Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያና ሩዋንዳ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነታቸውን ይፋ አደረጉ

ኢትዮጵያና ሩዋንዳ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነታቸውን ይፋ አደረጉ

ቀን:

ኢትዮጵያና ሩዋንዳ በኤሌክትሪክ ኃይል ሸያጭ፣ በከተማ ልማት፣ በሰላምና በፀጥታ መስኮች የደረሱባቸውን ስምምነቶችና ትብብር ይፋ አደረጉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባደረጉላቸው ግብዣ መሠረት፣ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ከባለቤታቸው ቀዳማዊ እመቤት ጃኔት ካጋሜ ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት በአዲስ አበባ አድርገዋል፡፡ በዚህም ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከቀዳማዊ እመቤት ሮማን ተስፋዬ ጋር በተለያዩ ትብብሮች ላይ መክረዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ቅንጅት፣ በሰላምና ፀጥታ፣ በፀረ ሽብር፣ በግብርናና በከተማ ልማት፣ እንዲሁም በሁለቱ አገሮች መካከከል ስለሚኖረው የንግድ ልውውጥ ተወያይተዋል፡፡

የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊዝ ሙሹኪዋቦ ጋር በከተማ ልማት መስክ ለመተባበር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ከዚህ የፊርማ ስምምነት በኋላ የጋራ መግለጫ የሰጡት የሁለት አገሮች መሪዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭና መልካም ተሞክሮዎችን ለመጋራት መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለሩዋንዳ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ማድረግ መቼ እንደሚጀምር የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ከወላይታ ሶዶ ወደ ኬንያ የሚዘረጋው አውራ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እንደተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሩዋንዳ 153 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨች ሲሆን፣ ይህን የኃይል መጠን እ.ኤ.አ. በ2018 ወደ 563 ሜጋ ዋት ከፍ ለማድረግ ታስባለች፡፡ ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ልትገዛው ያሰበችውን የኃይል መጠን ባይታወቅም፣ 450 ሜጋ ዋት ኃይል ድረስ ከጎረቤት አገሮች ለመግዛት ግን አቅዳለች፡፡

ይህ አውራ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር 1,068 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ባለ 500 ኪሎ ቮልት መስመር፣ እንዲሁም 2,000 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያለው ትራንስፎርመር በወላይታ ሶዶና በኬንያ ሱሰዋ የተባለች ግዛት ላይ ይዘረጋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚፈጅ አበዳሪ የሆነው የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡ ሌላኛው ብድር አቅራቢ የዓለም ባንክ ሲሆን፣ የኬንያና የኢትዮጵያ መንግሥታትም መጠነኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

ይህ መስመር እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 2017 እንደሚጠናቀቅ መረጃው ያመለክታል፡፡ ‹‹ይህ መስመር ተጠናቆ ከኬንያ ጋር ተገናኘን ማለት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ኔትወርክ ውስጥ ገባን ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ከሩዋንዳ ጋር መገናኝት ቀላል ነው፤›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ይህ አውራ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሲጠናቀቅ በቅድሚያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሚያገኙት አገሮች መካከል ኬንያ ቀዳሚዋ ናት፡፡ በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ኬንያ 200 ሜጋ ዋት ኃይል በመጀመርያው ዙር የምታገኝ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በግንባታ ላይ የሚገኙ ሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ደግሞ በአጠቃላይ 400 ሜጋ ዋት ታገኛለች፡፡

በሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ይፋዊ ጉብኝት ውስጥ ከተካተቱ ልዑካን መካከል የሩዋንዳ የግሉ ዘርፍ ፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ አቸው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በኢንቨስትመንት መስክ ለመተባበር የመግባቢያ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...