Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትፌዴሬሽኑ ከአሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ስንብት በኋላስ?

ፌዴሬሽኑ ከአሠልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ስንብት በኋላስ?

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስን መዋቅርና አደረጃጃት ከመለወጥ ይልቅ አማራጭ ሆኖ እየተወሰደ የሚስተዋለው አሠልጣኞችን ማፈራረቅ መሆኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑንም ሆነ ክለቦችን በተደጋጋሚ ሲያስተቻቸው ይደመጣል፡፡ በቅርቡ ስንብታቸው እውን የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ የማሪያኖ ባሬቶ ውሳኔም ከዚሁ ትችት አልወጣም፡፡

ምክንያቱ ደግሞ በሌሎች የእግር ኳሱ መዋቅሮች፣ አደረጃጀቶችና አሠራሮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎች ላይ የሚደርገው እንቅስቃሴ አናሳ መሆኑ፣ እንዲህም ሆኖ ለውጭ አሠልጣኞች ከሚደረገው ሽር ጉድና የሚከፈላቸው የገንዘብ ቁልል ያስገኘውን ውጤት በማነፃፀር በስፖርቱ መገናኛ ብዙኃን ትችቶችና አስተያየቶች  እንደቀጠሉ ይገኛል፡፡ የአገሪቱን እግር ኳስ የሚመራው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋም ለአገሪቱ ስፖርት መሠረታዊ መዋቅሮች ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ በግልጽ የሚጠይቁ በርክተዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ዘግይቶም ቢሆን ለወራት መነጋገሪያ ሆኖ የቆየውን የፖርቱጋላዊውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ስንብት ካስታወቀ በኋላ፣ የአመራሩ ውሳኔ በዚህ ሳያበቃ በየደረጃው ያስቀመጣቸውን የየክፍሉን ባለሙያዎች ማጥራትና አቅም ባላቸው ባለሙያዎች መተካት እንደሚጠበቅበት ጭምር እየተነገረ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በወቅታዊ እግር ኳስ ዙሪያ ሪፖርተር ካነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ አያሌው በላቸው ይጠቀሳሉ፡፡ አቶ አያሌው፣ ‹‹ፌዴሬሽኑ ከስፖርት ቤተሰቡም ይሁን ከስፖርት መገናኛ ብዙኃን በተደረገበት ጫና የብሔራዊ ቡድኑን ዋና አሠልጣኝ አሰናብቷል፡፡ ውጤት በሚጠፋበት ወቅት አሠልጣኝ የመጀመርያው ተጠያቂ እንደሚሆን ባይካድም፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከአሠልጣኙ ባልተናነሰ በተቋሙ ውስጥ ያለው ጠቅላላ አሠራርና የባለሙያዎች ጥንቅር ከሁሉ በፊት መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑ ትኩረት ሊያገኝ ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

በፌዴሬሽኑ በተለያዩ ክፍሎች በመልካም ፈቃደኝነትም ይሁን በቅጥር ሠራተኝነት እየሠሩ ከሚገኙት ከብዙዎቹ ጋር እንደሚተዋወቁ የሚናገሩት አቶ አያሌው፣ ‹‹እነ ማን ምን ዓይነት አቅምና ችሎታ ኖሯቸው ነው እግር ኳሱን እያስተዳደሩ የሚገኙት?›› ተብሎ ከሥር መሠረታቸው ሊገመገሙና ባላቸው አቅምና ዕውቀት መሠረት ኃላፊነት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ያስረዳሉ፡፡

ከተቋሙ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጀምሮ የቴክኒክ ዲፓርትመንት፣ የውድድር፣ የዳኝነትና የሌሎችም በፌዴሬሽኑን ንዑስ ክፍሎች የሚገኙ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ነፃና ሙያዊ በሆነ መሥፈርትና መመዘኛ ሊለዩ እንደሚገባም፣ የብዙዎች እምነት ሆኖ ፌዴሬሽኑን እያስተቸው ይገኛል፡፡

የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው፣ ‹‹ውጤት ሲጠፋ የመጀመርያው ተጠያቂ አሠልጣኝ ነው፡፡ ሆኖም አሁን በአገሪቱ ባለው የእግር ኳስ ተጨባጭ ሁኔታ በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በየደረጃው የምንገኝ አካላት በተሰጠን ኃላፊነት መሠረት የድርሻችንን ተጠያቂነት መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም አሠልጣኙ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት ከተሰጣቸው ጀምሮ የነበራቸውን አፈጻጸም በመከታተል ክፍተቶችን መሙላት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ የሚገባን ስለነበረ ነው፤›› ብለው፣  ከጽሕፈት ቤቱ ጀምሮ ሁሉም በነበረው የሥራ ድርሻ መሠረት ተገቢው ግምገማ በቅደም ተከተል ተፈጻሚ እንዲሆን፣ ይህም ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን ተመሳሳይ ችግር በማረም የተሻለውን አቅጣጫ ለመከተል መደላድል እንደሚሆን ጭምር አስረድተዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 22 ቀን 2014 ጀምሮ ለሁለት ዓመት ዋሊያዎቹን በዋና አሠልጣኝነት ለማሠልጠን ከፌዴሬሽኑ ጋር የተዋዋሉት ማሪያኖ ባሬቶ፣ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በዚህ ወር መጨረሻ ውላቸው በይፋ እንደሚቋረጥ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ለዚህ ውሳኔ መነሻው በጋራ መግባባትና በመመካከር ስሜት መሆኑን የገለጸው የፌዴሬሽኑ መግለጫ፣ በሁለቱ ተዋዋዮች መካከል የተደረሰው ውል ቢቋረጥ ሊመጣ የሚችለውን ውጣ ውረድ ለማስቀረት ያለመ መሆኑን አክሏል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣይ በትብብር መሥራት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ከመሆኑም ባሻገር፣ ለአሠልጣኙ የሦስት ወራት ደመወዝ ክፍያን የሚያጠቃልል መሆኑም ታውቋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...