Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክትኩረት የሚፈልገው የሕፃናት ቀለብ

ትኩረት የሚፈልገው የሕፃናት ቀለብ

ቀን:

ሕፃናት ወደዚህች ዓለም በፈቃዳቸው አይመጡም፡፡ ስለመምጣታቸው ከፈቀዱ ወላጆቻቸው ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆን ልጆቹን ለማምጣት በወሰኑበት ጊዜ የነበረው ፈቃድና እርስ በርሳቸው ያላቸው ፍቅር ግንኙነቱ በቆየበት ዘመን ላይቆይ ይችላል፡፡ የወላጆች ግንኙነት መሻከር በፈቃዳቸው ያልመጡ ልጆች ላይ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ሰፊ ነው፡፡ በኅብረተሰባችን ውስጥ የምናስተውላቸው ሕፃናት ያሉበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንዱ ምንጭ የወላጆች ግንኙነት መሻከር ነው፡፡ ሕግ በጋብቻም ሆነ ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ሕፃናት ጥበቃ የሚያገኙበትን ማዕቀፍ ስለሚቀርፅ የሕፃናቱን ችግር የተወሰነ ሊቀርፍ ይችላል፡፡ ሆኖም የሕጉና አተገባበሩ ክፍተት የሕጉ ዓላማ እንዳይፈጸም ምክንያት ይሆናል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆን ጉዳይ በዚህ ሰሞን ጸሐፊው ሰማ፡፡ ጉዳዩ ከሕፃናት ቀለብ አቆራረጥ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የሕፃናት መብት ጥበቃ ያለበትን ሁኔታ ሊያመለክት ስለሚችል መመልከቱ መልካም እንደሆነ ታሰበ፡፡ ለመነሻ ጉዳዩን እንግለጸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ባለትዳሮች ናቸው፡፡ ሁለት ልጆች ወልደዋል፡፡ አንዷ ሦስት ዓመት ሲሆናት ሌላዋ አምስት ዓመቷ ነው፡፡ ባልና ሚስት ለተወሰኑ ዓመታት በትዳር ከቆዩ በኋላ በመካከላቸው አለመግባባት ስለተከሰተ ወደ ፍቺ አመሩ፡፡ ጋብቻው በፍቺ ከፈረሰ በኋላ እናት ሁለት ልጆቿን እንድታሳድግ ባል ደግም በወር ብር 1,500 ቀለብ እንዲቆርጥ ፍርድ ቤቱ ወሰነ፡፡ እናት ምንም የወር ገቢ የሌላት ግን በኪራይ ቤት ለመኖር የምትገደድ በመሆኑ፣ እንዲቆረጥ በተወሰነው ቀለብ ልጆቹን ለማሳደግ አልቻለችም፡፡ ለጊዜው የታያት መፍትሔ ልጆቿን የማሳደግ መብትና ቀለቡን በመተው አባታቸው እንዲያሳድጋቸው መወሰን ነው፡፡ ይህም የሚሳካው ባልም ፍርድ ቤትም ከፈቀደ ነው፡፡ ለልጆቹ አስተዳደግ እናት ምቹ ብትሆንም፣ የቀለብ መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ እናት ልጆቿን ከረሃብ ለመታደግ ይህን ወሰነች፡፡ ይህ ተሞክሮ አብዛኛውን የአገራችንን ሕፃናት ሁኔታ ላይገልጽ ይችላል፡፡ ብዙ ሕፃናት በፍቺ ጊዜ ወይም አባታቸው በውል ባልታወቀ ጊዜ ከዚህ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ ስለ ሕፃናት የቀለብ መብት፣ የቀለብ አወሳሰንና አከፋፈል ሕጉ ምን ይላል? በተግባርስ ፍርድ ቤቶች የሕጉን ዓላማ የሚያስፈጽም አቋም ያንፀባርቃሉ? የሚሉትን ነጥቦች በቀጣዮቹ ክፍሎች እንመልከት፡፡ የሕግ መሠረት የቀለብ መብት የደም ወይም የጋብቻ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች የሚቋቋም ሲሆን፣ በዚህ ጽሑፍ የሕፃናት የቀለብ መብትን የምንመለከት በመሆኑ በዚሁ ዙሪያ ጠቃሚ የሆኑ የተወሰኑ ዓለም አቀፍና ብሔራዊ ሕግጋትን እንመለከታለን፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን የሕፃናትን ቀለብ የማግኘት መብት የተመለከቱ ድንጋጌዎች ይገኛሉ፡፡ የሰነዱ አንቀጽ 7 ሕፃናት በተቻለ መጠን ወላጆቻቸውን የማወቅና እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ አንቀጽ 27(4) ደግሞ ፈራሚ መንግሥታት ሕፃናት ከወላጆቻቸው ወይም ኃላፊነት ካለበት ሌላ ሰው ቀለብ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያስከብር ተገቢ የሆኑ ዕርምጃዎች እንዲወስዱ ግዴታ ይጥላል፡፡ የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተርም የማንኛውም ሕፃን ቀለብ የማግኘት መብት በወላጆች የትዳር ሁኔታ ምክንያት ሊነፈግ እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ቀለብን ጨምሮ ለሕፃናት የሚሰጡ መብቶች የሕፃኑን የፍላጐት ቀዳሚነት (The best interest of the child) መሠረት ያደረጉ ሊሆን እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ የተገለጹትን ዓለም ዓቀፋዊና አኅጉራዊ ስምምነቶች ከመፈረም ባለፈ የሕፃናትን መብት በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞራክሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ደንግጋለች፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሕፃናትን በተመለከተ በሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሕፃናት ደኅንነት በቀዳሚነት ሊታሰብ እንደሚገባ ደንግጓል፡፡ ቀለብን በተመለከተ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ለብዙ ዘመናት ገዥ ድንጋጌዎችን የያዘ ሲሆን፣ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በፌዴራል ደረጃ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የተሻረ በመሆኑ የፍትሐ ብሔር ሕጉን መሠረት ያደረገ ትንታኔ ጠቃሚ አይሆንም፡፡ ከተወሰኑት በስተቀር በክልሎችም የቤተሰብ ሕጎች ከፌዴራሉ ጋር በተመሳሳይነት ተሻሽለዋል፡፡ የተሻሻሉት የቤተሰብ ሕጎች በመግቢያቸው ላይ የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ለመሻሻላቸው መነሻ እንደሆኗቸው ከመግለጻቸው በስተቀር፣ በይዘታቸው የሕፃናት ፍላጐት ተቀዳሚ ቦታ ከመስጠት ውጭ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ከተደነገጉት አናቅጽ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የቀለብ መቁረጥ ግዴታ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 197-214 በዝርዝር የተደነገገ ሲሆን የልጆች ቀለብ በአንቀጽ 113 ተመልክቷል፡፡ ቀለብ አለመቁረጥ ወይም ማቋረጥ በአገራችን የወንጀል ሕግ ወንጀል ሆኖ ያስቀጣል፡፡ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 658 ይመለከቷል፡፡ የቀለብ አወሳሰን ፍርድ ቤቶች የፍቺ ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ ከሚወስኗቸው ነገሮች አንዱ የልጆች ቀለብ ሲሆን ይህም ወላጆች ለሕፃኑ ትምህርት፣ ጤና፣ አኗኗር፣ ልብስና ምግብ የሚሆን ገንዘብ በተከታታይ እንዲከፍሉ የሚያደርግበት ነው፡፡ የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 113 ይመለከቷል፡፡ በፍቺ ጊዜ ባልና ሚስት የሕፃናት ቀለብን በተመለከተ ተስማምተው በፍርድ ቤቶች ሊያፀድቁ ይችላሉ፡፡ ስምምነት በሌለበት ጊዜ ግን የልጆችን ቀለብ መወሰን የፍርድ ቤቶች ፈቃደ ሥልጣን ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የልጆች ቀለብ በሦስት መልኩ ይስተናገዳል፡፡ ፈረንሳይና ደቡብ አፍሪካን በመሰሉት በፍርድ ቤት፣ አሜሪካና ኖርዌይን በመሰሉት ለዚሁ ዓላማ በተቋቋመ ተቋም (Agency)፣ በኔዘርላንድ ደግሞ በሁለቱም መንገድ (Hybrid) የልጆች ቀለብ ይወሰናል፡፡ በኢትዮጵያ ቀለብ የመክፈል ግዴታ ያለበትን ወላጅ መለየትና የቀለቡን መጠን መወሰን የፍርድ ቤቶች ሥልጣን ነው፡፡ የአወሳሰኑ ዘዴ በጋብቻም ሆነ ከጋብቻ ውጭ ለተወለዱትም ልጆች ተመሳሳይ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች መጠኑን የሚወሰኑበት መመርያ፣ ማኑዋል ወይም ቀመር ስለሌላቸው በተግባር ለልጆች የሚቆረጠው ቀለብ ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት ይለያያል፡፡ አንዳንድ ጥናቶች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አካባቢ ቀለብ ለመወሰን የሚረዳ ፎርም እንዳለ ቢያመለክቱም፣ በተግባር ወጥነት ባለው መልኩ እንደማይሠራበት ይገልጻሉ፡፡ የልጆች ቀለብ ሲወሰን ፍርድ ቤቶች የሕፃኑን ፍላጐትና የወላጁን ገቢ ሊያገናዝቡ እንደሚገባ ሕጉ ይደነግጋል፡፡ (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 202) ስለዚህ ፍርድ ቤቶች ፈቃደ ሥልጣን ቢኖራቸውም፣ ቀለብ ሲወሰኑ ሁለት መሥፈርቶችን በአግባቡ ሊመዝኑ ይገባል፡፡ እነዚህም አቅምና ፍላጐት ናቸው፡፡ በአውስትራሊያ፣ በዴንማርክ፣ በኒውዚላንድ፣ በኖርዌይና በእንግሊዝ ቀለብን ለመወሰን የሚረዱ ጥብቅ ቀመሮች አሉ፡፡ በፈረንሳይ ፍርድ ቤቶች ሰፊ ፈቃደ ሥልጣን ቢኖራቸውም መደበኛ ያልሆኑ መመርያዎች (Informal guidelines) አሏቸው፡፡ ካናዳና ኖርዌይ የልጆችን ቀለብ ለመወሰን የሚረዳ ቀመር የያዘ የመረጃ መረብ (Child maintenance calculator) ስላለ ወላጆች መክፈል ያለባቸውን ቀለብ ከዌብ ሳይት ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ የልጆች ቀለብ በፍርድ ቤቶች ቢወሰንም አንዳንድ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከፍርድ ቤቶች ውጭ ቀለብን በተመለከተ ባልና ሚስት እንዲስማሙ ሰፊ ድርሻ ይወጣሉ፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ተጠቃሽ ነው፡፡ ቀለብን በዚህ መልኩ መወሰን ወጪ ከመቆጠቡ ባለፈ አፈጻጸሙ አስተማማኝ እንደሆነ አንዳንዶች ይገልጻሉ፡፡ አባትነት አጠራጣሪ በሆነበት ሁኔታ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ያለው አሠራር ለልጆችም ሆነ ለሚስት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በእርግጥ የሕፃናት ደኅንነት በቀዳሚነት እንዲታሰብ በማድረግ ፍርድ ቤቶች የተሻለ ደረጃ ላይ ናቸው ብለን ግምት ከወሰድን፣ ቀለብ ሁልጊዜም በፍርድ ቤት መወሰኑ ለሕፃናቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ቀለብ የማግኘት መብት ቀለብ የማግኘት መብት የሕፃኑ ነው፡፡ በተግባር ቀለብ የሚቆረጠው በአብዛኛው ለሚስት እንደሆነ የማሰብ ዝንባሌ ይስተዋላል፡፡ ለትዳር ጓደኛ (በአብዛኛው ለሚስት) ቀለብ የሚቆረጠው ፍቺ እስከሚወሰን ባለበት ጊዜ እንጂ ከፍቺ በኋላ ቀለብ የማግኘት መብት የልጆች ነው፡፡ ከፍቺ በኋላ ለትዳር ጓደኛ የሚሰጥ ቀለብ (Post divorce maintenance or alimony) በኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ አልተካተተም፡፡ ልጆችም ቢሆን ግን በወላጆች ላይ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ ወይም ለመፈጸም የሞከሩ ከሆነ ቀለብ የማግኘት መብታቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡ (አንቀጽ 200) ይህ ድንጋጌ የወንጀሉን ክብደት መጠን ካለማስቀመጡ በላይ ሕፃኑ ሁለት ጊዜ እንዲቀጣ ይፈቅዳል፡፡ ሌላው የተረገዘ ልጅ ቀለብ የማግኘት መብት አለው ወይስ የለውም የሚለው አከራካሪ ነጥብ ነው፡፡ የቤተሰብ ሕጉ በግልጽ የሚለው ነገር ባይኖርም የፀነሰች ሴት ለሕፃኑ ሕይወትና ደኅንነት ወጪ እንደምታወጣ ግልጽ ነው፡፡ የሕፃናት መብት ኮንቬንሽንም ሕፃናት በእናታቸው ማህፀን ካሉበት ጊዜ ጀምሮ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው በመግቢያው ስለሚገልጽ ቀለብ መቁረጥ የሕፃኑን መብት ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ ብዙ ዳኞች ግን ሕፃኑ እስካልተወለደ ድረስ የመብት ባለቤት ሊሆን እንደማይችል በመግለጽ ቀለብ እንደሚከለከሉ አንድ ጽሑፍ ይገልጻል፡፡ በሌሎች አገሮች (ለምሳሌ በፈረንሳይ) የልጆች ቀለብ ተጠቃሚ ልጅን የማሳደግ ግዴታ የተጣለበት ወላጅ ስለሆነ ጉዳዩ አዎንታዊ ምልከታ ሊኖረው ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የልጆች ቀለብ የሚቋረጥበት የዕድሜ ወሰን አከራካሪ ነው፡፡ የሕጉ አንቀጽ 201 ልጁ ቀለብ የሚፈልግ (in need) ከሆነና የራሱ ሥራ ወይም መተዳደርያ ከሌለው የቀለብ መብቱ እንደሚኖር ይደነግጋል፡፡ አንቀጽ 203 ደግሞ የቀለብ ግዴታ ባለበት ሰው ወይም የመብቱ ተጠቃሚ አመልካችነት ቀለብ እንደሚሻሻል ቢገልጽም፣ በምን ሁኔታ ቀለብ እንደሚቋረጥ አይገልጽም፡፡ በጥናት እንደተመለከተው በተግባር አንዳንድ ፍርድ ቤቶች ልጆች 18 ዓመት ሲሆናቸው የቀለብ መብት እንዲቋረጥ የቀረበላቸውን አቤቱታ የሚቀበሉ ሲሆን፣ አንዳንዶች ግን ልጁ ራሱን ችሎ ገቢ እስካላገኘ ድረስ የቀለብ መብቱ ሊቋረጥ እንደማይገባ ያምናሉ፡፡ በምዕራባውያን አገሮች ልጁ አካል ጉዳተኛ ካልሆነ ወይም ትምህርት ላይ ካልሆነ በቀር ልጁ የተወሰነ ዕድሜ ላይ ሲደርስ (16፣ 19፣ 21) ቀለብ ሊቋረጥ ይችላል፡፡ የወላጅን ገቢ መወሰን የልጆች ቀለብ መጠን የወላጅን ገቢ ያገናዘበ ሊሆን እንደሚገባ ሕጉ ይደነግጋል፡፡ አስቸጋሪው ነገር ግን የወላጅን ገቢ መወሰን ነው፡፡ ሕጉ የወላጅ ገቢ የሚወሰንበትን ሁኔታ በግልጽ አያመለክትም፡፡ በተግባር ደግሞ ወላጅ መደበኛ ገቢ ወይም ንግድ ከሌለው ገቢውን መወሰን አዳጋች ስለሚሆን ልጆች ተገቢ ቀለብ ላይቆርጥላቸው ይችላል፡፡ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ገቢን ለመወሰን የሚረዱ ፎርሞች እንዳሉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ሆኖም ፎርሞቹ ከመደበኛ ገቢ ውጭ ያሉ ገቢዎችን አይገልጹም፣ ገቢው ያልተጣራ (Gross) ይሁን የተጣራ (Net) አያመለክቱም፣ እንዲሁም ሌሎች ተቀናሾች (ፕሮቪደንት ፈንድ፣ ጡረታ፣ ዕዳ፣ ለወላጅ የሚቆረጥ ቀለብ ወዘተ.) ስለመኖሩ አይጠይቁም፡፡ አንዳንዶች ተቀናናሽ መኖር አለመኖሩ ተጣርቶ ቀሪው ገቢ ለቀለብ መወሰኛ ሊታሰብ ይችላል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ከማንኛውም ተቀናሽ የልጆች ቀለብ ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ከተገማችነት (Predictability) አንፃር መደበኛ ያልሆነን ገቢ (ከድለላ፣ የቀን ሥራ፣ የአደባባይ ንግድ ወዘተ. የሚገኝ ገቢ) መወሰንና ማስፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ፍርድ ቤቶች የሕፃናትን ደኅንነት በቀዳሚነት ግምት ውስጥ ማስገባት ስለሚኖርባቸው ገቢ የማስገኘት አቅም (Income earning capacity) በአግባቡ ተመርምሮ መደበኛም ሆነ መደበኛም ያልሆነ ገቢ ግምት ውስጥ ገብቶ ቀለብ ሊሰፈር ይገባል፡፡ የንብረት ምዝገባ ሥርዓት በሌለበትና ገቢን መደበቅ ባህል በሆነበት ሁኔታ ዳኞች ሕፃናትን ለመርዳት ሰፋ ያለ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማንኛውም ዓይነት ገቢ ቀለብ ለመቁረጥ ሊታሰብ ይገባል፡፡ ወላጅ በልቶ፣ ጠጥቶ፣ አልፎ አልፎም ተርፎት እየታየ ያለፈቃዱ የተወለደው ሕፃን የሚራበበት ሁኔታ ሊገታ ይገባዋል፡፡ የቀለብ መጠን የቀለብ መጠን የወላጅን ገቢና የልጁን ፍላጐት መሠረት አድርጎ መወሰን እንዳለበት ከመግለጹ ውጭ ሕጉ ዝቅተኛና ከፍተኛ የቀለብ መጠን አላመለከተም፡፡ ፍርድ ቤቶች የቀለብ መጠንን በመወሰን ረገድ ያላቸው ፈቃደ ሥልጣን ሰፊ ነው፡፡ በተግባር የኑሮ ውድነት መረን በለቀቀበት ሁኔታ እንኳን ከ50 ብር እስከ 120 ብር የሚወስኑ ዳኞች አሉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ያደረግነው ጉዳይም የገንዘብ መጠኑ ከፍተኛ ቢመስልም ለማኖር የማያስችል ስለመሆኑ ግንዛቤ መውሰድ ቀላል ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች የቤተሰብ ጉዳዮች በማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ስለሚታዩ የአወሳሰኑ ሁኔታ በተለይ የሚቆረጠው ቀለብ መጠን የሕፃኑን ፍላጐቶች (ለትምህርት፣ ጤና፣ ምግብ፣ ልብስ) ያገናዘበ ስለመሆኑ በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡ በአንድ ጥናት እንደተመለከተው በመዝገብ ቁጥር 111151 የብር 2,000 የወር ደመወዝ ካለው አባት ለልጅ ቀለብ 320 ብር (16%)፣ በመዝገብ ቁጥር 113144 የብር 2,100 ገቢ ካለው አባት ለሦስት ልጆች ብር 200 (9.5%) ቀለብ እንደተቆረጠ ተገልጿል፡፡ ይህ ፍርድ ቤቶች የልጆች ቀለብ አወሳሰን ላይ የሕፃናት ደኅንነት በቀዳሚነት እንዲታሰብ (Primary consideration of the best interest of the child) ለማድረግ ብዙ ርቀት እንዳልሄዱ አመላካች ነው፡፡ ጉዳዩ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን የምናስተውለው ይህንን ሃቅ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ዝቅተኛና ከፍተኛ የቀለብ መጠን የሚቀመጥ ሲሆን የአወሳሰን ቀመርም ተዘርግቷል፡፡ ለምሳሌ በጀርመን ዝቅተኛው ተመን (Standard amount) ከ0-5 ዓመት ሕፃን 204 ዩሮ፣ ከ6-11 ዓመት 247 ዩሮ፣ ከ12-17 ዓመት 290 ዩሮ በመቀመጡ ከዚህ በታች የቀለብ መጠን ሊሰፈር አይችልም፡፡ የጀርመን የቀመር ሥርዓት ለእኛ አገር ባይሠራም የልጆች ቀለብ መጠን መነሻው፣ መድረሻው፣ አወሳሰኑ ወዘተ. ግልጽ መመርያ ይፈልጋል፡፡ አከፋፈልና አፈጻጸም የሕጉ አንቀጽ 204 ቀለብ የሚከፈለው ለተጠቃሚው በሚመቸው ቦታ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ የልጅ ቀለብ የመቁረጥ ግዴታ ያለበት ልጁን የማሳደግ ግዴታ ያለበት ወላጅ ጋር በመሄድ በቀጥታ መክፈል አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በአገራችን ክፍያው ስለመከፈሉ የሚያረጋግጥ ተቋም ባለመኖሩ አሳዳጊ ወላጅ የመከታተል ግዴታ ይኖርበታል፡፡ በተግባር አንዳንድ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የአከፋፈሉን ሁኔታ ባልና ሚስቱን በማስማማት ስለሚፈጽሙት ውጤታማ ሲሆን ይታያል፡፡ ፍርድ ቤቶች የቀለብ ግዴታ አፈጻጸም በአሠሪዎች በኩል እንዲፈጸም የሚያዙበት ሁኔታ የተለመደ ነው፡፡ ይህ መደበኛ ለሆነ ገቢ ሲሆን፣ መደበኛ ባልሆነ ገቢ ላይ የሚፈጸም ቀለብ አፈጻጸሙ ባለገንዘብን (ልጅንና አሳዳጊ ወላጅን) የሚያንገላታ ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች የማስፈጸም ግዴታው ለሬጅስትራር ቢሮ ተሰጥቶ ግዴታ ያለበት ወላጅ ፍርድ ቤት በየወሩ እየሄደ ቀለብ የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌሎች አገሮች አፈጻጸሙን የሚከታተል አካል ስለሚያቋቁም ብዙ ችግር አይስተዋልም፡፡ በእኛ አገር ግን የቀለብ አፈጻጸምን የሚገዛ የተለየ የሕግ ድንጋጌም፤ ተቋምም ባለመኖሩ ቀለብ ጠያቂዎች በየፍርድ ቤቱና በየመሥሪያ ቤቱ ሲንገላቱ ይስተዋላል፡፡ ማጠቃለያ የሕፃናት ቀለብ የማግኘት መብት መከበር የሕፃናትን በሕይወት የመኖር፣ የጤንነት፣ የትምህርትና ወዘተ. መብቶችን ማስከበር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የሕፃናትን ደኅንነት በቀዳሚነት እንዲታሰብ የማድረግ ግዴታ ስላለባቸው የቀለብ አወሳሰን ላይ ያለባቸውን ግዴታ በጥንቃቄ ሊወጡ ይገባል፡፡ ሕጉ ገቢን ለመወሰን የሚያስችሉ፣ የቀለብ መጠን ዝቅታና ከፍታን እንዲሁም አፈጻጸምን የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ስላልያዘ በመመርያ ሊብራራ ይገባል፡፡ ሕጉና አተገባበሩ ልጆችን እየወለዱ ለሚበትኑ ወላጆች ድጋፍ ሊሰጥ አይገባም፡፡ በተለይ የቀለብ መጠን ለሕፃናት ጤና፣ ትምህርት፣ ምግብና ልብስ የሚበቃ ስለመሆኑ መመርመር ይገባዋል፡፡ ሕፃናት ከሚራቡ ያለፈቃዳቸው ያመጣቸውና ኃላፊነት የጎደለው ወላጅ ቢራብ ይሻላል፡፡ ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...