Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአለ በጅምላ አምስተኛ ቅርንጫፍ በሐዋሳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአሥራ አምስት ቀናት በፊት ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በሻሸመኔ የከፈተው አለ በጅምላ፣ ሁለተኛው ቅርንጫፉ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ይከፈታል፡፡ ከአለ በጅምላ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የተለያዩ የክልል ከተሞች ለማስፋፋት በያዘው ውጥን መሠረት፣ በሐዋሳ ቅርንጫፉን ከከፈተ በኋላም በመቀጠል ሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ደግሞ በባህር ዳር ቅርንጫፉን ይከፍታል፡፡

በሚቀጥለው ወር በባህር ዳር ይከፈታል ተብሎ የሚጠበቀውን ቅርንጫፉን ጨምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያሉትን ቅርንጫፎች ቁጥር ወደ ስድስት ያሳድግለታል፡፡

በየወሩ የሽያጭ መጠኑን በመጨመር ላይ ያለው አለ በጅምላ፣ የሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅትን (ጅንአድ) ሥራ በመረከብ አገልግሎቱን እያስፋፋ እንደሚሄድና በሌሎች የክልል ከተሞች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለመክፈት ውጥን እንዳለው ታውቋል፡፡ በቅርቡ ተጨማሪ ቅርንጫፎች ይከፈቱባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ከተሞች ውስጥ መቐለና ደሴ ይገኙባቸዋል፡፡ አለ በጅምላ አሁን ለቸርቻሪዎች ከሚያቀርባቸው ምርቶች በተጨማሪ፣ በቅርቡ ሌሎች የምርት ዓይነቶችን እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓትና የተረጋጋ የሸቀጥ ገበያ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ የቆየው ጅንአድ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በሚል በመቀየሩ፣ እስካሁን ሲያስመጣቸው የነበሩ ምርቶችን አለ በጅምላ እንዲረከበው የሚደረግ ስለመሆኑም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት በሚል እንደ አንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት እንዲንቀሳቀስ የተወሰነው አዲሱ ድርጅት ተጠሪነቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይሆናል፡፡ አዲሱ ድርጅት የተለያዩ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን በማሰራጨት ሥራ ላይ ይሰማራል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ድርጅቱ በሽግግር ሒደት ላይ ሲሆን፣ ቀድሞ ጅንአድ የሚሠራቸውን ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል፡፡ የሽግግር ጊዜው ሲያበቃ ግን በቀድሞ ጅንአድ በኩል ሲሠራጩ የነበሩ እንደ ዘይትና ስኳር እንዲሁም የተለያዩ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን አለ በጅምላ በማስመጣት ያሰራጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ ዘይት ያሉ ምርቶችን የማስመጣቱንና የማከፋፈሉን ሥራ አለ በጅምላ ተረክቦ እንዲሠራ መንግሥት ፍላጎት ማሳየቱን የአለ በጅምላ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑረዲን መሐመድ ይገልጻሉ፡፡ ከአለ በጅምላ ሌላም በዘይትና ስኳር ሥርጭት ውስጥ የግል ኩባንያዎች እንዲገቡ የማድረግ ዕቅድ እንዳለ የአቶ ኑረዲን ገለጻ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ግን ምንጮች እነዚህ የግል ኩባንያዎች ራሳቸው ከውጭ አስገብተው ያከፋፍላሉ? ወይስ መንግሥት ያስመጣውን ዘይት ተረክበው ያከፋፍላሉ? የሚለው ጉዳይ ውሳኔ አለማግኘቱን ይናገራሉ፡፡ ይህ ሥራ ለሁሉም ኩባንያዎች ክፍት ይሁን? ወይስ ከዚህ ቀደም በሥራው ላይ ልምድ ላላቸው ኩባንያዎች ብቻ ክፍት ይሁን? የሚለውም ጉዳይ እስካሁን ውሳኔ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አለ በጅምላ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የከፈታቸው አብዛኛዎቹ ቅርንጫፎች የሚገኙት በጅንአድ ይዞታዎች ላይ ነው፡፡ ወደፊትም የሚከፈቱት የአለ በጅምላ ቅርንጫፎች የጅንአድ ይዞታዎችን ይጠቀማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የኢንዱስትሪ ግብዓት ምርቶችን የሚያሠራጭ በመሆኑ፣ አንዳንድ ይዞታዎቹን ከአለ በጅምላ ጋር በመጋራት ይሠራበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እስካሁን ግን በቀድሞ ጅንአድ ይዞታ ሥር ያሉ ንብረቶችና ይዞታዎች ባለቤትነትን ጉዳይ አስመልክቶ የመንግሥት ውሳኔን የሚጠይቅና ወደፊት የሚታወቅ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ጅንአድ በመላ አገሪቱ 82 ቅርንጫፎችን ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አለ በጅምላ ባለፉት አሥር ወራት ውስጥ ከ164 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ ማከናወን የቻለ ሲሆን፣ ምርቱን ተረክበው የሚያሠራጩ ነጋዴዎች ደግሞ ከ2,500 በላይ ደርሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች