Monday, July 15, 2024

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ያለመው ሌላው አማራጭ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያና የኤርትራ ምሁራን በሁለቱ አገሮች ጉዳይ ላይ ሐሙስ ኅዳር 7 ቀን 2010 ዓ.ም. የጋራ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ በውይይቱ ላይ ኤርትራን በመወከል ለረዥም ዓመታት በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ፣ እንዲሁም ከኤርትራ ሸሽተው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራውያን፣ ከስደተኛ ካምፖች ተወክለው የመጡ ኤርትራውያን ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲገኙ፣ ኢትዮጵያን በመወከል ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ውጭ አገር የቆዩ ዳያስፖራዎች፣ የሚዲያ ኃላፊዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡

በሐርመኒ ሆቴል የተካሄደው የሁለቱ አገሮች የምሁራን ውይይት ዋና ዓላማም የሁለቱን አገሮች ወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦች ለማቀራረብ ያለመ ነበር፡፡ ‹‹የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች›› የሚል መሪ ቃል ነበረው፡፡ በመንግሥታት መካከል ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በመፍታት፣ እንዴት ነው ሁለቱን ሕዝቦች ማቀራረብ የሚቻለው የሚሉ ጉዳዮች ተነስተው ነበር፡፡

ውይይቱን በዋናነት ያዘጋጀው ‹‹ሰለብሪቲ ኢቨንትስ›› የተባለ ተቋም ነው፡፡ በውይይቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ኃላፊ አቶ ሀብቶም ገብረ ሊባኖስ፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹የዛሬው ውይይት ዓላማም በምሁራን መካከል መግባባት በመፍጠርና ወደፊት መሥራት ያለብንን ጉዳዮች በዝርዝር በመለየትና የጋራ መግባባት በመፍጠር ለመንቀሳቀስ ያመች ዘንድ የተዘጋጀ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች ምሁራን መካከል የጋራ መግባባት በመፍጠር ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ መታቀዱንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ በዚህም በቅርቡ ሁለት መቶ ኤርትራውያንን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ውይይት ለማድረግ መታቀዱንም ጠቁመዋል፡፡ ይህን ለማስፈጸምም ኤርትራ ድረስ አዘጋጆቹ በመሄድ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመነጋገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁለት መቶ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ መጥተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ኤርትራውያን አርቲስቶችን ታዋቂ ሰዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ አራት መቶ ያህል ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ውይይትና የተለያዩ ኮንሰርቶች ለማዘጋጀት መታቀዱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ሲባልም የኢትዮጵያ መንግሥት ለአራት መቶ ኤርትራውያን ነፃ ቪዛ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኤርትራን ምሁራን በመወከል የተገኙት አንድ ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹በሁለቱ አገሮች መካከል በ1990 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ጦርነት እስከ ዛሬ ድረስ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በዚህም የተነሳ አንድ የነበሩ ሕዝቦች በመለያየት ማዶና ማዶ ሆነው አብረው እንዳልበሉና እንዳልጠጡ ዛሬ ተለያይተዋል፡፡ ይህን በፖለቲካ ምክንያት የተለያየ ሕዝብ አንድ የማድረግ ኃላፊነት ደግሞ በእኛ ላይ የወደቀ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የሁለቱን አገሮች ምሁራን የጋራ ውይይት በዋናነት የመሩት በተመራማሪነታቸውና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በማስተማር የሚታወቁት ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ  ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኔ ለውይይቱ መነሻ ይሆን ዘንድ አጭር የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩ በመነሻ ጽሑፋቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያሉት ፖለቲካዊና ወታደራዊ ግጭቶች የሰው ሕይወትን በመቅጠፍ፣ የኢኮኖሚ ዕድገታቸውን በማጓተት፣ የተራዘመ አለመረጋጋት በመፍጠርና ለንዑስ ቀጣና የተረፈ ትርምስ በማስከተል በሁለቱም አገሮችና ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ የሁለቱ እህትማማች አገሮች ህልውናና ደኅንነት ላይ አውዳሚና የረዥም ጊዜ ተፅዕኖ ያላቸው አዳዲስ ሥጋቶች ጉልበት እያገኙ በመሄድ ላይ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር መድኃኔ በጽሑፋቸው ላይ ኢትዮጵያውያንንና ኤርትራውያንን ለማቀራረብ እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ቅንጅት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህ ደግሞ የተደቀኑባቸው የሰላምና የደኅንነት ፈተናዎችን ለመመከት ያላቸውን አቅም በሚገባ እንዳይጠቀሙ ከማገድ በተጨማሪ፣ አኮላሽቶ ለግል ሥቃይ ይዳርጋቸዋል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ አዙሪት የሚያወጣቸው የተቀናጀና ምልዓተ ቀጣናውን ያቀፈ ሥልት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን መካከል ዘላቂነት ያለው ገንቢ ግንኙነት እንዲያንሰራራ የሚረዳ ጥረት ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ ነው፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት እንዲኖር መወሰድ ያለባቸው የመጀመርያ ዕርምጃዎች ምን ምን ናቸው? ሁለቱም እህትማማች አገሮች የጥላቻ አዙሪት ውስጥ ተዘፍቀው ሊያስቀጥሉ የሚችሉ አሳማኝ ምክንያቶች አሉን? በዚህ ረገድ የታሪክና የባህል ሚና ምንድነው? ታሪክና ባህልን በተመለከተ ቀናነት ያለው ውይይት ሳይደረግ አሁን ያለውን የተካረረ ግንኙነት ለማስተካከል የሚረዳ የጋራ መደላደል ማግኘትስ ይቻላል ወይ? ዕርቅ ለማውረድና መልካም ዝምድናን ለመመለስ ያለው ዕድል ምንድነው? ዴሞክራሲና ልማት በሁለቱም አገሮች ለማረጋገጥ ያለው ዕድልስ ምን ያህል ነው? ግንኙነታቸውን ለማሻሻል፣ ቀውስን ለመግታትና ግጭቱን ለመፍታት የሚበጁ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችስ በምን መንገድ ሥራ ላይ ሊውሉ ይችላሉ? ለምንድነው ሁለቱ አገሮች እርስ በርሳቸው ለመፋለምና ለመጠፋፋት የተሠለፉት? ይህ እንዴት ነው በአገሮቹ ካለው የፖለቲካ ሁኔታና የሥርዓቶች ባህሪያት ጋር የሚያያዘው? ይህ ክስተት ስትራቴጂያዊ ጥቅምን ወይም ታሪክን በሚገባ አለመተንተን፣ እንዲሁም የጋራ ዕጣ ፈንታን በትክክል አለመረዳት ያስከተለው ሊሆን ይችላል? ስትራቴጂካዊ አቅሞቻቸው ወይም የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የወለደው ቢሆንስ? በአካባቢው ልዕለ ኃያል አገር ካለመኖሩ ጋር ተያይዞና የግብፅ በተጓዳኝነት መኖር ሲታይ ለግጭት ተጋላጭነቱ በንዑስ ቀጣናው ካለው የሥልጣን መዋቅራዊ አደረጃጀት ጋር የተሳሰረ ይሆን? እንዲያ ከሆነ ይህንን መዋቅራዊ ችግር ለማረም ምን ማድረግ ይቻላል?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ለመወያያነት አቅርበዋል፡፡

ፕሮፌሰር መድኃኔ ለመወያያነት የሚያግዙ ሌሎች ጥያቄ አዘል ሐሳቦችንም አቅርበዋል፡፡ ‹‹በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግጭት ለአገራዊ ደኅንነት ጠባብ አተረጓጎም ከመስጠትና መንግሥታዊ ሥልጣንን ለማስቀጠል ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች የመነጩ ከሆኑስ?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ምሁራን የጋራ ውይይት የማድረግ አስፈላጊነትንም በጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትን በተመለከተ ያለው ልዩ ሁኔታ ምንድነው? ግንኙነታቸውን በተመለከተ ሊኖሩ ይገባል የሚሉዋቸው ገዥ መርሆዎች ምንድናቸው? ይህንን ለማሳካት መቋቋም ያለባቸው ተቋማት ምን ዓይነት ናቸው?›› የሚሉትንም አቅርበዋል፡፡ በሁለቱ አገሮች ምሁራን መካከል ስብሰባ ማካሄድም ከፊት ለፊታቸው የተጋረጡ ሥጋቶች ምንነትና ውስብስብነታቸው ላይ መግባባት እንዲፈጥሩ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡ የምሁራንና የሲቪል ማኅበረሰብ ግንኙነቶች ከማድረግ  ባሻገርም አቅጣጫ ሊያሲይዙ በሚችሉ መርሆዎች ላይ በመመራት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ሁሉን አሳታፊ ቅኝት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

