Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትከርዕዮተ ዓለም ‹‹ወዳጅ›› ፍለጋ ያልወጣው ፖለቲካዊ ጉዞና ኢትዮጵያ

ከርዕዮተ ዓለም ‹‹ወዳጅ›› ፍለጋ ያልወጣው ፖለቲካዊ ጉዞና ኢትዮጵያ

ቀን:

በሒሩት ደበበ

ዓለም በቀዝቃዛው ጦርነት ከአርባና ከሃምሳ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ የተፋጠጠችበት የምሥራቅና የምዕራብ ጎራ ፍትጊያ በታሪክ ድርሳናት በስፋት ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ምሥራቁ በተለይ በሩሲያ ኮሙዩኒስት (ሶሻሊስታዊ ፍልስፍና) እየተመታ መልኩና ገጹ ቢለያይም ምሥራቅ ጀርመንና ደቡብ የመንን የመሳሰሉ አገሮች ተሠልፈውበት ነበር፡፡ ምዕራቡ ዓለምም በነአሜሪካና እንግሊዝ ፊታውራሪነት በርካታ ተከታዮችን እያፈራ ዓለምን በነፃ ገበያ (ኒዮሊብራል) አስተሳሰብ ለመጠቅለል ባዝኗል፡፡

ያ የፕሮፓጋንዳ፣ የፋይናንስ፣ የብድርና የዕርዳታ መፈለግና መገፋፋት በውስጡ በርካታ ውጥንቅጦችን አሳልፎ፣ ‹‹ሲጠናቀቅ›› ሁለት ገጽታዎች ተንፀባርቀዋል፡፡ አንድ ሕዝብ የነበሩት ጀርመናውያን በሁለት ተከፍለው ከመኖር በመውጣት የበርሊን ግንብን ንደው መልሰው ተቀላቅለዋል፡፡ በተቃራኒው ‹‹ታላቋ›› ሩሲያ (ሶቪዬት ኅብረት) ወደ አሥራ ምናምን ትንንሽ አገሮች ተበታትናለች፡፡ የምሥራቁ ጎራ አስፈሪነት ኮስምኖ በጥራዝ ነጠቅም ቢሆን ‹‹ሶሻሊዝምን›› ሲያቀነቅኑ የነበሩ እንደ ደርግ ያሉ የአፍሪካ መንግሥታትም በተለያየ ሁኔታ ለውድቀት ተጋልጠዋል፡፡ ቢያንስ የማሌ አቀንቃኞች ህልማቸው ‹‹ተዳፍኗል››፡፡

በተቃራኒው የሊብራል ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ አራማጅ የምዕራቡ ኃይል ባለጡንቻና ባለአቅም ስለሆነ ዛሬም ድረስ አሻራውን በየቦታው እያሳረፈ ነው፡፡ እንደ ቻይና ያሉት በራሳቸው ሶሻሊስታዊና ልማታዊ ባህርይ በራቸውን ዘግተው በመሥራት በአጭር ጊዜ የምዕራቡን ኃይል ግፊት ተቋቁመው በጥቂት አሥርት ዓመታት በኢኮኖሚያዊ ተገዳዳሪነት ቢመጡም፣ ማንም አሜሪካና ደጋፊዎቹን የምዕራብውያንን ተፅዕኖ አፈንግጦ ሊወጣ የቻለ የለም፡፡ እርግጥ ዛሬም ድረስ የቭላድሚር ፑቲን መራሹ የሩሲያ መንግሥት በቀላሉ የሚሰበር ኃይል ባይሆንም፣ ‹‹ድምፅን በድምፅ›› ከመሻር ውጪ በራሱ ደርጅቶ ሌሎችን የሚያሠልፍ ብርቱ አቅም መሆን አልቻለም፡፡

ዓለም ይኼን በሚመስል ደረጃ ላይ መሆኗን ለመግለጽ የተለያዩ የዘርፉ ምሁራን ከሁለት ጐራና ቀዝቃዛ ጦርነት ይልቅ በብዙ ዋልታዎች የምትሽከረከር ዓለም (Multi Polar World) ሆናለች ማለታቸው አሳማኝ ነው፡፡ ዛሬ እነአሜሪካ የአብላጫ ድምፃቸውን ይዘው የፈለጉትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ይፈጽማሉ፡፡ እንደ ‹‹ዋሽንግተን ኮንሰንሰስ›› ያለ የወጪ፣ የገቢና የፋይናንስ ሥርዓትን ሲተገብሩ ሌሎች ጫናውን ለመቋቋም በሚመስል ደረጃ እንደ “BRICS” (ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ) የጋራ ባንክና የኢኮኖሚ ፎረምን እስከ መጀመር ደርሰዋል፡፡

በጦርነት ፍጥጫ ረገድም አሜሪካ በተፈጥሮ ሀብት፣ በአክራሪነትና በሽብርተኝነት ስምም የዜጐች ‹‹ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በመንግሥታት ተገፏል›› ያለቻቸውን አገሮች እስከማፈራረስ ደርሰዋል፡፡ ለዚህ አባባል ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያ፣ አሁን ደግሞ ሶሪያ፣ ደቡብ ሱዳንና የመን ከኋላቸው የምዕራባውያንና የእነሱ ተቃራኒዎች ፍላጐት ባይኖርበት፣ ይህን ያህል እንደማይበታተኑ የሚናገሩ በርካታ ትንታኔዎች አሉ፡፡ የቅርብ ጊዜው የዩክሬን ሁኔታም ከፍጥጫ በስተጀርባ የተፈጠረ ትርምስ የወለደው መሆኑን መጠርጠር የዋህነት ነው፡፡

እንግዲህ በዚህ መልክ የርዕዮተ ዓለም ሁኔታውን በማንሳት መተንተን የጋዜጣ ገጽ ካለመብቃቱ በላይ፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ ይልቁንም የትኩረታችን ማዕከል የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነውና ወደዚያው እናተኩር፡፡

ኢሕአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ሃያ ሦስት ዓመታት በሥልጣን ላይ ሲቆይ በፅናት የሚያራምደው ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የተባለ ርዕዮት ነው፡፡ አንዳንዴ ነጭ ካፒታሊዝም፣ ነፃ ገበያና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚለው ድምፅ ሲጮኽ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ግራ ዘመም ገጽታው እየጐለበተ (ማሌሌትና አልባኒያ ሶሻሊታዊ ፍልስፍናን ልብ ይሏል) ታይቷል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አገሪቱ በነፃ ገበያ መመራቷና ‹‹ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው›› ማለቷ ባይቀርም ኒዮሊብራሊዝም የተባለው እንደሆነ በይፋ ይነገራል፡፡

ድርጅቱ ይህን አስተሳሰብ በተለያዩ ሰነዶችና በካድሬዎች እያስነገረ ቢሆንም፣ ‹‹በዲፕሎማሲያዊ ፖለቲካ››› መርህ ግን አገሪቱ ስተራቴጂካዊ ጠላትም ሆነ ወዳጅ እንደሌላት ይነገራል፡፡ ዛሬ የኒዮሊብራሊዝም ዋነኛ መሪ የሆነችው አሜሪካ የኢትዮጵያ ‹‹ቁልፍ›› የምትባል ወዳጅ አገር ነች፡፡ በተለይ በቀጣናው የፀረ ሽብር ዘመቻና የሰላም ደኅንነት ሥራ ላይ ያላቸው አጋርነት የሚነጠብ አይደለም፡፡ በማኅበራዊ ዘርፍ እንደ ጤናና ትምህርት ላሉ መስኮች የሚደረግ ድጋፍ፣ ከቀረጥ ነፃ የኤክስፖርት ምርት ማበረታቻ በኩልም የሚደረግ እገዛም አለ፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያስረዱት በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ብዛት ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚደርስ ሲሆን፣ በጣም ውስን የሆኑት ምሁራንና በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የፖለቲካ አመለካከት ጉዳይ የሚስተዋለው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ብዙዎች በአነስተኛ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ፣ በአገር ዕድገትም ረገድ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ የሚታመንባቸውም አሉ፡፡ ከእነዚህ ወገኖች በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ በተለያየ መንገድ ከሚገባው ‹‹ሬሚታንስ›› 2 ቢሊዮን ዶላር (40 ቢሊዮን ብር ገደማ) ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከአሜሪካ ዳያስፖራ የሚገኘው ‹‹ሬሚታንስ›› 80 በመቶ መድረሱ ነው፡፡

ከእነዚህ አሜሪካዊ ጥቅሞች በላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ አገራችን ትኩረት እያደረጉ ያሉ አሜሪካውያን ባለሀብቶች አስተዋጽኦም የሚናቅ አይደለም፡፡ በቅርቡ ከመገናኛ ብዙኃን እንደተከታተልነው አሜሪካ ለአፍሪካ የኃይል ምንጭ ኢንቨስትመንት ከመደበችው ከፍተኛ በጀት በኢትዮጵያ እስከ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ተመድቦ እየተጀመረ ያለ ተግባር አለ፡፡ በሪል ስቴትና በተፈጥሮ ሀብት (ማዕድን) መስክም ሥምሪት እየጀመሩ ያሉ ባለሀብቶች አሉ፡፡

በድምሩ እንደ ደሃ አገር አሜሪካ በፖለቲካ ርዕዮት ፈለጓን አለመከተል መብት ሆኖ ሲያበቃ፣ ማጥላላትና ‹‹ጭራቅ›› አድርጐ ማቅረብ የራሱ ችግር እንዳለው ይሰማናል፡፡ በተለይ በመካከለኛ ደረጃና በክልል ቢሮዎች ያሉ ኃላፊዎች ከገለጻም በላይ፣ የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ብሎ የአውሬ ካርቱን ወደሚስለው የደርግ አካሄድ እየመጡ ይገኛሉ፡፡ ዝቅ ባለው የመንግሥታዊ እርከንም ‹‹…የዚህ ወረዳ የዚህ ቀበሌ ሕዝብ ኒዮሊብራሊዝምን አወገዘ…›› ወደምትል ቀልድ መሰል ወግ እየተወረደ የመጣ መስሏል፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት ጥቅሙን በተለያየ መንገድ ተዟዙሮ ለማስጠበቅም ሆነ የ‹‹ግሎባላይዜሽን›› ተፅዕኖ በመፍራት ይህን ዓይነቱን መካረር አይወደውም ነበር፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ ዥዋዥዌን ከመፍጠርም የራሴ የሚለውን ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሞዴል›› ብቻ በማጥበቅ መገስገስ እንደሚፈልግም፣ በተለያዩ ሰነዶች ይገልጽ ነበር፡፡ አሁን አሁን ካልተዘነጋ በስተቀር፡፡

ለምሳሌ ‹‹የህዳሴ ጉዟችን ውጫዊ ሁኔታ›› (2005) በሚለው አንድ ሰነዱ ጉዳዩን በጥልቀት በመተንተን እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹…አሁንም ቢሆን አሜሪካ ማንም የማይጠጋት ወታደራዊ ኃይል ነች፡፡ ወታደራዊ በጀትዋ በዓለም ያሉ ሌሎች አገሮች ወታደራዊ በጀቶች አይመጣጠኑትም፡፡ በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከቻይና ከአሥር እጥፍ በላይ ሲሆን፣ ቻይና ከአሜሪካ የበለጠ ስፋት ያለው ኢኮኖሚ በምትይዝበት ወቅትም (በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት) የነፍስ ወከፍ ገቢዋ ከቻይና ቢያንስ በእጥፍ መብለጡ አይቀርም፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ረገድ እስካሁን ድረስ አሜሪካን ከሩቅ እንጂ የሚጠጋት አገር የለም፡፡ በዲፕሎማሲና በርዕዮተ ዓለምም መስክ ዋናዋ ተደማጭ፣ ሀብታምና ተደማጭነት ያለው ኢኮኖሚ አላት፡፡ በዚህ እንደሚቀጥልም ይገመታል፡፡ ስለሆነም ሽግግሩ አውሮፓና አሜሪካ ከቁጥር የማይገቡ አገሮች ወደሚሆኑበት የሚደረግ ሽግግር ሳይሆን፣ አሜሪካ ብቸኛ ዋልታ መሆኗ ቀርቶ አንድ ቁልፍ ዋልታ ሆኖ ወደ ምትቀጥልበት ሁኔታ የሚደረግ ሽግግር እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፤›› ይላል ገጽ 4 ላይ፡፡

አሜሪካ ለዘመናት ባከማቸችው የዚህ ዓይነቱ የወታደራዊና የኢኮኖሚ የተሰሚነት አቅም ብቻ ሳይሆን፣ የዲፕሎማሲና የርዕዮተ ዓለም የበላይነት ያውም በአፍሪካ መንግሥታት ልትጠራና ልትሸሽ የምትችል አገር እንዳልሆነች ይታወቃል፡፡ ይሁንና በአሜሪካና በሌሎች ምዕራባውያን መንግሥታት መዳፏ ሥር ያሉት የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ ዓለም አቀፍ ሞጋቾች (አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሲፒጄ፣ ሂዩማን ራይትስ ዎችና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ድርጅቶች) አሉ፡፡ አይኤምኤፍና የዓለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትም የምዕራቡ ዓለም የቀጥታ ትዕዛዝ የተጫናቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በስፖርት መስኮች የሚታወቁ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንኳን ከዚያ የፀዱ አይደሉም፡፡

ይህን ለተገነዘበ ማንኛውም ሰው ቢሆን በጥቂት የብድርና ዕርዳታ አማራጭ ብቻ ወደተረሳው ‹‹ቀዝቃዛው ጦርነት›› በመሄድ ራስን አጣብቂኝ ውስጥ መክተት አደጋ አለው፡፡ ያውም የነቻይና፣ ኮሪያ፣ ታይዋን ልምድም ቢሆን በ‹‹ልማታዊ›› ገጽታ ብቻ እንጂ ፍጹም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ገጽታን ተላብሰው የተጓዙ የኢኮኖሚ ርዕዮት የነበራቸው መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡

በኢትዮጵያ ሁኔታ ካሳለፍነው አስቸጋሪ የውጣ ውረድ የታሪክ ጐዳናም ሆነ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ዴሞክራሲን ለመዘንጋት መሞከር ወደኋላ መመለስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በቅርቡ ለአንድ መጽሔት ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ማብራሪያ የሰጡት የቀድሞ የኦነግ መሪ አቶ ሌንጮ ለታ እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹… ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ልትከተል የቻለችው በኢሕአዴግ በጐ ፈቃደኝነት ሳይሆን፣ ደርግ በተገረሰሰበት ወቅት ከሰባት የሚያንሱ የነፃነት ጥያቄ ያላቸው ድርጅቶች ትጥቅና የሕዝብ ድጋፍ ነበራቸው፡፡ ኦሮሞ፣ ቤንሻንጉል፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሌ…›› እነዚህን ኃይሎች ጨምሮ ሌሎችንም ወደ አሃዳዊ ሥርዓት ለመመለስ መሞከር ለዘመናት የነበረውን የውድቀት ዘመን በመመለስ መባላትን ያስከትላል፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓትን ገንብቶ ዴሞክራሲያዊ አለመሆን ደግሞ ፍፁም ሊታሰብ ካለመቻሉም ባሻገር፣ እንደ ሩሲያ መበታተንን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ በቃል ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ እያለ አስመሳይ ዴሞክራሲያውያንን ለማስቀጠል የሚያደርገው ጥረት የትም ሊደርስ የማይችልና አክሳሪ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ መንግሥትን ወይም ኢሕአዴግን ብቻ መተቸት አይደለም፡፡ የአገሪቱን የፖለቲካ ጉዞ በርዕዮተ ዓለም መንፈስ የሚፈትሽ እንደመሆኑ መጠን ተቃዋሚዎቹንም ይመለከታል፡፡ [በአገራችን የሚገኙ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ብዛት በተለይ በምርጫ ሰሞን ሁልጊዜም የሚያደናግር መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንዱ ከሌላው የሚለይበትና አንድ የሆነበት የማይታወቅ፣ የምርጫ ምልክቱ ብዛት የሚያደናግርና የሚያምታታ ነው፡፡]

ከሁሉ ነጥብ በላይ የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው ከብሔራዊ ጫማ መጫማት ወጥተው ወደ ኅብረ ብሔራዊ መለያ አለመምጣታቸው ብቻ አይደለም የሚያስተቻቸው፡፡ ይልቁንም በርዕዮተ ዓለም ‹‹ወዳጅ›› ፍለጋ ምዕራባውያንን ማምለክ የሚሹ መብዛታቸው ነው፡፡

ኢሕአዴግ ራሱ ተቃዋሚዎች ሕዝቡን በተጨባጭ አማራጭ ከማሳመንና ከጐናቸው ከመሠለፍ ይልቅ ኤምባሲዎች ጋር መመላለስን ያስቀድማሉ ይላቸዋል፡፡ ከነባራዊ ሁኔታ ባፈነገጠ መልኩም ለኤምባሲዎች፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ለሙያ አጋሮች ‹‹የኒዮሊብራሊዝም›› አስተሳሰብን ሳያለምጡ በመዋጥም ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ›› ዓላማቸውን ለማንገሥ ነው የሚሹት ሲል ይወቅሳቸዋል፡፡

በእኔ አስተያየት የኢሕአዴግ ትችት እውነት ያለው ነው፡፡ በተለይ ብዙዎች የ‹‹ሊብራሊዝም›› ርዕዮት አራማጆች ነን በማለት ምሳሌያቸውን ሁሉ እንግሊዝ፣ አሜሪካና ካናዳ ማድረጋቸው ያስገርመኛል፡፡ የሚጠቅሷቸው አገሮች ከሁለት መቶ ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በዴሞክራሲ መንገድ እየወደቁ የተነሱ መሆናቸውን ይዘነጉታል፡፡ ዛሬም ቢሆን በእነዚህ ‹‹አርዓያ›› በሚባሉት አገሮች ያለፍርድ የሚገደሉ ዜጐች (በተለይ በአሜሪካ ጥቁሮች) አሉ፡፡ በምርጫ ለመወዳደር ቢያንስ እስከ 10 ቢሊዮን ዶላር ሀብት መኖር የግድ ነው፡፡ የመራጭነት (በተለይ ሴቶችና ጥቁሮች) ዕድል የተጓደለ ሆኖ እስከ ቅርብ አሥርት ዓመታት የተጓዘ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

እነዚህ ወገኖች የያዙት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚም ሆነ ‹‹ሁሉም ነገር ለገበያ!›› መርህ ከነችግሩ በሙሉ እግሩ የቆመው አሁን ነው፡፡ ያም ሆኖ በቅርቡ በተከሰተ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ ተነቃንቆ ታይቷል፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ደረጃና ሁኔታ ምን የሚወሰድላቸው ቁም ነገር አለ ሳይባል፣ በምዕራቡ ርዕዮተ ዓለም ግድግዳ ላይ ሄዶ መለጠፍ ያለጥርጥር አዋጭ ሊሆን አይችልም፡፡

አደጋው የምዕራብ ጐራ ናፋቂነት የሚያስከትለው በልካችን ያልተሰፋ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እምነት ለመላበስ መሞከሩ ብቻ አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ የቀድሞዎቹ የምሥራቁ ጎራ አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ በራሳቸው ፍልስፍና የተሻለ ፈለግ መከተል የጀመሩትንም በአንድ ቅርጫት ውስጥ በመክተት ባላንጣ አድርጐ የማየቱ አካሄድ ተገቢነት ስለሌለው ነው፡፡

ዓለም ባለብዙ ዋልታ እየሆነች መምጣቷ ይታመናል፡፡ ግሎባላይዜሽን የሚባል የአንድ መንደር አስተሳሰብም አለ፡፡ ስለሆነም ለኢሕአዴግ የሰጠነውን ትችት በተመሳሳይ ለሌላው የፖለቲካ ኃይል ማቅረብ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ትልቅና ኩሩ ሕዝቦች ነን፡፡ የሺሕ ዓመታት የሥነ ሕንፃ፣ የነፃነት ተጋድሎ፣ የሃይማኖትና የባህል መስተጋብራችን ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በውስጥ ፖለቲካና በታሪካችን ላይ ውዝግቡ ባይቆምም፣ የራሳችን እሴቶች በርክተው ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገሩ ዘልቀዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ በአገሪቱ የተፈጠረ ጂኦፖለቲካዊ ሀቅ አለ፡፡ የተነቃቃ የመሰለ ኢኮኖሚያዊ አንድምታና ኢትዮጵያዊ አዲስ ገጽታ መኖሩም አይታበልም፡፡ ስለዚህ እየጠፋ የመጣውን የዓለም ፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ጎራ መልሶ በማንሳት በካምፕ ደረጃ መለጠፍም ሆነ በተቃራኒ ያለ የሚመስልን ከማብጠልጠል ወጥቶ የራስን መለያ (Identity) ይዞ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ባለብዙው ዋልታ ዓለም ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት፣ ተወዳዳሪነትና ኅብረትን ከመሻቱ ባሻገር ግልጽና የማያሻማ መርህና ፖሊሲን ይዞ መገኘትንም ይሻል፡፡

በድምሩ ፖለቲካችን ከርዕዮተ ዓለም ወዳጅ ፍለጋ ወጥቶ በራሱ የቆመ፣ የሁሉንም ወገን ልምድና ተሞክሮ የቀሰመ መሆን አለበት፡፡ ታላቋን ኢትዮጵያን ለመመሥረት ትኩረት የሰጠና የሕዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሊሆንም ግድ ነው፡፡ ካልሆነ ትንሽ ምኞት፣ ያልሠለጠነ አካሄድ፣ ያለልክም በምኞት መኖር ተመራጭ አይሆኑም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

              

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...