መንግሥት እስካሁን ሲያራምዳቸው ከነበሩት በተለየ መንገድ የአምስት ዓመት የተጋነነ ወይም የተለጠጠ የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ ይፋ አድርጎ ሲተገብር አምስተኛው ዓመት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ ይጠበቅ የነበረው ብዙ ለውጥና ትራንስፎርሜሽንም የሚጠበቀውን ለውጥ ሳያመጣ ተገባዷል፡፡
የዕቅዱ ይዘቶች ከሆኑት መካከል የአሥር ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ ማስመዝገብ አንዱ ነበር፡፡ በውጤቱ ግን ሦስት ቢሊዮን ዶላር ላይ እንዲገደብ ግድ ሆኖበታል፡፡ መንግሥት የአምስት ዓመቱን ዕቅድ ይፋ ከማድረጉ ቀድሞ ከሁለት ዓመት በላይ ዝግጅት ለማድረግ መገደዱም አይዘነጋም፡፡ የዝግጅቱ ዓላማም የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመቅረፍና የአስፈጻሚዎችን አቅም ለመገንባት ታስቦ እንደነበር መንግሥት መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖም በያመቱ የሚታየው አፈጻጸምና የታቀደው ዕቅድ መጠን አልገናኝ እያሉ ተራርቀው ቀርተዋል፡፡ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መገባደጃ የሆኑት የመጨረሻዎቹ ዓመታት እየተቃረቡ ሲመጡ፣ በታቀደውና በተፈጸመው መካከል የሚታየው ክፈተት እየሰፋ ሲመጣም፣ የመንግሥት መግለጫዎች ‹‹በሚቀጥለው በጀት ዓመት እናካክሳለን፤ አሁን ያልተፈጸመውን ጨምሮ የመጪውንም በጀት ዓመት ዕቅድ አብረው እንደሚያስኬዱ የሚገልጹ መሥሪያ ቤቶች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ቀጠለ፡፡
ከመነሻው መንግሥት ያወጣው ዕቅድ የተለጠጠ መሆኑን ማመን ጀምሮ ነበር፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ በተለይ የልማት አጋር ቡድኖች ከሚላቸው አገሮች ሳይቀር ይሰነዘር የነበረው ትችት አስተዋጽኦ ማድረጉም በወቅቱ ሲደረጉ የነበሩ ክርክሮች ዋቢ ናቸው፡፡ የልማት አጋር ቡድኖች የሚባሉት አገሮችና ዓለምአቀፍ ተቋማት ከሚያቀርቡት ትችት ባሻገር፣ ሦስት የእስያ አገሮች በተለየ የልማት ሞዴሎችን የኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳቦችን ለመንግሥት ሲተነትኑና ሲያማክሩ ሰነባብተዋል፡፡
የዓለም ሁለተኛዋ ልዕለ ኢኮኖሚ ቻይና፣ የቴክኖሎጂ ማማዋ ጃፓንና የእስያዋ ነብር ደቡብ ኮሪያ የአዝማችነት ሚናውን ይዘው፣ ለመንግሥት የፖሊሲና የልማት ሞዴሎቻቸውን ሲያስተዋውቁ፣ ልምዳቸውን ሲያካፍሉና ይበጃል ያሉትን መንገድ ለመንግሥት ሲጠቁሙ አምስት ዓመቱ ተገባዷል፡፡ ለሌላኛው አምስት ዓመትም የልማት አማራጮችን በየፊናቸው እያቀረቡ የመፍትሔ ሐሳብ እንካችሁ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ሦስቱም አገሮች ወደ አንድ አቅጣጫ ያጋደለ ምክር እየለገሱ ናቸው፡፡ የኢኮሚው ምህዋር በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚመራበትን ሥልት በማመላከት የተለያዩ ዓውደ ጥናቶችን፣ ስብሰባዎችንና ጉባዔዎችን እየዘረጉ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እያመከሩ ናቸው፡፡
ቻይኖቹ ከጃፓን የተዋሱትንና በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የገነቡበትን አካሔድ እየጠቆሙ ናቸው፡፡ ደቡብ ኮሪያውያኑ በአመዛኙ በመንግሥት ኢኮኖሚያዊና መሠረተ ልማታዊ መዋቅር ላይ ያተኮረ ምክር ይለግሳሉ፡፡ በአንጻሩ ጃፓኖች በአገሪቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ የምርት ዓይነቶችና የገበያ አማራጮች፣ የአሠራርና አመራረት ሥልቶች ይናገራሉ፡፡
ሦስቱም አገሮች ከፍተኛ ምሁራኖቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ምክክር እንዲያደርጉ፣ እንዲያስረዱና እንዲያስተምሩ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ሲያልፍም እንደ ጃፓን ያሉ ምሁራን በመጪው ዓምስት ዓመት በአገሪቱ ይተገባራል ተብሎ ለሚጠበቀው ሁለተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ላይ በቀጥታ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ስለመጋበዛቸውም ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
በቅርቡ የማጠቃለያ ሪፖርታቸውን ለመንግሥት ባለሥልጣናት ያሰሙት ኮሪያውያን በበኩላቸው የመጀመሪያውን የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ ገምግመው የደረሱበትን፣ ለሁተኛው የአምስት ዓመት ዕቅድ ይበጃል ያላቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችም በሪፖርት አሰምተው ነበር፡፡
ለአብነትም በጨርቃ ጨርቅና አልበሳት ኢንዱስትሪ መስክ መንግሥት በዚህ ዓመት መጨረሻ ከወጪ ንግድ ለማግኘጥ አቅዶት የነበረው የገቢ መጠን አንድ ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በውጤቱ ግን ከ200 ሚሊዮን ዶላር በእጅጉ የሚፈራ መጠን አግኝቶበት ዓመቱ እየተገባደደ ይገኛል፡፡ ዓምና ከዘርፉ ያቀደው ገቢ 700 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በተግባር የተገኘው መጠን 110 ሚሊዮን ዶላር ሆኖ ዓመቱ ተጠናቋል፡፡ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪም የታየው ተመሳሳይ ነው፡፡ ዓምና ከዚህ ዘርፍ 416 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል የተባለበት ይህ ዘርፍ፣ በውጤቱ ከ130 ሚሊዮን ዶላር በታች አስዝግቦ ተካተተ፡፡ በዚህ ዓመት ይገኛል የተባለው መጠን ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ሲሆን እስካፈው መንፈቅ ዓመት በታየው አፈጻጸም ግን 65 ሚሊዮን ዶላር ላይ መገደቡን በቅርቡ በፓርላማ ሪፖርት ያቀረበው ንግድ ሚኒስቴር መጥቀሱ የሚታወስ ነው፡፡
በመሆኑም የአገሪቱ የወጪ ንግድ ላይ ትልቅ ትኩረት የተሰጣቸው እነኚህ ሁለቱ ዘርፎች ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኙና መንግሥትም ከአገር ውስጥና ከውጭ ባለሀብቶችን እያባበለ፣ የተለየ ጥቅማጥቅምና ድጋፍ እያደረገባቸው የሚገኙ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ መንግሥት ያሰበውን ትራንስፎርሜሽን ሊያመጡለት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ የጃፓንና የዓለም ባንክ ባለሙያዎችም መንግሥት የአገሪቱን ኢኮኖሚ መዋቅር ለመለወጥ የሚያስችለውን ምዕራፍ መጓዝ፣ ሳይቻለው መቅረቱን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ መንግሥትም ይህንኑ ቢቀበልም የትራንስፎርሜሽን ምልክቶችን ማየት መጀመሩን ከመግለጽ አልተቆጠብ፡፡ ምናልባት አገሪቱ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጣው በመጪው አምስት ዓመት ውስጥ እንደሚሆን ጃፓኖቹ ተስፋ ሰጥተዋል፡፡
ከአራት ዓመታት በፊት ማለትም የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መተግበር ሲጀመር ጀምሮ የኮሪያ ልማት ኢንስቲትዩት ከተባለው ተቋም ጋር ግንኙነት የጀመረው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በኩል ነበር የኮሪያውያኑን ተሞክሮ መቅሰም የጀመረው፡፡ የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት እየጠነከረ መጥቶ ለሁተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ ዋና ዋና ለሚባሉ የፖሊሲ አጀንዳዎች የልማት መርሐ ድርጊት መንደፍ ጀመሩ፡፡
ከሰሞኑ የማጠቃለያ ሪፖርታቸውን ለመንግሥት ባለሥልጣናት አሰምተውና የመትሔ ሐሳቦችን አቅርበው የተመለሱት ኮሪያውያኑ፣ መነሻ ያደረጉት ባለፈው አምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ የነበረውን አፈጻጸም መገምገም ነበር፡፡ በመሆኑም ከአምስት ዓመት በፊት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የአሥር ዕድገት ሲያዝመዘገብ የነበረው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ፣ ከሦስት ዓመታት በኋላ ዕድገቱ ወደ 40 ከመቶ መስፈንጠሩን ተመልክተዋል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው ደህና የሚባል ዕድገት እያስዘመገበ መጥቶ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ግን የዕድገት ጉዞው ማዝመም እንደጀመረ አሳይተዋል፡፡
ከሁሉ የከፋው ግን የንግድ ሚዛኑ እንደነበር በኮሪያውያኑ ግምገማ ታይቷል፡፡ ከወጪ ንግድ እጅግ በራቀ መጠን እያደገ የመጣው የገቢ ንግድ፣ በአገሪቱ ያለውን የንግድ ሚዛን እያዛባውና ክፍተቱንም እያሰፋው መምጣቱን የኮሪያውያኑ ሪፖርት አመላክቷል፡፡ ዓምና የታየው የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብቻ የታየበት ነበር፡፡ በአንጻሩ የገቢ ንግዱ መጠን ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስመዝግቦ፣ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ አድርሶታል፡፡ ይህ በመሆኑም የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየዋለለ እንዲገኝ አስገድዶታል፡፡ የወጪ ንግዱ ከሚገባው በላይ በግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆንም ለዓለም አቀፍ ገበያ ተለዋዋጭ ጠባይ ተጋላጭና ያልተረጋጋ አድርጎታል በማለት ተችተዋል፡፡ የኮሪያውያኑ እንደሚሉት በአመዛኙ ከአምራች ኢንዱስትሪ ይልቅ ግብርና ኢኮኖሚውን ስለሚቆጣጠረው፣ የአምራች ኢንዱስትሪው አቅምም እንጭጭ መሆኑ ነው፡፡ ግብርና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው ድርሻ 90 ከመቶ ሲሆን በአንጻሩ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የያዘው ድርሻ ከስድስት በመቶ በታች ነው፡፡
ይህንን በመቀየር መንግሥት በኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተመረኮዘ የኢኮኖሚ ልማት ለመምራት የሚያስችለውን መሠረታዊ ሊባሉ የሚችሉ መሠረተልማቶችን መገንባቱ ከቱርክ፣ ከታይዋንና ከቻይና እየመጡ ያሉ ባለሀብቶችና እየከፈቷቸው የሚገኙትን ፋብሪካዎች ተስፋ አድርገዋል፡፡ በቦሌ ለሚ በተገነባውና ከ3500 በላይ ሔክታር መሬት በሚይዘው የኢንዱስትሪ ዞን፣ በቻይኖቹ የተተከለው የዱከሙ ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን፣ እንዲሁም በሰንዳፋ በቱርክ ባለሀብት ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው ግዙፍ የኢንዱስትሪ መንደር ለሁለተኛው የአምስት አመት የኢኮኖሚ ዕቅድ ተስፋ የተጣለባቸውና መዋቅራዊ ለውጥ ያስገኛሉ ተብለው፣ በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በቻይናና በዓለም ባንክ ባለሙያዎች የሚነገርላቸው ናቸው፡፡