የሁለቱን አገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ዕውን ለማድረግ በሦስት የተከፈሉ ግቦችን አቅርበዋል፡፡ የረዥም፣ የመካከለኛና የቅርብ ጊዜ ግቦች በማለት፡፡ የረዥም ጊዜ ግብ ብለው ያቀረቡት በኢትዮጵያና በኤርትራ አስተማማኝ የደኅንነት ቀጣና ማስፈን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የመካከለኛ ጊዜ ግብ ብለው ካስቀመጧቸው ጉዳዮች መካከል ደግሞ የሁለቱን አገሮች ምሁራንና ሲቪል ማኅበረሰቦች ጨምሮ በአገሮቹ መካከል ስላለው ግጭት  ሐሳብ በመለዋወጥ መፍትሔዎችን እንዲጠቀሙ ዕድል እንደሚፈጥር፣ የአገሮቹ የአሁንና የድሮ ባለሥልጣናትንና የሲቪል መብት ተሟጋቾችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ሁለቱንም ወገኖች የሚያግባቡ የጋራ አጀንዳዎችን ለመለየት ዕድል እንደሚሰጥ፣ በየመን ያለው ጦርነትና የውጭ ኃይሎች ወታደራዊ ግስጋሴዎችና ከፊት ለፊት የተደቀኑ ዓበይት የሰላምና የደኅንነት ተግዳሮቶችን በተመለከተ ውይይት ለማካሄድ ዕገዛ እንደሚያደርግ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ የአገራዊ ደኅንነት ፍላጎቶች የት የት ላይ እንዳሉ ለማሳየትና ለማጉላት እንደሚረዳና ሌሎች ግቦችንም ያካተተ እንደሚሆን ዘርዝረዋል፡፡

የቅርብ ጊዜ ግቦች ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከልም የምክክር ሒደቱን በመጀመር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የጋራ መድረክ ይፋ ማድረግ፣ በምሁራንና በሲቪል ማኅበረሰቦች ቡድኖች መካከል የምክክር ዓውድ መፍጠር፣ የጋራ ዓላማና ቁርጠኝነትን መገንባት፣ ማንፀባረቅና ምክክሩን ወደፊት ለማራመድ የሚረዳ መዋቅር ለመዘርጋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ ፕሮፌሰር መድኃኔ የውይይት መነሻ ጽሑቸውን ካቀረቡ በኋላ ጥያቄዎችና አስተያየቶች እንዲቀርቡ ለተሳታፊዎች ዕድል ተሰጥቷል፡፡

ኢትዮጵያን በመወከል ተሳታፊ የነበሩት የመጀመርያውን ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ጌታቸው አረጋዊ ሲሆኑ፣ እሳቸውም በሁለቱ አገሮች ምሁራን መካከል የተደረገውን ውይይት አድንቀው፣ ይህንን ዓላማ ወደ መሬት ለማውረድ በሚደረገው ጥረት የኢሳያስ መንግሥት ምን ያህል ፈቀደኛ ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ‹‹ከኢሳያስ ከራሱ ካልመጣ እሱን አሳምኖ መሥራት ይቻላል ወይ?›› ብለዋል፡፡ ለጥያቄያቸው ፕሮፌሰሩ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ይህን መሰል ውይይት ማድረግ ያለብን ኢሳያስ የሚመራትን ኤርትራን በመሣል ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት የሚመጣውን መንግሥትና ሕዝብ ጭምር በማካተት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አሁን ያለውን ኃይል አሟጦ በመጠቀም ኢሳያስንም ቢሆን በማሳመን ለመሥራት መታቀዱን አስረድተዋል፡፡

ማንነታቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ኤርትራን በመወከል ተሳታፊ የነበሩ አንድ ግለሰብ በበኩላቸው፣ ሁልጊዜ ከፖለቲካ አኳያ መሄድ የለብንም ብለዋል፡፡ ሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች በሌሎች ጉዳዮች ማስተሳሰርና የወደፊት መፃኢ ዕድላቸው በአንድነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መነሻ ጽሑፍ ላይም ኢትዮ-ኤርትራ እየተባለ ከሚቀርብ ኤርትራ-ኢትዮጵያ ተብሎ መቅረብ እንደነበረበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩም ኤርትራ-ኢትዮጵያ ብሎ ማስተካከል እንደሚቻል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ማንነታቸውን ያልገለጹ ሌላው ኤርትራን ወክለው የተገኙት ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹ኤርትራ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ሰው ስለሚተነፍሰው አየር ሁሉም እየተጨነቀ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግሥት የዴሞክራሲና የልማት ሁኔታ በማነፃፀርም ያቀረቡ ሲሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንኳን ዜጎች እኛ ከኤርትራ የመጣን ስደተኞች በነፃነት እየኖርን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀምም፣ የኤርትራ ሕዝብ ለወደፊት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለሚደረገው ውይይት ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ወገን የተገኙት አቶ አበበ ዓይነቴ ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ ውስጥ ስላላቸው ማኅበራዊ ኑሮ አውስተዋል፡፡ እንደ አቶ አበበ ገለጻ፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባ ቢኖሩም፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተቀራርበው እየኖሩ አይደለም፡፡ እሳቸው በሠሩት ጥናት ኤርትራውያን ስደተኞች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በማኅበራዊ ሕይወታቸው አብረው እንደማይኖሩ ማረጋገጠጣቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ባለፈው ዓመት በሠራሁት ጥናት ኤርትራውያን ስደተኞች በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ የሚኖሩት ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱና ገበያ ሲገበያዩ አብረው፣ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ እንዲሁም ማኅበር ሲጠጡ ኤርትራዊያንን እንጂ ኢትዮጵያዊያንን አይመርጡም፤›› ብለዋል፡፡

አውሮፓና አሜሪካ ለረዥም ዓመት የቆዩ አንድ ኢትዮጵያዊ በዚህ ሐሳብ እንደሚስማሙ ቢገልጹም፣ የ‹ሰለብሪቲ ኢቨንትስ› ኃላፊ ግን ውድቅ አድርገውታል፡፡ ‹‹እኛ ከኤርትራውያን ጋር ማኅበር አለን፡፡ አብረን የምንውለውና ማኅበራዊ ጉዳያችንን የምንከውነው ከእነሱ ጋር ነው፤›› ሲሉ የአቶ አበበን አስተያየት ተቃውመዋል፡፡

ኤርትራን ወክለው የተገኙት አብዛኞቹ ምሁራን ጥያቄና አስተያየታቸውን ያቀርቡ የነበረው በትግርኛ ሲሆን፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በትግርኛ ቋንቋ ሐሳብና ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን ተቃውመዋል፡፡ መድረኩን ሲመሩ የነበሩት አቶ ዳደ ደስታ፣ ኤርትራን በመወከል የተገኙት ምሁራን በትግርኛ ቋንቋ ሐሳባቸውን ያቀረቡበት ምክንያት ሐሳባቸውን በቀላሉ ለመግለጽ ከማሰብ እንጂ በሌላ ምክንያት እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

በውይይት ላይ ታሪክ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መካከል ቅራኔ እንደፈጠረ ተነስቶ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፣ ፕሮፌሰር መድኃኔ ‹‹የሚጠቅመንን ታሪክ ይዘን ሁለቱን እህትማማች ሕዝቦች ማቀራረብ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በባህልና በቋንቋ ከመመሳሰላቸው ባሻገር በደም የተሳሰሩ ሕዝቦች መሆናቸው፣ ሁለቱን ሕዝቦች ወደ ቀድሞ ግንኙነታቸው ለመመለስ ብዙ ሙከራዎች መካሄዳቸው፣ ከተለያዩ አገሮች እስከ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአገር ሽማግሌዎች እስከ ሃይማኖት አባቶች ሙከራዎች መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ በሁለቱ አገሮች በተለይም በ1990 ዓ.ም. በመካላቸው ከተቀሰቀሰው ጦርነት ወዲህ ሰላምም ሆነ ጦርነት በሌለበት ቀጣና ይኖራሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ግለሰቦች ሁለቱን አገሮች ለማደራደር በእንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ ቢታወቅም፣ የሁለቱ አገሮች ምሁራን ውይይት ደግሞ ሌላ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ብዙዎችም በዚህ ውይይት ላይ ተስፋ እንዳላቸው ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡

በሁለቱ አገሮች ምሁራን መካከል የተደረገው ውይይት ግማሽ ቀን የፈጀ ሲሆን፣ በቀጣዩም ተመሳሳይ ውይይት ለማካሄድ በመግባባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -