Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ የሃያ ዓመታት እስራት ፍርድ

የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ የሃያ ዓመታት እስራት ፍርድ

ቀን:

ለግብፅ አምስተኛው ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ በግብፅ ታሪክም የመጀመርያው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የፕሬዚዳንትነቱን መንበር የጨበጡ ሲቪል መሪ ነበሩ፡፡ ግብፅን ለሦስት አሥርት ያህል የገዟትን ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከገረሰሰው የግብፅ አብዮት በኋላ፣ እ.ኤ.አ. በሰኔ 2012 ሥልጣን የያዙት የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚደንት መሐመድ ሙርሲ፣ በሥልጣን የቆዩት ለአንድ ዓመት ያህል ብቻ ነው፡፡

በነበራቸው የዓመት ቆይታ ሥልጣን አግበስብሰው ይዘዋል፣ የሴቶችን መብት አላስከበሩም፣ ሕገ መንግሥቱን እንደ ሕዝቡ ፍላጐት አላሻሻሉም ተብለው ከመረጣቸው ሕዝብ ተቃውሞ የገጠማቸው ሙርሲ፣ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት ሥልጣን የያዙበትን አንደኛ ዓመት ባከበሩ ማግሥት ነው፡፡

ሥልጣን የያዙበትን አንደኛ ዓመት ተከትሎ ለተቃውሞ የወጣው የግብፅ ሕዝብ፣ በሙርሲ በደጋፊና በተቀናቃኝ ጐራ መከፈሉ፣ ለግብፃውያን ጉዳትና ሞት እንዲሁም ለንብረት መውደም ምክንያት ሆኗል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ሙርሲ እንደሆኑ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል፡፡

ሙርሲ ሥልጣን በሰላም እንዲያስረክቡ ተጠይቀው በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ምላሽ አለመስጠታቸው በግብፅ የነበረውን አመፅ አባብሶታል፡፡ የወታደሩ ጣልቃ ገብነት ደግሞ በወቅቱ የነበረውን አለመረጋጋት ለመቆጣር ቢያስችልም፣ በተለይ በሙርሲ ደጋፊዎች የእስልምና ወንድማማቾች ድርጅት አባላት ላይ ድብደባ፣ እንግልት፣ እስርና ሞት አስከትሏል፡፡

ግብፃውያን ለተቃውሞ በወጡበት ወቅት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎችን እርስ በርስ የሚያጫርስ መመርያ ከ14 ባለሥልጣኖቻቸው ጋር በመሆን ሰጥተዋል ተብለው የሞት ፍርድ ከሚያሰጠው ክስ ነፃ የወጡት ሙርሲ፣ ፍርድ ቤት በቆሙባቸው ሦስት ክሶች ሚያዝያ 13 ቀን 2077 ዓ.ም. የ20 ዓመት እስራት ተወስኖባቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 በሆስኒ ሙባረክ ላይ የተነሳውን አብዮት ተከትሎ በእስር ቤት የነበሩ የሙስሊም ብራዘርሁድ አባላትን በሕገወጥ መንገድ ለማስመለጥ ከውጭ ኃይሎች ጋር አሲረዋል፣ በግብፅ የሽብር ጥቃት ለማድረስ ከፍልስጤም ሃማስ፣ ከሊባኖስ ሂዝቦላህና ከኢራን ሪቮሊውሽነሪ ጋርድስ ጋር በስውር ሸፍጥ ሠርተዋል፣ የግብፅን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ሰነዶችን ዋና መቀመጫውን ዶሃ ባደረገው የአልጄዚራ መረብ በኩል ለኳታር አሳልፈው ሰጥተዋል በሚሉ ክሶች ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ 20 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው ሙርሲ፣ ከዚህ ቀደም ሞት እንደተፈረደባቸው አጋሮቻቸው ግድያ ይጠብቃቸዋል ተብሎም ተጠብቆ ነበር፡፡

በግብፅ ጦር ኃይል መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶብኛል በማለት ለመጀመርያ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በጩኸት ካሳወቁት  ሙርሲ ጋር በእስር የነበሩ 22 የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች፣ በፖሊስ ተቋማት ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ምክንያት የሞት ፍርድ የተበየነባቸው በዚሁ ሳምንት ነው፡፡ የ20 ዓመት እስራት የተበየነባቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጠበቃ ደግሞ በደንበኞቻቸው ላይ የተሰጠው ውሳኔ ኢፍትሐዊ ነው በማለት ይግባኝ ሊጠይቁ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሙርሲ ላይ የተላለፈው የ20 ዓመት እስራት ትክክል አይደለም፣ ‹‹የሚያሳፍር›› በማለት አውግዞ እንዲፈቱም የጠየቀ ሲሆን፣ ግብፃዊው የአልጄዚራ ዘጋቢ ያህያ ጋነም ደግሞ፣ የግብፅ መንግሥት ተቃዋሚዎችን እንደማይታገስና ከሙርሲ እስር ጀምሮም ሲያስተላልፍ የነበረው ውሳኔ የፍርድ ቤት ሳይሆን የፖለቲካ እንደነበር ገልጿል፡፡

ሙርሲ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የእሳቸውና የሙስሊም ብራዘርሁድ ደጋፊዎች ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሠልፍ ቢወጡም፣ ለግብፅ ያተረፈው መከፋፈልና መገዳደልን ነበር፡፡

ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን ለማውረድ ከተጠነሰሰው አብዮት ጀምሮም ግብፅ ሰላሟን በከፊል አጥታለች፡፡ በቱሪስት ፍሰቷ ላይም ፈተና ጥሎ አልፏል፡፡ የአንድ ዓመቱ የሙርሲ የሥልጣን ዘመንም በተቃውሞ የታጀበ ነበር፡፡

የግብፅን ሥልጣን አግበስብሰዋል የሚባሉት ሙርሲ የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተበት 50ኛ ዓመት በአዲስ አበባ ሲከበር መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ኢትዮጵያን በኃይል ለማስቆም ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር በድብቅ የመከሩት ይፋ መውጣቱ፣ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር ሲያስተቻቸው ከርሟል፡፡

ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ጋር በተያያዘ ሳይሆን፣ በአገራቸው የውስጥ ችግር ሳቢያ ከሥልጣን የተወገዱት ሙርሲ፣ ከተከሰሱባቸው ክሶች ውስጥ በሦስቱ ብቻ ነው የ20 ዓመት እስራት የተፈረደባቸው፡፡  

ሙርሲ ከሥልጣን በሰላም ባለመልቀቃቸው የተቀሰቀሰውን አመፅ ለመግታት በተሠለፈው የደኅንነት ኃይልና በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎች መካከል በተነሳ ግጭት ከ800 ያላነሱ ግብፃውያን ሞተዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የሙርሲ ደጋፊዎችም በአመፅ በመሳተፍ ክስ ተመሥርቶባቸው ሞትና እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2014 በኋላ የሙስሊም ብራዘርሁድ ሊቀመንበር የነበሩትን ሞሐመድ ባዴን ጨምሮ ከ1,200 በላይ የፓርቲው ደጋፊዎች የሞት ፍርድ ተበይኖባቸዋል፡፡ ሙስሊም ብራዘርሁድ ፓርቲም የታገደ ሲሆን፣ እንደ አሸባሪ ቡድንም ተፈርጇል፡፡

በሰሜናዊ ግብፅ በአልአድዋህ መንደር የተወለዱት የ64 ዓመቱ ሙርሲ፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 እስከ 2005 ድረስ ከፖለቲካ ፓርቲ ነፃና ገለልተኛ የፓርላማ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡

የሙስሊም ብራዘርሁድ ግንባር ቀደም አባልና የፍሪደም ኤንድ ጀስቲስ ፓርቲ (ኤፍጄፒ) ሊቀመንበርም ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 በግብፅ ለተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የተሳተፉትም ኤፍጄፒን ወክለው ነበር፡፡   

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...