በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙት ብሔረሰቦች አንዱ በርታ ነው፡፡ በርታዎች ካሏቸው የዕደ ጥበብ ዕውቀቶችና ክህሎቶች ውስጥ የሚጠቀሰው የሙዚቃ መሣሪያዎች አሠራር ነው፡፡ ‹‹ኢኚሊ›› ስለሚባለው የሙዚቃ መሣሪያ ሥራ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በክልሉ ብሔረሰቦች ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ያሰፈረው ሐተታ ያብራራል፡፡
የበርታ ብሔረሰብ ከአእምሮው በፈለቀ ዕውቀት የሚያበጃቸው የትንፋሽና የምት የሙዚቃ መሣሪያዎች አሉት፡፡ የትንፋሽ መሣሪያዎቹ ዋሳ፣ ቦሎና ቢልድኛ ሲሆኑ የምት መሣሪያዎች ደግሞ አኖባ፣ አደሆሎና ደሉቃ ናቸው፡፡ ዋሳ በቁጥር አሥራ ሦስት ሆኖ ይዘጋጃል፡፡ አሥራ አንዱ ዋሳዎች በመጠንና በድምፅ የተለያዩ ሆነው የሚዘጋጁ ሲሆን በመካከል ሁለቱ በእኩል መጠን ተመሳሳይ ድምፅ እንዲኖራቸው ተደርገው ይዘጋጃሉ፡፡
በመሆኑም አሥራ ሦስቱ ዋሳዎች አሥራ ሁለት ተደርገው ይታሰባሉ ማለት ነው፡፡ ዋሳ በቀጭኑ ተጀምሮ ቅሉ ተቆርጦ እየተደረበ የሚያድግና የተደረበውን ቅል ለማያያዝ ጐኑ እየተበሳና በቀርከሀ እየተያያዘ ይዘጋጃል፡፡ በዚህ ሁኔታ ትልቁ ዋሳ እስከ ሁለት ሜትር ድረስ ይደርሳል፡፡ ቦሎ ከቀርከሀ ይዘጋጀል፡፡ ቁጥሩ ከ15 እስከ 25 የሚደርስ ሲሆን እያንዳንዱ ቦሎ በመጠንና በድምፅ እንዲለያይ ተደርጎ ይዘጋጃል፡፡ ለቦሎ የሚሆን ቀርከሀ ወፈር ያለ መሆን አለበት፡፡ ቅጠሉ ከተላጠ በኋላ የቦሎ ማዘጋጀት ሥራው ከቀጭኑ በኩል በመጠን ትንሽ የሆነውን ቦሎ ከማዘጋጀት ይጀምራል፡፡ እየተነፋና ድምፁ እየተሰማ የሚቀጥለውን ቦሎ በመጠን ከፍ በማድረግ ይሠራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ድምጻቸው ተከታታይ የሆኑ ቁጥራቸው እንደሁኔታው ከ15 እስከ 25 የሚደርስ ቦሎዎች ይዘጋጃሉ፡፡ ቢልድኛም ከቀርከሀ የሚዘጋጅ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከፍ፣ በአንድ በኩል ደግሞ ድፍን ሆኖ የሚዘጋጀው ቢልድኛ በድፍኑ በኩል አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው አንድ ቀዳዳ ተበጅቶለት በእጅ አየተቃኘ የሚጫወት ዋሽንት መሳይ የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ ቢልድኛ በቁጥር ሁለት ስድስት ሆኖ ቢዘጋጅም ድምጹ ግን ሦስት ዓይነት ብቻ ነው፡፡ ሁለት ሁለቱ ቢልድኛዎች በተመሳሳይ ድምጽና መጠን የሚዘጋጁ ሲሆኑ ከሌሎቹ ሁለት መንታ ቢልድኛዎች ግን የመጠንና የድምፅ ልዩነት አላቸው፡፡
አኖባ በመጠኑ ከፍ ያለ ከበሮ ሲሆን ለአምልኳዊ ግልጋሎት ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ አኖባ ውስጡ በተቦረቦረ እንጨት ላይ እርጥብ የፍየል ቆዳ በመለበጥ የሚዘጋጅ ነው፡፡ አደሆሎ ባላ የሆነ ጥቁር እንጨት ተዘጋጅቶ በትከሻ በመያዝ በከርከሮ ጥርስ እየተመታ የሚጫወቱት ቁጥሩ ስድስት የሆነ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ አደሆሎ ለማዘጋጀት የሚሆነው የእንጨት ዓይነት በጣም ጠንካራ ስለሆነ መሣሪያው የሚዘጋጀው እንጨቱ እንደተቆረጠ በእርጥቡ ነው፡፡ ሲደርቅ ለአገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ ለመምቻው የከርከሮ ጥርስ ወይም የከብት ቀንድ ተሞርዶ የሚዘጋጅ ሲሆን ቄፄቤለ በመባል ይጠራል፡፡
ደሉቃ የተለያዩ መጠን ድምጽ እንዲኖራቸው ተደርገው የሚዘጋጁ የአራት ከበሮዎች መጠሪያ ነው፡፡ ሦስቱ በተቀራራቢ መጠን የሚዘጋጁ ሲሆን በአንድ ላይ ታስረው በአንድ ሰው የሚመቱ ናቸው፡፡ አራተኛው ደሉቃ በመጠን ከፍ ያለ ሆኖ ለብቻው በሌላ ሰው የሚመታ ነው፡፡ ደሉቃ በተቦረቦረ እንጨት ላይ በሁለት በኩል እርጥብ የፍየል ቆዳ ተለብጦ እንዲደርቅ በማድረግ ይዘጋጃል፡፡ ሌላው የሙዚቃ መሣሪያ አፄፄህ ነው፡፡ አፄፄህ ከቅል የሚዘጋጅ ሲሆን የቅሉ አፍ ተቆርጦ ውስጡ ከተፀዳ በኋላ ጽሄል የሚባል ፍሬ ተከቶበት አፍ በሙጫ ይታሸግና ሴቶች በእጃቸው ይዘው በማነቃነቅ የሚጫወቱት ነው፡፡ ለሙዚቃ መሣሪያ ዝግጅት የሚሆን እንጨትም ሆነ ቀርከሀ የሚቆረጠው በክረምት ወቅት ነው፡፡ የተቆረጠው እንጨትና ቀርከሀ እዚያው ይተውና ዝናብ እንዲመታው ይደረጋል፡፡ ይህ በመደረጉ ትል እንዳይበላው መከላከል እንደሚቻል ይታመናል፡፡ ከዚያ በኋላ የከብት አዛባ ባለበት አካባቢ ለሰባት ቀን ያህል ተቀብሮ ይቆያል፡፡
ይህም እንጨቱ ወይም ቀርከሀው እንዳይሰነጣጠቅ ያደርገዋል፡፡ በስምንተኛው ቀን ወጥቶ እንዲለሰልስ በጉሎ ፍታ ይታሻል፡፡ ማንኛውም ዓይነት የትንፋሽ መሣሪያ ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ አዋቂዎች እንዲያዩትና እንዲሞክሩት ይደረጋለ፡፡ ያልተስተካከለ ነገር ካለ አዘጋጁ ሰው እንዲያስተካክል ይነገረውና ያስተካክላል፡፡
በበርታ ብሔረሰብ ዘንድ የሙዚቃ ቅንብር በራሱ ሥርዓትና ደንብ ያለው ነው፡፡ ለምሳሌ ዋሳና ቦሎ በአንድነት የማይነፋ ሲሆን ዋሳ ሲነፋ በማጀቢያነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የሙዚቃ መሣሪያዎች አደሆሎና አፄፄህ ናቸው፡፡ በመሆኑም ትንሹን ዋሳ ከሚጫወተው ሰው ጀምሮ እስከ ስድስተኛው ሰው ድረስ ዋሳውን እየተጫወቱ በተመሳሳይ ጊዜም አደሆሎውን እየመቱ ሙዚቃውን ያጅባሉ ማለት ነው፡፡