Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከነጋዴዎች ቤተ ምክክር ወደ ንግድ መደብር!

ከነጋዴዎች ቤተ ምክክር ወደ ንግድ መደብር!

ቀን:

በሰለሞን በቀለ

ላለፉት 30 ዓመታት ዘወትር ከቤት ወደ ቢሮዬ ሳልፍና ሳገደም ታክኬ የማልፈውና በበርካታ ክንዋኔዎቹም ላይ የምታደመው ነባሩ የንግድ ምክር ቤት ሕንፃ ላይ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር የሜክሲኮ አደባባይ ቅርንጫፍ የሚል ማስታወቂያ ተሰቅሎበት ተመለከትኩኝ፡፡ ባንኩ በየትኛው የሕንፃው ክፍልና በምን ያህል ዋጋ እንደተከራየ ወደ ሥፍራው ጠጋ ብዬ ሁነኛ ሰው ብጠይቅ፣ ባንኩ የተከራየው የንግድ ምክር ቤቱን ትልቁን አዳራሽ ሲሆን የኪራዩም ዋጋ በወር 100,000.00 (አንድ መቶ ሺሕ) ብር መሆኑ ተገለጸለኝ፡፡

ተከራዩ ባንክም አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችለው መልኩና ደኅንነቱን ለመጠበቅ አዳራሹን እያዘጋጀው፣ እንዲሁም የውስጥ ክፍፍሎች እያደረገ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እንዴት በዚህ ዓይነት ዓይን ቦታ ላይ እስካሁን ድረስ ሌሎች ባንኮች ሊከራዩት እንዳልቻሉ እያሰላሰልኩኝ እንዳለሁኝ፣ ወዲያውኑ አንድ ነገር በአዕምሮዬ መጣ፡፡ ለመሆኑ በዚህ የስብሰባ አዳራሽ ይከናወኑ የነበሩ የምክር ቤቱ ስብሰባዎችና ሌሎች ሥነ ሥርዓቶች የት ሊደረጉ ነው ብዬ አሰብ አደርግኩ፡፡ አይ! በከተማው ውስጥ እንደ አሸን የፈሉት ሆቴሎችስ ምን ይሥሩ ብዬ ለራሴ ምላሽ ሰጠሁኝ፡፡

ጥቂት ቆይቼ በእርግጥ ሆቴሎች ዘንድ አስቀድሞ ፕሮግራም ከተያዘ አዳራሾች በተፈለገው ሁኔታ ሊያቀርቡ ቢችሉም፣ በተለይ ሠርግና መሰል ዝግጅቶች ካሉ ግን ማናቸውንም በአዳራሾች ለሚከናወኑ ሥነ ሥርዓቶች ዋጋቸው የሚቀመሱ እንደማይሆኑ አሰብኩኝ፡፡ ለዚያውም አዳራሹ ቢገኝ እንኳን ለስብሰባ ከሆነ የተፈለገው ምክንያቱን ለፀጥታ ሰዎች ማስታወቅና ከፈቃድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለስብሰባው መካሄድ ወይም አለመካሄድ ጫና ሊደርግ ይችላል፡፡

ስለ አገራችን የንግድ ምክር ቤቶች ሲወሳ ቀድሞ በአንባቢም ሆነ በተመልካች ዘንድ የሚሳለው ሥዕል በውስጣቸው ስለነበረውና ስላለው የአመራሩ ማለቂያ የሌለው አተካራና ጭቅጭቅ፣ በሕንፃው አመላለስና አጠቃቀም ላይ የነበረው ውዝግብ፣ ኢሕአዴግ ከገባ ወዲህ ደግሞ መንግሥት በሚወስዳቸውና በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ባፀናቸው አንዳንድ ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ሲከሰቱ የነበሩ አለመግባባቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የአዲስ አበባ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጽሕፈት ቤታቸው በዋናነት የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎች ማኅበራት፣ የግልና የመንግሥት ቢሮዎችም መኖራቸውንም ለማረጋገጥ ችያለሁኝ፡፡ ይህ ሕንፃ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን ከንግድ ምክር ቤቶቹ ጽሕፈት ቤትነት በተጨማሪ፣ በአንድ ወቅት የውጭ ንግድና የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከዚያም የገቢዎች ቦርድና የአገር ውስጥ ባለሥልጣን፣ ወዘተ የተባሉ መንግሥታዊ ተቋማት ቢሯቸውንና ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

የአገራችን ንግድ ምክር ቤቶችና አመራሮቻቸው በሌሎች አገሮች እንደምንመለከተው እርስ በእርስ ተስማምተው እንደ ማኅበር የአባሎቻቸውን ወጥ የሆኑ ጥቅሞች ለማስከበር የሚያስችል፣ በተለይም ከመንግሥትም ሆነ ከማናቸውም የተደራጀ አካል ጋር በአስገዳጅነትም ይሁን በፈቃድ ለመወያየትና ለመገዳደር የሚያስችል ጠንካራ አደረጃጀት፣ ጎልቶ በወጣና ሙሉ ተቀባይነት ባለው አመራር እየተመሩ ተፅዕኖ ለማሳደር ያልቻሉበትን ምክንያት ሳሰላስል፣ ምናልባት ይህ ሁኔታ በመላ አገሪቱ ካለው የማኅበራት አደረጃጀትና አመራር ችግር ጋር የተያያዘ ይሆን የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻል ይሆናል፡፡

ይሁን እንጂ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ በሆነኝ ጉዳይ የንግዱ ማኅበረሰብ ቢያንስ ጊዚያዊውንም ሆነ ዘለቄታዊ ጥቅሙን ለማራመድ በሚያስችለው ብቸኛ በሆነው ሕጋዊ የመሰባሰቢያ ተቋሙ ላይ ራሱን የመግደል ዕርምጃ ምክር ቤቱ ይወስዳል የሚል እምነት አልነበረኝም፡፡ በየትም አገር የንግድ ምክር ቤቶች በዋናነት ስለንግድ፣ ስለ ኢንዱስትሪ፣ ስለ እርሻና ዕደ ጥበብ፣ ወዘተ ሥራዎች ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችሉ ውይይቶች፣ ምክክሮችና ክርክሮች የሚደረጉባቸው ቋሚ መድረኮች ናቸው፡፡ አባላት ለተሰማሩባቸው ሥራዎች ምርጥ የሆኑ ተሞክሮዎች ወደ አገሮቻቸው እንዲመጡ አማራጭ ሐሳቦችን ለማፍለቅ፣ ከውጭ አገር ነጋዴዎች ጋር ግንኙነት ለማድረግ፣ ዓውደ ጥናቶችና ሴሚናሮች ለማካሄድ፣ የሚችሉባቸው ሥፍራዎች ናቸው፡፡ የመንግሥት ተቋማትም ቢሆን የተደራጀውን የንግዱን ማኅበረሰብ ለማናቸውም ተግባራት ማግኘት ቢያሻቸው፣ ምንም እንኳን ለተለያዩ ዓላማዎች የተቋቋሙ ሌሎች ጊዚያዊ ማኅበራት ቢኖሩም ሕጋዊና ዘለቄታዊነት ያላቸው ግዙፍ አሰባሳቢ ተቋማት የንግድ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡

የንግድ ምክር ቤቶች በመሠረቱ እንደ ተቋም በሕግ በተሰጡዋቸው ኃላፊነቶችና ግዴታዎች ዙሪያ በአባላቱ ዘንድ ምክክሮችን የሚያደርጉባቸው፣ የሚያዋጡባቸው፣ የሚለዋወጡባቸው፣ የሚቀባበሉባቸው፣ ውጤቱንም ለራሳቸውና ለአባላቶቻቸው፣ እንዲሁም ከመንግሥትና ከሌሎች ተቋማት ጋር ለመደራደር፣ ለመነጋገር፣ ለመግባባትና ለመስማማት ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማድረግም ተፅዕኖ ለማሳደር የሚችሉባቸው መድረኮች ናቸው፡፡ እነኚህን የንግድ ምክር ቤቶች ተግባራትን ለማከናወን ደግሞ መሰባሰቢያና መከራከሪያ ሥፍራዎች፣ ሐሳቦች የሚነሱባቸውና የሚጣሉባቸው አዳራሾች የግድ ይላሉ፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ሌላ መሰል አዳራሽ ይኑረው አይኑረው አላውቅም፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ግን ራሴንም ጨምሮ በርካታ ጓደኞቼ ከምክር ቤቱ ጋር በሚያገናኙን ሥራዎች ስብሰባ የሚጠራውና የሚደረገው ግን፣ በዚሁ አሁን የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ የሜክሲኮ አደባባይ ቅርንጫፍ እንዲሆን በተደረገው አዳራሽ ነበር፡፡

የሕንፃው ባለቤት ነው የተባለው የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በግንባር ስለሥራ ዘርፋቸው ችግርም ሆነ ስኬት ምክክር የሚያደርግበትን አዳራሽ ለመዝጋትና ማናቸውም በአዳራሹ ሲደረጉ የቆዩ ውይይቶችና ሌሎች ክንዋኔዎች አላስፈላጊ ስለመሆናቸው ምን ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ፣ እምነትና ውሳኔ ላይ ቢደርስ ይሆን ፍፁም ለአባላቱ ይህን ያህል ጠቀሜታ ያስገኛል ተብሎ ሊታሰብ ወደማይችል በኪራይ ወደ ንግድ መደብርነት የለወጠው? የንግድ ምክር ቤቱን የመሠረቱትና መዋጮ እያዋጡ ህልውናውን እየጠበቁለት ለሚገኙት ግለሰብ ነጋዴዎች፣ የንግድ ማኅበራት፣ የልማት ድርጅቶች፣ ወዘተ በምክር ቤቱ አዳራሽ ምን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በማቀዱ ይሆን መደብሩ እንዲቋቋም መፍቀዱ? ወይስ ምናልባት በምክር ቤቱ የወቅቱ አመራሮች እምነት የንግድ ምክር ቤቱ አባላት የሚጠይቁትንና ማግኘት የሚፈልጉትን አገልግሎት ተከራይ በሆነው መደብር አማካይነት ማግኘት ይችላሉ በሚል ይሆን?

 ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ስለሆነብኝ የንግድ ምክር ቤቱን አዳራሽ ተከራይቶ የሚሠራው የንግድ መደብር ንግድ ምክር ቤቱን ተክቶ ሊሠራ ይችል እንደሆነ፣ የመደብርን ትርጉም ከደስታ ተክለወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፍቺውን ሳፈላልግ፣  “በያይነቱ ዕቃና ልብስ ያለበት ሱቅ፣ መሰደሪያና መደርደሪያ፣ መሸጫና መለወጫ ቤት” የተሰኘ ትርጉም አገኘሁኝ፡፡ በእርግጥ መደብሩ የባንክ ቅርንጫፍ እንደመሆኑ መጠን አገልግሎት ሰጪ በመሆን ገንዘብ ወጪና ገቢ የሚደረግበት፣ የብድር ጥያቄ የሚቀርብበት፣ የሚፈቀድበትና ተያያዥ አገልግሎት የሚሰጥበት በመሆኑ ለየት ያለ ቢያስመስለውም መደብርነቱን ግን አይለውጠውም፡፡

እንግዲህ መደብር የምክክር ቤት ወይም ሥፍራ አለመሆኑ ትርጓሜው አሰገንዝቦናል፡፡ ይልቁንም ይህ የባንክ ቅርንጫፍ በሥፍራው መኖሩ ይበልጡኑ ተገልጋዩንና ባንኩን ለመጠበቅ ሲባል፣ በምክር ቤቱ ከመግቢያው ጀምሮ የነበረውን አንፃራዊ የነፃነት ድባብ ከሰፈነበት የውይይት መድረክነት ጭራሹኑ ለፀጥታውና ለደኅንነቱ በሚል በንግዱ ማኅበረሰብ  ላይ በበርካታ ሥፍራዎች የተለመዱ አንገፍጋፊ አካላዊ ፍተሻዎችና ክትትሎችን የሚተካ ነው፡፡ ከባንኩ ተገልጋይ በስተቀር የምክር ቤቱን ተገልጋይ የሚያስደነብርና የሚያሸሽ ሁኔታ ቀስ በቀስ መፍጠሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ የራሱን ኣዳራሽ ከመመካከሪያ መድረክነት ወደ መደብርነት በማሸጋገር በርካታ ሚሊዮኖች ገንዘብ ቢያገኝም እንኳን፣ ይህ ገንዘብ ምን ያህል የንግዱን ማኅበረሰብ መሠረታዊ ችግር ለመቅረፍና ለመፍታት ይችላል? ወይስ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱንና ግዴታውን በመተው ራሱን ዕዳ ውስጥ በጨመረ አክሳሪና ከፍተኛ ወጪን ባስከተለበት እንቅሰቃሴ ውስጥ ገብቶ ይሆን?

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የንግድ ማኅበረሰቡን የሚያወያይበትና የሚያሰባስብበትን አዳራሹን በማከራየት፣ ራሱን ከነጋዴዎች የመመካከሪያ መድረክነት ወደ ንግድ መደብርነት የመለወጡ አሳዛኝ ውሳኔ ላይ መድረሱ ምን ያህል በከባድ ራስን የማስከበር ፈተና ላይ እንደወደቀ ያስገነዝበናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...