የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ ያቀረቡ ባለሀብቶችን ማስተናገድ አለመቻሉ ተጠቆመ፡፡ አስተዳደሩ ለባለሀብቶቹ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያልቻለው ኅዳር 2004 ዓ.ም. የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምንጮች እንደገለጹት በሪል ስቴት፣ በጤናና በትምህርት ተቋማት፣ በባለኮከብ ሆቴሎች ልማት ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ከ15 በላይ ባለሀብቶችን ጥያቄ ማስተናገድ አልቻለም፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ንግድ እያካሄዱበት ያለውን ቦታ በአክሲዮን ተደራጅተው ለማልማት የሚፈልጉ፣ በአዋጅ 47/67 ምክንያት በይዞታቸው ውስጥ የተወረሱ የቀበሌ ቤቶች ያሉባቸውና የማስፋፊያ ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለሀብቶች፣ በአጠቃላይ በአዋጁ ምክንያት ሊስተናገዱ እንዳልቻሉ ምንጮች አስረድተዋል፡፡
በዚህ ምክንያት በርካታ ባለጉዳዮች በየጊዜው አስተዳደሩን ቢጎበኙም፣ ከአስተዳደሩ ምላሽ በማጣታቸው እያማረሩ የሚገኙ ባለሀብቶች ቁጥር በርካታ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አስረድተዋል፡፡ የሊዝ አዋጁ በተለይ መሬት ለተጠቃሚው የሚቀርበው በሊዝ ጨረታ እንዲሆንና አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች ደግሞ በልዩ ሁኔታ እንደሚስተናገዱ ይደነግጋል፡፡
ነገር ግን አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ፕሮጀክት በትክክለኛው መንገድ መግለጽ ባለመቻሉ ሪል ስቴቶች፣ ትምህርትና ጤና ተቋማት፣ ባለኮከብ ሆቴሎች በልዩ ጨረታ እንደሚስተናገዱ ይገልጻል፡፡
ከዚህ ውጪ ደግሞ አክሲዮን ኩባንያዎች አስተዳደሩ ባሉበት ቦታ ላይ መልሶ ማልማት አካሂዶ በነፍስ ወከፍ 25 ካሬ ሜትር ቦታ ካልቀረበላቸው በስተቀር አይስተናገዱም፡፡ በደርግ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት ትርፍ ቤቶች ሲወረሱ፣ በአንድ ግቢ ውስጥ የቀበሌ ቤቶች የሚገኙባቸው ባለይዞታዎች በንብረታቸው ላይ አዲስ ልማትም ሆነ፣ ዕድሳት ማካሄድ አለመቻላቸው ከፍተኛ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ ንብረታቸውም ወደ ግብይት ሥርዓት ማስገባት ባለመቻላቸውም ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸው ይነገራል፡፡
ሌላኛው አስቸጋሪ ማነቆ ሆኗል የተባለው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ልማቶች የሚያቀርቡት የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄ መስተናገድ ያለመቻሉ ነው፡፡ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡ ባለሀብቶች፣ ሕገወጦችን ሥርዓት ለማስያዝ ሲባል የወጣው የሊዝ አዋጅ የከተማውን ልማት አንቆ ይዟል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ይህ አዋጅ እንዲሻሻል ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለአስተዳደሩ ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዋጁን ማሻሻል የአስተዳደሩ ሥልጣን ሳይሆን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኃላፊነት ነው፡፡
ነገር ግን አቶ አባተ እንዳስረዱት፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚዎች በአጭር ጊዜ ጥያቄያቸው እንዲስተናገድ መመርያ ወጥቷል፡፡ ችግሩ ያለው ግን በአገልግሎት ዘርፍ ማለትም በሪል ስቴት፣ በትምህርት፣ በጤና ተቋማትና በሆቴል ዘርፍ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች እንደቀድሞው በድርድር መሬት የማግኘት ፍላጎት ያላቸው በመሆናቸው ነው ብለዋል፡፡
አልሚዎቹ ድርድር የሚፈልጉት የመሬቱ ዋጋ አነስተኛ ስለሆነና የሚያለማውም የማያለማውም ባለሀብት መሬቱን ለመያዝ የሚያደርገው መሯሯጥ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ያም ሆኖ ግን የአዋጁ አንዳንድ ክፍሎች በድጋሚ መታየት አለባቸው፤›› በማለት አቶ አባተ ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ የሊዝ አዋጅ የአዲስ አበባ የመሬት ወረራን በማስቀረት፣ የሙስናን በር በመዝጋትና ውስን የሆነውን የመሬት ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም እንዳስቻለ አቶ አባተ ገልጸው፣ ለልማቱ እንቅፋት የሆኑ የአዋጁ አንዳንድ ክፍሎች ግን በቀጣይነት ይታያሉ ብለዋል፡፡