Friday, June 14, 2024

ከዘመኑ እኩል መራመድ ያልቻለው የአደጋ መከላከል ዝግጁነት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ እንደ ምሥራቅ እስያ አገሮች ከፍተኛ ውድመት የሚያደርስ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅና አውዳሚ አውሎ ንፋስ አጋጥሟት ባለማወቁ ለአንዳንዶች የተቀደሰች አገር ተደርጋ ትቆጠራለች፡፡ ወይም በአሜሪካ የሚታየው የሰደድ እሳት ወይም በተደጋጋሚ ብራዚልን ሲያሰቃያት የቆየው የመሬት መንሸራተት አለመከሰቱ፣ ለኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊ ዕድለኝነት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከሌሎች ዓይነት አደጋዎች ሊኖር ከሚችለው ተጋላጭነት ነፃ ልትሆን እንደማትችል፣ በቅርብ ዓመታት እየታዩ ያሉ የአደጋ ምልክቶች አገሪቱ በምን ዓይነት ሥጋት ውስጥ እንዳለች ለማንም የተሰወረ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡

በ1999 ዓ.ም. በድሬዳዋ በደረሰ የጎርፍ አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ በዳሰነች አካባቢ በኦሞ ወንዝ መጥለቅለቅ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የደረሰው የሞት አደጋ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

አሁን ለብዙዎች አሳሳቢ እየሆነ የመጣው ከከተሞች መስፋፋትና ከኢንዱስትሪ ተቋማት መብዛት ጋር ተያይዞ ትኩረት የመስጠት ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁም ከኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ከሕዝብ ብዛት በተለይም ደግሞ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በማየት የተጋላጭነት ሥጋቶች እየተገለጹ ይገኛሉ፡፡

በእርግጥ የተለያዩ ተቋማት እንደየዘርፋቸው ለቅድመ አደጋ መከላከል የየራሳቸውን ጥረት የደርጋሉ፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለይ አደጋን በመቀነስ ረገድ ያሉትን ክፍተቶች በመቅረፍና አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ባለሙያዎችን በተለያዩ ጊዜያት የማሠልጠን ሥራ ሲሠራ ይታያል፡፡

ለአብነትም ባለፈው ወር አደጋ በሚከሰት ጊዜ በሕይወት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስና ፈጥኖ በመድረስ ነፍስ ለማዳን በጃንሜዳ የተግባር ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ በወቅቱ 400 ያህል የመጀመርያ ዕርዳታ ሰጪ ባለሙያዎችና ከ50 በላይ ከመንግሥትና ከግል ተቋማት የተውጣጡ አምቡላንሶች የተሳተፉበት የተግባር ሥልጠና ተከናውኗል፡፡

‹‹በአገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር በተያያዘ አዳዲስ ልማትና ኢንዱስትሪ ግንባታዎች የጎንዮሽ አደጋዎችን ቀድሞ በማሰብ፣ ለእነርሱ የሚሆን የተቀናጀ ምላሽ በተቋማት ዘንድ እንዲኖር በርካታ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡ በመሆኑም እንደዚያ ያሉ መሰል የአደጋ ልምምዶች ጉዳቶችን ይቀንሳሉ፤›› ሲሉ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የድንገተኛ አደጋ ሕክምና ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሄሌና ኃይሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በጃንሜዳ በተዘጋጀው ትርዒት መሰል ልምምድ በየዘርፉ የተለያዩ ተቋማትን መኖር ያለበት ትብብር የሚያሳይ መሆኑን ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት ውስጥ የጤና ድርጀቶች፣ የጤና ቢሮዎች፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን፣ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት፣ ኤርፖርቶች፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች ባለሙያዎችና አምቡላንሶች ተሳትፈዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ የትብብር ተግባር በበጎ ሁኔታ ቢታይም፣ በአገር አቀፍ ደረጃ መጠነ ሰፊ አደጋዎች ቢከሰቱና አደጋዎችን ለመቀነስ የሚያስፈልግ ጥረት ቢኖር፣ አሁን ያለው አሠራር፣ ቅንጅትና አቅም ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ በተለይ በርካታ ሕዝብን አደጋ ውስጥ የሚከትና ከአንድ በላይ ክልልን የሚሸፍን ክስተት ቢፈጠር፣ በምን ዓይነት መንገድ አደጋውን መከላከልም ሆነ ምላሽ መስጠት እንደሚቻል ያለው መዋቅራዊ አደረጃጀት በግልጽ አያሳይም፡፡

