– ጃፓን ለጭነት መቆጣጠሪያ መቶ ሚሊዮን ብር ለገሰች
የፈረንሳይ ልማት ኤጀንሲ ሚያዝያ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት የሃምሳ ሚሊዮን ዩሮ ወይም የ1.07 ቢሊዮን ብር ቀላል ብድር ሰጠ፡፡ በመሆኑም ፈጣን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት በአዲስ አበባ ለማስጀመር የሚውለው ይህ የብድር ገንዘብ፣ በሙከራ ደረጃ ከዊንጌት እስከ ጎፋ ገብርኤል ባለው መሥመር ላይ እንዲሁም ከጎፋ ገብርኤል እስከ ጀሞ ባለው መስመር ላይ የሚተገበር ይሆናል፡፡
በሚስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሺዴና በኤጀንሲው የአካባቢ ኃላፊ ክርስቲያን ዮካ የተፈረመው የብድር ስምምነት፣ ከፋይናንስ አቅርቦት በተጨማሪ የቀላል ባቡር ትራንዚትን ከሕዝብ ትራንስፖርት ኔትወርክ ጋር፣ ፈጣን የከተማ አውቶቡስ አገልግሎትን ከመደበኛው የአውቶቡስ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት እንዲሠራ የሚያስችል የቴክኒክ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር፣ በረጅም ጊዜ ውስጥ ከምድር በታች ለሚዘረጉ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ታሳቢ የሚሆን ድጋፍ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
የፈረንሳይ መንግሥት ዓምና ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ተርሚናል ግንባታ የሚውል የሃምሳ ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የጃፓን መንግሥት ከአዲስ አበባ ዓባይ በረሃን አቋርጦ እስከ ደብረ ማርቆስ በሚዘረጋው መንገድና በዓባይ ድልድይ ግንባታን በማካሄድና የፋይናንስ ዕርዳታ በመስጠት አስተዋጽኦ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ከተፈቀደ የጭነት ወሰን በላይ በመጫን ዕቃ የሚያጓጉዙ ከባድ ተሽከርካሪዎች በመንገዶች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ይውላል የተባለውን የአንድ መቶ ሚሊዮን ብር ዕርዳታ ጃፓን መስጠቷን ይፋ አድርጋለች፡፡
የጃፓን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ ስምምነቱን ሚያዝያ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ፈርመዋል፡፡ ከመጠን በላይ በጫኑ ተሽከርካሪዎች ሳቢያ መንገዶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት አሳሳቢ ነው ያሉት አምባሳደር ሱዙኪ፣ ጃፓን በምትለግሰው መቶ ሚሊዮን ብር ወይም አምስት ሚሊዮን ዶላር፣ የተሽከርካሪዎችን የጭነት መጠን በዘመናዊ መሣሪያ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡
ሥራ ላይ ይውላል የተባለው ቴክኖሎጂ ከጭነት ቁጥጥር ባሻገር፣ የትራፊክ መጨናነቅን ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን፣ የመኪኖችን የጭነት ልክ ለመለካከትም አሥር ሰከንድ ብቻ እንደሚወስድበት ታውቋል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን የመንገድ ሎጂስቲክስ የሚያሻሽል አሠራር ለመዘርጋት ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከመንገድ ጥገና ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ እድሳት የተደረገለትና ከአዲሱ ገበያ እስከ ደብረ ማርቆስ 988 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋው መንገድን ጨምሮ 303 ሜትር ርዝመት ያለው የዓባይ ድልድይና የአዋሽ ድልድይ ይጠቀሳሉ፡፡ ትልልቅ ከሆኑት ከእነዚህ ድጋፎች ባሻገር የጃፓን መንግሥት በጂኦተርማል ኃይል መስክ ድጋፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ ጥናት ከማካሄድ ባሻገር፣ የጂኦተርማል ልማት ማስተር ፕላን እንዲዘጋጅም ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