Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልላሊበላን ለመጠበቅ የተዘረጋው የብረት ጥላ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስላመዘነ ሊነሳ ነው

ላሊበላን ለመጠበቅ የተዘረጋው የብረት ጥላ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስላመዘነ ሊነሳ ነው

ቀን:

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ከተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል በሚል የከባድ የብረት ምሰሶ የተሠራው ጥላ፣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስላመዘነ ሊነሳ እንደሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ጥላው የተዘረጋው ቅርሱን ከዝናብ፣ ከንፋስና ከመሳሰሉት ተፈጥሯዊ ተፅዕኖዎች ለመከላከል በሚል ቢሆንም፣ ቅርሱን እየተጫነው ነው፡፡ በተለይም ከጊዜ ብዛት ጥላው ያረፈበት የቅርሱ ክፍል እየተሰነጠቀ መምጣቱ በጥናት መረጋገጡ ተገልጿል፡፡

የቅርሱን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በተመለከተ ኅዳር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ጥላው ቅርሱ ላይ እያሳደረ ያለው ጫና እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ምንም እንኳን ጥላው ቅርሱን ይጠብቃል በሚል እሳቤ ቢዘረጋም፣ ጉዳቱ እያመዘነ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለምም ቅርስ የሆኑት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተጋረጠባቸው አደጋ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በዕድሜ ብዛት ከሚደርስባቸው ጉዳት ለመከላከል የሚያስፈልገውን ጥገና በተገቢው ጊዜ አለማግኘታቸው ይጠቀሳል፡፡ በእርግጥ በመላው አገሪቱ ያሉ ቅርሶች ጥበቃና ጥገና ጉዳት ፈር እንዲይዝ ለዓመታት ቢወተወትም አመርቂ ውጤት አልተገኘም፡፡

- Advertisement -

እንደ ላሊበላ ያሉና የአገሪቱ ቱሪዝም የተመረኮዘባቸው ቅርሶች ጥበቃ ጉዳይ ዛሬም እያነጋገረ ነው፡፡ ቅርሶቹ በቱሪዝም ገቢ ማግኛ ከመሆናቸው ባሻገር እንደ አገር የዜጎች መገለጫም ናቸው፡፡ ቅርሶቹን የመጠበቅ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የመጠገን ኃላፊነት ያለበት አካል፣ ቅርሶቹ ለመጥፋት እስኪቃረቡ ድረስ ዕርምጃ ሲወስድም አልታየም፡፡

በላሊበላ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ካሉት ቅርሶች መካከል እነ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ መርቆሪዎስ ይገኙበታል፡፡ ‹‹በዕድሜ ብዛት በደረሰበት ተፈጥሯዊ ጫና ምክንያት እየተፈረካከሰ ፈተና ውስጥ ገብቷል፤›› ሲሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ቅርሱን ለመጠገን የተወሰዱ ዕርምጃዎች አንፃራዊ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ወደተባባሰ ችግር እያመሩ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡

ሚኒስትሯ ችግሩን፣ ‹‹የሼዱ [የጥላው] እግር የቆመው ቅርሱ ላይ በመሆኑ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ የንፋስ መጠን መጨመሩም ለቅርሱ አደጋ ሆኗል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ የላሊበላ ጉዳይ በሚኒስቴሩ ከመታየቱ አስቀድሞ የበርካታ ባለሙያዎችን አስተየየት ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ በቅርሱ ጥበቃ ዙሪያ ብዙ ቅሬታዎች ሲቀርቡም ነበር፡፡

መሥሪያ ቤቱ ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ ጥላዎቹ በቅርሱ ላይ እያደረሱ ያሉት ጉዳት ስለተረጋገጠ ጥላዎቹ እንደሚነሱ ዶ/ር ሒሩት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጥላው እንዲነሳ ተወስኗል፡፡ ለአስፈላጊው ጥገናም 20 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ ሥራው በዕውን የሚጀመርበትን ጊዜ ባያሳውቁም፣ ቅርሱ ስለሚገኝበት አሳሳቢ ሁኔታ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ማሳወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ቅርሱ በዓለም አቀፍ መዝገብ የሠፈረ እንደመሆኑ የተቋሙ ውሳኔ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡ ለጥገና የሚፈልገው ገንዘብ እስከሚገኝ እንዲሁም ሌሎችም ሒደቶች በሚከናወኑበት ጊዜ ውስጥ ቅርሱ የሚደርስበት አደጋ እየተባባሰ መምጣቱ አያጠያይቅም፡፡ ቅርሱን በመታደግ ረገድ መሥሪያ ቤቱ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው? የሚለውን ጥያቄም ያስነሳል፡፡

የተመደበው ገንዘብ ለአብያተ ክርስቲያናቱ በአጠቃላይ እድሳት ለማድረግ የታለመ ነው፡፡ ሚኒስትሯ እንዳሉትም፣ ከአብያተ ክርስቲያናቱ እንደ ጉዳት መጠናቸው የሚጠገኑበት ቅደም ተከተል ይወሰናል፡፡ ጥላው በተዘረጋበት ወቅት ለአምስት ዓመት ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ ታቅዶ ቢሆንም፣ የጊዜ ገደቡን አልፎ ተጨማሪ አምስት ካለፈ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጥላውን ለመዘርጋት በተወሰነበት ወቅት፣ ሊያደርስ የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ገብቶ ነበርን? የሚለው ጥያቄም ይነሳል፡፡

ሚኒስትሯ እንደሚናገሩት፣ ጥላው ቅርሱን ለመጠበቅ በሚል ተዘርግቶ ጉዳት ቢያደርስም፣ ባይዘረጋ ሊደርስ የሚችለው ጉዳትም መታሰብ አለበት፡፡ ጥላው ቅርሱን ከተፈጥሯዊ አደጋ የመከላከል ሚና እንደነበረውም ጠቅሰዋል፡፡ ጥላው በተዘረጋበት ወቅት ሊኖረው ስለሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቅድመ ጥናት አልተደረገም? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ስላልነበርኩበት ጊዜ አስተያየት መስጠት አልችልም፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ ሚኒሰትሯ ወደ ኃላፊነት ከመጡበት ጊዜ በፊት ስለነበረው ወቅት አስተያየት ከመስጠት ቢታቀቡም፣ የቅርሱ ጉዳይ ሰሞነኛ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በተለይም በማኅበረሰብ ድረ ገጾች የሚሰማው ቅሬታ እየጨመረ ነው፡፡

ዶ/ር ሒሩት በበኩላቸው፣ በቅርሶች ጥበቃና ጥገና ረገድ የተሠሩ ሥራዎች እውቅና ሊቸራቸው ይገባል ይላሉ፡፡ እንደ ምሳሌም አምና ለቤተ ገብርኤልና ቤተ ጎልጎታ የተደረገውን ጥገና ይጠቅሳሉ፡፡ በተያያዥም ቅርሶችን በመበጠበቅ በኩል የአገር በቀል ባለሙያዎችና የገንዘብ እጥረት እንደሚፈታተናቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቅርሶቹ ዕድሜያቸው ሲጨምር አደጋ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በሁሉም አካባቢ ያሉ ቅርሶች ትኩረት ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም የሰው ኃይልና ገንዘቡ ከቅርሱ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ቅርሶች በየጊዜው ተገቢውን ጥገና ካለማግኘታቸው ባሻገር፣ ጥገና ሲደረግላቸው ባለው ሒደት ላይም ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በጥበቃ ሒደቱ ማኅበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ፣ ማኅበረሰብ አቀፍ ቱሪዝም ሊተገበር እንደሚገባም በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ሆኖም ማኅበረሰቡን ያማከለ ቱሪዝም አለመስፋፋቱ በቅርሶችና በኅብረተሰቡ መካከል ክፍተት ፈጥሮ ይስተዋላል፡፡

‹‹የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ካልሆነ የኔነት ስሜት አይሰማውም፡፡ ቅርሱንም አይንከባከበውም፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ በዘርፉ ክፍተት መኖሩን አምነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ቅርሶችና ባለሙያዎች አመጣጠናቸው ለችግሩ መንስዔ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ላሊበላን በተመለከተ፣ ጥገናውን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን 20 ሚሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ኮሚቴ እንደሚዋቀር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ከአገሪቱ ዕድሜ ጠገብ ቅርሶች አንዱን ለመታደግ መንግሥት ምን ያህል ገንዘብ ያወጣል? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ገንዘቡን ለማሟላት ለዕርዳታ ሰጪዎች ጥያቄ በሚቀርብበት ሒደት ወቅትስ ቅርሱ የሚደርስበት ጉዳት አይባባስም? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ወር ባደረገው ጉባኤ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ የተዘረጉት ባለብረት ምሰሶ ጥላዎች ጉዳት እያደረሱ በመሆናቸው መንግሥት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰቡና ቅዱስ ፓትርያኩ አቡነ ማትያስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የማሳሰቢያ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...