ኢትዮጵያን ለዘመናት ሲፈትናት የኖረው ከባድ የሚባል ዓይነት አደጋ ሲወሳ ረሃብ ቅድሚያውን መያዙ በታሪክ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከረሃብ ባሻገር የጎርፍ አደጋ፣ ወረርሽኝና የጦርነት አደጋዎችም ትልቅ ሥፍራ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አደጋን በመከላከል ረገድም ሆነ የአደጋን ጉዳት ተከትሎ የዕርዳታ ሥራን (መልሶ ማቋቋም ጨምሮ) በተቀናጀ መልክ የተቋቋመ ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1966 ዓ.ም. የተቋቋሙ የዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ሲሆን፣ ከዚያ በፊት የተደራጀ ምንም ተቋም አልነበረም፡፡ ይህ ድርጅት በወቅቱ በወሎና በትግራይ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ለተጎጂዎች ዕርዳታ ለመስጠት ተብሎ የተመሠረተ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ራሱን እንደገና በማደራጀት ከሠፈራ ፕሮግራምና ከአዋሽ ሸለቆ ባለሥልጣን ጋር በአንድ ተጣምሮም ነበር፡፡ ከ1985 ዓ.ም. በኋላ ይኸው ድርጅት አዲስ ፖሊሲ ተቀርጾለት የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ስያሜ ተሰጥቶት እስከ 2005 ዓ.ም. ቆይቷል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በግብርና ሚኒስቴር ሥር እንደ አንድ መምሪያ ተዋቅሮ የአደጋ መከላከል፣ ዝግጁነትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ሆኖአል፡፡ ኮሚሽን በነበረበት ወቅት ራሱን የቻለና የተደራጀ ሆኖ ከመቆየቱም ባሻገር፣ በአደጋ ጊዜ ፈጥኖ መልስ በመስጠትም ሆነ በመከላከል ሔሊኮፕተር ድረስ የነበረው ዘርፈ ብዙ ተቋም ነበር፡፡

የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥና የገጠር ፖሊሲን በተሻለ አቅም ለማስፈፀም በማለት ነበር መንግሥት በግብርና ሚኒስቴር ሥር እንዲዋቀር ማድረጉን መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

ኮሚሽኑ ከተቋቋመቡት ጀምሮ ራሱን እያጎለበተና በአፍሪካ ደረጃ አደጋ በመከላከል እንደ ሞዴል እስከመታየት ደርሶ እንደነበርም በቁጭት የሚናገሩ አሉ፡፡ በተለይም ኮሚሽኑ የምድር፣ የየብስ እንዲሁም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በተደራጀ መንገድ ይጠቀም ነበር፡፡ የአደጋ ተጋላጭነት በታወጀባቸው ቦታዎች ራሱ ሙሉ በሙሉ የማስተዳደር ሥልጣንም የነበረው እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ከፍትሕ ተቋማት በስተቀር በተለይ በቀድሞው መንግሥት ዘመን ከሲቪል ሰርቪስ እስከ በጀት የመመደብ ሥልጣን ሳይቀሩ ነበሩት፡፡

‹‹በአፍሪካ ውስጥ ሳይቀር ትልልቅ አደጋዎችን መከላከል ይችል የነበረና በአግባቡ የተደራጀ ተቋምን በግብርና ሚኒስቴር ሥር እንደ አንድ መምሪያ ማዋቀር የሚያዝን ነው፤›› በማለት ድርጅቱን ለብዙ ዘመናት በቅርቡ የሚያውቁ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የዚህን ዓይነት ተቋማዊ አደረጃጀትና ውሳኔን በተመለከተ አስተያየታቸውን የገለጹት ባለሙያው፣ ‹‹ግለሰቦችን እያሸተተ ሥልጣን የሚሰጥ የአሠራር ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ችግር ሆኖ የቆየ ነው፤›› በማለት ይተቻሉ፡፡

የኮሚሽኑን በግብርና ሚኒስቴር ሥር የመዋቀር ውሳኔን፣ ‹‹አገሪቱ በምታፍርበት ታሪክ ውስጥ የተወለደን ድርጅት ለሌላ አካል እንደ ጉዲፈቻ መስጠት ነው፤›› በማለትም ይገልጹታል፡፡

አሁን አገሪቱን በመሥራት ላይ ባለው መንግሥት አመራር የተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች እንደየዘርፋቸው አደጋን በመከላከልና አስፈላጊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ የየራሳቸውን ሥራ ያከናውናሉ፡፡ በተቀናጀ መንገድ ባያስብልም በአደጋ ወቅት ግን መዋቅራዊ ባልሆነ በትብብር ሲሳተፉ ይስተዋላል፡፡

ለአብነትም ያህል ከእሳት አደጋ ጋር በተገናኘ የእሳት አደጋና የድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን በበላይነት ያስፈጽማል፡፡ ከጤና ጋር በተገናኘና ወረርሽኝ የመሳሰሉ የአካባቢና የኅብረተሰብ ሥጋት በሚሆኑ ጉዳዮችን በተመለከተ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይሠራል፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይ ጉዳዮች ሌሎች አጋር ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመሆን ይሠራሉ፡፡

የመከላከያ ሠራዊትና ፖሊስም በበኩላቸው የራሳችውን ተሳትፎ በስፋት ያሳያሉ፡፡ ከደኅንነት ሥጋት ጋርም ተያያዥነት ሲኖረው የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ ተቋም እንዲሁ እንደ ባለድርሻ አካል ተሳትፎ አለው፡፡

ማናቸውም አደጋዎች ሲከሰቱ ሁሉም የብዙዎቹ ተቋማት መተባበር፣ በጋራ የመከላከልና የነፍስ ማዳን ሥራ ለብዙ ጊዜያት የቆየ ቢሆንም፣ በተለይ አሁን በአገሪቱ እየታየ ካለው ኢኮኖሚያዊና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት አንፃር በሥራ ላይ ያለው በአደጋ መከላከልና በቅድመ አደጋ ዝግጁነት ላይ ክፍተት መኖሩን የሚገልጹ አሉ፡፡

በዘርፉ የተሰማሩት ተቋማትም ሆኑ ባለሙያዎች ቅድመ አደጋን የመከላከልና አፋጣኝ ዕርዳታ የመስጠት አቅምን፣ ካለው ተቋማዊ አደረጃጀት አንፃር መፈተሽ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡

በተለይም ጉዳዩ በቅርበት የሚመለከታቸው ወገኖች በመሠረተ ልማት ግንባታም ሆነ እየተመዘገበ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማስቀጠል፣ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከግምት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ አገሪቱ በአደጋ መከላከል ጉዳይ አቅሟን የበለጠ ማሳደግና የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማትን በተቀላጠፈ መንገድ የሚያስተባብር ተቋም መፈጠር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 በግብርና ሚኒስቴር የአደጋ ተጋላጭነትና መከላከል ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ አበበ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፣ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ለአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አገሮች መካከል ቅድሚያውን ሥፍራ እንደምትይዝ አመልክተዋል፡፡ ባለሙያው እንደሚገልጹት፣ አገሪቱ አሁንም ለድርቅ፣ ለጎርፍ፣ ለአየር ንብረትና ለግጭቶች ተጋላጭ ልትሆን ትችላለች፡፡

ከመዋቅራዊ ለውጥና የአደጋ መከላከል የሕግ ማዕቀፍ ከመለወጥ አንፃር ያለውን አስፈላጊነት፣ በቅርቡ በአገሪቱ የተከሰቱ የአደጋ ዓይነቶች በመግለጽ የሚያሳስቡ አሉ፡፡

በአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል ባለሥልጣን አንድ ኃላፊ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ በቅርቡ ከተከሰቱ ከእሳት አደጋዎች በመነሳት አገሪቱ አዲስ የአደጋ መከላከል ሥርዓት እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል፡፡

‹‹ከአንድ ወር በፊት በባሌ በተነሳው ሰደድ እሳት መንግሥት በቂ አቅም ስላልነበረው፣ ከደቡብ አፍሪካ ሔሊኮፕተር ማስመጣትን እንደ አማራጭ ማየቱ በቅድመ አደጋ መከላከል ጉዳይ ያለንን ክፍተት ያሳያል፤›› ሲሉ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሦስት ወራት በአገሪቱ ውስጥ ዘጠኝ ትልልቅ የእሳት አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ ታሪካዊውን የጣይቱ ሆቴልን በከፊል ያወደመው የእሳት ቃጠሎን ጨምሮ በሐዋሳ 800 ያህል ሱቆችን ያወደመውና በአርሲ ጭላሎ ተራራና በባሌ ተራሮች የተከሰተው የእሳት አደጋ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ክስተቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ከእነዚህ አደጋዎች በላይ ምንም ዓይነት የከፋ ማስጠንቀቂያ ሊኖር አይችልም፤›› የሚሉት የእሳት አደጋ መከላከል ባለሥልጣን ባልደረባው፣ መንግሥት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የአደጋ ቅድመ መከላከልና ዝግጁነት ጉዳይ ሊፈተሽ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሌላም የሚያነሱት ጉዳይ አለ፡፡ በተለይ በተለያዩ ከተሞች የእሳት አደጋ መከላከል ተቋማትን ለማቋቋም የገንዘብ እጥረትና የአቅም ችግር ቢኖርም፣ በተቻለ መጠን አቅምን በማሳደግ በእሳት ቃጠሎ በሕይወት ላይ የሚደርስ ጉዳትንና የሚወድም ሀብትን ማዳን ግድ ነው በማለት፣ ባለፈው ዓመት ብቻ በቡራዩ ከተማ የደረሰውን ጉዳት በምሳሌ ያነሳሉ፡፡

‹‹ለምሳሌ ያህል በ2006 ዓ.ም. ብቻ በቡራዩ በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ በዚች ከተማ አንድ የእሳት አደጋ መከላከል ተቋም ቢቋቋም ዓመታዊ በጀቱ 40 ሚሊዮን ብር ሊፈጅ እንደማይችል ይታወቃል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም በአገር አቀፍ ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያስፈልግም እንኳ፣ እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ሌላው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ከሚኖረው ሚና በተጨማሪ በርካታ ባለድርሻ አካላትን በማደራጀትና በማስተባበር ረገድ አገሪቱ ያሳካችው ሌላ በጎ ልምድ የለም ባይባልም፣ ብዙ መሥራት የሚጠይቅ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ለምሳሌ አገሪቱ ከተሳካላት የሕግ ማዕቀፍና በተደራጀ ተቋማዊ አመራር ከታዩ ስኬቶች ውስጥ አንዱ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው፡፡ ‹‹እንደሚታወቀው ኤችአይቪ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት አገሪቱን አስከፊ አደጋ ውስጥ ከቷት ነበር፡፡ ነገር ግን የዚህን በሽታ ሥርጭትና አደጋ ከመቀነስ አልፎ መቆጣጠር የተቻለው፣ በተዘረጋው የሕግ ማዕቀፍና ባለድርሻ አካላትን በአግባቡ እንዲሳተፉ በማድረግ በተሠራው ሁሉን አቀፍ የማስተባበር ሥራ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ተግባራዊ የተደረገው መዋቅራዊ አስተዳደርና አፈጻጸም የኤችአይቪ ሥርጭትን በ1990ዎቹ ውስጥ ከነበረው 2.6 በመቶ ወደ 0.4 በመቶ በማውረድ መቆጣጠር መቻሉን፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በፕሮጀክት አስተባባሪነት የሚሠሩ ባለሙያ ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡

ከሚስተዋሉ የአደጋ ተጋላጭነት ስፋትና ዓይነት፣ ካለው አጠቃላይ ዕድገት አንፃር የተሻለ ዝግጅትና አቅም በመፍጠር የተለያዩ አካላትን ማቀናጀት የሚያስችል ተቋማዊ ለውጥ አገሪቱ እንደሚያስፈልጋት ሁሉም ወገኖች ይስማማሉ፡፡ በአንፃሩ በአደጋ መከላከልም ሆነ ምላሽ በመስጠት ከ40 ዓመታት ያህል የተሻለ ልምድ የነበረውንና ራሱን የቻለ ተክለ ሰውነት የፈጠረውን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን፣ ለገጠር ፖሊሲና ልማት ማስፈጸሚያነት በማየት በግብርና ሚኒስቴር ሥር መወሰኑ አግባብ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ በፊት ይህ ዓይነት ኮሚሽን በመንግሥት ውሳኔ መቀየሩ ትልቅ የሥጋት ምንጭ ሆኗል፡፡ ለዓመታት በአደጋ መቆጣጠር ረገድ የተሻለ ልምድ አዳብሮ የቆየን ተቋም በዚህ ዓይነት ሁኔታ መታጠፉ አሁንም ቢሆን ሊታሰብበት የሚገባና በተለየ ሆኖ ሊቋቋም የሚገባው ነው፤›› በማለት ዶ/ር ሙሉጌታ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ውስጥ ያቀረቡት ሐሳብ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ፀሐፊ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ወርቁ በበኩላቸው፣ የአገሪቱ የአደጋ መከላከል ጉዳይ ገና ብዙ የሚሠራበትና አሳሳቢ መሆኑን ይጋራሉ፡፡ በተለይ በከተሞች ያለው የአኗኗር ሁኔታና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ያለው አለመመጣጠን፣ ነዋሪዎችን የባሰ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚለው በይበልጥ እንደሚያሳስባቸው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል፡፡ ለአብነትም ያህል በስፋት ግንባታ በሚካሄድባቸውና ካለፉት አሥር ዓመታት ጀምሮ ቁጥራቸው እየጨመረ በመጡት የጋራ መኖሪያ አካባቢዎች ሊኖር የሚችለው የአደጋ ተጋላጭነት፣ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ዋና ፀሐፊዋ ያስረዳሉ፡፡

‹‹ለእኔ አሁን በተለይ በከተሞች በኩል የቅድመ አደጋ መከላከል ጉዳይ በይበልጥ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች በርካታ ነዋሪዎች ስለሚኖሩ ከቤቶች የሕንፃ አሠራር አኳያ አደጋ ቢከሰት እንኳ፣ የተጎጂውን ቁጥር በፍጥነት ለመቀነስ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል፤›› በማለት ወ/ሮ ፍሬሕይወት ያብራራሊ፡፡ ቀይ መስቀል ማኅበር በከተሞች የቅድመ አደጋ መከላከል አሠራሮች ለመዘርጋት የዳሰሳ ጥናት ከአስተዳደሩና ከከተማው የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ባለሥልጣን ጋር ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ እንደ መፍትሔ በተለይ በኮንዶሚኒየሞች አካባቢ አደጋ ቢከሰት ለአምቡላንስ አገልግሎትም ሆነ ለድንገተኛ አደጋዎች አፋጣኝ መልስ ለመስጠት ቢሮዎች የመክፈት ፍላጎት እንዳለው ኃላፊዋ የማኅበራቸውን ውጥን ሐሳብ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ሁሉ ምክትላቸው አቶ ሐጐስ ገመቹ የአደጋ መከላከልንም ሆነ ቅነሳን በተመለከተ ያለውን ችግር ሲገልጹ፣ በከተማው ያለውን ፈታኝ የአምቡላንስ አገልግሎትና የትራፊክ ፍሰቱን እንደማሳያ ያስረዳሉ፡፡

አንድ አምቡላንስ ለአስቸኳይ የነፍስ አድን ሥራ አደጋ ወደ ተከሰተበት ቦታ ሲሰማራም ሆነ አፋጣኝ ሕክምና የሚያስፈልገውን ሰው ወደ ሆስፒታል ጭኖ በመሄድ ላይ እያለ፣ ወደሚፈለግበት ቦታ ፈጥኖ ደርሶ ነፍስ የማዳኑ ሥራ ከማከናወን ይልቅ በመንገድ ላይ በጩኸት የሚያቃጥለውን ሰዓት ማየትም ሆነ መስማትም የተለመደ ነው በማለት የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡

‹‹በዚህ በተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰት ባለበት ሁኔታ በአምቡላንሱ ጩኸት ከመደናቆር ውጪ፣ የነፍስ አድን ተግባሩ በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ የአደጋ መከላከልንና የዕርዳታ አሰጣጡን መፈተሽና አዲስ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልገው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአምቡላንስ አገልግሎትም ሆነ በመሠረተ ልማት ግንባታ አዲስ አበባ ከተማ የተሻለ ተብሎ ቢወሰድ እንኳ፣ ነፍስ በማዳኑ ረገድ ከገጠሩ ብዙም እንዳማይሻል ጨምረው ያስረዳሉ፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ በገጠር አካባቢ የተሻለ መንገድና የአምቡላንስ አቅርቦት ባመኖሩ ብዙ እናቶች ወይም ሕመምተኞች በሚፈለግበት ሰዓት ሕክምና ሳያገኙ በመንገድ ቃሬዛ ላይ ሆነው ሲሞቱ ይታያል፡፡ አዲስ አበባ ላይ የፈለገ የአምቡላንስ አቅርቦትና መንገድ ቢኖር በትራፊክ መጨናነቅ የተነሳ አንድ አምቡላንስ ሦስትና አራት ሰዓት መንገድ ላይ የሚያቃጥል ከሆነ፣ ከተማው ከገጠሩ በአስፋልት ካልሆነ በቀር በምን ይሻላል? ሲሉ ችግሩን አውስተዋል፡፡

‹‹በፖሊሲ ጉዳይም ሆነ በሕግ ማዕቀፍ በኩል ያሉ ነገሮች እንደገና አገሪቱ ካለችበት አጠቃላይ ዕድገት አንፃር መከለስ ይገባዋል፤›› በማለት የሚያስረዱት አቶ ሐጐስ፣ ከዚህ በፊት አገራዊ የውይይት ፎረምና በብዙ አቅጣጫ የተቃኘ ጥናት መኖር እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -