Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበሊቢያ የአይኤስ ኃይሎች ሰለባ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን መንግሥት ሊወስደው የሚገባ ዕርምጃ

በሊቢያ የአይኤስ ኃይሎች ሰለባ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን መንግሥት ሊወስደው የሚገባ ዕርምጃ

ቀን:

በዋለልኝ እምሩ

በኢትዮጵያ ዜጐች ላይ በሊቢያ የሚገኘው የእስልምና አክራሪ ቡድን አይኤስ እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ግድያ መፈጸሙን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ካየሁም ከሰማሁም በኋላ፣ የተሰማኝን ሐዘንና ቁጭት ለመግለጽና መንግሥታችንም ሊወስደው ስለሚገባ ዕርምጃ የግል አስተያየቴን ለመግለጽ እንድችል ያቀረበኩት አጭር ጽሑፍ ነው፡፡ የምግብ ሰንሰለት አስገድዶን እንስሳትን ለምግብነት ስናርዳቸው እንኳን የሚፈጠርብን የሐዘን ስሜት አለ፡፡ አይኤስ በሰዎች ላይ የሚፈጽመው ግድያ በዱር አውሬዎች ላይ እንኳ ለመፈጸም የሚከብድ ዓይነት ጭካኔ ነው፡፡ አይኤስ ውስጥ ያሉ ሰዎች ለሚፈጽሙት ግፍ የጸጸት ስሜት ሳይሆን የሚታይባቸው በተቃራኒው ደስታ ነው፡፡ ጭካያቸው እንደሚያስደስታቸው የሚፈጽሙትን ግፍ የዓለም ሕዝብ ሁሉ እንዲመለከተው ማድረጋቸው ነው፡፡ የአይኤስ ድርጊት አንድ ፈላስፋ በሕግ ሥር መኖር የማይችሉ ሰዎች ባህሪ ነው ብሎ የተናገረው ትዝ እንዲለኝ አድርጎኛል፡፡ ፈላስፋው የእነዚህን ሰዎች ባህሪ መሠረት አድርጐ ‹‹ሰው ለሰው ተኩላ ነው›› ነበር ያለው፡፡

የዱር አራዊት እንኳ ህልውናቸውን አደጋ ላይ የምንጥልባቸው መስሎ ካልተሰማቸው ብዙውን ጊዜ ሰዎችን አይተናኮሉም፡፡ የሥልጣኔ ዘመን ነው በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ከአውሬ ይልቅ በራሱ ዘር ላይ ከፋ፡፡ ይህ የሚያመለክተው የሰው ልጅ አሁንም ቢሆን ከእንስሳዊ ባህሪው ያልተላቀቀና ሙሉ በሙሉ ህሊናዊ ሆኖ በሚዛናዊ አስተሳሰብ መመራት ያልቻለ መሆኑን ያመለክተናል፡፡

አይኤስ ግፍ በተሞላበት መንገድ ሰዎችን ሲገድል ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹ አይደሉም፡፡ ምዕራባውያን፣ የሩቅ ምሥራቅ አገር ጋዜጠኞችን፣ ሲቪል ሠራተኞችን፣ የዕርዳታ አገልግሎት ሠራተኞችን፣ ወዘተ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፡፡ በሊቢያም በአይኤስ ሰለባ የሆኑት የመጀመሪያዎቹ ግብፃውያን ክርስቲያኖች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ በቅርቡ ሰላሳ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ለይቶ የገደለበት ሁኔታ ግን በጥልቀት ሊመረመር ይገባል፡፡ በቀላሉ ከሁለት አንፃር ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ክርስቲያን በመሆናቸው ኢትዮጵያውያንን የግፍ ተግባሩ ማሳያ አድርጓቸዋል፡፡ አይኤስ እስላማዊ አክራሪ እምነት የሚከተል በመሆኑ ማንኛውም ክርስቲያን የጥቃት ዒላማው ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪዎች በተለይም በሶማሊያ የእስልምና አክራሪ ኃይል ላይ ለፈጸመው ጥቃት የብቀላ ዕርምጃም ሊሆን ይችላል፡፡ የእስልምና አክራሪዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ዕድል ፈንታ እንደሌላቸው ሲረዱ፣ በማንኛውም አጋጣሚ የሚያገኙትን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የቁጭታቸው መወጣጫ ሊያደርጉት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም፡፡

