Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማነቆ የሆኑ ሕጎች እንዲሻሻሉ ጠየቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ ነጋዴዎች የብቃት መመዘኛ መመርያና የሊዝ አዋጁ እንዲሻሻል ጠየቁ፡፡ ሚያዝያ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ በተካሄደው ውይይት፣ ሁለቱ ሕጎች ለንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ማነቆ እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ይህንን ስብሰባ የመሩት የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማና የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ፣ ሁለቱ ሕጎች ያሉባቸው ችግሮች ታይቶ ማሻሻያ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ነጋዴዎች እንዳሉት፣ በተለይ የብቃት ምዘናው ነባራዊ ሁኔታን ያገናዘበ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አዲስ አበባ ጥንታዊ ከተማ በመሆኗ፣ ያሏት የመገበያያ ሕንፃዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም፡፡ ሕንፃዎቹም ሆኑ የንግድ ቤቶች የቀበሌና የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ንብረቶች ናቸው፡፡

በብቃት መመዘኛው መመርያ መሠረት በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሆቴል ሥራ ለማካሄድ የሚመጠጥ መፀዳጃ ቤት ይጠየቃል፡፡ የአትክልትና የፍራፍሬ ንግድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሴራሚክ ሊገነቡ ይገባል ይላል፡፡

‹‹ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?›› በማለት የአዲስ አበባ ነጋዴ ፎረም አባላት ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ የሚገኙ ጋራዦች 40 ዓመታት ያለፋቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጎናቸው ትምህርት ቤት ቢከፈት የብቃት መመዘኛው፣ ጋራዦች ከትምህርት ቤት አጠገብ ሊገነቡ አይገባም ተብሎ ጋራዦቹ እንዲነሱ ይደረጋል፡፡ ይህ አግባብ አይደለም በማለት በአጠቃላይ የብቃት መመዘኛ መመርያው በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባ ነጋዴዎቹ ጠይቀዋል፡፡ የነጋዴ ፎረም አባላቱ ጥያቄ ከተሰብሳቢዎች ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱን ሪፖርተር መረዳት ችሏል፡፡

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ እንዲሻሻል የተጠየቀው፣ በአክሲዮን ተደራጅተው ያሉበትን አካባቢ ማልማት የሚፈልጉ ነጋዴዎች ቦታ ማግኘት አለመቻላቸው ነው፡፡

እነዚህ ነጋዴዎች የንግድ ሥራ በሚያካሂዱበት ቦታ በአክሲዮን ተደራጅተው የንግድ ሥራ ለማካሄድ የቦታ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ በሊዝ አዋጁ ምክንያት ጥያቄያቸው መስተናገድ የማይችል በመሆኑ ምሬታቸውን በስብሰባው ላይ ገልጸዋል፡፡

‹‹መንግሥት 12 የገበያ ማዕከላትን ለመገንባት አቅዷል፡፡ የገበያ ማዕከላቱን የመገንባቱን ኃላፊነት ለእኛ ይስጠንና መንግሥት ትምህርት ቤት፣ ጤና ማዕከልና መንገድ ይገንባ በማለት ገልጸዋል፤››  በማለት ጠይቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መሬት ከጨረታ ውጪ የሚገኝበት መንገድ ጠባብ በመሆኑ ነጋዴዎቹ ሊያካሂዱት የሚፈልጉትን ልማት ማካሄድ ካለመቻላቸው በተጨማሪም፣ ከዛሬ ነገ መሬት ይገኛል በማለት እየተጉላሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ የሊዝ አዋጁ ያሉበት ክፍተቶች እየታዩ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ ውሳኔ ላይ እንደሚደረስና የከተማው ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

አቶ ከበደ በበኩላቸው፣ የብቃት ማረጋገጫ መመርያው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው ማነቆ የሆኑ ክፍተቶች እየታዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  መመርያውን ለማሻሻል ጥናት መጀመሩን ጨምረው አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች