Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናእነ አቶ መላኩ ፈንታ የቀረበባቸው ክስ ተሰርዞ እንዲሰናበቱ አቤቱታ አቀረቡ

እነ አቶ መላኩ ፈንታ የቀረበባቸው ክስ ተሰርዞ እንዲሰናበቱ አቤቱታ አቀረቡ

ቀን:

  • ዓቃቤ ሕግ አቤቱታውን ተቃውሞ ምላሽ ሰጥቷል
  • ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ሰጠ

በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ላለፉት ሁለት ዓመታት በክርክር ላይ የሚገኙትና በክስ መዝገብ 141352 ላይ ከተካተቱት ውስጥ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና ሌሎች ተከሳሾች፣ የቀረበባቸው ክስ ተሰርዞ በነፃ እንዲሰናበቱ ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቀረቡ፡፡

በፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ የተመሠረተባቸውን ክስ እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት አቤቱታ ያቀረቡት አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ስማቸው ከበደ፣ አቶ ገብረ ሥላሴ ኃይለ ማርያም፣ ነፃ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ሌሎችም ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ የአቤቱታ ማመልከቻ ያስገቡበትና ክሱ እንዲሰረዝላቸው የጠየቁበት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን የሚመለከተው አዲስ አዋጅ ቁጥር 859/2006 እነሱ የተከሰሱበትን ክስ ውድቅ እንዳደረገው በመግለጽ ነው፡፡

አቶ መላኩ በክስ መዝገብ 141352 ላይ ሦስት ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን፣ የመጀመርያው ለሆቴል አገልግሎት ከቀረጥ ነፃ የገቡ ዕቃዎች ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ መዋላቸውን በሚመለከት መረጃ ቢደርሳቸውም፣ ከባለሀብቱ ጋር በመመሳጠር ምርመራ እንዳይጀመርና ለሕግ እንዳይቀርብ አድርገዋል የሚል ነው፡፡ የቀድሞዎቹ አዋጆች፣ አዋጅ 60/89፣ 368/95 እና 622/01 በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጉ ድንጋጌዎች የነበራቸው ቢሆንም፣ በአዲሱ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 181(1) ሙሉ በሙሉ ተተክተው፣ በአንቀጽ 163(1) መሠረት በአስተዳደር ውሳኔ በገንዘብ መቀጮ ብቻ የሚያልቅ እንዳደረገው በመግለጽ አመልክተዋል፡፡

ሌላው ቀርቦባቸው የነበረው ክስ ምንም ዓይነት የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸው፣ ገደብና ቁጥጥር የተደረገባቸውን 32 ዓይነት ብዛት ያላቸው የተለያዩ ዓይነት የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲገቡ ይያዛሉ፡፡ ክስ ተመሥርቶባቸውና ለፍርድ ተቀጥረው እያሉ፣ ያለ ሕጋዊ ምክንያት ክሱ እንዲነሳ አድርገዋል የሚል ክስ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ይህም ክስ ገደብና ቁጥጥር ከተደረገበት ዕቃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በቀደመው አዋጅ ወንጀል የነበሩት ድንጋጌዎች፣ በአዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 156(1) መሠረት ወንጀልነቱ ቀሪ መሆኑ ቀርቶ በአስተዳደራዊ ውሳኔ በገንዘብ መቀጮ የሚያልቅ መሆኑን ጠቁመው ክሱ እንዲሰረዝ ጠይቀዋል፡፡

ሁሉም ተከሳሾች (አቤቱታ ያቀረቡት) እንደ አቶ መላኩ ፈንታ የቀረበባቸው ክስ በአዋጅ ቁጥር 60/89፣ 368/95 እና 622/01 የነበረ መሆኑን በማስታወስ፣ በአዲሱ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 181/(1) መሠረት ሙሉ ለሙሉ የተሻሩ መሆኑን በመጠቆም፣ በተዘረዘሩት ተገቢ አንቀጾች መሠረት የቀረበባቸው ክስ እንዲሰረዝላቸው ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በሰጠው የአቤቱታ መቃወሚያ መልስ እንዳብራራው፣ እነ አቶ መላኩ ፈንታ የተከሰሱት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)ሀ እና 411 የተመለከተውን በመተላለፍ እንጂ፣ የጉምሩክ አዋጅ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ድንገተኛ ቆጠራ ተደርጐ ባለበት ሁኔታ ድጋሚ ቆጠራ በማስደረግ ቀረጥና ታክስ እንዲቀንስ ያስደረጉ በመሆናቸው፣ ባልተሰረዘ አንቀጽ ክስ እንዲነሳላቸው መጠየቃቸው አግባብ አለመሆኑን ገልጾ፣ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

ሌላው ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የተባሉት ተከሳሽ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ያልተፈጸመባቸውንና ገደብና ቁጥጥር የሚደረግባቸውን 32 ዓይነት የተለያዩ ብዛት ያላቸው የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በአራት ሻንጣዎች በአየር መንገድ ሲያስገቡ መያዛቸውን፣ ክስ ተመሥርቶባቸውና ለፍርድ ተቀጥረው ባለበት ሁኔታ ክሱ እንዲቀር ተደርጎላቸዋል ስለተባለው ዓቃቤ ሕግ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ ዕቃውን በመጀመርያ ሲያስገቡ መስመሩን የተከተለ በመሆኑ ፈቃድ እንዲያቀርቡ መጠየቃቸውን ገልጿል፡፡ ማቅረብ ባለመቻላቸው በሕጋዊ መንገድ ከአገር ዕቃውን እንዲያስወጡ ቢደረጉም፣ በድብቅ መልሰው ሲያስገቡ መያዛቸውን አክሏል፡፡ በዚህ መሠረት በአዋጅ 622/01 አንቀጽ 91(1)ም ሆነ 859/06 አንቀጽ 168(1)ም የኮንትሮባንድ ወንጀል በመሆኑ ሕጉ አለመሻሩን ጠቁሟል፡፡ ዶ/ር ፍቅሩ የተከሰሱት በኮንትሮባንድ ወንጀል በመሆኑ ስለመንገደኞች የዕቃ ዲክለራሲዮን ኦዲትና አቀራረብ የተደነገገውን አንቀጽ 30/2/ለን በመጥቀስ ክሱ እንዲነሳ ማመልከታቸው ከጉዳዩ ጋር አግባብነት የሌለው በመሆኑ አቤቱታው ውድቅ እንዲደረግለት ዓቃቤ ሕግ ጠይቋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሌሎች ተከሳሾችም ያቀረቡትን ‹‹ክስ ይሰረዝልን›› አቤቱታ በመቃወም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...