ዋናው ልንገነዘበው የሚገባን ጉዳይ አክራሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው ፍላጐታቸውን ለመፈጸም ባይችሉ እንኳን፣ የትም ቢሆን ኢትዮጵያውያንን እስከገደሉ ድረስ የተጎዳነውም የተደፈርነውም እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ድንበራችንን ዘልቀው መግባት ስላልቻሉ አልደፈሩንም ማለት አንችልም፡፡ በሰው አገር ላይም ቢሆን በጅምላ እስከተገደልን ድረስ ብሔራዊ ክብራችንን ተዳፍረዋል፡፡ በሊቢያ በተፈጸመው ድርጊት ብሔራዊ ክብራችን ተደፈረ ማለት አንችልም የሚል ኢትዮጵያዊ ቢገኝ፣ ‹‹ለምን ኢትዮጵያውያን ብቻ ተመርጠው ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገደሉ?›› ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠት አለበት፡፡ አክራሪዎች በሊቢያ ውስጥ ኢትዮጵያውያንን የገደሉበት ሁኔታ የሚያመለክተው በኢትዮጵያውያን ወይም በክርስቲያኖች ላይ ያላቸውን ጥላቻና ብቀላ ለመግለጽ ብቻ ሳይሆን ንቀታቸውንም ለመግለጽ ነው፡፡ ‹‹ይኼው በጅምላ ጨፈጨፍናችሁ፤ ምን ታመጣላችሁ?›› ከሚል የትዕቢት ስሜት የመነጨ ግድያ ነው፡፡

እንደ እኔ ግንዛቤና እምነት ከሆነ በሰው አገርም ቢሆን ዜጐቻችን በተለየ ሁኔታ የጅምላ ጥቃት ሰለባ እስከሆኑ ድረስ ብሔራዊ ክብራችን ተደፍሯል፡፡ ባይወሩንም ዳር ድንበራችንን አልፈው ወረራ እንደፈጸሙብን ይሰማኛል፡፡ ብሔራዊ ክብሩ የተደፈረበት ሕዝብና መንግሥት ምን ሊያደርግ ይችላል? መልሱ ቀላል ነው፡፡ ማድረግ የሚችለውን ያደርጋል፡፡ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በዲፕሎማሲያዊ መንገዶች ሁሉ ብሔራዊ ክብሩንና ጥቅሙን የሚያስጠብቅ ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ያልታሰበና አስደንጋጭ ሐዘን ውስጥ የከተቱትን፣ ዜጐቹን በሰው አገር ለጨፈጨፉበትና ብሔራዊ ክብሩን በተዳፈሩት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ ምን ሊሆን ይገባል?

ይህ ክስተት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምን ያህል ለዜጐቻቸው ተቆርቋሪና ለክብራቸው ተጨናቂ መሆናቸው የሚፈተሽበት እጅግ አስቸጋሪ ክስተት ነው፡፡ መንግሥት ድርጊቱን በማውገዝና በመኮነን ብቻ ሊያልፈው አይገባም፡፡ እንደዚያ ከሆነ መንግሥት በአሸባሪዎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚያችለው ወታደራዊ አቅም የለውም ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና መከላከያ ሠራዊታችን በአክራሪ አሸባሪዎች ላይ ወታደራዊ ኃይል የመውሰድ አቅም የለውም እንዳንል፣ በቅርቡ በአልሸባብ ላይ የተጎናጸፈው ድል አቅሙ እንዳለው ይመሰክርለታል፡፡ ወታደራዊ አቅም ቢኖረውም በሊበያ የተከሰተው ችግር የተለየ ነውና ከባድ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደራዊ ኃይል መጠቀሙ ከሞራልና ከዓለም አቀፍ ሕግ አኳያ ተገቢነት ይኖረዋል? ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ቢችል እንኳ (የኢትዮጵያንና የሊቢያን የጂኦግራፊ ርቀት በማሰብ) ሊቢያ ውስጥ የሚገኝን ኃይል እንዴት ማጥቃት ይቻለዋል? የሌሎች አገሮችን ድንበር አቋርጣ ኢትዮጵያ በዜጐቿ ላይ በተፈጸመ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመከላከል ወታደራዊ ኃይሏን መጠቀም የቻለችባቸው ታሪካዊ ክስተቶች አሉ ወይ? ለአሁኑ ክስተት የሚኖረው ፋይዳ ምንድነው? ወታደራዊ ኃይል ኢትዮጵያ መጠቀም ባትችል ድርጊቱን በማውገዝ ብቻ ብታልፈው የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው?

እነዚህን ጥያቄዎች የታሪክና የፍልስፍና ዕውቀቴን እንዲሁም የግል እምነቴን መሠረት አድርጌ በአጭር በአጭሩ እንደሚከተለው ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

የመጀመሪያውን ጥያቄ በአጭሩ ለመመለስ ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮችም ውስጥ ቢሆንም እንኳ፣ ዜጐቿ ላይ ለሚደርስ የጅምላ በደል ወታደራዊ ኃይል እስካላት ድረስ ኃይሏን ለመጠቀም የሚከለክላት ሞራላዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌና አስተሳሰብ የለም፡፡ ምክንያቱም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ኢትዮጵያ የምታደርገው ጦርነት ፍትሐዊ ጦርነት እንጂ ፍትሐዊ ያልሆነ አይደለምና፡፡ ፍትሐዊ ጦርነት ተገቢ መሆኑን የክርስቲያን ፈላስፋዎች አጉስቲንና ቶማስ አኪዮናስ ሳይቀሩ ያመኑበትና ትክክለኛ መሆኑን የገለጹት ነው፡፡ ከሕግ በላይ የሆነን ኃይል በሕግ አስከባሪ ኃይል ማጥቃት ተገቢ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በአይኤስ ላይ ወታደራዊ ዕርምጃ ከወሰደች ከሕግና ከሞራልም አኳያ ነቀፌታ አይኖርባትም፡፡ ከድንበራቸው ባሻገር በጠላቶቻቸው ላይ ጥቃት ለመፈጸም ለአሜሪካና ለሌሎች ምዕራባውያን ብቻ የተሰጠ አይደለምና፡፡

አስቸጋሪው ጥያቄ ሁለተኛው ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሊቢያ ድረስ ዘምታ ዜጐቿን በጭካኔና በጅምላ የገደሉባትን እንዴት ልትበቀል ትችላለች? በኢትዮጵያና በሊቢያ መካከል እጅግ ሰፊ የሆነችው ሱዳን አለች፡፡ አይኤስን ለማጥቃት ሱዳንን መሻገር ወይም ሜዲትራንያን ባህርን ማቋረጥ ይጠይቃል፡፡ አይኤስ የመሸገባት ሊቢያ አልሸባብ በቅርብ ርቀት እንደመሸገባት ሶማሊያ አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አይኤስን በአጭር ጊዜ ውስጥ ድራሹን ማጥፋት የሚችል አቅም ቢኖረው እንኳ፣ አይኤስን በየት በኩል ሊያገኘው ይችላል? ሊቢያ ሩቅ ናትና፡፡ ነገሩ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ቁጭት መሆኑ ነው፡፡ የእንግሊዝ ንግሥት ኃይልና ማንገራገር ተመልክተው፣ ‹‹ባህሯን ተማምና ነው እንጂ እንግዲያ መሬት ወርዳ አትገጥመኝ፤›› እንዳሉት መሆኑ ነው፡፡

ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ አድርጌ የምወስዳቸው የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • በመጀመሪያ አይኤስን በወታደራዊ ኃይል ለማጥቃት መወሰን፡፡
  • ሊቢያ ውስጥ አይኤስን ማጥቃት የሚያስችል ወታደራዊ ኃይል መገንባት፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ባይኖራትም እንኳ በአየር ላይ ነዳጅ መሙላት የሚችል አውሮፕላን በግዥም፣ በኪራይም፣ በዕርዳታ ወይም በውሰት እንዲኖራት ማስቻል፡፡
  • ጐን ለጐን ወዳጃችን የሆነውን የሱዳንን መንግሥት የአየር ክልሉን እንዲፈቅድልን የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማከናወን፡፡
  • በአየር ኃይላችን አይኤስ የጉልበት ምንጭ የሆኑትን ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ መሠረቱን ማውደም፡፡
  • በመጨረሻ አጋር ከሚሆኑን የአፍሪካና የዓለም መንግሥታት ወታደራዊ ኃይሎች ጋር በመተባበር በእግረኛ ጦር አይኤስን ሊቢያ ውስጥ በማጥቃት ፍፃሜው ሜዲትራንያን  ባህር እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡

ሦተኛውን ጥያቄ በአጭሩ ለመመለስ ለተመሳሳይ ድርጊቶች ኢትዮጵያ በታሪኳ ያካበተችው ልምድ አለ ወይ? የሚል ነው፡፡ ብዙዎቻችን ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከተዳፈሯት ከወራሪዎች ጋር ያደረገቻቸውን ጦርነቶችና ያስገኘቻቸውን ድሎች በደንብ እናስታውሳለን፡፡ በውጭ አገር በሚኖሩ ዜጐቿ ላይ ለተፈጸመ ጥቃትስ? በቅርቡ እንደምናስታውሰው በመካከለኛው ምሥራቅ በዜጐቻችን ላይ ጥቃት ሲደርስባቸው በአየር በማጓጓዘ የነፍስ አድን ሥራ ተከናውኗል፡፡ የሶማሊያው አልሸባብ ገና ለገና አንገራግሮብናል፣ ፎክሮብናል ብለን እስከ መናገሻው ገብተን ቢያንስ ቢያንስ አፉን ሞልቶ ዳግም በድፍረት እንዳይናገረን አድርገነዋል፡፡ መኖሪያውም ጫካ ለጫካ እንዲሆን አድርገነዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያ በታሪኳ በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጐቿና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ እንዲሁም የክርስትና እምነት በሚከተሉት ሁሉ ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በየመን ውስጥ በሚኖሩ አይሁዶች አማካይነት በተፈጸመ ጊዜ፣ በንጉሥ ካሌብ የሚመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀይ ባህርን አቋርጦ የመን ውስጥ በመግባት፣ ከግፈኛው የአይሁድ ሠራዊት ጋር ከባድ ጦርነት ገጥሞ ድል በማድረግ የየመን ክርስቲያኖችንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑትን ሁሉ ነፃ አውጥቶ በድል አድራጊነት ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡

በካሌብ ዘመን በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ቁጥሩ ይነስ እንጂ አሁን በሊቢያ ውስጥ የሆነውን ዓይነት ነው፡፡ እዚህ ላይ መጠየቅ ያለብን ከዛሬ 1,400 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያውያን ባህር አቋርጠው ሰብዓዊ መብትን ያውም ለሌሎች አገር ዜጐች ሳይቀር ማስከበር ከቻሉ፣ በአሁኑ ጊዜ እንዴት አይቻለንም? የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን ባህር አቋርጠው መዋጋት ከቻሉ የአሁኖቹ ኢትዮጵያውያን በአየር ላይ መዋጋት እንዴት ያቅተናል?

አራተኛው ጥያቄ በወታደራዊ ኃይል የዜጐቻችንን ደም ባንመልስ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው? ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ መጀመሪያው ለአሸባሪዎች የልብ ልብ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ተጨማሪ ጥቃት ለመፈጸም ያነሳሳቸዋል፡፡ አንዱን ጉንጫችንን ሲመቱን ሌላውን ደግመን እየሰጠናቸው እስኪጨርሱ ዝም ብለን ማየቱ ተገቢ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ዘግናኝ ድርጊት ማውገዝ ብቻ ተገቢ አይሆንም፡፡ አውግዘን እጃችንን ሰብስበን ከተቀመጥን ሌላው ችግር ከፍተኛ የሆነ ብሔራዊ ውርደትንና ኃፍረትን ያስከትልብናል፡፡ በየትውልዱ የሚተላለፍ የማያቋርጥ ሐዘን፣ ከታሪካችን የማይጠፋ መጥፎ ጠባሳ ሆኖ ይቀራል፡፡

ኢትዮጵያ ማንነቷን የምታሳይበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ቢያንስ ግብፅ በአይኤስ ላይ የወሰደችውን ዕርምጃ የሚስተካከል ኢትዮጵያ እስካልወሰደች ድረስ፣ ብሔራዊ ክብራችን መጠበቅ የሚያስችለን ምንም ዓይነት ኃይል እንደሌለን የሚያመለክት አንገት የሚያስደፋ ክስተት ሆኖ ይቀራል፡፡ ግብፅ የወሰደችውን የሚስተካከል ጥቃት መፈጸም ባንችል በዓባይ ግድብ ላይ ግብፅ የሰላም አማራጭ መከተሏ ነው እንጂ፣ ወታደራዊ ኃይል በመጠቀም የግድቡን ሥራ ለማቆም ብትወስን ኖሮ የግብፅን ኃይል የሚገዳደር ኃይል አልነበረንም ነበር የሚል ስሜት በሕዝቡ ላይ ሊፈጠር ይችላል፡፡

ለነገሩ መከላከያ ሠራዊታችን ግዳጅ ከተሰጠው እንኳን አይኤስን ይቅርና ማንም ቢሆን እንኳ ሞቶም ቢሆን የአገሩን ክብር ለማስጠበቅ ወደ ኋላ እንደማይል ይታወቃል፡፡ ዋናው ነገር መንግሥት ወታደራዊ ኃይል ለመጠቀም መወሰንና መዘጋጀት አለበት፡፡ በዚህ ረገድ የሕዝቡ ድጋፍ አይለየውም፡፡ በዚህ ፈታኝ ሁኔታ መንግሥት ማንነቱን ማሳየት አለበት፡፡ የውግዘት ጋጋታ ብቻውን በአይኤስ ላይ የሚያመጣው አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡

ስለዚህ መንግሥት ብሔራዊ ክብርን መጠበቅ የሚያስችል ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡ ብሔራዊ ክብርን መጠበቅ የማይችል መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ምን ያህል እንደሚያስንቅና የተቃውሞ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ኢሕአዴግ ከራሱ ታሪክ አንፃር በደንብ ሊረዳው ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዋናው የፖለቲካ መሠረት በዜጐች ዘንድ ብሔራዊ ስሜትን መጠበቅና ብሔራዊ ክብርን መንከባከብ ነው፡፡ ብሔራዊ ስሜትን በሕዝቡ ዘንድ መጠበቅ ካልተቻለ በኢትዮጵያ ውስጥ ስኬታማና ተወዳጅነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር አይቻልም፡፡

በሊቢያ ለተፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት ጥሪዬ አንድ ነው፡፡ መንግሥት አይኤስ ላይ ወታደራዊ ኃይል ይውሰድ የሚል ነው፡፡ በመከላከያ ኃይላችን ድል ያነቡ የኢትዮጵያውያን ዓይን ይታበስ፣ ያዘኑ ይጽናኑ፣ በዜግነት ክብር ስሜታቸው የተጐዳ ሞራላቸው ይጠበቅ፡፡ ካልሆነ ግን በአሸዋ ጉድጓድ እንደ ውሻ በጅምላ ተወርውረው ተቀብረው የቀሩት የምስኪን ኢትዮጵያውያን ነፍስ የሰቆቃ ድምፅ በዙሪያችን እንደ ጮኸ ይኖራል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ባልደረባ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

                 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...