Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበገፀ ባሕሪያት ጥላ ሥር

በገፀ ባሕሪያት ጥላ ሥር

ቀን:

 በአንድ ወቅት ቺካጐ (አሜሪካ) ውስጥ የዊያም ሼክስፒር ድርሰት የሆነው ‹‹ኦቴሎ›› መድረክ ላይ እየቀረበ ነበር፡፡ ኢያጐ ኦቴሎና ዴዝዴሞናን ለመነጣጠል የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም፡፡ በሐሰት ዴዝዴሞና በኦቴሎ ላይ እንደማገጠች ለኦቴሎ ነገረ፤ ኦቴሎም ዴዝዴሞናን ገድሎ ራሱን አጠፋ፡፡ በኢያጐ ምግባር እጅግ የተበሳጨ አንድ ተመልካች ከኪሱ ሽጉጥ መዝዞ ወደ መድረኩ አነጣጥሮ ተኮሰ፡፡ የኢያጐን ገፀ ባህሪ በተመስጦ እየተወነ የነበረው ባለሙያ ድንገት በተተኮሰበት ጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል፡፡ ‹‹ኦቴሎ›› በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በየአገሮቹ ሲቀርብ በርካታ ተመልካቾች ለኢያጐ ያላቸውን ጥላቻ በልዩ ልዩ መንገድ ገልጸዋል፡፡

ተውኔቱ በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን ተተርጉሞ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት መድረክ ላይ ሲታይ፣ ኢያጐን ሆኖ በሚጫወተው ተዋናይ ላይ ጫማ ተወርውሮበታል፤ የስድብ ውርጅብኙም ቀላል አልነበረም፡፡ በተውኔቱ የሚካኤል ቃሲዩን ገፀ ባህሪ ተላብሶ የሠራው ፍቃዱ ተክለ ማርያም ወቅቱን ‹‹ሰው ኢያጐን ከመጥላቱ የተነሳ ተውኔት መሆኑን ረስቶ አንተ ክፉ፣ አንተ ቀጣፊ እያለ ይሳደብ ነበር፤ እስከመደባደብ የደረሱም ነበሩ፤›› ሲል ያስታውሰዋል፡፡

ፍቃዱ መልካም ባህሪ ያለውን ቃሲዩን ሆኖ ስለተጫወተ ተወዳጅ ነበር፡፡ በቴአትር፣ በቴሌቪዥን ድራማ ወይም በፊልም ላይ በብዛት የሚወክላቸው ገፀ ባህሪያት እንደ ቃስዩ በጐ ሰዎች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ከጥሩ ገፀ ባህሪ ውጪ ቢሠራም፣ መልካም ሰዎችን ሆኖ መተወን ይመርጣል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እኩይ ገፀ ባህሪ ሆኖ ከተወነባቸው አንዱ ‹‹ፍቅር ሲፈርድ›› ፊልም በሕግ ሰዎች እህቱ ተደፍራ ፍትሕ ለማግኘት ስለሚኳትን ሰው ይተርካል፡፡ በወንጀሉ ካሉ ፖሊሶች አንዱ ሆኖ የሚተውነው ፍቃዱ ነው፡፡

ፖሊሱ ክፉ ስለሆነ ተመልካቾች ፍቃዱም እንደ ገፀ ባህሪው ሆኗል ብለው አዝነው እንደነበር ይናገራል፡፡ ያኔ ወደ አንድ ዘመዱ ቤት ተጋብዞ ይሄዳል፡፡ ታስተናግድ የነበረች የቤት ሠራተኛ ማንም ሰው እንዳያያት ተጠንቅቃ ወደ ፍቃዱ ተጠግታ፣ ‹‹ለምን እንደዚህ ያለ ሰው ትሆናለህ? እኛ የምንወደው የድሮውን ዓይነት ሰው ነው፤›› ብላው ወደ ሥራዋ ተመልሳለች፡፡

