Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ ጭማሪ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹማምንት ጥያቄ ማንሳታቸው ተጠቆመ

በኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ ጭማሪ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹማምንት ጥያቄ ማንሳታቸው ተጠቆመ

ቀን:

‹‹ጭማሪው የቤት ባለቤት የመሆን ተስፋችንን አጨልሞታል›› ቤት የደረሳቸው ነዋሪዎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጋቢት 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ለአሥረኛ ጊዜ ለባለዕድለኞች ዕጣ ባወጣባቸው 35 ሺሕ ቤቶች ዋጋ ላይ ያደረገው ጭማሪ፣ ለምንና እንዴት ሊጨመር እንደቻለ የአስተዳደሩ ሹማምንት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው፣ የቤቶቹን ግንባታ ለማስፈጸም በኃላፊነት እየሠሩ ያሉትንና የሚመለከታቸውን አካላት ሰሞኑን መጠየቃቸው ተጠቆመ፡፡

ምክትል ከንቲባው አቶ አባተ ስጦታውና ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንት ሚያዝያ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በካቢኔው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ፣ በየክፍላተ ከተማው ለሚገኙት ለሚመለከታቸው የቤቶች ግንባታ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጆችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች፣ አብዛኛውና ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የግንባታ ግብዓቶች ከአገር ውስጥ መግዛት ተችሏል፡፡ የግንባታ ዋጋው ቀንሶ እያለ በኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ላይ ዋጋ ሊጨመር የቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲብራራላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አብዛኛዎቹ የስብሰባው ታዳሚዎች ምንም ምላሽ ሊሰጡ አለመቻላቸውን የገለጹት ምንጮች፣ ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የተገኙ አንድ ኃላፊ ዋጋ የጨመረበትን ምክንያት ለማብራራት የሞከሩ ቢሆንም፣ የሹማምንቱን ጥያቄ በአግባቡ ማስረጃ በማቅረብ አልቻሉም በሚል፣ ግሳፄ የተሞላበት የአፀፋ ምላሽ እንደተሰጣቸው ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በኮንዶሚኒየም ቤቶቹ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ዋና መነሻ፣ ግንባታውን ተከታትሎ የሚያስፈጽመው በቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን ቢሮ ሥር የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የማኔጅመንት ችግር እንጂ፣ የገበያ ጉዳይ አለመሆኑም እንደተገለጸ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ከግንባታ ግብዓት ግዢ፣ ከኮንትራክተሮች፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከሚቀርቡ ግብዓቶችና ከሌሎችም ጋር በተያያዘ የተፈጠረ ችግር ለዋጋ መጨመር ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ በስብሰባው ላይ መጠቆሙን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በተለይ በዕጣው ዕድለኛ የሆኑ የከተማው ነዋሪዎች በሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ነገር እንዲያነሱ ዓይነተኛ ምክንያት መሆኑን፣ ከፍተኛ የአስተዳደሩ ሹማምንት ባላወቁት ምክንያት የተደረገው የዋጋ ጭማሪ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ማብራራታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከግዢና ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር በተገናኘ የባከነን ገንዘብ ለማካካስ የሚደረገው ሩጫ አግባብ አለመሆኑን፣ አንድ ሕንፃ ሲገነባ የሚያስፈልጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ፣ ለሕንፃው የዋለውና የቀረው ግብዓት የሚታወቅበት የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ መሥራት ሲገባ፣ ይኼ ባለመደረጉ ችግሮች እንደተፈጠሩና እየተፈጠሩ መሆኑን ምንጮቹ አብራርተዋል፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማወራረድ ባለመቻሉ፣ ምናልባትም እሱን ለማካካስ የተደረገ ጭማሪ ሳይሆን እንደማይቀርም ተገምቷል፡፡ በግዢ ወቅት የሚፈጸም ክፍተትና የማስተዳደር ችግር በስፋት እየታየ መሆኑንም አክለዋል፡፡

በአሥረኛው ዙር ለባለዕድለኞች በዕጣ በወጡት ኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ በተደረገው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት፣ በተለይ በቂ የሆነ ገቢ የሌላቸው ዕድለኞች፣ የቤት ባለቤት የመሆን ተስፋቸውን እንዳጨለመባቸው እየገለጹ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም. መገባደጃ የ1997 ዓ.ም. ተመዝጋቢዎች በድጋሚ በሚመዘገቡበት ወቅት፣ እንዳቅማቸው መክፈል ለሚችሉት ቤት መመዝገባቸውን የገለጹት ነዋሪዎች፣  አስተዳደሩ ቤቱን የሚያስረክበው መቶ በመቶ ተገንብቶና ሁሉ ነገር አልቆለት መሆኑን በመግለጽ ዕጣ ሲደርሳቸው የተደሰቱ ቢሆንም፣ ጭማሪ የተደረገበትን ሲመለከቱ ግን ተስፋ በመቁረጥ ‹‹የቀበሌ ቤት ይሻለናል›› ለማለት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግሥትም ሆነ አስተዳደሩ ቤት የሌላቸውን ባለቤት ማድረግና ወደ ተሻለ የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር አንፃር፣ እንዲሁም ዜጐቹን የመደጐምና የመርዳትም ኃላፊነት ስላለበት፣ ቀድሞ ሲመዘገቡ በነበረው ዋጋ እንዲከፍሉ በማድረግ የሰጣቸውን ዕድል እንዳይነፍጋቸው ጠይቀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ከ240 ሺሕ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን የገነባና በመገንባት ላይ መሆኑን ከ136 ሺሕ በላይ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ማስተላለፉን የገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለ ማርያም ናቸው፡፡ በአሥረኛው ዙር በዕጣ የወጡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ፣ እንደሚወራው የተጋነነና ከአቅም በላይ የሆነ ሳይሆን 15 በመቶ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቤቶች ግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ላይ በ2005 ዓ.ም.፣ በ2006 ዓ.ም. እና በ2007 ዓ.ም. ጭማሪ እንደሌለ ያረጋገጡት የቢሮ ኃላፊው፣ በአስገራሚ ሁኔታ ከፍተኛ ወጪ እያስወጣ ያለው የሠራተኛ ዋጋ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ሳይቶቹ ከመሀል ከተማ እየራቁ በሄዱ ቁጥር የሠራተኛ ዋጋ ባለበት ሊቀጥል እንዳልቻለ የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ በቀን 35 ብር ይከፈለው የነበረ አንድ የቀን ሠራተኛ አሁን በእጥፍ መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡ የባለሙያውም ክፍያ በዚያው ልክ ምን ያህል እንደጨመረ መገመቱ አዳጋች አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩና መንግሥት 43 በመቶ የሚጠጋ ወጪ ለቤት ድጐማ ማድረጋቸውን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፣ በግንባታ ግብዓቶች ላይ ዋጋ ቢቀንስም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ዋጋ እንደሚጨምር መታወቅ እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ አሁን በወጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ 15 በመቶ ዋጋ የተጨመረ ቢሆንም፣ ቀደም ብለው በወጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ከተደረገው ጭማሪ በግማሽ ያነሰ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የቤቶች ግንባታ ፕሮግራም መኖሩ የቤት ችግርን መቅረፍ ብቻ ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ዓላማዎች እንዳሉት የገለጹት ደግሞ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን መንግሥቱ ናቸው፡፡ የቤቶቹ ዋጋ የሕዝቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በቤቶች ግንባታ ጥራት ላይ የሚነሳው አግባብ ያልሆነ አስተያየት ካለማወቅ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፣ አስተዳደሩ ቤት ከማስገንባቱ በፊት የአፈር ምርመራ ጥናት ያደርጋል፣ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ በሱፐርቫይዘር እያንዳንዱን አካሄድ ቁጥጥር ስለሚደረግበት ምንም የሚያጠራጥር ችግር የለም ብለዋል፡፡

በአሥረኛው ዙር በአንድ ጊዜ 35 ሺሕ ቤቶች በመውጣታቸው በርካታ ነዋሪዎች ባለዕድል መሆናቸውን የገለጹት አቶ መስፍን፣ አብዛኛዎቹ የተደሰቱ ቢሆንም ጥቂቶች ድጐማ ተደርጐላቸውም መክፈል ስለማይችሉ፣ እነሱን ምክንያት ተደርገው ብዙ ሊባል ቢቻልም እውነታው ግን የተገላቢጦሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡     

ዋጋው የተጨመረው በድብቅ ሳይሆን ከንቲባው ሳይቀሩ ይፋ አድርገው፣ እንዲሁም በምዝገባ ወቅት እንደ ግንባታው ወጪ ሁኔታ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል መገለጹን አስታውሰዋል፡፡ በነፃ በመገንባት ማስረከብ ካልሆነ በስተቀር መንግሥት የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡ የአሥረኛው ዙር ባለዕድለኞች እንዴት ቤታቸውን እንደሚረከቡና ውል እንደሚፈጽሙ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...