በከበደ ካሳ
አይኤስ ሰሞኑን በሊቢያ በፈጸመው ጭፍጨፋ ልቤ በሐዘን ደምቷል፡፡
ድርጊቱ የተፈጸመው በኢትዮጵያውያን ላይ መሆኑን ስሰማ ደግሞ ሐዘኔን ድርብ አድርጎታል፡፡ እናም ይህን አስነዋሪ ድርጊት በግሌ አወግዘዋለሁ፡፡ ፈጣሪ የሟቾችን ነፍስ በገነት ያኑርልን፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውም መፅናናትን ይስጥልን።
በየትኛውም ሁለተኛ አገር በስደት መኖር በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባት ዋስትና አይሰጥም፡፡ ለሰው ልጅ በማይመጥን ኢሰብዓዊ አያያዝ ሥር ሊጥል እንደሚችልም በቅርብ ጊዜያት በደቡብ አፍሪካ፣ በየመን፣ በሳዑዲ ዓረቢያና አሁን በሊቢያ በዜጎቻችን ላይ የተደረጉ ጥቃቶች ማሳያ ናቸው። ነገ በሌሎች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ከአገራቸው በተሰደዱ ዜጎቻችን ላይ ላይደገም ምንም ዋስትና የለንም። እናም ወገኖቻችን በያሉበት አገር ከመሰል ጥፋቶች እንዲጠበቁ ፈጣሪ እንዲረዳቸው እፀልያለሁ።
ይህን ሰይጣናዊ ዕርምጃ በማወግዘው ልክ ታዲያ ሁለት ነገሮችንም አወግዛለሁ፡፡ አንደኛው በማኅበራዊ ድረ ገጾች የአይኤስን ድርጊት በአብነት በማንሳት በእስልምናና በክርስትና እምነቶች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር የሚተጉትን ነው። አንዳንዶች በዚህ ዕርምጃ አስታከው ያልተገራ ምላሳቸውን በእስልምና እምነትና በእምነቱ ተከታዮች ላይ ሲያውለበልቡ አይቻለሁ።
አይኤስ ቀድሞውንም የእስልምና እምነትን አይወክልም። ለመሆኑ በየቀኑ በአይኤስ ጥይት የሚለበለቡት ኢራቃውያን፣ ሶሪያውያንና የመናውያን ሙስሊም አይደሉምን? ከነሕይወቱ ያቃጠሉት ዮርዳኖስያዊው ፓይለትስ ሙስሊም አይደለምን? እስልምና ሰላምን እንጂ አንገት መቅላትን የሚሰብክ እምነት ባለመሆኑ፣ በየትኛውም ንፁህ ዜጋ ላይ የሚፈጸም ግድያ በመላ የሰው ልጆች ላይ እንደተፈጸመ የሚቆጥረውን፣ አንዲትን ነፍስ ያዳነን የሰው ልጆችን ሁሉ እንዳዳነ የሚያስበውን የእስልምና እምነትና አስተምህሮ ከአይኤስ ጋር ለማስተሳሰር መሞከር ፍትሐዊ አይደለም። የዓረብ አገሮችን ጨምሮ በሌሎች በርካታ አገሮች የሚኖሩ ሙስሊሞችም የአይኤስ የጥፋት ድርጊትን በተደጋጋሚ በይፋ አውግዘውታል።
እውነት ነው አክራሪዎች ከዚህ ዓይነት የጭካኔ ተግባራቸው ጎን የሚሠለፍ ኃይል ለመመልመል ያመቻቸው ዘንድ ሃይማኖታዊ የሚመስሉ አጀንዳዎችን ያነሳሉ፡፡ ነገር ግን ይህ እንደሚያጠልቁት ጥቁር ጭምብል ድብቅ አጀንዳቸውን የሚከልሉበት መፈክር እንጂ እውነተኛ ባህሪያቸው አይደለም። ስለሆነም የአክራሪና የሽብርተኛ ቡድኖች ድርጊት አዕምሯችንን ሰልቦት በስህተትም ይሁን በእምነቶች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር በዕውቀት የሚደረጉ መሯሯጦችን አምርሬ አወግዛለሁ፡፡
