Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ

የቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዩቤልዩ

ቀን:

የ‹‹13 ወር ፀጋ›› የሚለው መሪ ቃል ለዓመታት የኢትዮጵያ ቱሪዝም መገለጫ ሆኖ አገልግሏል፤ በርካታ ቱሪስቶችን ወደ አገሪቱ በመሳብም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ መሪ ቃሉ በፖስተሮች፣ በፖስት ካርዶች፣ በመጽሔቶች እንዲሁም የቱሪስቶች ዓይን ሊያርፍባቸው በሚችሉ ቁሳቁሶችና አካባቢዎች ላይ ሰፍሮ ለዘመናት ዘልቋል፡፡

የመሪ ቃሉ ባለቤትና ‹‹የቱሪዝም አባት›› በሚል የሚጠሩት አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ ከዚህ መሪ ቃል በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ካበረከቷቸው መካከል የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ይጠቀሳል፡፡ ድርጅቱ በዋነኛነት ከቀረጥ ነፃ የሆኑ ቁሳቁሶችን ከውጪ በማስገባትና በመሸጥ ይታወቃል፡፡ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ለቱሪስቶች በማቅረብ ረገድም ተጠቃሽ ነው፡፡

ድርጅቱ በ1957 ዓ.ም. ሲመሠረት ኃላፊነቱ የተሰጣቸው አቶ ሀብተሥላሴ፣ የኢትዮጵያን መስህቦች በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት በሚል ነበር በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያው የገፀ በረከት መደብር እንዲከፈት ያደረጉት፡፡ በመደብሩ የኢትዮጵያን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶች የሚያንፀባርቁ ቅርጻ ቅርጾችና ፖስት ካርዶች ለገበያ ቀርበዋል፡፡

በፖስተር ከቀረቡት መካከል ብዙዎች የሚያስታውሷቸው የአርሲ ልጃገረድ፣ የቡና ሥነ ሥርዓት፣ የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያንና የዓባይ ፏፏቴ ምሥሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ በአቶ ሀብተሥላሴ የተዘጋጁና በቱሪዝም ዘርፍ የአገሪቱን ሀብቶች በማስተዋወቅ ፈር ቀዳጅ የሚባሉ ናቸው፡፡ ድርጅቱ አሁን የሚታወቅበት ከቀረጥ ነፃ ንግድ የተጀመረው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡

አቶ ሀብተሥላሴ ቱሪዝምን ለማስፋፋት የሚያስችል ገንዘብ የሚገኝበትን ከቀረጥ ነፃ ንግድ ለማካሄድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሲጠይቁ ‹‹አየርም ይሸጣል›› ማለታቸው ይነገራል፡፡

ድርጅቱ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩውን ሚያዝያ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰበታ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ሲያከብር ከተገኙ መካከል የድርጅቱ መሥራችና ለዓመታት በሥራ አስኪያጅነት የመሩት አቶ ሀብተሥላሴ አንዱ ናቸው፡፡ ዕድሜ ቢጫጫናቸውም በዕለቱ ከተገኙ የቀድሞ የሥራ አጋሮቻቸው ጋር ስላለፉ ትዝታዎቻቸው ይጨዋወቱ ነበር፡፡ ለድርጅቱ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማት ሲሰጣቸውም ከአንገታቸው ዝቅ ብለው ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጉያ እንደተናገሩት፣ ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በአምስት አሥርታት 10 የቀረጥ ነፃና 10 ገፀ በረከት መደብሮች አቋቁሟል፡፡ በተጨማሪ የገበያ አዳራሽ፣ የዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ምርቶች ማምረቻና ማከማቻ ማዕከል ከፍተዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ከቀረጥ ነፃ መደብርና የአዲስ አበባ ሒልተን የቀረጥ ነፃና ገፀ በረከት መደብሮችም ይገኙበታል፡፡

በአየር መንገድ የተከፈተው የገፀ በረከት መደብር አጠገብ የተከፈተው ከቀረጥ ነፃ ቁሳቁሶች መሸጫ በዘርፉ ከአፍሪካ ተቀዳሚ ከሆኑ አልጄሪያ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ጋር ኢትዮጵያን አሰልፏታል፡፡ ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ አካባቢዎች የዕደ ጥበብ ውጤቶች መሸጫዎች ተከፍተዋል፡፡

ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ለሆኑ ዲፕሎማቶች የከቀረጥ ነፃ ሽያጭ በመስጠትና ለቱሪስቶች በአመቺ ሁኔታ ቁሳቁሶችን ከማቅረብ ጐን ለጐን አገር በቀል ቁሳቁሶች በጃፓን፣ በካናዳ፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን፣ አልጄሪያና ሱዳን እንዲታዩ ተደርጓል፡፡

ስለድርጅቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት ከ50 ዓመት በፊት ሥራ ሲጀምር በጀቱ 260,000 ብር ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም. 12,191,000 ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያገኘው ድርጅቱ 50ኛ ዓመቱን ባከበረበት ቀን በድርጅቱ ከ30 ዓመታት በላይ ያለገሉ ሠራተኞች ከድርጅቱ ዳይሬክተር የሜዳልያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...