Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕብር ስኳር በተደጋጋሚ የከለሰውን የግንባታ ፕሮጀክት ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕብር ስኳር ከብረታ ብረትና ኢንጂንሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የስኳር ፋብሪካና የሸንኮራ አገዳ መስኖ እርሻ ሥራዎችን ለማከናወን መግባቢያ ሰነድ የፈረሙት ከአንድ ዓመት በፊት፣ በመስከረም ወር 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ በስምምነታቸው መሠረት የመከላከያው ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር ከ250 ሚሊዮን ዶላር ባነሰ ወጪ የስኳር ፋብሪካ ሊገነባለት የሚችልበትን የመግባቢያ ሰነድ ፈርሞም ነበር፡፡

ከአንድ ዓመት በኋላ የተፈረመው የሥራ ውል ስምምነት ግን ወደ 165 ሚሊዮን ዶላር ቀንሶ በአንፃሩ የሚገነባው ፋብሪካ በቀን ስድስት ሺሕ ቶን አገዳ ይፈጫል ተብሎ የሚታሰብ ነው፡፡

ከዓመት በፊት የተፈረመው ስምምነት ሲደረግ ተገልጾ የነበረው ለስድስት ወራት እንደሚቆይና በሁለቱ ወገኖች መካከል የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት እንደሚጀመር፣ በሦስት ዓመታት ውስጥም የፋብሪካው ግንባታ እውን እንደሚሆን ነበር፡፡ ይሁንና ከአንድ ዓመት መዘግየት በኋላ፣ የመግባቢያ ስምምነቱ ወደ መጨረሻው የሥራ ውል ስምምነት መሻገሩን የሚያመለክት ሥነ ሥርዓት ሚያዝያ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ተካሒዷል፡፡ ስምምነቱም በ165 ሚሊዮን ዶላር ሊገነባ የሚችል ፋብሪካ እውን ያድርጋል ተብሎለታል፡፡

ከዚህ ቀደም በምሥረታው ወቅት ያቀረበውንና በቀን ከ12 ሺሕ ቶን በላይ አገዳ የሚፈጭ ፋብሪካ መገንባት ላይ የተመሠረተውን የቢዝነስ ሐሳብ በማሻሻል ካለፈው ዓመት ጀምሮ የሚታሰብ ሆኖ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደሚገነባ የሚጠበቀው፣ በቀን 4,800 ቶን የሸንኮራ አገዳ የሚፈጭ ፋብሪካ ሲሆን፣ ለዚህ ሥራ 2.2 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሎ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት መቶ ሚሊዮን ብር ከባለአክሲዮኖች የሰበሰበው ሕብር ስኳር ግን ይህንን ያህል ገንዘብ የለውም፡፡ ገንዘቡን ለማሰባሰብ አማራጭ አድርጎ ያቀረበው የፋይናንስ ምንጭ ደግሞ ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ የውጭ ኩባንያዎችን በባለድርሻነት በማስገባትና ለሌሎችም ባለድርሻዎች አክሲዮን በመሸጥ ካፒታሉን ማሳደግ ነበር፡፡ ይህንኑ በማስመልከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር የቦርድ አመራሮችም ይህንኑ ይገልጻሉ፡፡

ሕብር ስኳር በአሁኑ ወቅት ያሰባሰበው አጠቃላይ ካፒታል ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር ያነሰ ቢሆንም፣ ብርታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ግን የፋብሪካ ግንባታውን ለማካሔድ ዝግጁ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የሕብር ስኳር ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ደምሴ ከሪፖርተር ተጠይቀው እንዳብራሩት፣ ሕብር ስኳር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ለፋብሪካ ግንባታና ለመስኖ እርሻ ሥራ የሚለውን መሬት ያስረክባል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በራሱ ዲዛይን አማካይነት ይገነባዋል ተብሎ የሚታሰበው ፋብሪካ፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ካጠናቀቀው የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተሰምቷል፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሚካኤል ደስታ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ሕብር ስኳር ለግንባታው የሚያስፈልገው ገንዘብ ባይኖረውም፣ ወደፊት አክሲዮን ሸጦ ያሟላል፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ ወደፊት በሚታሰብ ዕዳ ፋብሪካውን ይገነባል ብለዋል፡፡

‹‹እነሱ [ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን] ገንዘብ እንደሌለን ያውቃሉ፡፡ ባለው ገንዘብ ሥራውን ለመጀመር ስምምነት አድርገናል፤›› ያሉት የሕብር ስኳር ዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ጥላዬ ካሳሁን ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለግንባታ የሚሆነው መሬት በአፋጣኝ እንዲሰጠው መጠየቁንም ገልጸዋል፡፡ እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስም የፋብሪካ ግንባታ ቦታ መለየት፣ ቅየሳ ማካሔድ፣ ለፋብሪካ ገጠማ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማምረትና ማሽነሪዎችን ማጓጓዝ ኮርፖሬሽኑ ያከናውናቸዋል ተብለው የሚጠበቁ ሥራዎች ናቸው ተብሏል፡፡

ዶ/ር ጥላዬ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የመግባቢያ ስምምነቱን ወደ ሥራ ውል ስምምነት ለማምጣት መዘግየቱ የታየው በሁለቱም ተዋዋዮች በኩል ነበር፡፡ በሕብር ስኳር በኩል የአደረጃጀት ችግሮችን ከማስተካከል ባሻገር ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጮችን መፈለጉ ጊዜ ወስዶበታል ተብሏል፡፡ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኩል ደግሞ እየገነባቸው በነበሩት የኩራዝ፣ የጣና በለስና ሌሎችም ፋብሪካዎች ሥራ ላይ ተጠምዶ በመቆየቱ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ከአንድ ዓመት በፊት ከሕብር ስኳር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሲፈርሙ ለጋዜጠኞች ገልጸው እንደነበረው፣ Anchorፋብሪካውን ለመንባት የኮርፖሬሽኑ ተፎካካሪዎች ከ360 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚጠይቁ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ ግን የሕብር ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት የተሟላ መሣርያና አቅም ስላለው ባነሰና በርካሽ ዋጋ ሊገነባው እንደሚችል አስታውቀው ነበር፡፡ 

ሆኖም የሕብር ስኳር ፍላጎትን ተከትሎ የሚካሄደው ግንባታ 250 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ የሚችልባቸውን ነጥቦች የገለጹት ሜጀር ጄነራል ክንፈ፣ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ሆኖ በአማራ ክልል አዊ ዞን፣ ጃዊ ወረዳ፣ በጣና በለስ ተፋሰስ ውስጥ የሚገነባውን ፋብሪካ በርቀት መቆጣጠር የሚፈለግ ከሆነ፣ የሚያመርተው ስኳር የተጣራና የአውሮፓ ደረጃን እንዲያሟላ የሚፈለግ ከሆነ፣ የሚገለገልበት ጀነሬተር 60 ሜጋ ዋት ኃይል የሚፈልግ (እስከ 30 ሜጋ ዋት ሊወርድ ይችላል) ከሆነና ሙሉ ለሙሉ አውቶሜትድ እንዲሆን ካስፈለገ፣ የስኳር ፋብሪካው የግንባታ ወጪ ወደ 250 ሚሊዮን ዶላር ሊጠጋ እንደሚችል አብራርተው ነበር፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በተደረው ስምምነት ግን 165 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጀውን የሕብር ስኳር ፋብሪካ ለመገንባት፣ ወደፊት ይመጣሉ ተብለው ከሚታሰቡ የውጭ ኢንቨስተሮችና ከባንክ ብድሮች ለማሟላት እንደሚታሰብ ዶክተር ጥላዬ ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በግንቦት ወር 2001 ዓ.ም. የተመሠረተው ሕብር ስኳር በወቅቱ በስድስት መቶ ሺሕ ብር ካፒታልና በ30 ሰዎች በአክሲዮን ማኅበርነት ሲቋቋም፣ በአገሪቱ የስኳር ፋብሪካ ለመገንባት፣ ከሚያመርተው ውስጥ 50 ከመቶውን ለአገር ውስጥ የተቀረውን 50 ከመቶ ለውጭ ገበያ ለማዋል፣ በቀን 12,500 ቶን አገዳ በቀን የሚፈጭ ፋብሪካ ለመገንባት ወጥኖ፣ በሐምሌ ወር አክሲዮን በመሸጥ በይፋ ወደ ተግባር ገብቶ ነበር፡፡

ከስድስት ዓመታት በላይ የተቋቋመበትን ዓላማ መተግበር ሳይቻለው የቆየው ሕብር ስኳር ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ከአክሲዮን ባለድርሻዎች ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ የተነሳበትን ዓላማ ለመተግበር ሳይቻለው በመቆየቱ ተስፋ እየቆረጡ የመጡ የአክሲዮን ባለቤቶች፣ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ከማንሳት ባሻገር በፍርድ ቤት ክስ መመሥረት ይጀምራሉ፡፡ በሕብር ስኳር የቀረበው የቢዝነስ ሐሳብ አዋጪነቱ በአግባቡ አልተጠናም በሚል ንግድ ሚኒስቴር ጣልቃ እንዲገባ ጭምር የሚጠየቁም ነበሩ፡፡ ‹‹መሬት የላቸውም፣ ገንዘቡን ዘርፈው ኮብልለዋል (ኩባንያውን በሥራ አስኪያጅነትና በቦርድ አባልነት ይመሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ከአገር መውጣታቸው ይታወቃል)›› የሚሉትን ከፍተኛ ቅሬታዎችን ጨምሮ መንግሥት እንኳ ያቃተውንና ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቀውን ዘርፍ ሆነ ብለው ዘርፈው ለመጥፋት በማሰብ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው የሚሉ ቅሬታዎች ሲስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

በዚህ ያላቆሙት ቅሬታዎች የአክሲዮን ኩባንያው እንዲፈርስ የሚያስገድዱ ጫናዎችን እስከማድረግ ደርሰው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ እንባ ጠባቂ ተቋም ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠይቆ እንደነበርና ንግድ ሚኒስቴርም ማብራሪያ እንዲሰጠው ማድረጉም የሚታወስ ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴር አክሲዮን ማኅበሩ መፍረስ እንደሌለበት በመሟገት ጭምር የአክሲዮን ማኅበሩን ሕልውና የማስቀጠል ምክንያት መሆኑም ይታወሳል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሕብር ስኳር ባለአክሲዮኖች የሚያነሷቸው የይፍረስ ጥያቄዎች የማኅበሩ የውስጥ ጉዳዮች በመሆናቸው ምላሽ እንደማይሰጡ በመግለጽ፣ ከዚህ ይልቅ ግን ሕጋዊ ሰውነት ካለው ተቋም ጋር ሕጋዊ ውል በመዋዋል ሥራ ለመሥራት መነሳቱን አቶ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

በአብላጫ የባለአክሲዮኖች ድምፅ ከመፍረስ ከዳነ ከወራት በኋላ ከአዲስ አበባ ከ540 ኪሎ ሜትር ርቃ፣ በአማራ ክልላዊ መንግሥት፣ በአዊ ዞን፣ ጃዊ ወረዳ ውስጥ በ2004 ዓ.ም. ከግብርና ሚኒስቴር በተሰጠው 6,183 ሔክታር ላይ የግብርና ሥራ ለማካሄድ መነሳቱን በማስመልከት በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም. ከዳግላ ከተማ 52 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የሕብር ስኳር እርሻ መሬት ላይ ጉብኝት መደረጉ አይዘነጋም፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቅሬታቸውን በአደባባይ እያሰሙና አክሲዮን ማኅበሩ የተነሳለት ዓላማ የማያዋጣው ነው በሚል የሚሟገቱ ባለአክሲዮኖች መፍረስ አለበት የሚል አቋማቸውን እንደያዙ ቀጥለዋል፡፡ በአንፃሩ የአክሲዮኑ አመራሮች የመጨረሻ መፍትሔ እንደሚሆን የሚገልጹት፣ ቅሬታ የሚያሰሙ ባለአክሲዮኖች ድርሻቸውን ሸጠው እንደሚሰናበቱ ነው፡፡

በመንግሥት ከሚገነባው የጣና በለስ ተፋሰስ ስኳር ፋብሪካ ጋር የሚዋሰነው የሕብር ስኳር እርሻ መሬት ጦሙን እንዳያድር በሚል ምክንያት ማቆያ ሰብሎችን ማምረት እንደጀመረ አቶ በለጠ የገለጹ ሲሆን፣ እስካሁንም አንድ ሺሕ ኩንታል ሩዝ መመረቱን ይፋ አድርገዋል፡፡ ሽምብራና ሌሎችም ሰብሎች ወደፊት ይመረታሉ ብለዋል፡፡

በምሥረታው ወቅት ያቀረበው የቢዝነስ ሐሳብ 12,500 ቶን አገዳ የሚፈጭ ነበር፡፡ ለዚህ ይፈለግ የነበረው ገንዘብ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ ይህ ሳይሳካ ቀርቶ የታሰበው ቢዝነስ ዕቅድ ተሻሽሏል ተብሎ በአምስት ዓመት ውስጥ እንደሚገነባ የታሰበው የሕብር ስኳር ፋብሪካ በቀን 4,800 ቶን የሸንኮራ አገዳ መፍጨት የሚችል እንዲሆን ተደረገ፡፡ ለዚህ ሥራ 2.2 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ ነበር፡፡ ይህም በከፍተኛ ደረጃ ከመነሻው ከነበረው ዕቅድ ዝቅ የተደረገ ነው፡፡ ይህ ዕቅድም በድጋሚ ተከለሰና በአሁኑ ወቅት ስምምነት ተደረገበት የተባለው የግንባታ ውል ደግሞ ከ3.3 ቢሊዮን ብር ወይም ከ165 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በቀን ስድስት ሺሕ ቶን አገዳ ይፈጫል የተባለ ፋብሪካ ለመገንባት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች