ኬንያ ለምታስተናግደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ውድድር 27 ተጨዋቾችን ያቀፈው የአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን የሚገባንው ያህል ብሔራዊ ክብር እያገኘ እንዳልሆነ አስተያየት የሚሰጡ የስፖርቱ ቤተሰቦች ቁጥር እየተበራከተ ነው፡፡
ለዚህም እንደማሳያ የሚያነሱት ነጥብ፣ ብሔራዊ ቡድኑ በፕሪሚየር ሊግ ከሚጫወቱ ክለቦች ከሁለት በላይ ተጨዋቾች እንዳይመረጥ በመጥቀስ ነው፡፡ አሠልጣኙ የብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሠልጣኝነት ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ እያስተናገደው በሚገኘው ተደጋጋሚ ሽንፈት ምክንያት ቡድኑ እንደ ብሔራዊ ቡድን ከመታየት ይልቅ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑንም ሆነ ተጨዋቾቹን ለከፋ ትችት እየዳረገ መምጣቱን የሚናገሩት እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች፣ ለአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ተሳትፎ ይበቃ ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ ያገኘውን የቻን የማጣሪያ ውድድር ማለፍ አለመቻሉ ነገሩን ሁሉ ‹‹ከድጡ ወደ ማጡ›› ማድረጉን ጭምር ይናገራሉ፡፡
በእነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ ቀደም ብሎ የተጀመረው ፕሪሚየር ሊግ ከሚቋረጥ፣ ወይም ቡድኖች ከሁለት በላይ ተጨዋቾች አስመርጠው ሊጉ ከሚንዛዛ ይልቅ፣ ከአንድ ክለብ ከሁለት በላይ ተጨዋቾች እንዳይመረጡ በማድረግ ሊጉ እንዲቀጥል የተደረገበት የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በበጎነቱ መወሰዱን የሚናገሩ አሉ፡፡
የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ በበኩላቸው፣ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ አክብረው ከሁሉም የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተጨዋቾችን መርጠው ዝግጅት እንደሚጀምሩ ነው የሚናገሩት፡፡ እንደ ዋና አሠልጣኙ ከሆነ፣ የመረጧቸው ተጨዋቾች ተጠቃለው ሆቴል የሚገቡ ከሆነ ኅዳር 13 እና 14 ቀን 2010 ዓ.ም. መደበኛ ዝግጅት ይጀምራሉ፡፡
ከኅዳር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚካሄደው የሴካፋ ውድድር፣ ለ27 ተጨዋቾች ጥሪ ማድረጋቸውን ያከሉት ዋና አሠልጣኙ፣ ከፊት ለፊታቸው ለሚጠብቃቸው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትና ተሞክሮ ለመውሰድ 25 ወይም 23 ልጆችን በመያዝ ወደ ኬንያ መጓዝ እንደሚፈልጉም ይናገራሉ፡፡
ይሁንና የፌዴሬሽን ምንጮች ለሪፖርተር እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ፌዴሬሽኑ ከ18 ተጨዋቾች በላይ እንዲያዙ ፍላጎት የለውም፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ቡድኑ አሁን ባለው አቋም የተሻለ ውጤት አያመጣም ከሚል እሳቤ እንደሆነ ይታመናል፡፡
በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአመራር ደረጃ የተቀመጡ፣ ነገር ግን ለቡድኑ ሞራል ሲባል ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ዋሊያዎቹ በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያስመዘገቡት ያለው የውጤት ማሽቆልቆል፣ ለእግር ኳሱ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ የአሠልጣኙ መልካም ፈቃደኝነት ቢታከልበት፣ ለወደፊቱ ብሔራዊ ቡድን ተስፋ ያላቸው ለወጣት ተጫዋችነት ትኩረት ቢሰጡ ምርጫቸው እንደሆነ ጭምር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
አሠልጣኝ አሸናፊ ግን በእግር ኳስ ቤተሰቡም ሆነ በፌዴሬሽኑ አስተያየትና እምነት የሚስማሙ አለመሆናቸው ጥሪ ካደረጉላቸው ተጨዋቾች መረዳት ይቻላል፡፡ ዝግጅታቸውን አስመልክቶ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው አሸናፊ በቀለ፣ እሳቸውና ቡድናቸው ወደ ኬንያ የሚያመሩት ውጤት ለማምጣት ነው፡፡
የብሔራዊ ቡድኑ ብሔራዊ ክብር በዚህ መልኩ እንዲወርድ ተጠያቂነቱ የዋና አሠልጣኙ ብቻ እንዳልሆነ የሚናገሩም አሉ፡፡ እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምን ዓይነት እግር ኳሳዊ ባልሆነ ፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ መገኘቱ የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ እያለ እንዴት ነው ስለ እግር ኳስ ዕድገትና ውድቀት የሚታሰበው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
በምድብ ‹‹ለ›› ከኡጋንዳ፣ ከቡሩንዲ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከተጋባዥዋ ዚምባቡዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከመከላከያ ቴድሮስ በቀለ፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አበባው ቡጣቆና አቡበከር ሳኒ፣ ከሐዋሳ ከተማ ተክለማርያም ሻንቆና ፍሬው ሰለሞን፣ ከአዳማ ከተማ ከነዓል ማርክነህና ዳዋ ውጤሳ፣ ከደደቢት ታሪክ ጌትነትና አቤል ያለው፣ ከሲዳማ ቡና አበበ ጥላሁንና አዲስ ግደይ፣ ከፋሲል አብዱራህማን ሙባረክና አምሳሉ ጥላሁን፣ ከድሬዳዋ ከተማ አናጋው ባደግ፣ ከወልድያ ከተማ ተስፋዬ አለባቸውና ብሩክ ቃልቦሬ፣ ከኢትዮጵያ ቡና ሳምሶን ጥላሁንና ሙሰድ መሐመድ፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግርማ በቀለና በኃይሉ ተናገር፣ ከመቐለ ከተማ አማኑኤል ገብረ ሚካኤል፣ ከወልዋሎ አዲግራት በረከት አማረ፣ ከአርባ ምንጭ ከተማ ተመስገን ባሰትና እንዳለ ከበደ፣ ከወላይታ ድቻ ፀጋዬ ብርሃኑ እንዲሁም ከጅማ አባ ጅፋር ሔኖክ አዱኛና ዮናስ ገረመው መያዙ ታውቋል፡፡