Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት የደቡብ አፍሪካውያን ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት የደቡብ አፍሪካውያን ጥቃት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

ቀን:

በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ስደተኛ አፍሪካውያን ላይ የአገሪቱ ዜጐች የሰነዘሩትን የዘረኝነት (ዚኖፎቢክ) ጥቃት፣ የአገሪቱ መንግሥት በፍጥነት እንዲያስቆም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በጋራ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጥሪው የተላለፈው በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የሩዋንዳውን ፕሬዚዳንት የአዲስ አበባ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በተመለከተ ሚያዝያ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት የፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜን የሥራ ጉብኝት አስመልክቶ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ የተገኙ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች ግን አጀንዳውን ቀይረው በደቡብ አፍሪካ ወደተከሰተው የዘረኝነት ጥቃትና ግድያ ወስደውታል፡፡

‹‹እንደ አፍሪካዊ ሁላችንም የሚሰማን ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድና ከቅኝ ግዛት ጭቆና ነፃ ለማውጣት ሁላችንም አስተዋጽኦ ማድረጋችንን ነው፤›› በማለት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ይህንን በማድረጋችንም ሁሉም አፍሪካዊ በመተባበርና በጋራ በተመቸው የአፍሪካ አገር የመኖር መብት ይኖረዋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን የዚያን አገር ሕግና ደንብ መከበር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተከሰተውን የዘረኝነት ጥቃት ድንገተኛ ክስተት አድርገው እንደሚቆጥሩት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የአገሪቱ ገዥ ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረንስ (ኤኤንሲ)፣ እንዲሁም የአገሪቱ መንግሥት እንዲገታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ አክለውም የአገሪቱ መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ይህንኑ እንደሚያደርግ እርግጠኝነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ‹‹ግጭቱ ባይከሰት እንመኝ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት ግጭቱ ሳይስፋፋ እንደሚገታው እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

የአፓርታይድ ጭቆና በደቡብ አፍሪካ ካበቃና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ1994 ከተመሠረተ በኋላ፣ የጥቁር ደቡብ አፍሪካውያንን የበላይነት ለማረጋገጥ የዘረኝነት እንቅስቃሴ ጅምር መታየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የደቡብ አፍሪካ የስደተኞች ፕሮግራም እ.ኤ.አ. በ2004 አጥንቶ ያሳተመው ሰነድ እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ ደቡብ አፍሪካውያን ደቡብ አፍሪካውያን ካልሆኑ ዜጐች ጋር ተቻችሎ የመኖር ባህል ማጣት መጀመራቸውን፣ የውጭ ዜጐችንና አፍሪካውያን ስደተኞችን ማጥቃት መጀመራቸውን ይገልጻል፡፡

‹‹ሂዩማን ሳይንስ ሪሰርች ካውንስል›› የተባለ ተቋም በሌላ በኩል ባደረገው ጥናት፣ ደቡብ አፍሪካውያን ሌሎች የውጭ አገር ዜጐችና አፍሪካውያን ስደተኞችን ለማጥቃት የተነሱባቸውን አራት ምክንያቶች ያስቀምጣል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ሥራ ማግኘትን፣ የፍጆታ ዕቃዎችና የመኖሪያ ቤቶችን ለማግኘት ፉክክር ውስጥ መግባታቸውን በዋነኛ አንስቷል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ አካባቢ ለደቡብ አፍሪካ ፓርላማና ለሕዝባቸው ንግግር ያደረጉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ ‹‹ደቡብ አፍሪካውያን በአጠቃላይ ዘረኞች አይደሉም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ከፍተኛ ቁጥር ካለውና ውጤታማ በሆነ መንገድ ከማኅበረሰቡ ጋር ከተቆራኙት የውጭ ዜጐች ጋር በየአካባቢው ባልኖሩ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የዘረኝነት ስያሜውን ይከላከሉ እንጂ ድርጊቱን ግን በእጅጉ አውግዘዋል፡፡ ‹‹ይህ አስደንጋጭና ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ነው፡፡ በምንም ሁኔታ የሚገለጽ የበታችነት ስሜትና ንዴት ለድርጊቱ ምክንያት ሊሆን አይችልም፤›› ብለዋል፡፡

በተፈጠረው ግጭት ሦስት ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን፣ ሁለቱ በተኙበት በደቡብ አፍሪካውያን ቤታቸው በመቃጠሉ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን፣ የሌሎች አገሮች በርካታ ዜጐች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉና በሕይወት እያሉ በእሳት ሲቃጠሉ በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል፡፡  

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ በጥቃቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ መገደሉን፣ የአገሪቱ መንግሥት የፖሊስ ሠራዊት በአግባቡ በማሰማራት ኢትዮጵያውያንን እንዲከላከሉ እንዲደረግ፣ ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር መነጋገሩን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...