ፍቃዱ ያን ቅፅበት በደንብ ያስታውሰዋል፡፡ ከዛ የባሱ ምላሾች ሊፈጠሩ ስለሚችሉም ክፉ ሰው ሆኖ አይተውንም፡፡ ተመልካች ስሜታዊ ሆኖ ተዋናይን ከሚላበሰው ገፀ ባህሪ ጋር አስተሳስሮ የሚያይባቸው አጋጣሚዎች ሰፊ በመሆናቸው የመልካም ሰው ገፀ ባህሪ ብቻ ወክሎ ይሠራል፡፡ ከሙያ አንፃር የተለያየ ገፀ ባህሪ መላበስ የተዋንያን ብቃት የሚፈተሽበትና የሚደገፍ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ‹‹ሰው የሚጠላብኝን ክፉ ገፀ ባህሪ ተላብሼ መሥራት አልሻም፤›› ይላል፡፡

ተዋንያን በሚላበሱት ገፀ ባህሪ አመል ተፈርጀው ከማኅበረሰቡ አሉታዊ ምላሽ ሲያገኙ ቢስተዋልም አንዳንዴ በትወናው ጥበብ የበለጠ የሚደነቁ እንዳሉ ጠቅሷል፡፡ እንደ ምሳሌ የወሰደው ‹‹ሰው ለሰው›› ድራማን ነው፡፡ የአስናቀን ገፀ ባህሪ የሚጫወተው አበበ ባልቻ እኩይ ባህሪ ቢላበስም ተመልካች እየተበሳጨበትም ቢሆን ሊመለከተው ይፈልግ ነበር ይላል፡፡

ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ጥቂት እንደሆኑና ተዋንያንን ከገፀ ባህሪ ነጣጥሎ ማየት አዳጋች የሚሆንባቸው እንዳሉ በአጽንኦት ይናገራል፡፡ ብዙዎች ይህን ሐሳብ የሚጋሩ ሲሆን፣ የሚጫወቱት ገፀ ባህሪ በመደበኛ ሕይወታቸው ላይ ተፅዕኖ ያሳደረባቸው ተዋንያን አያሌ ናቸው፡፡

እኩይ ሆነው ከተወኑ በኋላ ከስድብ እስከ አካላዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሙያተኞችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በገሀዱ ዓለምም እንደ ገፀ ባህሪው ጨካኝ፣ መሰሪ እንደሆኑ በማሰብ ከተዋንያኑ የሚሸሹ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንድ ገፀ ባህሪያት በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ከሚያሳድሩት ተፅዕኖ ለመላቀቅ ጊዜ እንደወሰደባቸው የሚናገሩ ተዋንያን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሕፃናት የሚፈሯቸው አዋቂዎችም የሚዝቱባቸው ባለሙያዎች በዚህ ይካተታሉ፡፡

በተቃራኒው አስቂኝ ገፀ ባህሪ ተላብሰው የተወኑ ቅጥያ ስም ይሰጣቸዋል፤ በእውንም ዘወትር ፌዘኛ እንደሆኑ በመገመት ብዙዎች ሊቃለዷቸው ይሞክራሉ፡፡ መሰል አጋጣሚ አዝናኝ የሚሆንበት ጊዜ ቢኖርም፣ መስመሩን ስቶ ተዋንያኑን ሲረብሽ ይስተዋላል፡፡ ከሙያ አንፃር አንድን ገፀ ባህሪ በጥሩ ሁኔታ የተወጡ ተዋንያን ሁልጊዜ ያንን ባህሪ እንዲወክሉ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡ ይህ ፈጠራውን የሚያቀጭጭና የተዋንያን ብቃት እንዳይፈተሽ የሚያግድ በመሆኑ በዘርፉ ባለሙያዎች ይተቻል፡፡

የተጫወቱት ገፀ ባህሪ አሉታዊም ይሁን አዎንታዊ ተፅዕኖ ሲያሳድር፣ ገፀ ባህሪውን ተዓማኒ አድርገው እንደተላበሱት እንደሚያሳይ የገለጹልን ተዋንያን አሉ፡፡ በሌላ በኩል አንድ ገፀ ባህሪ በማኅበራዊ ሕይወታቸው የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ባለመፈለግ ገፀ ባህሪ መርጠው እንደሚጫወቱ የነገሩን ይጠቀሳሉ፡፡

ሱራፌል ተካ በቴአትሮችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሚጫወተው ገፀ ባህሪያት አንዱ ልዩ አክብሮት አሰጥቶታል፡፡ ዘወትር ረቡዕ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የሚታየው ‹‹የቴዎድሮስ ራዕይ›› ላይ አፄ ቴዎድሮስን ወክሎ ይጫወታል፡፡ መንገድ ላይ ሲያገኙት ጉልበቱን ለመሳም የሚንደረደሩ ትልልቅ ሰዎችና ንግሥናውን ፈርተው በሙሉ ዓይናቸው ለማየት የማይደፍሩ ተመልካቾች ገጥመውታል፡፡ ከገጠመኞቹ የአንዲት አዛውንት የልጅ ልጆች ያቀረቡለት ጥያቄ አይዘነጋውም፡፡

አዛውንቷ መነኩሴ ሲሆኑ፣ ጐንደርን ለቀው አዲስ አበባ ከከተሙ 58 ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ አዛውንቷ ታመው አልጋ ከያዙም ሰነባብተዋል፡፡ ለአፄ ቴዎድሮስ የተለየ ፍቅርና አክብሮት ያላቸው እኚህ አዛውንት፣ ተውኔቱን ቴአትር ቤት ሄደው መመልከት አልቻሉም፡፡ እንደሚሳካ ባይገምቱም ለልጅ ልጆቻቸው ጉዳዩን ያጫውቷቸዋል፡፡ ወጣቶቹ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ሱራፌልን ያገኙትና ስለአያታቸው ይነግሩታል፡፡ እሱም ስሜቱ ስለተነካ ቤታቸው ለመሄድ ይስማማል፡፡

ሙሉ አልባሳቱን ለብሶ አዛውንቷ ፊት ለፊት ሲቆም ፊታቸው ላይ ያነበበውን ሐሴት ለማመን እንዳዳገተው ያወሳል፡፡ አቅመ ደካማዋ አዛውንት እንባቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር፡፡ ከትውልድ ቀዬአቸው ጐንደር ከወጡ በኋላ የተሰማቸው ባዶነት የተሞላ ያህል እንደተሰማቸው አጫውተውት ነበር፡፡ በሰው ሕይወት በዋጋ የማይተመን በጐ ስሜት መፍጠር አንድ ገፀ ባህሪ መወከል ካስገኙለት አዎንታዊ ምላሾች መካከል ያነሳዋል፡፡

በሌላ በኩል አፄ ቴዎድሮስን ሆኖ ከሠራ በኋላ ሌላ ገፀ ባህሪ ሲወስድ የሚበሳጩበት ሰዎች አሉ፡፡ ‹‹እንዴት አፄ ቴዎድሮስን ከሚያህል ንግሥና ወርደህ ትርኪ ምርኪ ሥራ ትሠራለህ?›› ያሉ ተመልካቾችን ያስታውሳል፡፡ በተለይ በ‹‹ቴዎድሮስ ራዕይ›› ማግሥት የሚቀርበው ‹‹ሦስተኛው ችሎት›› ቴአትር ላይ የአንድ ባለፀጋ ዘበኛ ሆኖ ሲሠራ ከፍተኛ ነቀፌታ ይገጥመዋል፡፡ እሱ ማንኛውንም ዓይነት ገፀ ባህሪ መጫወት ተዋናይን ሙሉ ያደርገዋል ብሎ ስለሚያምን ሁሉንም ፀባይ የመወከል ፍላጐት አለው፡፡

በ‹‹ሰው ለሰው›› ድራማ ላይ የአስናቀ ተባባሪ የሆነና ኩራባቸው የተባለ ገፀ ባህሪ በሚጫወትበት ወቅት የሚሰድቡት፣ የሚሸሹት ለመደብደብ የሚጋበዙም ሰዎች ነበሩ፡፡ ድራማው አጋማሽ ላይ ሸዊት ከበደን ያግታታል፡፡ ሲያግታት የሚያሳየው ክፍል የሚጠናቀቀው ምን ሊያደርጋት እንዳቀደ ባልለየ መልኩ ነበር፡፡ ቀጣዩ ክፍል በቴሌቪዥን እስከሚተላለፍ በነበሩ ቀናት ‹‹አንድ ነገር ብታደርጋት ወዮልህ›› የሚል ማስፈራሪያ ይደርስው ነበር፡፡

ሱራፌል ከማኅበረሰቡ ጋር ባለው ግንኙነት አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ገፀ ባህሪያትን ከመጫወት ወደኋላ እንደማይል ይናገራል፡፡ ከፍተኛ ጫና ቢያሳድሩም ጥላቻውና ዛቻውን ፈርቶ ከመሥራት መቆጠብ ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ ኅብረተሰቡ ላይ የሚስተዋለውን በጐም ይሁን መጥፎ ምላሽ ‹‹የሥራዬን ውጤት የምመዝንበት መለኪያ፤›› ሲል ይገልጸዋል፡፡

‹‹ሳራ››፣ ‹‹ውሳኔ›› እና ‹‹አስከሬኑ›› ፊልሞች ላይ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውና ጭካኔ የተሞሉ ገፀ ባህሪያት ተላብሶ የተጫወተው ተዋናይ አድማሱ ከበደ ነው፡፡ ‹‹ሣራ›› ላይ አንዲት ሕፃንን በመድፈር ተደጋጋሚ ወሲባዊ ጥቃት የሚያደርስ ግለሰብ ሆኖ ይተውናል፡፡ ‹‹ሣራ››ን ለማሳየት ወደ ሐዋሳ በሄዱበት ጊዜ የገጠመውን  አካፍሎናል፡፡

በወቅቱ የፊልሙ ፖስተር መለጠፍ ከነበረበት ቦታ በአንዱ ስላልተለጠፈ ከሚመለከታት ግለሰብ ጋር ውዝግብ ይፈጠራል፡፡ ሴቲቷ አድማሱን ለረጅም ሰዓት እያመነጫጨቀች ታናግረው ነበር፡፡ ፊልሙ በከተማው ከታየ በኋላ፣ ‹‹እንደዛ የተናገርኩት ይህን ዓይነቱን ጨካኝ ሰውዬ ነበር፤›› ብላ እንደፈራችው ያስታውሳል፡፡

እኩይ ገፀ ባህሪ ከተጫወተበት የብዙዎችን ልብ በመንካት ታዋቂ የነበረው ‹‹ውሳኔ›› ፊልምን አድማሱ ያነሳል፡፡ ፊልሙ ይታይበት ከነበሩ ሲኒማ ቤቶች አምባሳደርን አቅራቢያ ሲገኝ፣ ፊልሙን አይተው የሚወጡ ሰዎች በትንሹ እንባቸውን የጠራረጉበትን ሶፍት ላዩ ላይ ከመወርወር አንስቶ ‹‹አንተን መግደል ነበር›› የሚሉ ዛቻዎች ደርሰውበታል፡፡

በተከታታይ የተጫወታቸው ገፀ ባህሪያት ሴቶችን የሚያጠቁ በመሆኑ ያንን ገፀ ባህሪ ብቻ እንዲተውን ይገደድ እንደነበር ይናገራል፡፡ አድማሱን እንደ አረመኔ ሰው ቆጥረው ይሸሹ የነበሩ ሰዎች ረገብ ያሉት ‹‹የወንዶች ጉዳይ›› ላይ ከተወነ በኋላ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በሚጫወተው ገፀ ባህሪ ሳቢያ ነፃነት ያጣባቸውና ያልሆነውን ዓይነት ግለሰብ ተደርጐ የተቆጠረባቸው ቅጽበቶች ምቾት ነስተውታል፡፡ ቢሆንም ከሙያው ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው ብሎ ይቀበለዋል፡፡

ተዋንያን በገፀ ባህሪያት ሳቢያ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ከሚገጥሟቸው ነገሮች በተጓዳኝ በሙያው ያለውን ተፅዕኖ የምትገልጸው ተዋናይት ሰላም ተስፋዬ ናት፡፡ ከዓመታት ወዲህ በበርካታ ፊልሞች ላይ የተወነችው ሰላም፣ በቅርብ ከሠራቻቸው ‹‹በጭስ ተደብቄ›› ሌሎችም ፊልሞች ይጠቀሳሉ፡፡ በብዛት አፍቃሪና ጭምት ሆና ትተውናለች፡፡ በዚህ ምክንያት የፊልም ባለሙያዎች ሁልጊዜ መሰል ገፀ ባህሪ ሊሰጧት ይፈልጋሉ፡፡ አንዳንዴ ገፀ ባህሪያት ሲሳሉ አንድ ተዋናይ ታስቦ እንደሚሆንና ለፈጠራ በማይጋብዝ መልኩ ተዋንያን በአንድ ገፀ ባህሪ ብቻ እንዲወሰኑ ይደረጋል ትላለች፡፡

ሰላም እንደምትለው፣ አንዳንዴ ‹‹ከዚህ በፊት የሠራሽው ፊልም ላይ ያሳየሽውን ትወና ድገሚልን፤›› የሚሉ አዘጋጆችና ፕሮዲውሰሮች አሉ፡፡ ሌላው በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚሰጣት ቦታ ነው፡፡ ፊልም ላይ ሀብታም ሆና ስለተወነች ብዙ ገንዘብ እንዳላት የሚገምቱና ዝምተኛ ሆና ስለተወነች በጽሞና ታልፋለች በሚል መንገድ ላይ ክፉ የሚናገሯት አሉ፡፡ አግባብ ባልሆነ መንገድ ሲናገሯት ለማረም ከሞከረች ‹‹አንቺ እንደዚህ ዓይነት ሰው ነሽ እንዴ? ፊልም ላይ ጥሩ ሰው አልነበርሽ?›› ይላሉ፡፡ በተለይ ሴቶች የሚሰጣቸው ገፀ ባህሪና በእውን የሚሣሉበት መንገድም ተመሳሳይ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ በቅርብ የሠራችው ‹‹የፍቅሬ ፍቅረኛ›› ከተለመደችበት የጥሩ ሰው ገፀ ባህሪ ወጥታ የተወነችበት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ሥራዎች የተለየ መሥራቷ ለሙያዋ ቢጠቅምም ተመልካች በቀላሉ ሊቀበለው እንደማይችል ታምናለች፡፡    

በጉዳዩ ያነጋገርነው ተዋናይ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ገፀ ባህሪያት በተዋንያን የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በመላው ዓለም እንዳለ ጠቅሶ፣ አንድ ገፀ ባህሪ የሚላበስን ባለሙያ ማንነት ከገፀ ባህሪው ነጥሎ መመልከት ከተቻለ እንደ ጥበብ ማድነቅ ይቻላል ይላል፡፡ በተለይ በተከታታይ ድራማዎች ላይ ሰው የመግደል፣ የማሰቃየት፣ የማሴርና ሌሎችም መጥፎ የተባሉ ገፀ ባህሪያትን የሚጫወቱ ተዋንያን በተከታታይ በቴሌቪዥን ስለሚቀርቡ ተመልካች ስሜታዊ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ ተፅዕኖ ቢያሳድርም የትወና ጥበቡ የሚበረታታ ነው ሲል ያስረዳል፡፡

ተዋንያን በሚጫወቱት ገፀ ባህሪ ዓይን መቃኘታቸው ለማስቀረት እንደሚከብድ ይገልጻል፡፡ ‹‹ውበትን ፍለጋ›› ላይ ይገረሙ የተባለ ገጣሚ ገፀ ባህሪ የተጫወተው ቴዎድሮስ፣ የግል ባህሪው ልክ እንደ ገፀ ባህሪው እንደሆነ እንደሚታሰብ ይናገራል፡፡ ጠጪ፣ አጫሽና አስቸጋሪ ባህሪ ያለው ሰው ተደርጐ ቢወሰድም በእውን ተቃራኒውን ሰው እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በተውኔቱ ላይ ‹‹አጥሚት አልጠጣም›› ሲል ስለሚደመጥ ለተወሰነ ጊዜ መቀለጃም ሆኖ ነበር፡፡ በተቃራኒው ‹‹ሥራ አስኪያጁ›› በሚል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ሚስቱን የሚደበድብ ሰው ወክሎ ሲጫወት ተመልካች የገፀ ባህሪውን ፀባይ ባይወደውም እሱ ብዙም አለመጠላቱ አስገርሞት ነበር፡፡

ገፀ ባህሪያት በተዋንያን የሚያሳድሩት ተፅዕኖ በክፉ ባህሪ ቢያመዝኑም መልካም የሚባሉትም የሚያስከትሉት ውጤት አለ፡፡ ተዋንያን የትኛውንም ዓይነት ገፀ ባህሪ ሲላበሱ የተመልካችን ስሜታዊነት ማስቀረት የሚቻል አይመስልም፡፡ ያነጋገርናቸው ተዋንያን ገፀ ባህሪያት በማንኛውም መንገድ ተፅዕኖ ቢያሳድሩባቸውም ከሙያ አንፃር ምን ያህል አሳማኝ አድርገው እንደተወኑ ማሳያ እንደሚሆኑ ያምናሉ፡፡  

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...