Tuesday, September 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹የከፋ የሚባል ቀውስ ቢያጋጥም በጣም ተጋላጭ ነን ብዬ አስባለሁ››

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት ወርቁ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት ወርቁ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሲሆኑ፣ ማኅበሩን ካለፉት አራት ዓመታት ጀምረው በኃላፊነት በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ፡፡ የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት በቅርቡ ለማክበር እየተዘጋጀ የሚገኘው አንጋፋው ቀይ መስቀል ማኅበር፣ ላለፉት 80 ዓመታት ከመንግሥት ጐን በመሆን የአገሪቱ የሰብዓዊ ድጋፍ አካል ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ በቻርተር የተቋቋመ ብቸኛ ሰብዓዊ ማኅበር ሲሆን፣ በአደጋ መከላከልና ምላሽ ላይ ከሚሠራው ዋናው ተልዕኮ ባሻገር በአካባቢና በጤና፣ እንዲሁም በተለያዩ የልማት ተግባራት እስከዛሬ ድረስ በስፋት ተሳትፏል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ሲያጠቋት የቆዩት ድርቅ፣ ጦርነትና የጐርፍ አደጋዎች በዜጐች ላይ ሰብዓዊ ቀውሶችን ሲያደርሱ ማኅበሩ ምላሽ በመስጠት ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ከቅድመ አደጋ መከላከልና ምላሽ መስጠት ጋር ተያይዞ ማኅበሩ በሚያከናውናቸው አደጋን ቀድሞ መከላከል፣ እንዲሁም ምላሽ ከመስጠት አኳያ በአገሪቱ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ፣ አደጋን በመከላከል ረገድ የአገሪቱ ፖሊሲና ተቋማዊ አደረጃጀት፣ አጋሮችን ለማስተባበር አገሪቱ ያላትን አቅምና አሳታፊነት፣ የአደጋ ሥጋቶችንና የመፍትሔ ሐሳቦችን በተመለከተ ዮናስ ዓብይ ከወ/ሮ ፍሬሕይወት ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ከተመሠረተበት ጀምሮ ላለፉት 80 ዓመታት በሰብዓዊ ሥራዎች ሲሳተፍ ይታወቃል፡፡ ከተመሠረተበት መርህ አንፃር አሁን ምን እያከናወነ እንደሆነ ቢነግሩን?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ማኅበራችን የተመሠረተበትን 80ኛ ዓመት በቅርቡ የሚያከብር ሲሆን፣ እኛም ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ እንግዲህ እንደሚታወቀው እንደማንኛቸውም አገር የቀይ መስቀል ማኅበራት ሁሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርም በቻርተር የተቋቋመ ሰብዓዊ ድርጅት ነው፡፡ በዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በቻርተር የተቋቋመ ብቸኛ ሰብዓዊ ድርጅት ሲሆን፣ የመንግሥት ደጋፊ ሆኖ ያሉትን ቀዳዳዎች በመድፈን አጋዥ ሆኖ እየሠራ ይገኛል፡፡ በቻርተር እንደ መቋቋሙ ሰብዓዊ ተግባራትን ሲያከናውን ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባሮች ውስጥ በዋናነት የአደጋ መከላከል ዕርዳታ መስጠት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ኅብረተሰብን ከችግር ለማላቀቅ የሚደረግ እገዛ፣ ክፍተት ባለበት ማንኛውም ቦታ ሁሉ በመገኘት የሚያከናውናቸው ሰብዓዊ ተግባራት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ከተለያዩ አገሮች ወደዚህ ከሚመጡ የቀይ መስቀል እህት ማኅበራት ጋር በአጋርነት ይሠራል፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከዕድሜው አንፃር የሚያከናውናቸውን ተግባራት እየለየ በተለያዩ ዘርፎች ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ይታመናል፡፡ አደጋ መከላከል ዋናው የተቋቋመበት ዓላማው ነው፡፡ በአደጋ ምንም የሚመረጥ ጉዳይ የለም፡፡ ግን ሌሎች ተግባራት ላይ ከልማት፣ ከውኃ ሥራ፣ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የልማት ሥራዎች እናከናውናለን፡፡ እነዚህ ሥራዎች ላይ መርጠን፣ የተለየ ዳሰሳ አድርገንና ለይተን በተወሰኑ ዘርፎች ላይ ግን የምንሠራ ማኅበር መሆን መቻል አለብን፡፡ ሁሉ ነገር ላይ በተበተነ ሁኔታ ብንገባ የአቅም መበተን ስለሚያጋጥም፣ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት እንሳተፋለን፡፡ በአጠቃላይ ማኅበሩ በለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከላይ እንደገለጹት ማኅበሩ ዋና ተግባሩ አደጋ መከላከል ነው፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ በአንድ አደጋ ምክንያት ጉዳት ሲደርስ ዕርዳታ የመስጠት ተግባር ስላለ፣ ዋና ትኩረታችሁ ቅድመ አደጋ ላይ? ወይስ በአደጋ ጊዜ ለዜጐች ዕርዳታ መስጠት ነው የሚቀድመው?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- እንግዲህ ቀይ መስቀል ማኅበር የተቋቋመው አደጋ ከመከላከል ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በጦርነት ወቅት መመሥረቱን ነው ታሪኩ የሚያወሳው፡፡ ሰዎች በጦርነት ወድቀው፣ ቁስለኛ ሆነውና የሚያነሳቸው አጥተው፣ እነዚያን ሰዎች የተመለከተ ባለሀብት እንዴት ሰው እንዲህ ወድቆ የሚያነሳው ያጣል በማለት ዕርዳታ መስጠት አለብን በሚል አስተሳሰብ ነው የተቋቋመው፡፡ ከዚያ በኋላ በስዊድን እንደ አገር ዕውቅና ተሰጥቶት ነው የተጀመረው፡፡ በአገራችን ግን እንደሚታወቀው ትልቁ ችግራችን የነበረው ከድርቅ ጋር የተያያዘው ነበር፡፡ በተለይ በትልቁ ድርቅ ጊዜ የነበረው መንግሥትም ሶሻሊስት ስለነበር ከብዙ የአውሮፓና ከሌሎች አገሮች ጋር ግንኙነት ስላልነበረው፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አገሮችን አሰባስቦ በሰፊው ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ የድርቅ ተጐጂዎችን ከዕርዳታ ማሰባሰቢያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ጋር በመሆን በሰፊው ሲረዳ የነበረ ማኅበር ነው፡፡ ከዚያም የድርቅ ችግሩ ካለፈ በኋላ ሌሎች የዕርዳታ ተግባራትን አምቡላንስ የመስጠትና የመሳሰሉትን ቋሚ ሥራዎች መሥርቶ፣ አጋሮችንና በጐ ፈቃደኞችን በማፍራት አገልግሎቱን እያሰፋና ወደ ክልሎች በመሄድ ሲያገለግል ነው የቆየው፡፡ እንግዲህ ጦርነት በሌለበት ጊዜ የልማት ሥራዎችን፣ አደጋ የመከላከል ሥራዎችን፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ የመከላከል አቅሙን እንዲያዳብር የማንቃት ሥራዎችን ይሠራል፡፡

  ሪፖርተር፡- የመከላከል ሥራችሁ የሚያተኩረው ለአደጋ ተጋላጭነት አለባቸው ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ነው? ወይስ ከልማት ጋር በማቆራኘት በማንኛውም ቦታ ታተኩራላችሁ?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- በአብዛኛው የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን በመክፈት እየሠራን ነው፡፡ የአደጋ መከላከል ሥራዎች ከሌሉ የዝግጁነት ሥራዎች ላይ አተኩረን እንሠራለን፡፡ ኅብረተሰቡን በተለይ ከውኃና ከንፅህና እንዲሁም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተገናኘ እያስተማርን ነው፡፡ ቋሚ ከሆኑ ችግሮች ማለትም እንደ ኤችአይቪና ወረርሽኝ ዓይነቶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ እናስተምራለን፡፡ በተለይ ደግሞ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ከሌሎች እህት ማኅበራት ጋር በመቀናጀትና ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ፣ ለችግር ተጋላጭ እንዳይሆኑ በትኩረት እንሠራለን፡፡ በተጨማሪም የሰው ልጅ ለችግር ተጋላጭ ከሚሆንባቸው ነገሮች መካከል ከኢኮኖሚ አቅም ማነስ ጋር የሚያያዝ አንዱ ይችላል፡፡ የጊዜው የሰው ልጆች ጠላት ድህነት ነው እንደሚባለው ሁሉ፣ ከድህነት ማጥፋት ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን በመተግበር ላይ ነን፡፡ በተለይ ለኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ በሆኑትና በተለይም ሴት እማወራዎች በሚመሩት ላይ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ቢያንስ ለኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ የሚሆኑበትን ሁኔታና ደጋፊ ፕሮጀክቶችን በመለየት ከምንሠራቸው ውስጥ ይካተታል፡፡ ተመሳሳይ ተግባራትን እንዲሁ በማከናወን ላይ ነን፡፡

  ሪፖርተር፡- በተለይ በምትንቀሳቀሱባቸው የልማት ቦታዎች የአደጋ ተጋላጭነታቸውን ደረጃ ለመለየትና የተለየ ጥናት ለማድረግ የራሳችሁ አሠራር አለ? ወይስ በመንግሥት ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ሥፍራዎች ውስጥ ነው የምትሳተፉት?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ተጋላጭነትን በተመለከተ መንግሥትም በራሱ የሚሠራቸው የዳሰሳ ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይም በስፋትና በጥሩ ሁኔታ እየተሠሩ ነው ያሉት፡፡ በራሳችንም በኩል ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና ከእህት ማኅበራት ጋር በመሆን የምንገባባቸው የራሳችን የጥናት መንገዶች አሉን፡፡ ተጋላጭነትን በራሳችን በማጥናት ነው ለከፍተኛ ተጋላጮች የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የምናከናውነው፡፡ በእህት ማኅበራትም በተከናወኑ ጥናቶች መሠረት የምንገባባቸው አሉ፡፡ ምክንያቱም እኛ ከፍተኛ አቅም ላይኖረን ይችላል፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ችግር ያለበት አካባቢና የተጋላጭነቱ ስፋት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበትን አካባቢ በቅድሚያ ነው ትኩረት የምንሰጠው፡፡

  ሪፖርተር፡- ይህ የአደጋ መከላከል ሥራ የብዙዎችን ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥትን ጨምሮ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር እንዴት እየሠራችሁ ነው?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ከዚሁ የአደጋ መከላከልም ሆነ የዝግጁነት ሥራ ጋር በተያያዘ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የጠበቀ አጋርነት አለን፡፡ እነሱ ከተጋላጭነት ጋር የተያያዙ ችግሮችና ክፍተቶች ሲኖሩ ይጠሩናል፡፡ ያሉትን ችግሮች ለይተው ያሳውቁናል፡፡ እኛም ተባብረን እንሠራለን፡፡ በተመሳሳይም ከእሳት አደጋ መከላከል፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሴቶችና ሕፃናት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጋር የአጋርነት ግንኙነት ስላለን በመተባበር እንሠራለን፡፡ እኛ ደግሞ አቅማችን በሚፈቅድልን መጠን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በጐ ፈቃደኞችን በማደራጀት የምንሠራ ሲሆን፣ ከስደተኞች አስተዳደር ባለሥልጣን ጋር በተመሳሳይ በቅንጅት እንሳተፋለን፡፡ በአጠቃላይ ጥሪ ሲደረግልንና አስቸኳይ ምላሽ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ባሉት ክፍተቶች ላይ በቅንጅት አስተዋጽኦ እያደረግን ነው፡፡ ከራሳችን አቅምና ከመንግሥት አቅም በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በፌዴሬሽናችን አማካይነት ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር የገንዘብ ድጋፍ በማሰባሰብ፣ እንደ አደጋው ስፋትና አስቸኳይነት የምንገባበት ሥራ አለ፡፡ በተጨማሪም በተለይ በክልሎች አካባቢ በራሳችን ጥናት የምናያቸውን ክፍተቶች ለመለየት የምንገባበትም አጋጣሚ አለ፡፡

  ሪፖርተር፡- በሥራ ላይ ያለው ቅንጅት አደጋዎችን ከመከላከልም ሆነ የዝግጁነት ተግባርን ከማከናወን አኳያ አመቺ ነው ማለት ይቻላል?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- በእኛ እምነት ሁልጊዜ ሊሻሻል ይችላል የሚል ነው፡፡ የቅንጅት ሥራ በሒደት ይሻላል ባይ ነን፡፡ መንግሥት ተግባራዊ የሚያደርጋቸው አሠራሮች አሉ፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ያሉም እንዲሁ፡፡ ከሌሎችም ተቋማት ጋር ተባብረን እንሠራለን፡፡ በተሻለ መሳለጥ ሊደረግባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት በኩል የእኛን ማኅበር ጠርተው የሚያስገቡበት ጊዜ አለ፡፡ ወይም ሌሎች ድርጅቶችን የሚያስገቡበት አሠራርም አለ፡፡ ነገር ግን በዋናነት አንድ የተጠናከረ የማስተባበር ሥልት ቢፈጠር፣ ሁሉንም በመምራትና የተሳለጠ ማድረግ የሚቻልበት አሠራር ቢኖር የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ካለው በተሻለ የሚሻሻልበት ሁኔታ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ተጋላጭነትን ስናስብ በመንግሥት ደረጃ እየተደረገ ያለው ዝግጅት በተለይም ከተፈጥሮ ተጋላጭነት ጋር የተያያዙ የድርቅ፣ የአካባቢና ሌሎች ሁኔታዎች ጋር ያሉትን ክህሎት እያሳደገና እየተጠናከረ የመጣበት አጋጣሚ አለ፡፡ ምናልባት ክፍተት ሆኖ የሚያሳስብ ነው ብዬ የማስበው ዘርፍ ቢኖር ከከተሞች ዕድገት ጋር በተያያዘ ያለው ነው፡፡ ከከተሞች መስፋፋትና ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጡት ተጋላጭነቶች ያላቸው ቅንጅት የተጠናከረ አይደለም፡፡ ሥጋታቸው እንዲሁ ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡

  ከባድ የሚባሉ እንደ መሬት መንቀጥቀጥ ዓይነት ያሉ አደጋዎች ይቅሩና እንደ እሳት አደጋ ያሉ መለስተኛ አደጋዎች ላይ የቅንጅት ክፍተት እንዳለ ይታያል፡፡ ሁልጊዜም ኢትዮጵያ ያላት አንድ ጠንካራ ጐኗ አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ሁሉም ተረባርቦ መደረግ ያለበትን ለማድረግ ወደኋላ የሚል የለም፡፡ ነገር ግን ባለው አሠራር በሚፈለገው ደረጃ ወጥ የሆነ ዘዴ አለ ወይ የሚለውን ስናየው ራሱን የቻለ ጉድለት አለበት፡፡ አንድ ችግር ሲፈጠር ማንን ነው የሚመለከተው? ማንስ ነው በቅድሚያ የሚጠየቀው? የሚባሉት ሲፈተሹ ሁሉም እንደየዘርፉ መሰባሰቡና ተጠናክሮ መሥራቱ ላይ ግልጽ የሆነ ክፍተት አለ፡፡ በእርግጥ ባለፈው ዓመት ከዚሁ ከአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጋር በተያያዘ አዲስ ሕግ ለማውጣት መሞከሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከከተማ ተጋላጭነት ጋር በተያያዘ አሁንም ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ለዚያም ነው ተጠናክሮ የመሥራቱን አስፈላጊነት የማስበው፡፡

  ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንደገለጹት በከተሞች ከሚኖረው ተጋላጭነት ባሻገር ባለፉት አሥር ዓመታት ብቻ ብንመለከት ከፍተኛ የጐርፍ አደጋ፣ ድርቅና መጠነ ሰፊ የእሳት አደጋ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡ ምናልባት ለወደፊት ከእነዚህ የባሱ አደጋዎች ቢከሰቱ፣ አሁን እየተከናወኑ ያሉት የቅድመ ዝግጁነት ተግባራት አደጋዎችን ለመቀነስ በቂ ናቸው ተብሎ ይታሰባል?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- አሁንም ቢሆን አደጋ ቢፈጠር ተረባርቦ የመሥራቱ ነገር ይኖራል፡፡ መቼም ቢሆን፡፡ በደንብ በተቀናጀ መንገድ ከተሠራ የተሻለ አቅም ሊኖረን ይችላል፡፡ አሁን በከተማ ውስጥ አንዱ ችግር የእሳት አደጋ ነው፡፡ የአምቡላንሶች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የእሳት አደጋ መከላከል ጣቢያዎች ቁጥርም እንዲሁ እየተስፋፋ ነው፡፡ በከተማ ተጋላጭነት ጉዳይ የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልም እየተሳተፈ ነው፡፡ ከከተማው ስፋትና ከመሠረተ ልማት ግንባታዎች ፍጥነት አንፃር ሲታይ ግን፣ ያለው የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ተግባር በፍጥነት እየሄደ አይደለም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለዚህ የከፋ የሚባል ቀውስ ቢያጋጥም በጣም ተጋላጭ ነን ብዬ እሰጋለሁ፡፡ እሳት ከሆነ ምናልባት ልናጠፋው እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ዋናው የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ከሆነ የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ምናልባትም በቅርቡ እየተፈጠሩ ያሉት አደጋዎች ማሳያ ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ የከተማው መጨናነቅ እንዲሁም የመንገድ ግንባታውና ተያያዥ ችግሮች ለአደጋ በፍጥነት ምላሽ መስጠቱን አዳጋች ያደርጉታል፡፡ በተጨማሪም የትራፊክ ሕጉና የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ራሱ ሌላው ችግር ነው፡፡ አምቡላንስ ሲጮህ እንኳ አሽከርካሪዎች መንገድ እንደማይለቁ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ በተመሳሳይም የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪ በምን ዓይነት ፍጥነት ነው ደርሶ ምላሽ መስጠት የሚችለው? ከዚያ አንፃር በከተሞች ላይ ተጋላጭነት አለ የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- አደጋ በሚያጋጥምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከአጋሮች በኩል ያለው የማስተባበር ሁኔታ እንዴት ይታያል?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ከዚህ ከአደጋ መከላከል ጋር እነዚህን ሁሉ አስተሳስሮ ለመምራት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ለአደጋ መከላከል ሥራ የሚረዳ ረቂቅ ሕግ እየተዘጋጀ ይመስለኛል፡፡ ያስፈልጋል የግድ ነው፡፡ ከማስተባበር አንፃር እንደተነጋገርነው ሁሉም የየራሳቸው ኃላፊነት ኖሯቸው፣ ግን አንድ አደጋ በሚፈጠርበት ጊዜ ተጠራርተውና ተረዳድተው የመሥራት ነገር አለ፡፡ ነገር ግን የሕግ ማዕቀፍ ኖሮት ተጠናክሮ የሚመራው ወይም ደግሞ በድንገተኛ አደጋ ጊዜ የሚመራው እከሌ ነው ተብሎ በግልጽ መቀመጥ የግድ ይላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ይኼ በጣም ወሳኝ ቦታ ስለሆነ፣ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ተፈላልጎ ማሰባሰብና ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አደጋው የሚያመጣውን ጉዳት ለመቀነስ በተሻለ ማስተባበር በሚችል አካል እንዲመራ የሚያደርግ አካሄድ ሊኖር ያስፈልጋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከአምቡላንሶችና ከሌሎች ፈጣን ምላሾች ጋር በተገናኙ ሥራዎች ላይ በትራፊኩ በኩል ያለው ችግር ምንድነው?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- ትልቁ እንደ ክፍተት የማየው ይኼ ነው፡፡ እኔ ራሴ በየጊዜው መንገድ ላይ ስለማይ ነው፡፡ በውጭ አገሮች እንደምናየው አንድ መንገድ ላይ የአምቡላንስ መስመር ተለይቶ ይገነባል፡፡ አንድ አምቡላንስ መሄድ ካለበት ሌላ መኪና በዚያ መስመር አይሄድም፡፡ አምቡላንስ በሚመጣበት ጊዜ ሁሉም ቀኛቸውን ይዘው አምቡላንስ ማሳለፍ ወይም መቆም አለባቸው፡፡ ይህ ሲባል እዚህ እንደዚህ መንገድ ተጨናንቆ ተሽከርካሪዎች በሚቆሙበት ጊዜ አምቡላንስ ሲመጣ እንዴት ነው የሚያሳልፉት? እዚህ አምቡላንስ የሚያልፍበት መንገድ ሲያጣ ነው የማየው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አምቡላንስ በመመለሻ መንገድ ይሄዳል፡፡ አንድ ነገር ማድረግ አለብን ተብሎ የማስፈጸሙ ነገር በስፋት አይታይም፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ ጠንካራ አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብለን እንደገለጽነው በከተማችን ካለው ተጋላጭነት አንፃርም እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በጣም በጣም ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ የመኖርና ያለመኖር ነገር ሊሆኑ ስለሚችሉ ማለት ነው፡፡ ከዚያ አንፃር ክፍተት አለ፡፡

  ሪፖርተር፡- አሁን ያለውን ፖሊሲ በመከለስ አዲስ አደረጃጀት ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- እንግዲህ ቅድም ብለነዋል፡፡ በተደጋጋሚ የሕግ ማዕቀፉን በተመለከተ ወጥ መሆን አለበት፡፡ አደጋን የመከላከልና ያንን ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ መንግሥት የሚመራው ሆኖ፣ ዋና ዋና የሚባሉ ተዋናዮችንና የአገር ውስጥ ሰብዓዊ ድርጅቶች የተባሉትን የሚያቅፍ አሠራር መፍጠር መቻል አለበት፡፡ ተጋላጭነት በሚኖርበት ጊዜ እነዚያ ዋና ዋና ተዋናዮች በምን ሁኔታ ነው የሚመጡት? ምንድነው የሚጠበቅባቸው? ምንድነው ማድረግ ያለባቸው? የሚለው ከታወቀ እነዚያ ተዋናዮች አቅማቸውን በዚያ ደረጃ ይገነባሉ፡፡ አንድ ነገር በሚፈጠርበት ጊዜ የማይተባበር አካል አይኖርም፡፡ ክፍተቱም ይዘጋል ማለት ነው፡፡ ለሁሉም የተለያየ ኃላፊነት ከተሰጠው በአደጋ ጊዜ ሁሉም በዚያ ደረጃ አቅም በመገንባት ሁኔታ ስለሚሠራ የሚረዳ አካሄድ ይሆናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ መንግሥት እንደ መዋቅርም ሆነ እንደ ሕግም ይህንን ቀርጾ የተቀናጀ አደጋ የመከላከል አቅም መፍጠር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እንግዲህ ሕጉ የተወሰነ ተጀምሯል፡፡ እሱ ግን መጠናከርና መቀናጀት አለበት፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚህ ረገድ ከመንግሥት ጋር በመቀራረብ ሁሉም አካላት የሚወዳደሩበትንና ሐሳብ የሚዳብርበት አስፈላጊነትን እንዴት ያዩታል?

  ወ/ሮ ፍሬሕይወት፡- እንግዲህ አሁን ባለው አካሄድ ሳየው ብዙ ጊዜ ሕጎች ሲረቀቁ ግብዓት ይጠየቃል፡፡ ግብዓት የመስጠቱ ነገር የሁላችንም አቅም እስከፈቀደ ድረስ ክፍተት አለ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁልጊዜ ሕጎች ሲረቀቁ በኋላም ለምክር ቤቱም ሲቀርቡ ግብዓት ይጠየቃል፡፡ ስለዚህ ያገባኛል የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል እንደዚህ ዓይነት ሕጎች በሚረቀቁበት ጊዜ ያሉትን ክፍተቶች አጠናክሮ ለመንግሥት እነዚያን ግብዓቶች መስጠት ከቻለ ብዙ ነገር መሥራት የሚቻል ይመስልኛል፡፡ እኛም ዝግጁ ሆነን መከታተል መቻል አለብን፡፡ አንደኛ ሕጎቹም ሲቀረፁ ክፍተቶች ስላሉ በእኛ በኩል መንቀሳቀስ አለብን፡፡ በመንግሥትም በኩል መከታተል አለብን፣ ማቅረብ አለብን፡፡ ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት በኩልም በሩን መክፈትና ያንን ዕድል መፍጠርም አስፈላጊ ይሆናል ማለት ነው፡፡

   

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹ነዳጅ በዋጋ ጭማሪ ምክንያት አቅርቦቱ ዝቅተኛ ስለሆነ አማራጮችን መፈለግ አለብን›› መንግሥቱ ከተማ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ

  ከስድስት ወራት በፊት በሁለቱ የአውሮፓ አገሮች በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት ሲጀመር፣ የዓለም ኢኮኖሚ እያገገመ ከነበረበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ለመላቀቅ እየተፍጨረጨረ ነበር፡፡ ሆኖም ጦርነቱ የዓለም...

  ‹‹የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቢኖሩ ግጭቶች ላይከሰቱ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ ይሆን ነበር›› አቶ ፋሲካው ሞላ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር

  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ከአራት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ ሪፎርም ካደረገባቸው የዴሞክራሲ ተቋማት መካከል ቀዳሚው የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፉን የሚመራው ባለሥልጣን...

  ‹‹በንግድ ሕጉ የተናጠል ክሶችን ማቋረጥ አንዱ ዓላማ ብክነትን ለማስቀረት ነው›› አቶ ፍቃዱ ጴጥሮስ፣ የሕግ ባለሙያ

  ኢትዮጵያ ከ60 ዓመታት በኋላ የንግድ ሕጓን አሻሽላለች፡፡ የተሻሻለው የንግድ ሕግ ሦስት መጻሕፍት ታትመው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ይህ የንግድ ሕግ ኢትዮጵያ ከወቅቱ ዓለም አቀፋዊ ነባራዊ...