Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ከሦስት መቶ ሺሕ ሔክታር በላይ የቡና እርሻ እንደሚኖረን ይጠበቃል››

  አቶ ሰማን አባ ጎጃም የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ

  በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት ከተሞች በትልቀነቷ የምትጠቀሰው ጅማ ከተማ በኦሮሚያ ክልል ትገኛለች፡፡ ጅማ በክልሉ ከሚገኙት 18 ዞኖች አንዷ ስትሆን በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን የከፋ ጠቅላይ ግዛት (በደርግ ክፍለ ሀገር) ዋና ከተማ ነበረች፡፡ በቡና ምርቷ የምትታወቀው ጅማ ከ1950ዎቹ ጀምሮ በደቡብ ምዕራባዊ ኢትዮጵያ ታላቅ የገበያ ማዕከል ነበረች፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዞን ደረጃ ያገኘችው ጅማ ከያዘቻቸው ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችዋ መካከል የ19ኛው ምእት ዓመት የጅማ ንግሥናን የሚያመለክተው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥትና ሙዚየም ይገኝበታል፡፡ ስለዞኑ ገጽታና እንቅስቃሴ የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰማን አባ ጎጃምን ሻሂዳ ሁሴን አነጋግራቸዋለች፡፡ 

  ሪፖርተር፡- ከጅማ አባ ጅፋር ባሻገር ያለው የአካባቢው ታሪክ ምን ይመስላል?

  አቶ ሰማን፡- ጅማ በኦሮሚያ ከሚገኙት አሥራ ስምንቱ ዞኖች አንዱ ነው፡፡ በቀደምት አባቶቻችን ታሪክ የ‹‹ሸነን ጊቤ›› መንግሥታትን ያጠቃልላል፡፡ ማና፣ ሰቃ፣ ቀርሳ፣ ዴዶን ጨምሮ ሌሎች 78 ወረዳዎች በሸነን ጊቤ መንግሥት ይጠቃለላሉ፡፡ ጌራ ራሱን የቻለ መንግሥት ነበረው፡፡ ጉመይ ሌላው ሲሆን፣ የዛሬው ጉመይ ወረዳና ሰንጠማሲሞ ከዚያም አልፎ እስከ ደንቢ ይደርሳል፡፡ አምስተኛው ሊሙ እናሪያ ነው፡፡ እነዚህ አምስቱ መንግሥታት በጅማው ንጉሥ አባ ጂፋር ይገዙ ነበር፡፡

  ጅማ በንግድ እንቅስቃሴ ቀደምት ከሚባሉት ጎራ ትመደባለች፡፡ ለምሳሌ ከግሪኮች፣ ከዓረቦችና ከሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ጋር የንግድ ትስስር ነበራቸው፡፡ የቡና መገኛ ከመሆኗ አንፃርም የከተማዋ ኢኮኖሚ የቆመው በቡና ነው፡፡ ከደርግ ሥርዓት በፊት በንግዱ ቀደምት ነበረች፡፡ ኢኮኖሚውም ትንሽ የዳበረ ነበር፡፡ የተለያዩ ጅምር ፋብሪካዎች ነበሩ፡፡ በሙያና በሌሎች የዕደ ጥበብ ሥራዎች ትታወቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በደርግ ሥርዓት የነበሩት ሁሉ እየተናዱ የግል ንብረቶችም ወደ መንግሥት እየተዘዋወሩ፣ በኢኮኖሚም ትንሽ ብቅ ብቅ ያሉ የሚሰደዱበት ሁኔታ ስለነበር የነዋሪዎቹን የመሥራት ፍላጐት ገድሎት ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ መንግሥት በፈጠረው ምቹ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ጅማ ዳግም እያንሰራራች ትገኛለች፡፡

  ሪፖርተር፡‑ የጅማ ዕድገት እንዴት ይታያል?

  አቶ ሰማን፡‑ ጅማ ዞን 17 ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር እንዲሁም 520 ቀበሌዎች አሏት፡፡ እንደ ማንኛውም የአገራችን ከተማ በዕድገት ላይ ትገኛለች፡፡ ዕድገትን ከብዙ አቅጣጫዎች መግለጽ ይቻላል፡፡ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ ሕዝቡ ለልማት ያለው ተነሳሽነት፣ መንግሥትና ሕዝቡ ያላቸው መስተጋብርና የመሠረተ ልማት አውታሮች ዕድገት አንፃራዊ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ በደርግ ዘመን የነበረው አገዛዝ አብዛኛውን ሰው ተስፋ ያስቆረጠ ነበር፡፡ ሕዝቡ በሚገባ አያመርትም ነበር፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ኢኮኖሚዎች ላይ የመሳተፍ ሁኔታ ሻል ያለ ነው፡፡ በዚህም ሕዝቡ ለሥራ ያለው ተነሳሽነት ማደጉን ማየት ይቻላል፡፡ የመሠረተ ልማት አውታሮችን በተመለከተ ለምሳሌ በዞናችን ውስጥ የመንገድ ግንባታዎች እየተካሄዱ ነው፡፡ ግንባታዎች በፌዴራል ደረጃ እየተገነቡ ሲሆን፣ በክልልና በዞን የሚሠሩ የገጠር መንገዶችም አሉ፡፡

  ቀበሌን ከቀበሌ ጋር፣ ቀበሌን ከዋና ከተማ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች በስፋት እየተሠሩ ነው፡፡ የትልልቆቹን መንገዶች ግንባታ ስናይ በመሠራት ላይ ያሉና በዕቅድ ደረጃ ያሉ አሉ፡፡ ዲዛይንና ጥናት ላይ ያሉም አሉ፡፡ ለምሳሌ ከጅማ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ አዲስ የተሠራና አሁን ደግሞ የተወሰነ ጥገና እየተደረገለት ያለ መንገድ ነው፡፡ ከጅማ ከተማ ወደ ደዴሳ የሚወስደውን መንገድ በተመለከተም በጥናት ላይ ያለ ሲሆን፣ በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ (ጂቲፒ) ውስጥ ተካትቶ ተይዟል፡፡ እንዲሁም ከጅማ ሚዛን ያለው መንገድ እስካሁን ድረስ አስታዋሽ አጥቶ ምንም ያልተሠራ ነው፡፡ በአሁን ወቅት ከኢኮኖሚ አዋጭነቱ  አንፃር ቅድሚያ ተሰጥቶት ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ሙሉ ለሙሉ ተገንብቶ ተጠናቅቋል፡፡ ኤርፖርታችንም እንዲሁ ወደ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትነት ተለውጦ አስፈላጊው ግንባታ ተጠናቋል፡፡ ከአንድ ወር በኋላ በይፋ ይመረቃል፡፡ እስካሁን ባስመዘገብነው የመንገድ ግንባታ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጀምሮ እስከ ደርግ መንግሥት ድረስ 800 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረው የአስፓልት ሽፋን አሁን በተደረጉ ግንባታዎች ከ2,300 ኪሎ ሜትር ከፍ ብሏል፡፡

  ሪፖርተር፡- አገልግሎት ላይ በዋሉ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የተበላሹ አስፓልቶች አስተውለናል?

  አቶ ሰማን፡- በአንደኛ ደረጃ የዲዛይንና የሙያ ብቃት ችግር ነው፡፡ በሌላ በኩልም  ጅማ አካባቢ ያለው አፈር አመቺ አይደለም፡፡ ይህ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ሲሆን፣ ብዙ ቦታዎች ጥቁር አፈር አላቸው፡፡ ጥቁር አፈር ላይ ደግሞ ከሌላው በተለየ መልኩ ውኃ የመያዝ ባህሪ ስላለው በግንባታው እክል ይፈጥራል፡፡ ይህ ለመበላሸቱ ዋና ምክንያት ሲሆን፣  ተሠርቶ አገልግሎት ላይ ከዋለ በኋላም የእንክብካቤ ማነስ የበኩሉን ያበረክታል፡፡ ከዲዛይንና ከጥራት ጋር የሚገናኙ ችግሮችም አሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ችግር በብዙ መንገዶች ላይ የሚስተዋል ሲሆን፣ አንዱ ከአንዱ በመማር ኪሳራ መቀነስ ይገባል፡፡

  ሪፖርተር፡- ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮች እንደ ኤሌክትሪክ፣ ንፁህ ውኃና ጤና የመሳሰሉት በገጠሩ ምን ያህል ተደራሽ ሆነዋል?

  አቶ ሰማን፡- ውኃን በሚመለከት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ተሠርቷል ማለት ይቻላል፡፡ በጂቲፒው ዓመት ስናቅድ በወቅቱ የነበረው የውኃ ሽፋን 35 በመቶ ነበር፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ግን ትልልቅ ሥራዎች በመሠራታቸው የውኃ ሽፋኑ ከ35 በመቶ ወደ 81 በመቶ ሊገባ ችሏል፡፡

  በያዝነው ዓመትም የውኃ ሽፋንን መቶ በመቶ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ እንቅስቃሴዎች በማድረግ ላይ ነን፡፡ በኤሌክትሪክ ረገድ መንግሥት የአገልግሎቱን ዘርፍና መሠረተ ልማቱን የሚሠሩትን ለሁለት ከፍሏል፡፡ መብራት ኃይል ራሱን በመከፋፈል እኛ ጋ አንድ ቢሮ አለው፡፡ በጅማ አካባቢ ላሉ ወረዳዎች የሚሠሩ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህን በመጠቀም የኤሌክትሪክን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ጥረት አድርገናል፡፡ እስካሁንም መብራት ያልነበራቸው የገጠር ከተማዎች ኤሌክትሪክ ማግኘት ችለዋል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው ሰፊ ከመሆኑ አንፃር የቀሩን ነገሮች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የኤሌክትሪክ ሽፋን ያልደረሳቸው አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤቶችና ሞዴል አርሶ አደሮች በፀሐይ ኃይል ከሚጠቀሙት ውስጥ ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡‑ የጤናው አገልግሎት ተደራሽነትስ ምን ይመስላል?

  አቶ ሰማን፡‑ ጤናን ስንመዝን ከፖሊሲው አንፃር ነው፡፡ ፖሊሲው ለጤና አመቺ ነው፡፡ በእያንዳንዱ የገጠርና የከተማ ቀበሌ መንግሥት ሁለት ሁለት የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች መድቧል፡፡ ሌላው የተቋማት ግንባታ ነው፡፡ በዞናችን ከ20 ዓመት በፊት አምስት ጤና ጣቢያ ብቻ ነበር፡፡ አሁን 114 ጤና ጣቢያዎች ተገንብተዋል፡፡ በፊት ለደቡብ ምዕራብ ክልል የሚሠራ አንድ ሆስፒታል ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ወደ 10 ከፍ ያለ ሲሆን፣ ሦስቱ ሥራ ጀምረዋል፡፡ ሌሎቹ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ሌላው እስካሁን ድረስ ያልተሠራበትና ከተጀመረም በኋላ ጥሩ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የአንቡላንስ አገልግሎት ነው፡፡ አንቡላንሶቹ የእናቶችንና ሕፃናትን ሕይወት በማትረፉ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በመሆኑም ለየወረዳዎቹ ከአንድ እስከ ሁለት የሚሆኑ አንቡላንሶች ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ ተገዝቶ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም ዞኑ 12 አንቡላንሶችን በማስገባት ላይ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡‑ የዞኑ ኢኮኖሚ መሠረት ያደረገው በቡና ምርት ላይ እንደመሆኑ መጠን በዘርፉ ምን ዓይነት እንቅስቃሴዎችና ተግዳሮቶች ይታያሉ?

  አቶ ሰማን፡- 60 በመቶ የሚሆነው የጅማ ኢኮኖሚ መሠረቱ የቡና ምርት ነው፡፡ ከቡና ቀጥሎ በእህል ምርትም በአገሪቱ ከሚገኙ እህል አምራች አካባቢዎች በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ የበቆሎ ምርት በከፍተኛ ደረጃ በጅማ ይመረታል፡፡ ሆኖም ግን ቡና ለረጅም ጊዜ ከኅብረተሰቡ ጋር ተሳስሮ የኖረ ነው፡፡

  በመሆኑም ቡና ላይ የመሥራት ጥያቄ ለዞኑ ኅብረተሰብ ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ የልማቱን ሁኔታ ስናይም ቡና በሦስት አካላት ይለማል፡፡ አንደኛውና ዋነኛው አርሶ አደሩ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ቡና በባለሀብቶች ይለማል፡፡ ከ250,000 ሔክታር በላይ የሚሆነው መሬታችን በቡና ተሸፍኗል፡፡ ዕቅዳችን 300,000 ሔክታር ለማድረስ ሲሆን ከግብ ለመድረስ አስፈላጊው ችግኞች ተዘጋጅተዋል፡፡ ይህም ጊዜው ሲደርስ ይተከላል፡፡ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይም ከ300,000 ሔክታር በላይ የሚሆን የቡና እርሻ እንደሚኖረን ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም በዘርፉ በርካታ ችግሮች ሲኖሩ በባህላዊ መንገድ ማምረትና መገኘት ካለባት ምርት በታች መሰብሰብ ዋናው ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን አርሶ አደሩን በማስተማር ችግሩ ተቀርፏል፡፡ በፊት በሔክታር ከስድስት እስከ ሰባት ኩንታል ቡና የሚሰበሰብ ሲሆን፣ አሁን በአማካይ እስከ 12 ኩንታል ቡና ይገኛል፡፡ አብዛኛዎቹ ሞዴል አርሶ አደሮችም በሔክታር ከ20 እስከ 25 ኩንታል ይሰበስባሉ፡፡ ሌላው ጥራቱ ሲሆን ከሞላ ጎደል ብዙ ሥራዎች ተሠርተው ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ቡና የተገኘው በዚህ ዞን ውስጥ ነው፡፡ ነገር ግን መገኘቱ ብቻ ዋጋ አይኖረውም፤ በጥራት ተዘጋጅቶ ለገበያ መቅረብ አለበት፡፡ ይህንን በተመለከተም በርካታ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ አርሶ አደሩም ከወዲሁ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡

              

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹እንደ አገር ቢያንስ ኮንዶም ማቅረብ አልቻልንም››   አቶ ባይሳ ጫላ፣ የኔፕ ፕላስ ተጠባባቂ ዳይሬክተር

  ቀደም ሲል በኤችአይቪ የተያዙ ሰዎችን የጋራ ድምፅ ለማሰማትና ተደራሽ ለማድረግ፣ ‹ከኤችአይቪ ኤድስ ጋር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበር› በጥቅምት ወር 1997 ዓ.ም. መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ ይኸውን ማኅበር...

  ‹‹የንባብ አብዮት ለትውልድ ብለን ተነስተናል›› አቶ ሰለሞን ደርቤ፣  የሕያው ፍቅር ለኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

  ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው አዕምሯቸው እንዲዳብር ማንበብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ዜጎች ዕውቀት፣ ብልኃት፣ ሥልት፣ ዘዴና ችሎታ እንዲኖራቸው ማንበብ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ይነገራል፡፡ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ...

  የቤት ፍላጎትንና አቅርቦትን ለማጣጣም የተነሳው ተቋም

  በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ሲፈተኑ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ኖሯቸው መኖሪያ ቤት ለመሥራት...