በኢትዮጵያ ሙዚቃ አንጋፋና ተጠቃሽ ሙዚቀኞች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ተሰባስበዋል፡፡ ዓመታዊው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተሰናዳው መርሐ ግብር በይፋ እስኪጀመር ይጠባበቃሉ፡፡
የቴአትር ቤቱ ሙዚቀኞች ጥቂት ረቂቅ ሙዚቃዎች አስደምጠው ዝግጅቱ ‹‹ሀ›› ተብሎ ተጀመረ፡፡ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቀን ሚያዝያ 10፣ 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በቀረበ የሙዚቃ ትዕይንት ነበር የተጀመረው፡፡ በዕለቱ ወጣትና አንጋፋ ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
ሚያዝያ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በቴአትር ቤቱ በተካሄደው የክብረ በዓሉ ማጠናቀቂያ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡
ሽልማቱ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆኑ ባለሙያዎችን አካቷል፡፡ አብዛኞቹ በቦታው ቢገኙም በጤና ምክንያት ዝግጅቱን መታደም ያልቻሉ እንዲሁም ሽልማታቸውን በተቀመጡበት ሆነው ለመቀበል ዕድሜ ያስገደዳቸው ይገኙበታል፡፡ ሽልማቱ ባለሙያዎቹ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ባበረከቱት አስተዋፅኦ እንዲታወሱና እንዲመሰገኑ ያለመ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
ሽልማቱ ለግጥምና ዜማ ደራሲዎች፣ ለሙዚቃ አቀናባሪዎች፣ ለሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች፣ ድምፃውያን፣ ተወዛዋዦችና ዳንሰኞች እንዲሁም ለሙዚቃ አልበም አሳታሚዎችና አከፋፋዮች ተሰጥቷል፡፡ እውቅና ከተሰጣቸው ተሸላሚዎች በተጨማሪ ገንዘብ የተሸለሙ ሦስት ባለሙያዎችም ይገኙበታል፡፡ አብዛኞቹ ተሸላሚዎች ከ1950ዎቹ አንስቶ በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱ ናቸው፡፡
በዜማና ግጥም ደራሲያን ዘርፍ ከተሸለሙት አንዱ በፒያኖና ክራር ተጫዋችነታቸው የሚታወቁትና በርካታ ወጣቶችን በኪነ ጥበብ ዘርፍ የሚያሰለጥኑት ዶ/ር ተስፋዬ አበበ ሲሆኑ፣ በክብር ዘበኛ በተወዛዋዥነት፣ ድምፃዊነት እንዲሁም ብቸኛ የማንዶሊን ተጫዋች በመሆን ለዓመታት ያገለገሉት አየለ ማሞ ሌላው ተሸላሚ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ከግጥምና ዜማ በተጨማሪ በቴአትር ድርሰት የሚታወቁት ጌታቸው ደባልቄም የዘርፉ ተሸላሚ ነበሩ፡፡
በሙዚቃ አቀናባሪዎች ዘርፍ በምድር ጦር ኦርኬስትራና በሌሎችም መድረኮች የሙዚቃ መሣሪያ የተጫወቱና ሙዚቃ ያቀናበሩት ተሾመ ሲሳይ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ቫዬሊን፣ ኦርጋንና ቤዝ ጊታር በመጫወት የሚታወቁትና በመሣሪያ ብቻ የተቀነባሩ ከስምንት በላይ የሙዚቃ አልበሞች ያሏቸው አርቲስት ይስሐቅ ባንጃውም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሌላው ተሸላሚ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራና በምድር ጦር ኦርኬስትራ ውስጥ በሙዚቃ ቅንብር የሚታወቁት መላኩ ተገኝ ናቸው፡፡
ካቴነር ሳክስ ተጫዋችነታቸው በተጨማሪ በተለይም በሳክስፎን የኢትዮጵያን ሽለላ ለዓለም በማስተዋወቅ ዝናን ያተረፉት ጌታቸው መኩሪያ ከሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች መሀከል ተሸልመዋል፡፡ ሁለተኛው ተሸላሚ ሙዚቃ አቀናባሪና በክላሪኔት የኢትዮጵያን ቅኝቶች የሚጫወቱት መርአዊ ስጦት ናቸው፡፡
ከድምፃውያን መካከል በሙዚቃ አቀናባሪነት፣ በሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችነትና በጥዑመ ዜማዎቻቸው ተወዳጅ የሆኑት ግርማ በየነ ተሸልመዋል፡፡ ሌላው ከድምፃዊነቱ ጎን ለጎን በድራም ተጨዋችነቱ ስሙ የሚነሳው ጌታቸው ካሳ ነው፡፡ ከበርካታ ባንዶች ጋር ሥራዎቹን ያቀረበው ዝነኛው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ ከተሸላሚዎቹ ይጠቀሳል፡፡ በተወዛዋዥነትና በኬሮግራፈርነት ለዓመታት የሠሩት ታደለ ታምራት የውዝዋዜና ዳንስ ዘርፍ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ለዓመታት የሙዚቃ አልበሞችን በማሳተምና በማከፋፈል የሠራው አምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤት አቶ ፍቃዱ ዋሪ የሙዚቃ ዘርፉን ከሚደግፉ ተቋሞች ዘርፍ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
የገንዘብ ሽልማት ከተሰጣቸው አንዱ ግጥምና ዜማ በመድረስ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ያገለገሉት ወንዱሙ ቶላ ናቸው፡፡ በወላይትኛ ሙዚቃ ታዋቂውና የመጀመሪያውን የወላይትኛ ሙዚቃ ካሴት ያሳተሙት ኩዌሻ ሴታም ተሸልመዋል፡፡ ከተለያዩ ባንዶች ጋር የመዚቃ ሥራዎቻቸውን ያቀረቡት ተማም አርጎ ሌላው ተሸላሚ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው 5,000 ብር ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሌላው ተሸላሚ የመርሐ ግብሩ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ ሲሆኑ፣ በአገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዘመናዊ ሙዚቃን በማሠልጠን፣ ሙዚቃ በማቀናበርና የሙዚቃ መሣሪያዎች በመጫወት ዝነኛ ናቸው፡፡
የሙዚቃ አቀናባሪ ይስሐቅ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃና ሙዚቀኞች የሚወሱበት ቀን ታላላቅ ሥራዎችን ያበረከቱ ባለሙያዎች መሸለማቸው አስደስቷቸዋል፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ሽልማት እንደሚገባቸው በመግለጽ መርሐ ግብሩ ቀጣይነት እንዲኖረው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ወጣት ሙዚቀኞች ከአንጋፋዎቹ ተሞክሮ መውሰድ አለባቸው፤ ሙያውንም በእጅጉ ማክበር ይገባቸዋል፤›› ያሉት ባለሙያው፣ በርካታ ወጣት ሙዚቀኞች በክብረ በዓሉ አለመገኘታቸውን በቅሬታ ተናግረዋል፡፡ አዘጋጆቹም ወጣት የሙዚቃ ባለሙያዎች ጥሪ ቢደረግላቸውም አለመገኘታቸውን ተችተዋል፡፡ ወጣቶች የመሰል መድረኮች ተካፋይ መሆን እንዳለባቸው ያሳሰቡ ባለሙያዎችም ነበሩ፡፡
‹‹ሙዚቀኞች ለሙያው ክብር መስጠትና ለዕድገቱ በአንድነት መቆም አለባቸው፤›› ያሉት ዳዊት ለጥበቡ ባለውለታዎች ሽልማት መሰጠቱ ወጣቶችንም የሚያነሳሳ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በዓሉ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ አንድ ቀን ተወስኖለት የሚከበር ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ የተወለደበት ዕለት (ሚያዝያ 5) የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበርበት ቀን እንዲሆን ሐሳብ የሰጡም አሉ፡፡
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ የሙዚቃ ቀን ሲከበር የሙዚቃ ትዕይንቶች ለሕዝብ የሚቀርብበት፣ ለአንጋፋ ሙዚቀኞች ዕውቅናና አቅመ ደካማ ለሆኑ ባሙያዎች ድጋፍ የሚሰጥበት እንዲሆን እየሠሩ ነው፡፡
ክብረ በዓሉን በተዋቀረ መልክ ማክበር፣ ተሰጥኦ ኖሯቸው ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ወጣቶች የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትንና መድረክ ላጡ ሙዚቀኞች መድረክ የሚፈጠርበትን መንገድ ለማመቻቸት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ የሙዚቃ መሣሪያ ወይም መለማመጃ ቦታ ለማግኘት ያልቻሉ ወጣት ሙዚቀኞች ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ እንዲፈለግና በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ውይይቶች እንዲካሄዱ የሙዚቃ ቀን መንገድ ይከፍታልም ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩን ከኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አልባብ የቴአትርና የሙዚቃ ፕሮሞሽን ሲሆን፣ በዓሉ ከዚህ በፊት በሐዋሳ ከተማ መከበሩ ይታወሳል፡፡