Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በኢትዮጵያውያን ላይ የፈተጸመውን ጭፍጨፋ በመቃወም መፈክር ይዘው የወጡ ሠልፈኞች

ትኩስ ፅሁፎች

ፎቶ በሪፖርተር/ታምራት ጌታቸው

ፈሪ ቁም

“ፈሪ ቁም – ፈሪ ቁም፣

ምንተ ላል-ይበላ

ሲሸሽ የሞተ ሰው፣

ተዝካሩ አይበላ፡፡”

እንዲል ያበው ብሂል

ሁሉም የየራሱን፣ የመከራ መስቀል

ደፍሮ በመሸከም፣ ሳይደማ-ሳይቆስል

ሞት ሳይኖር፡ ትንሣኤ፡ የሚገኝ ይመስል…

ስንቶች እዚያ ማዶ፡ ከነጭ ሠራሹ

የነገደ ያንኪን

መንግሥተ-ሰማያት፣ ለመውረስ የሚሹ

(ያውም በቀውጢ ቀን)፡

ያቺን ምስኪን አገር፡ እየጣሏት ሸሹ፡፡

  • ሰሎሞን ሺፈራው “ተወራራሽ ሕልሞች” (2004)

**************

ከጠብታ ማር

ለምሳሌ ልጅህ ሲጋራ እንዳያጨስ ብትፈልግ ስለ ሲጋራ መጥፎነት አትስበክለት፡፡ ሆኖም ሲጋራ ማጨስ የአንድ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች እንዳይሆን ወይም በሩጫ ውድድር እንዲሸነፍ የሚያደርገው መሆኑን ንገረው፡፡

የሌላውን ፍላጎት የመጠበቅ ነገር ከማንኛውም ነገር ጋር ማለትም ከሕፃናት ወይም ከጥጃ ወይም ከዝንጀሮ ጋር በምናደርገው ግንኙነት ሁሉ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰንና ልጁ አንድ ቀን አንድ ጥጃ ወደ ጋጥ ለማስገባት ሞከሩ፡፡ ሆኖም አብዛኛው ሰው የሚፈፅመውን ስህተት ፈፀሙ፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን እንጂ ጥጃው የሚፈልገውን አላደረጉም፡፡ ኤመርሰን ከኋላ ወድሮ እምቢ አለ፡፡ ይህን ከንቱ ጥረቱ ታይ የነበረችው ሠራተኛ ጥጃው ምን እንደፈለገ ገባት፡፡ ጠጋ አለችና ጣቷን በዘዴ ለጥጃው አጎረሰችው፡፡ ጥጃው ጣቷን መጥባት ሲጀምር ቀስ ብላ ወደጋጡ እየተራመደች ይዛው ገባች፡፡ ሠራተኛው ምንም እንኳን ድርሰት የመፃፍ ችሎታ ባይኖራትም በዚያች ወቅት ከኤመርሰን የበለጠ ማስተዋል ችላ ነበር፡፡

ከተወለድክ ጀምሮ ያደረግካቸውን ለምሳሌ ለቀይ መስቀል ማኅበር 100 ብር የሰጠህበት ጊዜ ቢኖር እንኳን ሌላውን ከመውደድ የመነጨ በጎ ሥራ ለመሥራት ስለፈለግህ ነው፡፡ ከመርዳት ፍላጎትህ ይልቅ የብር ፍላጎትህ ቢያይልብህ መቶ ብሩን ባልሰጠህ ነበር፡፡ እርግጥ አስተዋጽኦው እንድታደርግ የጠየቀህ ሰው እምቢ የማትለው ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ እውነት አለ፡፡ ብሩን የሰጠኸው ምናልባት ከሰውየው አንድ የፈለግከው ነገር ስለነበረ ነው፡፡

  • ዴል ካርኒጌ፣ “ጠብታ ማር” (1989)

***********

ዘራፊው

በአንድ ወቅት አንድ በጣም ታዋቂ የሆነ አንድ አገረ ገዢ ሌሎች ነገስታትና መሪዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ግብር ጠርቶ ህዝቡን ያበላ ነበር፡፡ ህዝቡም በጣም ይወደው ነበር፡፡

