ጅማ ከተማ ቆጪ በመባል የሚታወቀው አካባቢ በከተማዋ የጫት ንግድ በስፋት ከሚከናወንባቸው ሥፍራዎች አንዱ ነው፡፡ ጫት በብዛት በሚያመርቱና በሚያቀርቡ በሌሎች አካባቢዎች እንደሚታየው ሁሉ በዚህ ሥፍራም እናቶች በተለይም ሕፃናት ጫት ቀንጥሰው ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ኑሮዋቸውን ይደጉማሉ፡፡ ለመቃም የሚውለውን ጫት ከገረባው የሚለዩት ሕፃናት በቅጠል እየተከፈላቸው ይሠራሉ፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታየውም ሕፃናቱ የጥበቃ ቤት ከሚመስለው ቆርቆሮ ቤት ሆነው ጫት ሲያዘጋጁ ነው፡፡ ጣሪያው ላይ ያለው ደግሞ የጫት ነጋዴው ነው፡፡
(በሻሂዳ ሁሴን)
****************
ጥቅስ
ቅጠል ቅርንጫፎቹ
በንፋሳት ንዴት ተሰብረው ወደቁ
በርስት አገራቸው
የበረሃ ወይራ አንተን አጸደቁ!
እናም ለእነርሱ
ከነርሱ ጋር ሆነህ
ዘይት ሆንክላቸው
ከሥራቸውም ጋር አብረህ አበርካቸው፡፡
እንግዲህ ልንገርህ
የበርሃ ወይራ ሆይ
በመፍራት ተቀመጥ እውነቱን ላስረዳህ
አልያ ትወድቃለህ፡፡
ምክንያቱም
በተፈጥሮም ትእዛዝ
መቼም አንተ ሳትሆን ሥርን የምትይዘው
ጥንትም ሥር ነውና አንተን የሚሸከመው፡፡
****************
ናፍቆት
ስኮትላንዳዊው ወዳንድ ምግብ ቤት ጐራ ብሎ ‹‹ቁርስ ይኖራችኋል?›› ሲል ጠየቀ፡፡
አስተናጋጅ፡- ‹‹አዎን አለን፤ ምን ልዘዝልዎ?››
ስኮትላንዳዊው፡- ‹‹እንቁላል ፍርፍር ከብርቱካን ጭማቂ ጋር ይዘጋጅልኝ፡፡ ምግቡን ካዘዝሽ በኋላ ግን ፈጥነሽ ተመለሺ፡፡ አስቸኳይ ሥራ ከሌለሽ እፈልግሻለሁ፡፡››
አስተናጋጅ፡- ‹‹ኧረ የለኝም፣ ጌታዬ፡፡ ምን ፈልገው ነው?››
ስኮትላንዳዊ፡- ‹‹ቤቴ ስለናፈቀኝ ምግቡ እስኪቀርብ እንድትጨቀጭቂኝ ፈልጌ ነው››
- አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)
**************
ሬኮርድ ሲሰብሩ
ስኮትላንዳውያኑ በአካባቢያቸው የሚገኝ ቡና ቤት ገብተው ለእያንዳንዳቸው በደስታ መንፈስ ደብል ዊስኪ አዘዙ፡፡
አስተናጋጁ ምን እንዳስፈነጠዛቸው ለማወቅ ጓጉቶ፣ ‹‹የተደሰታችሁ ትመስላላችሁ›› አላቸው፡፡
‹‹እንዴታ! ልክ ወደዚህ ከምጣታችን በፊት በእንጨት የሚገጣጠም መጫወቻ በመሥራት ሬኮርድ ሰብረን ነበር፡፡ አንድ መቶ ቁርጥራጮችን ለመገጣጠም የፈጀብን ስድስት ወር ብቻ ነው!›› አለ አንደኛው በኩራት፡፡
‹‹ስድስት ወር ረጅም ጊዜ ነው›› በማለት አስተናጋጁ መለሰ፡፡
‹‹አይመስለኝም›› አለ ሰውየው በበኩሉ፤ ‹‹ቁርጥራጮቹ ማሸጊያ ሳጥን ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት የሚል ነው፡፡››
አስተናጋጁ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ለካስ የሚገጣጠመው ጨዋታ የተዘጋጀው ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ላላቸው ሕፃናት ኖሯል፡፡
- አረፈዓይኔ ሐጐስ ‹‹የስኮትላንዳውያን ቀልዶች›› (2005)
******************
እባብ ከሰውየው ተሻለ
በአንድ ወቅት አንድ ድሃ ሰው ወጥመድ የሚሆንለት ጉድጓድ በማዘጋጀት ጉድጓዱን በሣር ሸፍኖ እንስሳትን ያጠምድበት ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ ለድኩላ ባዘጋጀው ወጥመድ ውስጥ አንበሳ፣ ነብር፣ ሰው፣ እባብና ተኩላ አንድ በአንድ ጉድጓዱ ውስጥ ወደቁ፡፡
ያጠመደውም ሰው የያዘውን እንስሳ ለማየት ሲመጣ አምስቱን ወጥመዱ ውስጥ ተይዘው አያቸው፡፡ ሰውን ጨምሮ አምስት የተለያዩ እንስሳትን መያዙ አስገረሞታል፡፡
እናም ሁሉም በአንድነት “ከዚህ ጉድጓድ ውስጥ አውጣንና ውለታህን እንከፍላለን፡፡” አሉት፡፡
ሰውየውም “ከበላችሁኝስ?” ብሎ ሲጠይቃቸው እነርሱም “በፍፁም አንጎዳህም፡፡ ቃል እንገባልሃለን፡፡” አሉት፡፡
ሰውየውም በቅድሚያ አንበሳውን “እኔ በጣም ድሃ ሰው ነኝ፡፡ ከወጥመዱ ብትወጣ ምን ታደርግልኛለህ?” ብሎ ጠየቀው፡፡ አንበሳውም “የፈለከውን የቤት እንስሳት ላመጣልህ እችላለሁ፡፡ ሃምታምም ትሆናለህ፡፡” አለው፡፡
ሰውየውም አንበሳውን ከወጥመዱ አወጣው፡፡
ቀጥሎም ይህንኑ ጥያቄ ነብሩን ጠየቀው፡፡ ነብሩም “ይህንን ወጥመድ ያዘጋጀኸው ጥሩ ስጋ ለመብላት ብለህ አይደለም? ስለዚህ እያንዳንዱን ወፍራም በሬ፣ላም፣በግና ፍየል አመጣልህና ለቤተሰብህ ከበቂ በላይ ምግብ ይኖርሃል፡፡” አለው፡፡
ሰውየው ነብሩንም አወጣው፡፡
“አንተስ፣ አያ እባብ?”
“እኔ ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ባጋጠመህ ጊዜ አድንሃለሁ፡፡” ብሎ እባቡ ቃል ገባ፡፡
ነብሩንም አወጣው፡፡
“አንተስ፣አያ ተኩላ?”
ተኩላውም “እኔ ምንም ልረዳህ አልችልም፡፡ አንተን ልረዳ የምችልበት አቅም የለኝም፡፡ ሆኖም አንድ ምክር ልሰጥህ እችላለሁ፡፡” አለው፡፡
ተኩላውንም አወጣው፡፡
ከዚያም በወጥመዱ የተያዘው ሰውዬ “እኔ ደግሞ እረኛህ ሆኜ ከብቶችህን እጠብቅልሃለሁ፡፡” ብሎ “ከብቶች ስላሉህ ከብቶችህን ብቻ ከመጠበቅ ባሻገር ስላንተ ለሌላ ሰው ሳልነግር ምስጢረኛህ እሆናለሁ፡፡” አለ፡፡
አጥማጁም “እሺ” ብሎ ሁሉንም ከወጥመዱ አወጣቸው፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ከወጡ በኋላ ተኩላው ሰውየውን “የእኔ ምክር እነሆ! ሰውየውን ብቻ ተጠንቀቀው፡፡” ብሎ ወደ ጫካው ሮጦ ሄደ፡፡
ሰውየውም ያጠመደውን እረኛ ይዞ ወደቤቱ ሄደ፡፡ ሌሎቹም ሁሉ የገቡትን ቃል ለመፈፀም ወደየፊናቸው ሄደው ነብሩ ሰውየው ስጋ እንዲበላ በግና ፍየል ይዞለት መጣ፡፡ ከሁለትና ከሶስት ዓመታት በኋላም አንበሳው የበግ፣ የፍየልና የከብቶች መንጋ አምጥቶ የሰውየውን በረት ሞላው፡፡ ሰውየውም ሃብታም ሆነ፡፡
ታዲያ አንድ ቀን ሶስት ሰዎች በሃብታሙ ሰው በረት አጠገብ ሲያልፉ ምርኮኛው እረኛ ሰዎቹ የሚነጋገሩትን ነገር ይሰማ ነበር፡፡ ከሰዎቹም አንዱ ከብቶቹን ሁሉ እየተመለከተ “አሃ! ያ ፈረስ በአንበሳ የተሰረቀብኝን የእኔን ፈረስ የመስላል፡፡” አለ፡፡
ሌላኛውም ሰው “ያቺን ላም ደግሞ ተመልከቱ! ከእኔ ላም ጋር በቀለምም ሆነ በመልክ ትመሳሰላለች፡፡ ምናልባትም አንበሳው የእኔንም ላም ወስዷት ይሆናል፡፡” አለ፡፡
ሶስተኛውም ሰው “ያንን በሬም ተመልከቱ! የእኔን በሬ ይመስላል፡፡” አለ፡፡
እረኛውም እያዳመጠ ነበር፡፡ መንገደኞቹ ሰዎች ከብቶቹ የእነርሱ መሆናቸውን አያውቁም ነበር፡፡ ከብቶቻቸው በአንበሳው የተበሉባቸው መስሏቸው ነበር፡፡
ታዲያ አሽከሩ እረኛ ታሪኩን ሁሉ ለሰዎቹ ከመጀመሪያው ከወጥመዱ ጉዳይ አንስቶ የሆነውን ነገር ሁሉ ነግሯቸው “ንጉሱ ችሎት ላይ ለምን አትከሱትም? እኔም ምስክር እሆናችኋለሁ፡፡” ብሎ መከራቸው፡፡
“እንግዲያውማ ምስክር መሆን ከቻልክ መጥተህ ክሰሰውና እናም ውለታህን ከፍለንህ ሃብታም ትሆናለህ፡፡” አሉት፡፡
በዚህ ዓይነት ሰውየውን በንጉሱ ችሎት ከሰሱት፡፡ በችሎቱም ላይ “ምስክር አለን፡፡” አሉ፡፡
ተከሳሹ ሰው ግን ወደ ችሎቱ ቀርቦ ሁሉም እንስሳት የራሱ እንደሆኑና እርሱም ንፁህ መሆኑን ተናገረ፡፡
ንጉሱም “ከሳሾች ምስክር አለን እያሉ ነው፡፡” አለ፡፡
ሰውየውም “እነርሱ እየዋሹ ነው፡፡ ምንም ማስረጃ የላቸውም፡፡” ብሎ ተከራከረ፡፡
በዚህ ጊዜ አሽከሩ እረኛ በምስክርነት ቀርቦ ሊናገር ሲል ንጉሱ የሃብታሙን ሰው ሃያልነት ስለፈራ ሰውየውን ለመስቀል ምክንያት ሲፈልግ ስለነበረ በሰውየው አናት ላይ ሸምቀቆ ገመድ በማዘጋጀቱ ሰውየው ተስፋው ተሟጦ ነበር፡፡
በዚያች ቅፅበት ከየት መጣ ሳይባል እባቡ መጥቶ ምስክሩ አንድም ቃል ከመናገሩ በፊት ነደፈው፡፡ የተነደፈውም ሰው ራሱን ስቶ ወዲያው ሞተ፡፡
የተከሰሰውም ባለጸጋ ሰው ንጉሱን “ጃንሆይ ሆይ! ይህ እንግዲህ የእግዚአብሔር ፍርድና የታላቅነቱ መገለጫ ነው፡፡ ሃሰተኛ ምስክር ስለሆነ ሞተ፡፡” አለ፡፡
ንጉሱም ሰውየው የተናገረው ነገር እውነት ነው ብሎ በነፃ አሰናበተው፡፡
- በወርቁ ዓለሙ የተተረከ የከፋ ተረት
*****
‹‹በር በሬ››
አንዲቷ ጉብል ዘወትር የፍቅር ጥያቄ ያቀርብላት ለነበረ ኮበሌ፣
‹‹ልጅ ሆኖ አረንጓዴ በእርጅና ቅላት፣
ይህንን የፈታ ይግባ ይጫወት፣››
ስትል ምሥጢር አዘል ጥያቄውን ከፈታ በፍቅር ጨዋታዋ ልታስተናግደው መፍቀዷን ገለጸችለት፡፡
ኮበሌውም የዋዛ አልነበረምና ጥያቄዋን በረቀቀ ሐሳብ የመለሰላት እዚያው በፍጥነት በመግጠም ነበር፡፡
‹‹በመዝጊያ ስምና በገበሬ ሀብት፣
ይኸው ፈታሁልሽ ልግባ ልጫወት››
ብሎ ድንቅ በሆነ ሁኔታ መልስ ሰጥቶ ያፈቀራትን ሴት ማግኘት ችሏል፡፡
እሷ ልጅ ሆኖ አረንጓዴ እና በእርጅና ቅላት በማለት በምሥጢር አዘል የጠየቀችው ‹‹በርበሬ›› ብሎ ከመመለስ ይልቅ በምሥጢር የመዝጊያ ስም (በር) የገበሬ ከብት (በሬ) ነው በማለት አስተሳስሮ አቀረበላት፡፡
**********
ቀራፂ እና ጎብኚ
- – ይቅርታ ይህን ቅርጽ የሠራኸው አንተ ነህ?
- * እኔ ነኝ
- – ሰውየው…
- * ያው ወታደር ናቸው
- – ማለቴ..
- * መነሻ ሐሳቡን ሊጠይቁኝ ነው?
- – የለም! ማዕረጋቸውን ለመለየት…
- * ጄኔራል ናቸው
- – ምነው ታዲያ?!
- * ምነው?
- – ሽብርክ ማለታቸው ትንሽ ፈገግ አላሰኘም
- * ጉዳዩ ሌላ ነው
- – እንዴት?
- * ሥራው ሲጀመር ፈረሰኛ እንዲሆኑ ነበር
- – ታዲያ?!
- * አሠሪ ኮሚቴው ገንዘብ ስለአጠረው ፈረሱ ቀረ
- ‹‹ጠብታ›› (1999)