ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የዓለም የሕፃናት ቀንን አስመልክቶ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ባዘጋጀው መርሐ ግብር ብሌን ገመቹ የተባለች ታዳጊ የተናገረችው ነው፡፡ ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደው መርሐ ግብሩ የሕፃናት ፓርላማ አባላት የተለያዩ ሚኒስትሮችን እንዲወክሉ የተደረገበት ነበር፡፡ ታዳጊዋ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ሆና ባደረገችው ንግግር፣ የጎዳና ተዳዳሪነት ችግርን ለመቅረፍ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ አንዱ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ጠቁማለች፡፡ ‹‹ሁሌ ወደ ውጪ ልጆችን መላክ ሳይሆን አገር ውስጥ እያንዳንዱ ቤተሰብ አንድ ልጅ ማሳደግ ይችላል፤›› ብላለች፡፡ ከጉዲፈቻ በተጨማሪ የአደራ ቤተሰብ እንደ አማራጭ እንዲወሰድም ጠይቃለች፡፡ ‹‹የአገሪቱ ሕዝቦች ለአገሪቱ ሕፃናት መቆም ይችላሉ፤›› ብላለችም ታዳጊዋ፡፡