በዚያን ጊዜ ብርዱን ሳይፈሩ፣ ቆላው ሳይበግራቸው፣ ተራራዎችና በረሃውን እንዲሁም ቁጥቋጦውን አቋርጠው የሚነግዱ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ታዲያ ሽፍቶችና ዘራፊዎችን ይፈሩ ስለነበር ብቻቸውን አይጓዙም ነበር፡፡ በቡድንም ሆነው ይጓዙ ነበር፡፡

አንድ ነጋዴ ታዲያ አብሮት የሚጓዝ ቡድን ስላጣ በቡድን መጓዝ የተለመደ ቢሆንም ብቻውን ለመጓዝ ወሠነ፡፡ እናም ተራራውን ሁሉ አቋርጦ ብቻውን መጓዝ ቀጠለ፡፡ ታዲያ እንደፈራውም አንድ ሽፍታ አጋጠመው፡፡

“አንተ ማነህ አለው?” ሽፍታው

“ነጋዴ ነኝ::”

“ብቻህን ነህ?”

“አይ፣ ጓደኞቼ ከኋላ ናቸው አሁን ግን ብቻዬን ነኝ፡፡”

በዚህም ጊዜ ሌላ ነጋዴ ከኋላ ደረሰ፡፡ ነጋዴውም ከፊት ያለው ነጋዴ በሽፍታ መያዙን ሲያይ ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቆ የሚሆነውን ሁሉ ማየት ጀመረ፡፡ እናም ሽፍታው የመጀመሪያውን ነጋዴ ገድሎ ሲቀብረው ሁለተኛው ነጋዴ በድንጋጤ ይመለከተው ነበር፡፡

ነጋዴውም እንዲህ ብሎ አሰበ “እንዴት ነው መጓዝ የምችለው? እኔም ይኽው ችግር ይገጥመኛል፡፡” ብሎ ለማለፍ በጣም ፈርቶ ስለነበረ እዚያው ባለበት ከቆየ በኋላ እንዲህ ብሎ አሰበ፡፡ “እዚህ እስከዘለአለሙ መቆየት አልችልም፡፡ ስለዚህ ጉዞዬን መቀጠል አለብኝ፡፡” ሽፍታው ነጋዴውን የገደለበትን ስፍራም አልፎ በመጓዝ ወደአንድ መንደር ደረሰ፡፡ መጥፎው ግድያ በአእምሮው እየተመላለሰ ስላስቸገረውና ዘግናኝ ሃሳቦች ስላበሳጩት ፈገግ ማለት አልቻለም፡፡ የመንደሩም ሰዎች “አንተ ነጋዴ፣ ድሮ ስናውቅህ በጣም ተጫዋች ነበርክ:: አሁን ግን ምን ሆነህ ነው የጨፈገገህ?” ብለው ጠየቁት፡፡ “ደክሞኝና ውሃ ጠምቶኝ ነው፡፡” አላቸው፡፡

ያንን ዕለት ሌሊትም እዚያው አሳልፎ በማግስቱ ጠዋት ጉዞውን ለመቀጠል ሲነሳ ሰዎቹ “ምን ሆነሃል? እያሉ ጥያቄያቸውን ይገፉበት ጀመር፡፡”

እሱም ልንገራቸው ወይስ አልንገራቸው እያለ ከራሱ ጋር ሲታገል ቆይቶ በመጨረሻም የሆነውን ሁሉ እንዲህ ብሎ ተረከላቸው “ኑና ያየሁትን እነግራችኋለሁ፡፡ ትናንት ያየሁት ዘግናኝ ነገር ነው፡፡ አንድ ሰው ከፊት ፊቴ ይጓዝ ነበር፡፡ ሰውየውን አላውቀውም ነበር፡፡ ሆኖም በቅሎዎቹና አህዮቹ ላይ የሚሸጡ ቁሳቁሶች ጭኖ ስለነበር ነጋዴ መሆን አለበት፡፡ ታዲያ አንድ ሽፍታ በቅሎዎቹንና አህዮቹን በሙሉ ከወሰደበት በኋላ ገድሎ ቀበረው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቁጥቋጦ ውስጥ ተደብቄ እመለከት ስለነበረ ያየሁት ዘግናኝ ነገር ከአእምሮዬ አልጠፋልህ ስላለኝ ነው ደንዝዤ መናገርም ሆነ መጫወት ያቃተኝ፡፡”

ይህንን ታሪክ የሰሙት የመንደሩ ሰዎች ሽፍታው የመንደራቸው ሰው መሆኑን ያውቁ ስለነበር ታሪኩን ሰምተው ሲያበቁ በዝምታ ተውጠው እንዲህ እያሉ ማሰብ ጀመሩ “ይህ ነገር እዚህ ሲከሰት ማየት በጣም መጥፎ ነው፡፡ የሞተውንም ሰው ማንነት ማወቅ አለብን፡፡”

ሆኖም ስለሽፍታው ምንም ነገር አላሉም፡፡

ነጋዴውም ጉዞውን በመቀጠል በመንገዱ ላይ ለሚያገኛቸው የመንደሩ ሰዎች ሁሉ አንድ ሰው ተገድሎ ሲቀበር አይቻለሁ፡፡ ሰውየውንም ሆነ ሽፍታውን አላውቃቸውም፡፡ ስለዚህ ሁለተኛ ወደዚህ ሥፍራ አልመለስም፡፡” እያለ ይነግራቸዋል፡፡

አገረ ገዢውም ነጋዴዎች በግዛቱ ሲያለፉ በሽፍታዎች ተይዘው እንደሚገደሉና እንደሚቀበሩ በሰማ ጊዜ በጣም ተበሳጨ፡፡

“በእኔ ግዛት ውስጥ ሽፍቶች እንዴት ይህንን ይፈፅማሉ?” በማለት ለችግሩ መፍትሔ ማፈላለግ ጀመረ፡፡

“ግብር ጥዬ ሁሉንም ሰው በመጋበዝ ሽፍታውን ልይዘው እሞክራለው፡፡” ብሎ ወሰነ፡፡ እናም እንደተለመደው አገረ ገዢው ግብር ጥሎ ሁሉም ሰው ታደመ፤ ገበሬዎች፣ ቄሶችና ሁሉም ሰዎች መጥተው ይበሉ፣ ይጠጡና ይዝናኑ ጀመር፡፡

አገረ ገዢውም ከመቀመጫው ተነስቶ “እባካችሁ አድምጡኝ አንድ ነገር ላማክራችሁ እፈልጋለሁ፡፡” አለ፡፡ በመቀጠልም እንዲህ አለ “አባቶች፣እናቶች፣ወንድሞችና እህቶች ሆይ፡፡ ሴት ልጄ ታማብኛለችና መድሐኒቱ ትርንጎ ነው፡፡ እወንዝ ዳር ጫካ ውስጥ የበቀለ ትርንጎ ካገኘች ልጄ ትድናለች፡፡ ወንዝ ዳርና ጫካ ውስጥ ብቻ ሣይሆን በመንደሩ ሰዎች የማይታወቅና በሌሎች ሰዎችም ከማይዘወተር ሞቃታማ ቦታ መገኘት አለበት፡፡ እናም ይህንን ትርንጎ ማን ሊያመጣልኝ ይችላል?”

እድምተኞቹ ሁሉ “እንደዚህ ዓይነት ትርንጎ ከየት ሊገኝ ይችላል?” በማለት ያስቡ ጀመር፡፡ ሁሉም በፀጥታ ተውጠው ሣለ ሽፍታው ከመቀመጫው ድንገት ብድግ ብሎ “ክቡርነትዎ ትርንጎውን እኔ ማምጣት እችላለሁ፡፡ ነገር ግን የሁለት ሣምንታት ጊዜ ይስጡኝ፡፡” ብሎ ጠየቀ፡፡

እናም ከአገረ ገዢው ሽልማትን ለማግኘት ሲል ሽፍታው ነጋዴውን የቀበረበት ቦታ ላይ ትርንጎ ስለነበር ሌላ ሰው ሳይቀድመው ባስቸኳይ ወደዚያው በመሄድ ትርንጎውን ይዞ ወደ አገረ ገዢው ተመለሰ፡፡ በቦታው ላይ ከነበሩት በርከት ያሉ ትርንጎዎች ሁለቱን በከረጢት አድርጎ ይዞ ተመለሰ፡፡

ሁለቱንም ትርንጎዎች በመያዝ ወደ አገረ ገዢው ቤት በመሮጥ ጠባቂውን “አገረ ገዢውን ማነጋገር እፈልጋለሁ፡፡” አለው፡፡

ሁለትና ሶስት ቀናትን ከደጃፉ ቁጭ ብሎ ከጠበቀ በኋላ በመጨረሻ አገረ ገዢው ዘንድ እንዲገባ ተፈቀደለት፡፡

“ትዕዛዞዎትን ፈፅሜአለሁ፤ የሚፈልጉትንም ይዤ ስለመጣሁ እባክዎ ይቀበሉኝ፡፡”

አገረ ገዢውም እንዲህ አለ “ያዘዝኩህን ይዘህ ስለመጣህ ደስ ብሎኛል፡፡ ሆኖም እንድትሰጠኝ የምፈልገው ሰው በተሰበሰበበት ነው፡፡”

ከዚያም ለመንደሩ ሰው ሁሉ መልዕክት ልኮ ወደ መኖሪያ ቤቱ ጠራቸው፡፡ ሰውም ካለበት ሁሉ ተሰባሰበ፡፡

ግብርም ጥሎ ሰው ሁሉ እየበላ እየጠጣ ሳለ አገረ ገዢው እንዲህ አለ “እንደሰማችሁት ይህ ሰው ቃሉን ጠብቋል፡፡ ትርንጎውን አመጣለሁ ባለው መሠረትም አምጥቷል፡፡ ይህ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ያመጣውንም በእናንተ ሁሉ ፊት መቀበል እፈልጋለሁ፡፡”

ሰዎቹም የሽልማት ገንዘብ ያገኛል ብለው ስላሰቡ ቀኑበት፡፡ ትርንጎዎቹንም እንዴት ሊያገኝ እንደቻለ ማወቅ ፈለጉ፡፡ ሽፍታውም ከረጢቱን ፈትቶ ትርንጎዎቹን አስረከበ፡፡ ሆኖም ትርንጎዎቹን ከከረጢቱ ሲያወጣቸው ትርንጎ ነበሩ፡፡ ታዲያ ለአገረ ገዢው በሰጣቸው ጊዜ ወደ ሁለት የሰው ጭንቅላት ተቀየሩ፡፡

ይህም በሆነ ጊዜ ህዝቡ ሁሉ ተቆጣ፤ ሽፍታውም ዓይኑን ማመን አቃተው፡፡ አገረ ገዢውም ፈገግ አለ፡፡ ስለሆነውም ነገር ምክንያት ስለነበረው አልተገረመም፡፡ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሽፍቶች ህዝቡን ገድለው እንዳይቀብሩበትና አንድ ቀን ክፉ ስራቸው ይጋለጥ ዘንድ አገረ ገዢው ለአምላኩ ይፀልይ ነበር፡፡

“እባክህ አምላኬ እውነቱን አሳየኝ፡፡” ብሎም ይፀልይ ነበር፡፡

እናም የዚያን ዕለት አምላክ እውነቱን ገለጠለት:: ስለዚህ ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ መሆኑን አውቆ ጠባቂዎቹ እንዲያስሩት አዘዘ፡፡ (አገረ ገዢው ነፍሰ ገዳዩን የለየው እንደዚህ ወዳለ ቦታ ሌላ ማንም ሊሄድ እንደማይችል ስለሚያውቅ ነው፡፡)

የዚህ ተረት መልዕክትም የሟች ደም በከንቱ ፈሶ እንደማይቀርና አምላክ እንደሚፋረደው የሚያሣይ ነው፡፡

  • በድረስ ገ/መስቀል የተተረከ የአማራ ተረት

**********

ማስታወቂያ ከመቶ ዓመት በፊት

ስለ ሳሙና የንግድ ማስታወቂያ S.F. ይህ ምልክት ያለበት ሳሙና ጥሩ የሚበልጥ ሳሙና ነው፡፡ እሱ ብቻ ልብስ የማያገማ የማያቃጥል ጥሩ አዲስ አበባ ተሰራ፡፡ ይህ ሳሙና ረኪስም ጤናም ነው፣ በብር 14 ኪሎ ይገኛል፡፡ ይህ ሳሙና ለጤና እጅግ ማለፊያ ውስጡ የሚጨመረው ጥሩ የጤና የሚሆን መድኃኒት ተመርጦ ነው፡፡ ገላ ነክ ልብስ ቢያጥቡበት ጤና ይሆናል፡፡ ለጤና ገላ ቢያጥቡበት ይሆናል፡፡ ያንን የድሮውን የሚገማውን የሞራ ሳሙና አትግዙ ቆይቶ ይቆማምጣል አሉ፡፡

  • “የአማርኛ መድበለ ምንባብ” (1916)

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች