Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እናንተየ ዘመኑ እንዴት ነው የሚበረው! እንደቀልድ እንደዋዛ ሁለት አሠርታትን ፈጽመን ወደ ሦስተኛው ለማምራት እኮ ከመንፈቅ ያነሰ ቀረን ጃል፡፡ ‹‹ነፃ ፕሬስ፣ ነፃ ሐሳብ፣ ነፃ መንፈስ›› በሚል መርሕ ማዕደ ፕሬሱን የተቀላቀለው ሪፖርተር ለእኛ ታዳሚያኑ እነሆ ‹‹ሰው በዜና ውኃ በደመና›› ብሎ ሲገናኘንና እስታሁን ሲዘልቅ ታማኝነቱን አላጎደለብንም፡፡ ለብር ኢዮቤልዩውም ያድርሰውና፡፡ መሰንበቻውን ግን ወሬው እያደር የሕትመት ብርሃኑ አልደርስለት እያለ መቸገሩ ምነው ሲያሰኘኝ ሰነበተ፡፡ እንደሰማነው ወሬ ማተሚያ ቤቱ አንዴ ፈተና አትማለሁ፣ ሌላ ጊዜ ማሽን ተበላሽቶብኛል፣ ሁነኛ ባለሙያም አጣሁ እያለ ጋዜጦቹን በዕለታቸው ሳያወጣቸው እያሰነበታቸው መጣ፡፡ የእሑዱን ሮብ የሮቡን ዓርብ ማየት እየተለመደ መጣ፡፡ ወሬውም ቋንጣ እየሆነብን መጣ ምነው ባባጃሌ! ለወትሮ ለዓመታት የምናውቀው ሪፖርተር በዓል በመጣ ቁጥር በተለይ ትንሣኤ (ፋሲካ) ሲመጣ በዋዜማው ቅዳሜ ያሠራጭልን ነበር፡፡ የዛሬውን አያድርገውና፡፡ ለዘንድሮው ፋሲካ ሚያዝያ 4 እንጠብቀው የነበረው እትም አይደለም በዋዜማው በማግስቱም፣ በሣልስቱም፣ በራብዑም በኃምሱም አልተከሠተም፡፡ ድምፁም አልተሰማም፡፡ ዓርብ ላይ በስድስተኛው ቀን ከእጃችን ገባ፡፡ የወሬ ቋንጣ እንዴት ነው ነገሩ፡፡ የደም ሥር የሆኑት ዜና እና መረጃ ከዕለታዊና ሰሙናዊ ጉዳዮች ቃርመው በአግባቡ በወቅቱ ካልደረሱልን እንዴት እንኖረዋለን፡፡ ሰው’ኮ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ልዩ ዓመት የሚያሰኘው አገራዊው ምርጫ የሚካሄድበት መሆኑ ነው፡፡ ስለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ወቅታዊ መረጃ ከሁሉም አቅጣጫ የሚመግቡንን የግል ፕሬሶች (የመንግሥቱም እንዳለ ሆኖ) ሕትመቶቻቸው በጊዜ ካልወጣ እንዴት እንኳኳናለን፡፡ ‹‹ምርጫው ፍትሐዊ›› እንዲሆን የሚለው አዝማች ኃይለ ቃል ገቢራዊነቱ ያለ ፕሬስ እንዴት ሊታሰብ ይችላል? አገሪቱ ባለሁለት አኀዝ ዕድገት አስመዝግቤያለሁ ያለችው ፕሬስን እንደማያካትት የሚታይ ነፀብራቅ ሆነ’ኮ፡፡ ከጋዜጣው ራስጌ በስተቀኝ ያለው የፕሬስ ሥነ ስቅለት አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡ ፕሬሱን ከስቅለት አድኑ የሚለው ለካ ለዋናው ጉዳይ ባለፈ ለካ ዕለቱን ጠብቆ ሳይዛነፍ እንዲወጣ በመመኘቱም ኖሯል ለካ፡፡ የመጋቢት 30 ረቡዕ እትም የዓርብ ስቅለት ዕለት ሚያዝያ 2 ቀን መውጣቱ አጀብ ያሰኘው የመንደሬ ልጅ፣ የአይሁድ ሊቀ ካህናት፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ዓርብ ለመስቀል በዶለቱበት ዕለት፣ ሪፖርተር ረቡዕ ያልወጣው ማተሚያ ቤቱ አልሆነልኝም ብሎ በስቅለቱ ዕለት ሪፖርተርንም መስቀሉ፣ ማውጣቱ አጀብ አሰኝቶኛል ብሏል፡፡ ማተሚያ ቤቱ ሰበባሰበብ ቢደረድርም ከግል ውጪ ያሉት የሕትመት ውጤቶችን በየዕለታቸው ማውጣቱ ግማሽ ጎፈሬ ግማሽ ሉጩ መሆኑ ነው፡፡ ልጅና የእንጀራ ልጅ ዓይነት እንዲሉ፡፡ ከሕግ አውጪ፣ ከሕግ ተርጓሚና ከሕግ አስፈጻሚ ለጥቆ እንደ አራተኛው አካል የሚታሰበውን ፕሬስ በሌላው ዓለም እንዳለው ሁሉ ይቺ የአፍሪካ መዲና፣ አርአያ በምትባለው ኢትዮጵያ እውን የማታደርገው ለምን ይሆን? ኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናት፣ የአፍሪካ ፖለቲካ መድረክ ናት እየተባለ በፕሬሱ ግን ለአፍሪካ አርአያ መሆን ያልቻለችበት ሁነት ጭራ የመሆኗ ክስተት ምነው እያሰኘ ነው፡፡ ‹‹ሰው በዜና ውኃ በደመና›› እንዲሉ የበልጉ የፀደዩ ዝናብ እንደጠፋው ሁሉ የግሉ ፕሬስ ሳምንት ሙሉ እንዲጠፋ መደረጉ ምነው? የንግድ ተቋም ያውም የመንግሥት ደንበኞቹን እኩል ለማስተናገድ ፍላጎት የለውም እንዴ አሰኝቶናል፡፡ ሮብ ማለዳ ካዛንቺስ አካባቢ ጋዜጣ አዟሪዎችን አገኘሁና አንዱን ሻጭ እጅህ ከምን የእሑድ ሪፖርተርን ስለው ዘፈነብኝ፡- ‹‹አልመጣም ቀረሁኝ ሸግዬ ካንቺ የተሻለ ስላገኘሁኝ ሸግዬ›› እንዴት ነው ማተሚያ ቤቱ ይለያያል እንዴ? ‹‹ከልጅ ልጅ ቢለዩ …›› የተባለው ብሂል አድራሻው የት ይሆን? እናንተየ ዓመትና የካቲት ከተገናኙበት አንስቶ ለተከታታይ ወራት የፈተና ሕትመት ሰበብ ሆኖ፣ እንዲሁም የማሽን ብልሽት ምክንያት ሆኖ የፕሬስ ውጤቶች በወቅት ያለመውጣት አባዜ እስከ መቼ ይዘልቃል? እስከመቼስ ይነከሳል? (ፍሥሐ ገብረ ኪዳን ከካዛንቺስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...