የንግዱ ማኅበረሰብ ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን እንደሚቆም አስታወቀ
በሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ራሱን አይኤስ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በአረመኔያዊ ግድያ ሕይወታቸውን ላጡ ሁለት ኢትዮጵያውያን ፀሜክስ ግሎባል ሁለት መቶ ሺሕ ብር ለገሰ፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ማክሰኞ በማዘጋጃ ቤት የተሰበሰቡ የአዲስ አበባ ነጋዴዎች፣ የአሸባሪ ቡድኑን ድርጊት በማውገዝ፣ በማንኛውም ጉዳይ ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን እንደሚቆሙ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በጥልቀት በመሄድ ከተጎጂ ወገኖች ጎን በመቆም ፀሜክስ ግሎባል ኢንተርፕራይዝ ተጎጂዎችን በመርዳት ቀዳሚ ሆኗል፡፡ በውኃ ሥራዎች የሚታወቀውና በቅርቡ አገልግሎት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ባለአምስት ኮከብ ክራውን ፕላዛ ሆቴል ባለቤት የሆነው ፀሜክስ ግሎባል፣ በውል ለታወቁት ሁለት የተጎጂ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው አንድ መቶ ሺሕ ብር ሰጥቷቸዋል፡፡
የፀሜክስ ግሎባል ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት አቶ ረዘነ አያሌው፣ ባለፈው ማክሰኞ በአረመኔያዊ ግድያ ሕይወታቸው ላለፈው ለወጣት እያሱ ይኩኖአምላክ እናት ወ/ሮ አኻዛ ካሳዬና ለወጣት ባልቻ በለጠ ታላቅ እህት ወ/ሮ በላይነሽ በለጠ ገንዘቡን በቼክ አስረክበዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያውያን ላይ የተካሄደውን አረመኔያዊ ግድያ እንደሰማሁ ራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ለቅሶ ለመድረስ ጨርቆስ አካባቢ በሚገኘው የተጎጂዎቹ መኖሪያ ቤት ተገኝቼ የሰማሁት የወጣቶቹ ታሪክ እጅግ አሳዝኖኛል፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ረዘነ፣ ቢያንስ የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት ለመለወጥ መሰደድን ለመረጡት ወጣቶች ህልም ማካካሻ ይሆን ዘንድ ይህንን ገንዘብ ማበርከታቸውን አቶ ረዘነ ተናግረዋል፡፡
ፀሜክስ ግሎባል ከሚያካሂዳቸው የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ሥራዎች በተጨማሪ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ የሚገኝ አገር በቀል ኩባንያ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎችም ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ተጎጂ ቤተሰቦች ጎን እንደሚቆሙ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ ዘርፍ ምክር ቤትንና የወፍጮ ባለንብረቶች ማኅበርን ወክለው ሐሳባቸውን የገለጹት አቶ ሁንልኝ ጥጋቡ፣ ‹‹እንደ በግ እየተጎተቱ ለተሰው ልጆቻችን የንግዱ ማኅበረሰብ ሐዘን ወደር የለውም፤›› ካሉ በኋላ፣ በማንኛውም መንገድ ከተጎጂ ቤተሰቦች ጎን የንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚቆም አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በበኩሉ ለሪፖርተር በላከው የሐዘን መግለጫ፣ ራሱን አይኤስ ብሎ የሚጠራው ሽብርተኛ ቡድን ሥራና መተዳደርያ ፍለጋ በሊቢያ በሚገኙ ንፁኃን ኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ግድያ መሪር ሐዘን እንደተሰማው ገልጿል፡፡ ‹‹ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን እንመኛለን፤›› በማለት ምክር ቤቱ ሐዘኑን ገልጿል፡፡