ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በየመን ግጭት ሕይወታቸው አደጋ ውስጥ ገብቶ የነበሩ 168 ኢትዮጵያውያንን በማውጣት፣ ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ ማጓጓዙን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ባከናወነው ሰብዓዊ ተግባር በአጠቃላይ 171 ኢትዮጵያውያንን ወደ አዲስ አበባ አጓጉዟል፡፡
መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 86 ሲሆን፣ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ለሁለት ቀናት ቆይታ ካደረጉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መግባታቸውን ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡
ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አምባሳደር ሲራጅ ረሺድና የአይኦኤም የአዲስ አበባ ኃላፊዎች ተቀብለዋቸዋል፡፡
አይኦኤም ከ38 አገሮች በቀረበለት የዕርዳታ ጥያቄ መሠረት በየመን ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጐችን በማውጣት ላይ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን መንግሥታት የአውሮፕላን ማረፊያዎቻቸውን በመፍቀዳቸውም የሌሎች አገር ዜጐችን መታደግ እንዳስቻለው ገልጿል፡፡
በአየር ከሚደረግ የማጓጓዝ ተግባር በተጨማሪ 131 ኢትዮጵያውያን ከየመን ወደ ጂቡቲ፣ ከዚያም በየብስ ትራንስፖርት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረጉን አስረድቷል፡፡