ሁለተኛው ከአይኤስ እኩይ ድርጊት እኩል የማወግዘው ጉዳይ በየጊዜው በውጭ ኃይሎች ሰለባ በሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ነፍስ ላይ የሚደረግን የፖለቲካ ቁማር ነው። ባለፈው ሳምንት በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ የዙሉ ጎሳ አባላት የፈጸሙትን ድርጊት መነሻ በማድረግ፣ ድርጊቱን እጅጉን በማጋነንና አድማሱን በማስፋት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲራኮቱ የነበሩ ኃይሎችን ተመልክተናል። እነዚህ ቁማርተኞች ቁጥሮችን በማብዛት፣ የሐሰት ምስሎችን በመቀላቀል፣ እውነታዎችን በማጣጣል የነበራቸው ሥምሪት ሲታይ የቁማር መጫወቻ ሜዳው ከሰፋላቸው ለእነሱ ግብ ስኬት የሰው ሕይወትን ለማስያዝ የማይመለሱ ጨካኞች መሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል። የጭካኔው ልካቸው ከተመዘዘ የአጥፊዎቹን ያህል የሚረዝም መሆኑን ነው ያረጋገጡት።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጣቸውን መረጃዎች፣ ያወጣውን የውግዘት መግለጫ፣ የአገሪቱ መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ ያቀረበውን ጥያቄና ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በማጣጣል፣ በደቡብ አፍሪካ ላይ መንግሥት የበቀል ዕርምጃ እንዲወስድ መጎትጎት የጤንነት ምልክት አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ‹በአፍሪካ ኃያል የተባለው ሠራዊት ለምን ወደ ደቡብ አፍሪካ አይዘምትም?› እያሉ ሲያላግጡ ሌሎች፣ ‹አዲስ አበባ ያለው የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ካልተዘጋ ብሔራዊ ክብራችን አይመለስም›፣ የተወሱት ደግሞ፣ ‹እዚህ ያሉት ደቡብ አፍሪካውያን ካልተባረሩ› በማለት ሲቀውጡ መስማት እነዚህ ሰዎች እንኳን ለአገር የሚጠቅም ለያዙት የፖለቲካ አቋም እንኳን የሚመጥን ብስለት እንደሌላቸው የሚያሳብቅ ነው።
በደቡብ አፍሪካ የዙሉ ጎሳ የተወሰኑ ወሮበላዎች ሠርተው ባለፈላቸው አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የሰነዘሩትን ጥቃትና ዘረፋ፣ ልክ ደቡብ አፍሪካና ሕዝቦቿ ተስማምተው የፈጸሙት ተግባር በማስመሰል የእኛን ያህል ሰብዓዊነትና ሉዓላዊነት ያላቸውን ሕዝቦች፣ የእኛ የምንላትን አገር ያህል ክብርና ልዕልና ያላትን አገር ሲያራክሱ ተመልክተናል፡፡ ይህ በየትኛውም ሚዛን ቢለካ ተገቢ አይደለም።
አይኤስ በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን ድርጊት በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶችም የዚሁ ሌላ ግልባጭ ናቸው። በእርግጥ የተፈጸመው ድርጊት የሚያበሳጭ ነው፡፡ ግለሰቦችንም ስሜት ውስጥ ሊከት እንደሚችል እሙን ነው። በዚህ ወቅት ስሜታዊነት ምክንያታዊነታችን አሸንፎት ያልተገባ ነገር ብንናገር፣ የተሳሳተ አቋም ብንይዝ ተፈጥሯዊ ነው። ሰው በስሜት ውስጥ ሲሆን የሚናገረውን ነገር መለስ ብሎ ማሰላሰል፣ ከዚያም ያልተገባውን ንግግር ማረም ሲገባ ተጨማሪ ስህተት መፍጠር ግን ሰዋዊ አይደለም።
የኢትዮጵያ መንግሥት የተፈጠረውን ጉዳይ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ ድርጊቱን ኮንኗል። አይኤስ ኢትዮጵያውያንን ስለመግደሉ መናገሩን እንጂ ሰዎቹ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ስለመሆናቸው እንዳላረጋገጠ፣ ጉዳዩን ግን እያጣራ እንደሆነ ገልጧል። ኢትዮጵያዊ ይሁኑም ሌላ ዜጋ ተግባሩን እንደሚያወግዝ አክሎ አስታውቋል። ለነገሩ መንግሥት ባለው መሠረትም ጉዳዩን አጣርቶ በ24 ሰዓት ውስጥ ዳግመኛ መግለጫ ሰጥቷል።
የመጀመሪያውን መግለጫ ተከትሎ በርካታ የማኅበራዊ ድረ ገጾች ተጠቃሚዎች ‹አይኤስ በራሱ አረጋግጦ ሳለ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዴት እንዲህ ይላል?› ሲሉ ለሰማቸው ድርጊቱን በአካል ተገኝተው ያስፈጸሙ ነው የሚያስመስልባቸው። ለመሆኑ አይኤስ የተናገረውን ሁሉ የአንድ አገር መንግሥት ቀርቶ እኛስ ብንሆን እንደወረደ መቀበል አለብን እንዴ? ለመሆኑ ይህ ‹‹አረመኔ›› እያልን የምንጠራው ቡድን ንፁኃን ዜጎችን ለመቅላት ወደኋላ ያላለ፣ ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻው ሲል ውሸት እንደማይናገር ያመንነው በምን አመክንዮ ነው? መንግሥት የሰጠው መግለጫ ይልቁንም ጉዳዮችን ሳያጣራ፣ በነፈሰበት የሚነፍስና ኃላፊነት የማይሰማው መንግሥት አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።
መንግሥት የሟቾቹን ኢትዮጵያዊነት አጣራለሁ ማለቱ በምን ሒሳብ በቁስላችን ላይ ጨው መነስነስ እንደሆነ ሳይናገሩ፣ በድፍኑ እርግማን ማዝነብ ቀናት ሲያልፉ ለትዝብት ይዳርጋል። መንግሥት ‹መግለጫውን እስከማጣራ ድረስ› በሚል ድርጊቱን ባይኮንን ኖሮ በእርግጥም እንደተባለው ‹ጨው መነስነስ› በሆነ ነበር፡፡ በተቃራኒው ግን በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው ተጠቂዎቹ ኢትዮጵያዊ ይሁኑም የሌላ አገር ዜጎች መንግሥት ድርጊቱን አውግዟል። በግፍ የተገደሉት ዜጎቻችን ከእኛው አብራክ የወጡ መሆናቸው ሐዘናችንን ድርብ ያድርገው እንጂ፣ እኛም ከዜግነት ቀድሞ ለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር በቀለሙም ይሁን በእምነቱ የተነሳ እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል ሲፈጸምበት ማዘን ነው የሚገባን።
በሌላ በኩል የመንግሥትን መግለጫ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ጋር በማስተሳሰር ‹ሁሉም ሚዲያ ኢትዮጵያውያን ስለመገደላቸው እየዘገበ ባለበት ኢቢሲ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አላውቅም አለ› በሚል የስም ማጥፋት ዘመቻ ተካሂዷል። ይህ ደግሞ ከዕውቀት ነፃ የሆነ ትችት ነው። የሠለጠኑት ሚዲያ የዘገቡትማ ‹‹አይኤስ እንዳለው›› እያሉ ነው። ስም ያላቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ለምሳሌ የዴይሊ ሜይል፣ ቴሌግራፍ፣ ሃፊንግተን ፖስት፣ ሮይተርስ፣ ኤኤፍፒ፣ ወዘተ ዘገባን ማየት ይቻላል። እንዲያውም ለዚህ ዘገባ ሰፊ ሽፋን የሰጡት ኤፍፒ እና ሮይተርስ በዓይናችን ያየነውን ቪዲዮ ሳይቀር ‹‹በገለልተኛ ወገን ባይረጋገጥም…›› ወይም “The video, released via militant social media accounts and websites, could not be independently verified by The Associated Press.”, “Reuters was unable to verify the authenticity of the video,…”, “the video is not verified.” እያሉ ነው የዘገቡት፡፡ የመንግሥት መግለጫም ሆነ የኢቢሲ ዘገባ ይኼንኑ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ የጠበቀ ነው።
ለአይኤስ እነዚህን ሰዎች ለመግደል ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ብቻ በቂ ምክንያት ሆኖለታል። ለአይኤስ ኢትዮጵያ ማለት የክርስቲያኖች አገር ብቻ ነች። እናም ከእነዚህ ሰለባዎች ውስጥ ሙስሊሞች ስለመኖራቸው እንኳን ለማጣራት አልሞከረም፣ አይፈልግምም። ምክንያቱም የእሱ ዓላማ እስልምናን የመጠበቅ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ ሳይሆን እስላማዊ መንግሥት የመመሥረት የፖለቲካ አጀንዳ ነው። ኢትዮጵያ ግን የሙስሊሙም፣ የክርስቲያኑም፣ የሌላውም እምነት ተከታዮች አገር ነች። እስካሁን የሞቱት ኢትዮጵያውያን መሆናቸው እንጂ፣ ሁሉም ክርስቲያን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ አላየሁም። በሌላ አነጋገር አይኤስ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ከኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ነጥሎ ስለመግደሉ የተዘገበ አላነበብኩም። እናም በእኔ እምነት የአንዲት አገር ልጆች የሆኑ ሙስሊም፣ ክርስቲያንና ሌላ እምነት ተከታዮች በአንድነት ደማቸው ፈሷል። ሐዘናችንም ለእነዚህ ሁሉ መሆን አለበት።
ለማንኛውም እኛን እዚህ አገር ውስጥ የሚያነታርክን ጉዳይ በሥደት አጣብቂኝ ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን የሚፈይድላቸው ነገር የለም። መፍትሔው ለብሔራዊ ውርደታችን መንስዔ የሆነውን ድህነትና ኋላቀርነት ማስወገድ ነው። ዜጎቻችን ከእንዲህ ዓይነት ከሰብዓዊነት በታች የሆነ ድርጊት የመጠበቅ ዋስትና የሚሰጣቸው አገራችንን በስደት ከሚያስጠጉን ሀብታም አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ የጀመርነውን ጥረት ዳር ማድረስ ነው። አገራችንን ማበልፀግ ደግሞ የእኛው የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት እንጂ፣ ሌሎች አልምተዋት ስታበቃ ተመልሰን የምንገባባት አይደለችም፡፡ ስደት ይብቃ በማለት ሠርቶ ለመለወጥ የተመቻቹ ዕድሎችን አሟጠን መጠቀም ይኖርብናል።
እስከዚያውም ቢሆን ግን በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚፈጠርን ሽብርና አክራሪነትን መከላከል የምንችለው በመካከላችን የፀብ ግድግዳ በማቆም ሳይሆን፣ ከምንም በላይ የሆነ ሰብዓዊነታችን አንድ ሲያደርገን ነውና በዜጎቻችን ላይ የተፈጠረውን ዘግናኝ ድርጊት ከእምነትና ከቀለም ድንበሮች ተሻግረን በጋራ ማውገዝ አለብን። በአገር ውስጥ ብቻም ሳንወሰን ዓለም በሽብርተኝነት ላይ የሚያደርገውን ትግል ይበልጥ መደገፍ አለብን። ሠልፋችን ከመላው ዓለም ሰላም ፈላጊዎች ጋር ነውና።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