Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ለሕፃናት በሕፃናት››

‹‹ለሕፃናት በሕፃናት››

ቀን:

ለወትሮው ሕፃናትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ሲደረግ፣ አዋቂዎች ተሰባስበው ይመክራሉ፡፡ ሕፃናትን ይገጥሟቸዋል ብለው ላመኑባቸው ችግሮች የመፍትሔ ሐሳቦች አስቀምጠውም ይለያያሉ፡፡ ሕፃናት፣ በአዋቂዎች የተደነገገላቸውን  ያለ ጥያቄ ተቀብለውም ይዘልቃሉ፡፡ የዘንድሮው የዓለም ሕፃናት ቀን ይኼንን የዘልማድ አካሄድ ለመለወጥ ያለመ ነበር፡፡

የዓለም ሕፃናት ቀን በተለያዩ አገሮች በተለያየ ቀን ተከብሮ ይውላል፡፡ ኢትዮጵያም በብዙኃኑ ዘንድ የሚከበርበትን ኅዳር 11 ተቀብላ ቀኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ተከብሯል፡፡ ‹‹አክሽን ፎር ችልድረን ባይ ችልድረን›› በሚል መሪ ቃል የተከበረው የዘንድሮ የዓለም ሕፃናት ቀን በኢትዮጵያ ዐውድ ‹‹ለሕፃናት በሕፃናት›› ተብሏል፡፡

መሪ ቃሉ እንደሚያመለክተው፣ በቀኑ ሕፃናት ጉዳዮቻቸውን ለይተው እንዲወያዩባቸው እንዲሁም ለሚገጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ ድርሻ እንዲኖራቸው ዕድል ተሰጥቷል፡፡ ለችግሮቻቸው የመፍትሔ ሐሳብ ከመጠቆም ባሻገር፣ ከውሳኔ ሰጪ አካላት ጋር ፊትለፊት በመገናኘት ሐሳቦቻቸው ተቀባይነት ማግኘታቸውን እንዲያረጋግጡ ለማድረግም ተሞክሯል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ለሕፃናት በሕፃናት›› የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲከበር ሕፃናት ለተለያዩ ዘርፎች እንደ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ሆነው ጥያቄ እንዲሰነዝሩ ተደርጓል፡፡ ሕፃናቱ በሚኒስትሮቹ ቦታ እንደሆኑ በማስመሰልም ለችግሮቻቸው መፍትሔ የሚገኝበትን መንገድ እንዲያመለክቱ ተደርጓል፡፡

ከሕፃናት ፓርላማ የተውጣጡ ታዳጊዎች፣ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ፣ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎችም መሥሪያ ቤቶች ‹‹ሚኒስትር›› ሲሆኑ፣ ሕፃናት ተኮር ችግሮችን በምን መንገድ እንደሚፈቱ ተናግረዋል፡፡ ሰባት መሥሪያ ቤቶችን የወከሉት ሰባት ሕፃናት በዋነኛነት ከጠቀሷቸው ችግሮች መካከል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የጉልበት ብዝበዛና ጎዳና ተዳዳሪነት ይገኙበታል፡፡

በርካታ ሕፃናት ዕድሜያቸው ሳይደርስ ስለሚዳሩ ትምህርት የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው፡፡ ባላቻ ጋብቻ ምክንያት ከወሊድ ጋር ለተያያዙ ውስብስብ የጤና እክሎች የሚጋለጡ ሴት ሕፃናት ቁጥርም ከፍተኛ ነው፡፡ ታዳጊዎችን ከትምህርት የሚያሰናክሉ ችግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ሕፃናቱ እንደተናገሩትም፣ ትምህርት ቤቶችን ከማስፋፋት ጀምሮ፣ ታዳጊዎች ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙም መሠራት አለበት፡፡

ሕፃናት በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ቢኖሩ የንፁህ የመጠጥ ውኃ ተደራሽነት ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ተቋሞች ብቻ ሳይሆን በገጠራማ አካባቢዎችም የጤናና ትምህርት ተቋሞች መስፋፋት አለባቸው ብለዋል፡፡ ሕፃናት ላይ ብቻ አተኩረው የሚያገለግሉ የሕክምና መስጫዎች መበራከት አለባቸው፡፡ ሕፃናት የሚጫወቱባቸው ንፁህ የመዝናኛ ቦታዎችና ክፍት አካባቢዎች ጉዳይም ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሕፃናትን በሚመለከቱ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች ሕፃናት ያላቸው ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት ተመልክቷል፡፡ ከነዚህ መካከል ሕፃናትን ያማከለ የፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ታዲጊዎቹ አስረድተዋል፡፡ በተለያየ ዘርፍ ሕፃናት ከሚገጥሟቸው ችግሮች መካከል የጎዳና ተዳዳሪነትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ደሚቱ ሒምቢሳ፣ በሕፃናት ጉዳዮች በትኩረት ከሚሠራባቸው መካከል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው ብለዋል፡፡ ጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን ከቤተሰቦቻቸው በማቀላቀል ወይም በሌላም መንገድ ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻልም ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሕፃናት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ሕፃናት በራሳቸው ጉዳይ መሳተፍ አለባቸው፡፡ የሚሠራው ሥራ የነሱን ፍላጎት መመርኮዝ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ የሕፃናትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚከናወኑ ሥራዎች የአንድ ወቅት ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣይነት ያላቸው እንዲሆኑም አሳስበዋል፡፡ ቀጣይነት ያለው ሥራ እውን ሊሆን የሚችለው ደግሞ ሕፃናትን ማሳተፍ ሲቻል ብቻ መሆኑም ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ ከተለያዩ ሚኒስትሮች በተውጣጡ ኃፊዎች ቦታ ስለ ሕፃናት ጉዳይ አስተያየት የሰጡ ታዳጊዎችም በአገራዊ ጉዳዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ በሕፃናት ምክር ቤቶችና በሕፃናት ፓርላማ እንዲሳተፉና ሐሳቦቻቸው ተሰሚነት እንዲያገኙም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ከሕፃናት ቀን ጎን ለጎን የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ 65ኛ ዓመትም በዕለቱ የተከበረ ሲሆን፣ ተቋሙ በሕፃናት ጉዳዮች ያደረገውን እንቅስቃሴ የሚዳስስ መጽሐፍም ተመርቋል፡፡ የዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ተወካይ ጁሊያን መልሶፕ፣ ባለፉት ዓመታት የሕፃናትን መብት የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎች በመተግበር በኩል የታየውን ለውጥ ጠቅሰዋል፡፡ በሕፃናት ጉዳዮች የሕፃናት ተሳትፎ ሲያደርግ የበለጠ ርቀት መጓዝ እንደሚቻልም አመልክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉት ተመራማሪ አንጅላ ሬቨን፣ የዩኒሴፍን መጽሐፍ የጻፉ ሲሆን፣ ‹‹ልጆች ዝም በሉ ከሚባልበት ጊዜ አልፎ ጥያቄ የሚጠይቁበትና በጉዳዮቻቸው የሚሳተፉበት ጊዜ መጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...