Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ የሩቅ ምሥራቅ ኩባንያዎች ተስፋ ተጥሎባቸዋል

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በሁለተኛው ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል ተባለ

የቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ሁጂያን ግሩፕና የታይዋኑ ግዙፍ ኩባንያ ጆርጅ ሹ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን የቆዳ ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ ተባለ፡፡ ሁለቱ የሩቅ ምሥራቅ ግዙፍ ኩባንያዎች በአዲስ አበባና በሞጆ ከተሞች የኢንዱስትሪ ዞን መገንባት ጀምረዋል፡፡

ሁጂያን ግሩፕ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባገኘው 134 ሔክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት ባለፈው ሐሙስ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡ የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታውም ከወዲሁ መጀመሩ ታውቋል፡፡

የመሠረት ድንጋዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባስቀመጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በሁጂያን የሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን ኢትዮጵያ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ለጀመረችው ጉዞ ስኬታማነት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ዞን ግንባታው በሦስት ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን፣ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሏል፡፡

ሁጂያን በሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን የቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ፣ የሠራተኞች መኖሪያ መንደር፣ መዝናኛ ማዕከላትና የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ግንባታዎችን እንደሚያካት ታውቋል፡፡

ኢንዱስትሪ ዞኑ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ከ35 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ሠራተኞችን እንደሚቀጥር የሁጂያን ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሚስተር ዛንግ ሆሩንግ፣ የኢንዱስትሪ ዞኑ የመሠረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

ሁጂያን በሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን ጫማ፣ ጓንት፣ ቦርሳና የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ከተጓዳኞቻቸው ጋር እንደሚያመርት ታውቋል፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኑ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ወጪው አምስት ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑንና ይህንን ገንዘብ ከራሱና ከቻይና ልማት ባንክ የሚሸፍን መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሁጂያን በአሁኑ ጊዜ ዱከም አካባቢ በአገሩ ኩባንያ በተገነባው ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ጫማና የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡

ሌላኛው ግዙፍ ኩባንያ የታይዋኑ ግዙፍ ጆርጅ ሹ ነው፡፡ ጆርጂ ሹ ቦሌ ለሚ አካባቢ በገነባው ፋብሪካ በቀን ሦስት ሺሕ ጥንድ ጫማዎች በማምረት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ኢንቨስትመንቱን በጥልቀት በማስፋፋት ከሞጆ ከተማ አስተዳደር በተረከበው 50 ሔክታር መሬት አዲስ የኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ከአራት ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ወጪው 600 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሏል፡፡ ፋብሪካው ጫማ፣ ያለቀለት ቆዳና ሌዘር ከማምረቱም ባሻገር ለምርቶቹ የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ ተጓዳኞችን እንደሚያመርት ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዱ ለገሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህ ኩባንያዎች የሚያቋቁሟቸው ቀላል ኢንዱስትሪዎች፣ የኢትዮጵያን የቆዳ ኢንዱስትሪ ወደ ሌላ ምዕራፍ ያሸጋግራሉ፡፡

‹‹የቆዳ ኢንዱስትሪው ይህ ነው ሊባል በሚችል ሁኔታ ከእስያ በኢትዮጵያ በኩል፣ ወደ አፍሪካ መግባቱን ያሳያል፤›› በማለት አቶ ወንዱ እነዚህ ፋብሪካዎች የኢትዮጵያ ተስፋዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ወንዱ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሲጠናቀቅ፣ መንግሥት ከቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ በዓመት 800 ሚሊዮን ዶላር የማግኘት ዕቅድ አለው፡፡ ይህንን ዕቅድ ለማሳካት የሁለቱ ፋብሪካዎች ድርሻ ከፍተኛ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ከዚህ ዘርፍ በዚህ ዓመት መጨረሻ የሚጠብቀው የወጪ ንግድ ገቢ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ በስድስት ወራት የተገኘው ገቢ ግን ከ65 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች