተጉላላሁ፣ ለሚል ቆም ብሎ አንድም የሚወስን ኃላፊ የለም፡፡ ቀናውን ሁሉ ማጣመም ይቀላል፡፡ በዚህም ነው የመንግሥትን ስምና ተግባር ጥላሸት እየቀባው ነው ያልኩት፡፡ ዞር በልልኝ ቃሊቲ ልሂድህል፣ ቂሊንጦ ልግባልህ የሚሉ አባባሎች ዘወትር ይደመጣሉ፡፡ ይቺ መሸሽ ናት፡፡ ኃላፊዎችም ሥራ የሚመሩት ለሚጥረው ነው፡፡ ሌላው ኮምፒዩተር ከፍቶ ኢንተርኔት ላይ ተጥዶ ይውላል፡፡ የግል ጉዳይ ካለው በፈለገው ሰዓት ይገባል፡፡ በፈለገው ሰዓት ይወጣል፡፡ ሳይት ይባላል፡፡ ሥራውም የማያስወጣው ሁሉ የት ሄደ ሲባል ሳይት ነው፡፡ ምንም ተቆጣጣሪ የለም፡፡ እንደ ሰንበቴ ማኅበር ማነው ያልደረሰው እየተባለ ሠራም አልሠራም የወሩ ምርጥ ፈጻሚ አቶ… ይባላል፡፡

ከወራት በፊት ክቡር ከንቲባው ግቢውን ይጎበኛሉ፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንጃ የዚያን ዕለት ረቡዕ ነበር፡፡ ባለጉዳይ እንዳይገባ ተብሎ በሩ ተዘጋ፡፡ የዚያ ሁሉ ባለ ጉዳይ የመኪና ትርምስ አካባቢውን አጨናነቀው እንዲያው ለነገሩ በእግሩም የገባው ሲርመሰመስ ላየው ሌላ ተቋም እንጂ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤት አይመስልም፡፡ ሂዱ በየክፍላተ ከተሞች፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ከሰኞ እስከ ዓርብ የተገልጋዩ ወረፋ፣ በዚህ ላይ መሥሪያ ቤቱ ያለበት ቦታና ውስጥ ሲገቡም አጠገቡ ያለው መፀዳጃ ሽታ፡ ይኼ ባይኔ ያየሁት ነው፡፡ ያ ሁሉ ሰው ተሠልፎ ሲንገላታ ከመስኮት ማዶ ያሉት ሠራተኞች በሰው መሀል ጉዳይ ለማስፈጸም ሲሽለኮለኩ ማንንም አይፈሩም፡፡ ሽማግሌ የለ አሮጊት የለ በቦሌም በየካም እንዲሁ መሯሯጥ ነው፡፡ ስልክ እየደወሉ አልቆልሃል ውሰድ ይባላል፡፡ አንድ ባለጉዳይ አገልግሎት ፈልጎ ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ሐሙስ ቢመጣ ረቡዕና ዓርብ ነው የባለጉዳይ ቀን ተመለስ ይባላል፡፡ ረቡዕና ዓርብ መጥቶ እነሱ ከሌሉ ግን እያዘነና እየተበሳጨ መመለስ እንጂ መብቴ ነው ብሎ መጠየቅ አይችልም፡፡ ይህ በየቢሯችን የሚመላለሰው ሁሉ የራሱ የሆነ ኑሮ ያለውና ቤተሰብ የመሠረተ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ የእኛ ኃላፊዎች ከታች እስከ ላይ ያሉት የሚንቀባረሩበት መኪና፣ ምቾት ያለው ቢሮ፣ የቤተሰቡ ቅምጥል መሆን ይህ ደጅ የሚጠና ኅብረተሰበ በሚከፍለው ግብር ነው፡፡ ዛሬ የጣፈጠው ምግብና መጠጡም ቢሆን ብላክ ሌብልና ጎልድ ሌብል ቢሉት ሁሉም መገኛው አባ ሳሙኤል ወንዝ ነው፡፡ ወገኖቼ ይኼ ሁሉ ሲሆን ግን እጅግ ከበሬታ የሚገባቸው፣ ፊጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ቢሯቸው የሚመጣውን ባለጉዳይ እንደ ቤታቸው እንግዳ በትህትና የሚያስተናግዱ እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሥራቸውም ይኮራሉ፡፡ ኑሯቸውም የተቃና ነው፡፡ ነፃ ህሊና፡፡ ፈጣሪ ይህን ፀባያቸውን አይቀይርባቸው፡፡ ሁሉም የሚያልፍ ነው፡፡ እናም ቢቻል ቢዘከሩ ደግ ነው፡፡ ለነገሩ በጎ የተባሉት ሠራተኞች ቁጥራቸው በማነሱ በሌሎቹ ተዋጡ፡፡ ስለዚህ የከተማው ነዋሪ መፍትሔ ይሻል፡፡ እያንዳንዱ ሴክተር መሥሪያ ቤት ሊፈተሽ ይገበዋል፡፡ በየቢሮው መሳቀቁና መንገላታቱ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በከፊል ይቁም፡፡ በተለይ አውቀው የጠየቁት ሙስና ካልተሳካላቸው ደንብና መመርያን ሽፋን እያደረጉ የሚዘርፉት ተለይተው የማያዳግም ውሳኔ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮም፣ የከተማው ካቢኔም ብዙ ሥራ አለበት፡፡ አሥር ዓመቴ ነው ከሚለው ጀምሮ አንድ ቀን እስከሚለው ባለጉዳይ ድረስ ጉዳዩ ታይቶ ውሳኔ ሊሰጠው የግድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምሥጋና ይግባው በቅርቡ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የጣለው ዝናብ በመሥሪያ  ቤታችን ግቢ የቆሙትን መኪናዎች አጠባቸው፡፡ እንደዚሁም የከተማውን ቦይ ቆሻሻ በሙሉ ጠራርጎ ወስዶት አሳረፈን፡፡ እንግዲህ ዝናብ እየጠበቅን ካልፀዳ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት ሥራውን እርግፍ አድርጎ ትቶታል፡፡ ለዚህም ማስረጃው በየሠፈሩ ሕፃናትና አዋቂዎች በጉንፋን መሰቃየታቸው ነው፡፡ እርግጥ ዝናብ በየቢሮው ያለው ቀበኛም ላይ ዘንቦ ፈውስ ቢሆን ደግ ነበር፡፡

በቅርቡ ‹‹ይኸውልህ ቤታችን አርፈን የተቀመጥነውን ሰዎች ትርፍ ቦታ የያዛችሁ ብለው ጠርተውን መጣን፡፡ ይኸው ከዚያ በኋላ መመላለስ ሆነ ሥራችን፡፡ ላይጨርሱ ለምን እንደሚጀምሩት አይገባኝም፤›› ያሉኝ የካ ክፍለ ከተማ ያገኘኋቸው አዛውንት ናቸው፡፡ ቀጠሉ ‹‹እንደ እንደ ሕፃን ልጅ ያጓጉናል፡፡ አሁን በቅርቡ አንድ ጎረቤቴ ካርታ እንሥራልህ ብትለው ብር ተቀበሉ፡፡ ብሩንም በልተው ጉዳዩን ሳይጨርሱ ጭራሽ ይገላምጡት ጀመር፡፡ እንደ ደላላ ሁለትና ሦስት ስልክ አላቸው፤›› አሉኝ፡፡ ይኼን እኔም አረጋግጣለሁ፡፡ አብዛኛው ባለጉዳይ ቢሮው ውስጥ አስቀምጦ በየደረጃው ሥር ሲንሾካሾክ ይውላል፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶም ያገኘኋቸው ሌላው ‹‹ጎልማሳ እያቸው ገና ከመሬት ሳይነሱ የሰው ገንዘብ ለምደው ሲንቀዥቀዡ ይውላሉ፤›› ነበር ያሉኝ፡፡ ለነገሩ በሚያገኙት ጥቅም ልክ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ስሙን ቀይረው ዱባይ፣ ኳታር፣ ጅዳና ዳርፉር እያሉ መሰየማቸውን ከዚህ በፊት ስለገለጽኩት አሁን መድገም አያሻኝም፡፡ አንዳንዴ ቀደም ብለው የነበሩት ከንቲባ አንዴ ከች ቢሉና ይኼንን ሕዝብ ያስመረረ ሙሰኛ ሁሉ ያንን አይምሬ አርጩሜያቸውን ባቀመሱት እያልኩ እመኛለሁ፡፡ አለቃ የለ፣ ምንዝር የለ አጅሬ ልክ ያገቡት ነበር እስከ ወረዳ ድረስ ወርደው፡፡ ወይ በተደራቢነት በመጡ ያሰኛል፡፡ የሰሞኑ የዕቅድ አፈጻጸም ስብሰባ ደግሞ ተገልጋዩ የሚፈልገው ሌላ ውይይቱ ሌላ፡፡ ምን ይደረግ ቢያንስ ኃላፊዎቹ ቢበረቱ? ስለዚህ ከላይ እስከ ታች የሰሞኑ የኮልፌው ዓይነት ግምገማ ያስፈልጋል፡፡ ከከተማው ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ካቢኔ፣ ወረዳና ሴክተር ቢሮ ድረስ፡፡ አበቃሁ፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

 

 

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles