Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለምን አንከባበርም?

ሰላም! ሰላም! ‘ሐበሻ ጥበቡን ባህላዊ ቀሚስና ምሳሌ ላይ ጨረሰው’ ስል ባሻዬ ሰምተውኝ ኖሮ፣ “ወሬስ የት ሄዶ?” ብለው ቀብ አደረጉኝ። እሳቸው ደግሞ ሲመጣባቸው አንዴ ቀጨም ያደረጉትን ነገር በዋዛ አይለቁም። እናም ቀጠል አድርገው (ተቀጣጣይ እሳት እንጂ የማልወደው ነገር ሲቀጣጠል በጉጉት ደሜ ትግ ትግ እንደሚል የታወቀ ነው)፣ “ይመስለናል እንጂ ይኼ ሳይለፉ ማካበት፣ ተቀምጦ መብላት፣ በተቆራጭ ገንዘብ መነዛነዝ የመጣው እኮ ማልደን ተነስተን ላብ ስናፈስ ከዋልን፣ ለወሬ ለምንቀንሰው ሰዓት በውስጠ ታዋቂነት ዕረፍት ስለሚነሳን ይመስለኛል። አይመስልህም? ‘ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው’ ይባላል ባገራችን፤” ብለው ነገሩን ወደኔ መሩት። እንኳን በ‘ይመስለኛል አይመስልህም?’ ዴሞክራት ሆነው ነገሩን ወደኔ መሩት እያልኩ በውስጤ “ልክ ነው” ብዬ ዝም አልኩ። አዎ! ታዲያ እንደኔ በቤተ ሙከራ የማይለካ፣ የማይረጋገጥ፣ የማይመሳከር ነገር እየደመደሙ ነገር ከማስረዘም ማሳጠር ይልመድባችሁ። ሌላ ምን እላለሁ? ዘንድሮ ነገርና ኳስ የሚያስረዝሙት ናቸው ከዋንጫ ፉክክር ሲርቁ ያየናቸው። ይኼ እኔን ብቻ ነኝ የሚታየኝ? አይ እናንተ!

‹መሐረቤን አያችሁ አላየንም ከመጫውታችን በፊት የባሻዬን ጨዋታ ልጨርስላችሁ። ምናሉኝ፣ በአንድ ቀዬ ትዳራቸው የሚያስቀና አካላቸው ቢያረጅም ከሚስታቸው ጋር ያላቸው ፍቅር እያደር የወጣት የሆነ አዛውንት ነበሩ አሉ። መቼም አበባ ካለ ንብ ያንዣብባል። ስኬታችሁና ደስታችሁ እያደር ምቀኛ ሲያፈራ ስታዩ ፅጌሬዳ ጉያ እሾህ ጠፍቶ እንደማያውቅ አስታውሱ። ምነው ስንት መርሳት የሚገባንን ነገር አንረሳም እያልን? በጎሳ እያበርን? የማይገነባ ነገር ከማስታወስ ሜዳ ላይ ባለ ሳር ጤዛ መመሰጥ ለኑሮ የሚበጅ ሚስጥር ያካፍላል ይባላል። እናም አንድ ቀናተኛ የአዛውንቱን ጎጆ ማፍረሻ መላ ሲፈልግ (መቼም ኑሮ ያልተወደደበት መሆን አለበት የቻፓ መላ ትቶ ፍቅር ማፍረሻ መላ ሲፈልግ ጊዜ የሚያጠፋው) ሰነባብቶ ማምለጫውንም አዘጋጅቶ (የቀናተኛም ብሩህ አለው ማለት ነው? ይታያችሁ እንግዲህ) ጠጋ ብሎ፣ “አንቱ! ኧረ ይህቺ ሚስትዎ ትሄዳለች። ምን ሆና ነው?” ይላቸዋል። “አይተሃታል?” ይላሉ በቸልታ። “በዓይኔ በብረቱ” ይመልሳል። ሰውዬው ሚስታቸውን ወዲያው ጠርተው፣ “ሰማሽ ስምሽን? ሂያጅ ነች ይልሻል። ይኼው ወሬኛው ፊት ጠየቅኩሽ፤” ሲሏቸው ሚስታቸውን፣ ወሬኛው ጣልቃ ገብቶ፣ “አንቱ! እንዴት ያሉ ሰው ነዎት ግን? ትሄዳለች ስልዎ በሐሳብ ትነሆልላች ማለቴ እንጂ ትወሰልታለች መቼ ወጣኝ?” ብሎ ሲቆጣ፣ “በል ተወው ወንድሜ። ያለዛሬም ሐሳብ ሲዎሸም አልሰማሁ፤” ብለው አባረሩት። ላልደረሰበት የቃላት ጨዋታ አይመስልም አሁን ይኼ ታሪክ? እንዲያው እኮ!

        ያለ ነገር ስለወሬና ወሬኞች ጎነታትዬ እንዳልጀመርኳችሁ ይገባችኋል። አጉል በአሉባልታ አጥብቀን ያላሰርነው ዘቅዝቀን እየተሸከምን የምንደፋው እህል፣ የምንዘጋው ዕድል እያደር ብሷል። እኔም ክፉኛ እያዘንኩ ነው። ሰሞኑን ስሜ በሚያውቁኝ ሁሉ በሐሰት ሲብጠለጠል፣ ሲነሳና ሲጣል ሰነበተ። ካለእናንተ ለማን ይነገራል ብዬ እኮ ነው? ምን ተባልኩላችሁ መሰላችሁ? አንድ ‘ሲኖትራክ’ እዚህ ጫንጮ ተበላሽቶ በቆመበት በተገመተው ይሸጥልኝ የሚል ደንበኛ አላስቆም አላስቀምጥ አለኝና ወጣ ወጣ አበዛሁ። እንደ ወትሮው ፊቴ የሚመታባቸው ሥፍራዎች ‘አንበርብር የት ደረሰ? በሚሉ ጥያቄዎች ደመቁ። ኋላ አንዱ የወሬ ፈላስፋ፣ “አልሰማችሁም እስካሁን? አንበርብር እኮ የሰብዓዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ በሌለበት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በማላይበት አገር መኖር በቃኝ’ ብሎ ወደ ጎረቤት አገር ተሰደደ፤” ብሎ ነዛው። የእህል ዘር እንደ ወሬ ብንዘራ ይህቺ ድንግል መሬት ለሰባት ትውልድ የሚበቃ እህል አታስወቃንም ነበር ግን? ይገርማል እኮ።

       ወዲያው ትናንሽና ጥቃቅን ወሬኞች (አንዴ ለኳሽ ያግኙ እንጂ አይቻሉም)፣ “እውነት ነው ካንደበቱ ሰምተናል። ‘ከዕለት ወደ ዕለት ቅሬታዬ እየበረታ ሄዷል። ልማት ያለ ዴሞክራሲ በአፍንጫዬ ይውጣ ሲል በጆሬዬ ሰምቻለሁ፣ የሰማሁ መስሎኛል…” እየተባባሉ ጫንጮ ተቀምጬ የፖለቲካ ጥገኝነት ፈቃድ በወሬ አስጠይቀው በወሬ አሰጡኝ። ወዳጅ፣ ዘመድ፣ ጓደኛና ደንበኛ የሰማ ሁሉ ጉድ አለ። አምኖ ያበደረ ክስ መሠረተ። የተበደረ ውስኪ አወረደ። እውነትም ጦር ከፈታው ወሬ . . . ! “አኖርሽ ነበረ በሬዬንም ሸጨ፣ አበላሽ ነበረ ወይፈኔን አርጄ፣ በምኔ ልቻልሽ ባንገቴ ተይዤ፤” አልኩ የተባልኩትን ስሰማ። ማንጠግቦሽ “እንኳን አንተ ዝም ያለው ፈጣሪም፣ ዝም አለ ተብሎ ይወነጀላል። በአሉባልታ ይወገራል። ያለ ነው …” ብላ ልታፅናናኝ ሞከረች። ላያስችል አይሰጥ ሆነና ደግሞ ስመለስ ቀንቶኝ ኮሚሽኔን ተቀብያለሁ። እንዳልኳችሁ አስችሎኝ ጭራሽ የሥራ ሞራሌ ተነሳስቶ አንዳንድ ቦታ ልደውል ትኩረቴን ሰበሰብኩ። ማስታወሻዬን ገላለጥኩ።

በእንጥልጥል የያዝኩትን ድለላ ካቆምኩበት ልቀጥል ስልኬን አንስቼ ልክ ልደውል ስል ይደወላል። “ሃሎ” ስል ወደኔ እምነት የጎደለው ድምፅ “አንበርብር!” ብሎ ይጮሃል። “አዎ ነኝ” ከማለቴ፣ “ምንድነው የምሰማው?” ብሎ አንድ የሚያውቀኝ ያናዝዘኛል። አስተባብዬና አስረድቼ ወሬኛውን በትብብር የእርግማን ናዳ አሸክሜ ስዘጋ ሌላ ስልክ መጣ። “ሃሎ” እያልኩ ሳለሁ፣ አገላብጬ እመልሳለሁ ብዬ የተበደርኩት ሰው እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ይጮህብኛል። “አሁን ከዚህ ወዲያ ለእኛ ገንዘብ እንጂ ፖለቲካ ምናችን ነው? ሰው መቼስ ጫፍ ሳይዝ አይቀጥልም፤” ሲል መአት ወረደብኝ። እሱንም እንዲሁ አባብዬ ወሬውን ሳስተባብል ሰዓቴ ነጎደ። በልቤ ግልጽነትና ተጠያቂነት ይሰፍን  ቢባል መንግሥታት በጀታቸውን በሚቀጥሯቸው ቃል አቀባዩችና የማስተባበያ መድረኮች ሊጨርሱት ይችላሉ ማለት ነው? እላለሁ። በትዝብት በመገረም እተክዛለሁ። ከሁሉ ከሁሉ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቀ መባሌ ትዝ ሲለኝ የደመኛዬን ማንነት ዕወቅ፣ ማንነት ድረስበት እያለኝ እረበሻለሁ። እንዲያረጋጋኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ስደውል ደግሞ እሱ ያው የምታውቁት ነው ቀለል አድርጎ “እንኳን የኢኮኖሚ ጥገኝነት ጠየቀ አላሉህ። እንዲያ ቢሉህ ኖሮ ሠርተህ እየኖርክ የምትበላው ሳታጣ ምን ልትሆን ነበር? ይልቅ የስም ኪራይ ጀምር። ሰው በእጅ አዙር በሰው መታወቂያ የልቡን መዘክዘክ የሚፈልግበት ጊዜ ሆኗል፤” ይለኛል። እስኪ አሁን ካልጠፋ ‘ቢዝነስ’ ስሜን አጥፉ ብዬ ለብሶት መተንፈሻ ላከራይ? ይህ ነበር የቀረኝ!

እጄ ላይ ምን የመሰለ የሚሸጥ ቪላ ስለነበረ የማስተባበል ሥራዬንና አካባቢዬን የማራጋጋት ተግባሬን ለጊዜው አቆይቼ ለመጨረሻ ውሳኔ ቤቱን አሳየን ወዳሉኝ ደንበኞቼ ከነፍኩ። ቤቱን ዓይተው ጥቂት እርስ በእርሳቸው ከተነጋገሩ በኋላ (በዕድሜ ጠና ጠና ያሉ ወይዘሮዎች ናቸው) በትንሹ ተደራድረው እንደሚገዙት አበሰሩን። ገዥውም እኔም ፈንድቀን፣ “እንኳን ለውሳኔ አበቃችሁ” ብለን ሳናበቃ በማናውቀው ምክንያት፣ “ምን መሆንሽ ነው? ምን መሆንሽ ነው?” እየተባባሉ ፊታችን ዱላ ቀረሽ ንትርክ ጀመሩ። የማላየው ነገር የለም መቼም! ቆየት ብዬ እንደተረዳሁት በአንድ ዓመት የሚበላለጡ እህትማማቾች ኖረዋል። የንትርኩ መንስዔ ታዲያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ‘እኔ ነኝ መነጋገር ያለብኝ አንቺ አርፈሽ አዳምጪ! የለም አንቺ ምን ስለሆንሽ ነው እኔ ነኝ መናገር ያለብኝ’ በሚል ግብግብ የተፀነሰ መሆኑ ነው። ለታዛቢ ቀላል ይምሰል እንጂ ለባለቤቶቹ ግን የልጅነት ትውስታን እያስመዘዘ ስንት መስማት የማይገባንን ገመና ያዘካዘከ ጭቅጭቅ ነበር። እኔማ ትክ ብዬ ሳያቸው ወይዛዝርቱ የሕፃንነቱ ዓለም ውስጥ ያሉ መሰሉኝ፡፡ ሲያሳዝኑ? ሁለቱንም አረጋግተን ጥቂት በሊቀመንበርነት ቦታው ማን ይቀመጥ የሚለውን እንዲነጋገሩ ፈቀቅ አልንላቸው። “ትልቅ ሰው ሲበላሽ ቅራሪ የለውም’ የሚባለው ለካ እውነት ነው፤” ስል፣ የቤቱ ባለቤት እንደ ቀልድ፣ “ድሮስ የዚህች አገር የዘመናት ጥያቄ ይባስ ሲተበተብና ሲከር የኖረው በአዋቂው አይደል እንዴ?” ብሎ ማኖ አስነካኝ። ቀይ ወይ ቢጫ በማላይበት ማኖ ብነካ ‘ኮሚሽኔን’ ሳልቀበል ንቅንቅ እላለሁ እንዴ? ነገር እንሸሽ ብለን የምንጎትተው ነገር ብሷል ስላችሁ! እንዲያው ምን ይሆን አንተ ቅደም እኔ ልከተል መባባልን የነሳን? በታላቅና በታናሽ ባሰ እኮ ጎበዝ! ድሮማ በደጉ ጊዜ፣ ‹‹እስከ ዛሬ ድረስ የሥጋን ጣዕም ሳላውቅ፣ እንዴት ይጣፍጣል ታናሽና ታላቅ፤›› ተብሎ ጉድ መፍላቱን አረሳውም፡፡

በሉ እንሰነባበት። ‘እንግዲህ ልጓዘው ቅሌን ወርውሩለኝ፣ መንገድ ነው ጥማቴ ውኃ ውኃ የሚለኝ” ይላሉ ባሻዬ። የዕድሜ ጫናም ነው መሰል የሚታይና የሚሰማው ተጨምሮ፣ የወደፊታቸውን አስቀድመው ሁሉንም በጣዕም የለሽነት ሲፈርጁ ይህቺን ቅኔ ይደጋግሟታል። እኔ በበኩሌ ከባሻዬ አጋር አልስማማም። እንደማልስማማ በግልጽ ስነግራቸው ያኮርፉኝና፣ “ወተት ወተት ይላል ብዙ ዕድሜ ያልኖረ፣ መለየትን ያህል ሬት ጣዕም ሳለ” ብለው ያስገቡልኛል። “በተስፋ መቁረጥ ተኮርኩመን ሁሉን ንቀን ሁሉን ተችተን እንዴት ይሆናል?” ስላቸው ግን መለስ ይላሉ። “‘እኔ ከሞትኩ ሰርዶ መቃብሬ ላይ ብቻ ትብቀል’ አያያዝ፣ የነኮረውን በማነኮር፣ እጅ እጅ ያለውን በማባባስ፣ ለወገን እጁ እንደማይፈታ የአገር ተቆርቋሪ ነኝ ባይ መሆን አይገባም” ስላቸው በጥሞና አዳምጠውኝ ራሳቸውን ወዝውዘው ዝም ይላሉ። ከባሻዬ ጋር በዚህ ስስማማ ከልጃቸው ጋር ተያይዤ ወደ ግሮሰሪያችን አመራለሁ። “ካልጨለጥን እንቅልፍ የማይጨልጠን እኮ እያደር በዛን፤” እያለኝ የባሻዬ ልጅ ከአፍ እስከገደፏ የሞላችዋን ግሮሰሪ በትዝብት ቃኝተን ወደ ውስጥ እንዘልቃለን።

ስንገባ ደግሞ ሰው በያዘው ብርጭቆና በሚጠጣው መጠጥ በመደብ ተከፋፍሎ፣ በጥርጣሬ እየተገላመጠና በጥላቻ ድባብ ታጥሮ ሊዝናና ፍዳውን ያያል። ይኼን ጊዜ የባሻዬ ልጅ ያላሰብኩት ጥያቄ ጠየቀኝ፡፡ “አንበርብር አገር ማለት ምን ማለት ነው?” ተደናብሬ ጥያቄው እንዲደገምልኝ ስጠይቅ፣ “አገር ማለት ሕንፃ፣ መንገድ፣ ተራራ፣ ሜዳ፣ ሸለቆ ነው ወይስ ሰው ነው አገር ማለት?” አለኝ። “ሰው!” አልኩት። “ታዲያ ይኼ ሁሉ በረባ ባረባው እርስ በእርሱ በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት፣ በውበትና በቀለም ዓይነት እየተፋጨ፣ ‘እኔን እዩኝ እናንተ አትረቡም! እኔን አዳምጡ እናንተ አታውቁም’ መባባልን ምን አመጣው? ሰውን እንደ ሰውነቱ ማየት ቢያቅተን ወገን እንደ ወገን፣ ዜጋ ስለዜግነቱ ብቻ ለምን አይከበርም? አይከባበርም?” ብሎ የባሰውን አመጣው። መልሱን ለመመለስ በላይ በላዩ ስጎነጭ ጥያቄው ጠፍቶኝ አረፈው። ምን ነበር ጥያቄው? አዎ! ለምን አንከባበርም? መልካም ሰንበት!   

 

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት